"ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሃብት ከባንክ እስከ ታንክ መጋራት ይኖርብናል"
መድረክ
"የምንሰጋው የመድረክ ሰዎች እርስ በርሳቸው ሲተራመሱ፣ ራሳቸውን አጥፍተው እኛንም ይዘውን እንዳይሄዱ ነው"
ኢሕአዴግ
(በየማነ ናግሽ)
"ምርጫና ሰብዓዊ መብት" በሚል የተካሄደው ውይይት ኢሕአዴግንና መድረክን አወዛገበ፡፡ መድረኮች የዝምባብዌንና የኬንያን ተሞክሮ ከማንዴላ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ጋር ያመሳሰሉት ሲሆን፣ ኢሕአዴግ በበኩሉ መድረክ የሚባል ፓርቲ "ለራሱ ጠፍቶ ይዞን እንዳይጠፋ እሰጋለሁ" ብሏል፡፡
ተባባሪ ፕ/ር ዶ/ር አሰፋ ፍሰሃ ትናንት "ምርጫና ሰብዓዊ መብት" አስመልክቶ ለተጠራው ውይይት መነሻ እንዲሆን ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ተቃዋሚዎችንና ኢሕአዴግን አከራክረዋል፡፡ ዶ/ር አሰፋ በፅሑፋቸው፣ ምርጫና ሰብዓዊ መብት የሚቆራኙበት፣ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በአፍሪካ ለብጥብጥ ምክንያት እየሆነ እንደሆነ፣ ፍትሃዊና ተአማኒነት ያለው ምርጫ እንዴት ማካሄድ እንደሚቻል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን መብዛታቸው፣ የመንግሥት ተቋማት ገለልተኛ ስለመሆናቸውና አለመሆናቸው አስመልክተው የሰጡዋቸው አስተያየትንና ያነሱዋቸው ጥያቄዎች በተለይ መድረክንና ኢሕአዴግን አወዛግበዋል፡፡
ስለአሳታፊነት፣ የመንግሥት ተቋማት ገለልተኝነት እና የ97 ምርጫ ስህተቶችን አስመልክተው የተነሱ ጉዳዮች በአንዳንድ የውይይት ተሳታፊዎች አስተያየት የተሰጠበት ሲሆን በተለይ መድረክን ወክለው የተገኙት የፓርላማ አባላት አቶ ወንድሙ ኢብሳ (ኅብረት) እና አቶ ገበየሁ አያቶ (ኦፌዴን) የሰጡዋቸው አስተያየቶች ኢሕአዴግን ያስዳሰቱ አልነበሩም፡፡
አቶ ገበየሁ፣ "አንድ ቤት የሚሰሩ ሰዎች የቤቱን ክዳን አይሻሙም" በሚል ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡ በአሁኑ ወቅት በህንድና በቻይና ያለውን መልካም ለውጥ አድንቀው፣ በኢትዮጵያ ግን "ስልጣን መከፋፈሉ ይቅርና ሰዎች በያሉበት በመልካም ሁኔታ ቢሰሩም ጥሩ ነበር" ይላሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ እና በጋና የመሳሰሉ የአፍሪካ አገሮች ያለውን የዴሞክራሲ ሂደትም አድንቀዋል፡፡ አቶ ገበየሁ፣ በተለይ ትኩረት የሰጡት ጉዳይ ከ97 ምርጫ ምን ተምረናል በሚል ከውይይቱ መድረክ ለተወረወረ ጥያቄ ነበር፡፡ "በ97 የተለቀቀው መልካም አየር (ኦክስጂን) ብዙዎቻችንን ጠቅሟል" ያሉት አቶ ገበየሁ፣ ከምርጫው በኋላ የተፈጠረው ፓርላማ መግባት አለመግባት ውዝግብ ውስጥ የገቡት ወገኖች ግን ወደተሳሳተ መንገድ እንደወሰዱትና፣ ለብዙ ሰው ህይወት ማለፍ ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ እንደዚያ ዓይነት ብጥብጥ የሚባል ነገር መቅረት አለበት፡፡ ነገር ግን አሁንም አባሎቻቸው በየቦታው እንደታሰሩባቸውና ይህን የመጪውን ምርጫ ሂደት እንደሚያበላሽ ገልፀው ታች ያለው የገዢው ፓርቲ ካድሬን መንግሥት አላስተማረም ሲሉ ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል፡፡ እንዲሁም፣ ፓርቲያቸው መድረክ ሰፊ የአገሪቱን ሕዝቦች እንደሚወክልና በግሉ ከኢሕአዴግ ለመወያየት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከድርድር ውጪ እንዲሆን በመደረጉም ኢሕአዴግን ወቅሰዋል፡፡ በፓርላማ የፀደቀው የሥነ ምግባር ህግም፣ አሳሪ እንደሆነ ገልፀው የምርጫ ቦርድ አመሰራረትና በዚሁ ድርድር ሂደት የተጫወተው ሚና አግባብ እንደሌለው አስረድተው፣ መድረክ "ምርጫ ቦርድ" ገለልተኛ ነው የሚል እምነት እንደሌለው አስምረውበታል፡፡ ኢሕአዴግ በአንፃሩ ድርድሩን ረግጦ የወጣው ራሱ መድረክ እንደሆነና የያዘው መስመር ቀና እንዳልሆነ ገል"ል፡፡
