Saturday, Jul 31st

English Version

ፓርላማው መመሪያን በመጣስ ሕግ እያወጣ ነው ሲል ኢዴፓ ወቀሰ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በኃይሌ ሙሉ

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የፓርላማ ተጠሪ አቶ አብዱራህማን አህመዲን ፓርላማው ራሱ ያወጣውን መመሪያ በመጣስ ሕግ እያወጣ መሆኑን ለሪፖርተር ገለጹ፡፡


አንድ የሕግ ረቂቅ ለፖርላማ ሲቀርብ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ተጽፎ መቅረብ እንዳለበት፣ የሕግ ረቂቁን አላማና ግብ ያካተተ ማብራሪያ መያዝ እንዳለበት፣ የሕግ ረቂቅ ጸድቆ ተፈጻሚ ቢሆን በመንግሥት በጀት ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ እና የሕግ ረቂቅን ለማዘጋጀት የተደረገ ጥናት ካለም መጠቀስ እንደሚኖርበት የተወካዮች ምክር ቤት መመሪያ እንደሚያስገድድ የጠቆሙት አቶ አብዱራህማን፤ ፓርላማው ሃሙስ እለት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ይህንን መመሪያ ጥሶ ሁለት ረቂቅ ህጐችን ለቋሚ ኮሚቴ እንደመራ ተናግረዋል፡፡

የፌደራል ዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤትን አዋጅ ለማሻሻል የወጣው ረቂቅ አዋጅ እና የባለሞተር ተሽከርካሪዎች ታሳቢ መለያ መመርመሪያና መመዝገቢያ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት በቀረቡበት ወቅት ከላይ የተጠቀሱትን ቅድመ ሁኔታዎች እንዳላሟላ የጠቆሙት አቶ አብዱራህማን በተለይ የፌዴራል ዋናው ኤዲተሩ ረቂቅ አዋጁ ፊርማና ማህተም የሌለው መሆኑ እንዳስገረማቸው ተናግረዋል፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት አንድ ረቂቅ አዋጅ በም/ቤቱ አባል የሚቀርብ ከሆነ በአባል ፈርማ መረጋገጥ አለበት፡፡ በኮሚቴ የመነጨ ከሆነም በኮሚቴው ሊቀመንበር ፊርማ መፈረም አለበት፡፡ ሕግ የማመንጨት ሥልጣን ባላቸው ሌሎች አካላት የመነጨ ከሆነ ደግሞ በተቋሙ የበላይ ኃላፊ ፊርማና በተቋሙ ማህተም የተረጋገጠ መሆን ይኖርበታል፡፡ የፌዴራል ዋናው ኤዲተር መሥሪያ ቤትን አዋጅ በማሻሻል የወጣው ረቂቅ አዋጅ ግን ፊርማም ሆነ ማህተም የለበትም፡፡

ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረቡት ሁለቱ ረቂቅ አዋጆች መመሪያን የጣሱ መሆናቸውን በመጥቀስ ተስተካክለው እንዲቀርቡ መደረግ አለበት በሚል አቶ አብድራህማን የቃል ሞሽን ቢያቀርቡም 1/3ኛ ድጋፍ በማጣታቸው ጥያቄያቸው ውድቅ ሆኗል፡፡

የመመሪያ ጥሰት ተፈጽሟል ብለው አቶ አብድራህማን ከዘረዘሯቸው ነጥቦች መካከል በአንዱ ላይ ምላሽ የሰጡት የመንግሥት ምክትል ተጠሪ አቶ ወንድሙ ገዛህኝ የህግ ረቂቁን ለማዘጋጀት ጥናት እንደሚካሄድ ጠቁመው ሙሉ ጥናቱ ተባዝቶ ለምክር ቤት ያልቀረበበት ዋናው ምክንያት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ አቶ አብድራህማን ግን የመንግሥት ተጠሪው ምላሽ አሳማኝ አይደለም ይላሉ፡፡


መመሪያው ላይ የተቀመጠው ረቂቅ አዋጅ ሲወጣ ጥናት መደረጉን፣ በመነሻነት የታዩት ሀገሮች እነ ማን እንደሆኑ እና ከየትኞቹ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደተካሄደ መገለጽ እንዳለበት የሚጠቀስ እንጂ ዝርዝር ጥናቱ ይቅረብ የሚል እንዳልሆነ የጠቆመት አቶ አብዱራህማን "የአቶ ወንድሙ የበጀትን ጉዳይ ያነሱት ማምለጫ መንገድ ያገኙ መስሏቸው ነው" ብለዋል፡፡

የቃል ሞሽኑን ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት፣ ምክንያትን መሰረት አድርገው ውሳኔ የሚሰጡ የምክር ቤት አባላት ካሉ ይቀበሉታል በሚል እምነት እንደነበር የጠቆሙት አቶ አብዱራህማን የኢህአዴግ በተለይም የመንግሥት ተጠሪዎች የራሳቸውን ድክመት ለመሸፈን ጥረት ያደረጉበትን ሁኔታ እንደተመለከቱ ገልጸዋል፡፡