ሌላኛው የመድረክ ተወካይ አቶ ወንድሙ ኢብሳ በበኩላቸው ስለ የመንግሥት ተቋማት ገለልተኛነት ያላቸውን ቅሬታ በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ በእርግጥ ካለፈው ተምረነዋል ወይም የፈጠርነው ስህተት ነበር ያሉት አቶ ወንድሙ፣ ለመንግሥት ተቋማት ዕውቅና ሰጥተን አልነበረም የምንቀሰቅሰው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ጉዳይ መድረክን አይመለከትም፡፡ የተፈጠረው ስህተትም በተቃዋሚዎች በኩል ብቻ እንዳልሆነ፣ ሲገልፁ፣ ምርጫ 97 እስከ ግንቦት 7 ምሽት "ወርቃማ" እንደነበር በኋላ ግን መንግሥት በሰጠው መግለጫ ሂደቱ መበላሸት መጀመሩን ያስረዳሉ፡፡
መንግሥት የምርጫ ቦርድን ሚና ወክሎ ኢሕአዴግ ምርጫን አሸንፏል ማለቱ ስህተት እንደነበርም ይገልፃሉ፡፡ "ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆነ አልሆነ ኢሕአዴግ የምርጫውን ውጤት አስቀድሞ መግለፅ አልነበረበትም" በማለት እንዲህ ዓይነት ስህተት እንዳይደገም አሳስበዋል፡፡ "መንግሥት ዋርካ ነው፣ ጃንጥላውን ግን አልተጠቀመም"፡፡
ያም ሆኖ ግን የ97 ምርጫ እንደ አቶ ወንድሙ እምነት "አንፀባራቂ ጭላንጭል ነበር፡፡" "አሁን ያ ጭላንጭል ወዴት እየሄደ ነው?" በማለት አሁን ካለው ቀዝቃዛ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ያያይዙታል፡፡
"የነበረው ዕድገት መቀጠሉ ቀርቶ በነበረበት መቆምም ተስኖታል" በማለት ሂደቱ ወደኋላ እየተመለሰ እንደሆነ ይተቻሉ፡፡
አቶ ወንድሙ ለዚሁ ትችታቸው በመገናኛ ብዙኃን አድሏዊ አሰራር ይጀምራሉ፡፡ መድረክ በቅርቡ በባህርዳር ያካሄደውን ህዝባዊ ስብሰባ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ቢቀርፅም እስከአሁን ያልተላለፈበት ሁኔታ በምሳሌነት አንስተው ይወቅሳሉ፡፡
አንዱ ፓርቲ ሌላውን ማግለል እንደሌለበትም ያክላሉ፡፡ ውጭ ያሉት ዓማፂ ኃይሎችም ጭምር በድርድርና በውይይት ማቀራረብ እንደሚቻል እና በአገራቸው በጎ ሚና ሊያበረክቱ የሚችሉበት መንገድ ቢኖር እንደሚመርጡ ይናገራሉ፡፡
አቶ ወንድሙ አክለው፣ የመድረክ እምነት በቅርቡ ህግ ሆኖ የፀደቀው የሥነምግባር ደንብ ህገመንግሥቱን የጣሰ ነው የሚል ነው፡፡ "የሥነምግባር ደንቡ ህገመንግሥቱን ከመሰረቱ እስከ ጣራው እየሰነቆረ ነው"፡፡ በስንት ሰማዕታት ህይወት የተገኘው ህገመንግሥት እየተከበረ አይደለም የሚለው አቋማቸው አጥብቀው ተከራክረዋል፡፡ ምርጫ ቦርድም በህገ መንግሥቱ ከተሰጠው ኃላፊነት ውጪ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ወንድሙ አባባል፣ መድረክ በኬንያና በዝምባብዌ የሆነውን በኢትዮጵያ እንዲደገም አይፈልግም፡፡ በህዝቦቹ መካከል የተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭትና ቀውስ በኢትዮጵያ እንዳይከሰት መድረክ ጠንክሮ እንደሚሰራም ይናገራሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን፣ ድርድርን ማስቀደም እንልመድ የሚለውም የመድረክ አቋም መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ የጥምር መንግሥት አስፈላጊነትን ሲያስረዱ፣ "ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነገር ከባንክ እስከ ታንክ መጋራት ይኖርብናል" ብለዋል፡፡ ኬንያ እና ዝምባብዌ የተከሰተው ቀውስ መጥፎ ቢሆንም፣ መሪዎቻቸው ቀውሱን በመፍታት ያደረጉት ጥረት ግን "የማንዴላ" ዓይነት ጀግንነት እንደፈፀሙ ይቆጠራል ይላሉ፡፡ "የጥምር መንግሥት የምንጠላው ለምን እንደሆነ አይገባኝም" ያሉት አቶ ወንድሙ፣ ነገሮችን ማስታረቅና ማቻቻል ኢሕአዴግ መልመድ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡
ኢሕአዴግን ወክለው የተገኙት የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው በበኩላቸው በመድረክ የቀረበውን ወቀሳና ትችት አስተባብለዋል፡፡ አቶ ሴኩቱሬ፣ ምርጫ 97ም ቢሆን ነፃና ፍትሃዊ እንዲሆን ያደረገው ራሱ ኢሕአዴግ እንደነበር አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ የምርጫ ውጤትም ቀድሞም አሸንፈናል ያሉት ራሳቸው ተቃዋሚዎች እንደነበሩና አሁን ወደ ኢሕአዴግ እየመለሱት እንደሆነ ገልፀው ወቅሰዋል፡፡ በምርጫ ቅስቀሳም ቢሆን፣ ተቃዋሚዎች የግለሰቦች ክብርና ሞገስ እየገፈፈ፣ ሕገ መንግሥቱን ህገአራዊት እያሉ፣ በአንድ ዘር ላይ አነጣጥረው ያደረጉት ቅስቀሳ፣ እንዲሁም የግል ፕሬሱና ሲቪል ማህበረሰቦች የተጫወቱት አፍራሽ የፖለቲካ ሚና ዘርዝረዋል፡፡ የግለሰቦች የአመለካከት ነፃነት የሚጥስ ድርጊት መፈፀሙንም ገልፀዋል፡፡ ይህን በምሳሌነት ሲያስረዱ የጉራጌ ብሔረሰብ "እኛን ካልመረጥክ ጥቁር ውሻ ውለድ" ተብሎ በባህላዊ መንገድ ተገዝቶ እጅና እግሩን ታስሮ ወደ ምርጫ መግባቱን ያስታውሳሉ፡፡
መድረክ በድህረ ምርጫ 97 ትርምስ የተፈጠረው በመንግሥት ምክንያት ነው ለሚለው፣ "ትርምስ የተፈጠረው ተቃዋሚዎች የህዝብ ድምፅ ባለመቀበላቸው ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል አቶ ሲኩቱሬ፡፡ "መንግሥት ግን አገር ሲቃጠል እያየ ዝም ማለት አይችልም፡፡ ኃላፊነት አለበት፡፡ የትርምስ ፖለቲካ በአገራችን አልሰራም፣ አይሰራምም"፡፡
መድረክ ሥልጣን መጋራትን አስመልክቶ ስለያዘው አቋምም፣ "በሕዝብ የሚተማመኑ ከሆነ ትክክለኛ የዴሞክራሲ መንገድ ይሄ ብቻ ነው" በማለት፣ ምርጫም ተፈልጎ፣ ሥልጣን መጋራትም ተፈልጎ አይሆንም ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ሴኩቱሬ፣ አሁንም መሰመር ያለበት ጉዳይ ባለፈው ያጠፉ ይቅርታ ተደርጎላቸው ተፈተዋል፣ አንዳንዶቹም ጦር መዘዋል፣ መድረክ ግን የተከፈተው የድርድር መድረክ ጥሎ መውጣቱ የያዘውን አቋም አጠያያቂ እንደሚያደርጉም ሴኩቱሬ ይናገራሉ፡፡ የድርጅቱ አመራሮች የሚሰጡት መግለጫ ከኃላፊነት የራቀ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ በተለይ ዶ/ር መረራ የዝምባብዌና የኬንያ ተሞክሮዎች በኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ እንፈልጋለን ማለታቸው፣ "ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚንድ ነው" ብለውታል፡፡
"እኛ በመጪው ምርጫ የምንሰጋው የመድረክ ሰዎች እርስ በርሳቸው ሲተራመሱ ራሳቸውን አጥፍተው እኛንም ይዘውን እንዳይሄዱ ነው"፡፡ የሕዝቡ የመምረጥ መብት የሚያደናቅፉ ማናቸውም ኃይሎች በፅናት እንታገላቸዋለንም ብለዋል አቶ ሴኩቱሬ፡፡
ዶ/ር አሰፋ በተለይ በጀርመን ያለውን መልካም የውክልና ተሞክሮ ያሉትን በመጥቀስ የምርጫ አሳታፊነት (Inclusiveness) አስመልክተው በሰጡት አስተያየት አሳታፊነት በምርጫ ወቅት ብቻ ሳይሆን፣ በሲቪል ሰርቪስና በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ማረጋገጥ ለአንድ ምርጫ ፍትሃዊነት እና ታማኒነት እንዲሁም ለዴሞክራሲ ዘላቂነት ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
አቶ ሴኩቱሬ በሰጡት ምላሽ፣ በኢትዮጵያ በተለይ አናሳ ብሔሮች በበቂ ሁኔታ በመንግሥት መወከላቸውን ጠቅሰው በአገሪቱ የውክልና ችግር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር አሰፋን በአንዳንድ ጉዳዮች አቋም ሳይዙ በጥናታቸው በጥያቄ መልክ ማለፋቸውን የተቹት ሴኩቱሬ፣ የኢትዮጵያ ምሁራን በአገሪቱ ሊጫወቱት የሚገባ ሚና እየተጫወቱ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡
አጥኚው በብሔራዊ ነፃ አውጪ ድርጅት አወቃቀር የተመሰረተ ፖለቲካ አስመልክተው፣ ዘላቂና ተቋማዊ ዴሞክራሲ ለመፍጠር የሚመች አይሆንም ስለማለታቸው፤ አቶ ሴኩቱሬ ትችቱ በቀጥታ ፓርቲያቸውን እንደሚመለከት ገልፀው ኢህአዴግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር የሚመራ እንጂ በብሔር ብቻ የተመሰረተ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ለምሳሌ በብሔር ተወላጅነታቸው ምክንያት ብቻ EDU (ኢድኅ) የህውሓት አባል፣ ትምክህተኛ አመለካከት ያላቸው ደግሞ የብአዴን አባላት መሆን አይችሉም ብለዋል፡፡
ዶ/ር አሰፋ በበኩላቸው፣ ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤት፣ የፀጥታ ሃይሎች እና መገናኛ ብዙኃን ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሳይሆኑ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አይታሰብም ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን መብዛት ሳይሆን የፖለቲካ ፕሮግራማቸው ጥራትና ወደ ጥቂት መሰባሰብ ለዴሞክራሲ እንደሚረዳ፣ በተቃዋሚዎችና በኢሕአዴግ ስላለው የኩርፊያ ፖለቲካ፣ ተቃዋሚዎች ለመንግሥት ተቋማት ዕውቅና ስለመንፈግ (deligetmization) ያለውን ጉዳት አስመልክተውም አጥኚው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ "በኢትዮጵያ ላለፉት 7 ክፍለ ዘመናት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አልነበረም" ያሉት ዶ/ር አሰፋ፣ ችግሩ የዘመኑ በሽታ ነው የምንለው አይደለም ብለዋል፡፡
የቅንጅት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለገሰ ቢራቱ በበኩላቸው፣ በ97 ምርጫ ስለተፈጠረው ስህተት አውስተው፣ ፓርቲያቸው የመንግሥት ተቋማትና ህገመንግሥቱን አክብሮ እንደሚንቀሳቀስ፣ በምርጫ እንጂ በሥልጣን መጋራት እንደማያምን ተናግረዋል፡፡ የኢዴፓ ተወካይ፣ በበኩላቸው በ97 ምርጫ ሰለባ መሆናቸውን፣ ነገር ግን ፓርቲያቸው አሁንም በምርጫ ብቻ እንደሚያምን እና ሥልጣንን የመጋራት መርህን ፓርቲያቸው እንደማይቀበል ተናግረዋል፡፡
የውይይት መድረኩን ያዘጋጁት ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሲሆኑ፣ በዋልታ መሰብሰቢያ አዳራሽ የተካሄደ ነው፡፡



