ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ፣ የፍሊንስቶን ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር
ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ ከሃያ ዓመታት በላይ ቆይተዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ባለሙያ የሆኑት ኢንጂነር ፀደቀ፣ የፍሊንስቶን ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከ1,300 በላይ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ምክትል ሊቀመንበርም ሆነው ሠርተዋል፡፡ የሐበሻ ሚሲንቶ አክሲዮን ማኅበር ቦርድ አባል ናቸው፡፡ ከሙያቸው አንፃር በቅርቡ የወጣው የሊዝ አዋጅ ከኮንስትራክሽን ግንባታዎች ጋር ሊኖረው ስለሚችለው ግንኙነት፣ በአሁኑ ወቅት እየተስተዋሉ ካሉት የግንባታዎች መቀዛቀዝ አንፃር፣ እንዲሁም ድንገት ሳይጠበቅ የሲሚንቶ ዋጋ በመቀነሱ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስቶ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- አዲሱ የሊዝ አዋጅ በኮንስትራክሽን ግንባታዎች ላይ የሚኖረው አሉታዊና አዎንታዊ ገፅታው ምን ሊሆን ይችላል ብለው ያምናሉ?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- በመጀመርያ አዋጁ ላይ የተቀመጠውና የአዋጁ ዓላማ ሰዎች በመሬት ግብይት ብቻ ሀብት እንዳያካብቱ ለማድረግ ነው፡፡ በመሬት ላይ በትንበያ የሚካሄድ ግብይት እንዳይኖር ለማድረግና ለመከላከል ነው፡፡ ድርጊቱን ለመከላከል በአዋጁ ውስጥ የተጠቀሰው በአካባቢው ማስተር ፕላን መሠረት በመሬቱ ላይ ሊሰፍር የሚገባውን ንብረት በከፊል ሳታጠናቅቅ የምትሸጥ ከሆነ፣ ሽያጩን የመከታተያ ሥርዓት በአዋጁ ውስጥ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ ውስጥም አንዱ ከንብረቱ ሌላ በመሬቱ ላይ የሚገኝ 95 በመቶ ጥቅም አስተዳደሩ እንዲወስድ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው መሬቱ ላይ የሰፈረው ንብረት በከፊል ሳይጠናቀቅ የሚሸጥ ከሆነ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ስታየው ግንባታን ያበረታታል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ግንባታን እንደሚያበረታታ መጀመርያ ኢንቨስተሩ መረዳት አለበት፡፡ ኢንቨስተሩ ይህንን እስኪረዳና አሁን ያለው ብዥታ እስከሚጠፋ ድረስ ግን አዋጁ በጥርጣሬ እንዲታይ ነው የሚሆነው፡፡
ብዙ ሰዎች አዋጁን ጠጋ ብለው ያለማንበባቸው፣ ብዙ ነገሮችም በወሬ ደረጃ የሚናፈሱ በመሆናቸው 95 በመቶ የሚሆኑት ንብረታቸው የሚወስድባቸው መስሎ ይሰማቸዋል እንጂ፣ አዋጁ ለኮንስትራክሽን ግንባታዎች ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብዬ አስባለሁ፡፡
በአዋጁ ውስጥ እንደተጠቀሰውም ግንባታ ያልተጠናቀቀባቸው ወይም ባዶ ቦታዎች ሥርዓት እንዲይዙ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የመሬት ዋጋን በማዋደድ ያልተገባ ጥቅምን ለመከላከል ስለሆነ ያልተገባ ጥቅምን በማስቀረት ሕዝብና የግል ባለሀብቱ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት የሚያስችል ነው፡፡
ይህም የመነጨው መሬት የወል መብት በመሆኑ ነው፡፡ በሕገ መንግሥታችን መሬት የወል መብት ነው እንጂ የግል መብት አይደለም፡፡ ስለዚህ የወል መብቱ በፍትሐዊነት መከፋፈል ያለበት ከሕዝብ ጋር ነው ማለት ነው፡፡ ማንም በግል መብቱ በኩል ያለውን ጥቅም ግን አያጣም፡፡ ይህም ሆኖ መሬቱ ላይ ግንባታውን ሙሉ ለሙሉ ካጠናቀቀ ግን መቶ በመቶ ጥቅሙ ለእሱ ነው የሚሆነው፡፡ ግንባታ ያልገነባ ግን ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም፡፡
አንድ ሰው መሬት በሊዝ ወስዶ ወይም በራሱ ቦታ ላይ በማስተር ፕላኑ ወይም የአካባቢው ግንባታ በሚፈቅደው መሠረት ንብረት ካሰፈረ፣ ንብረቱን በሚሸጥበት ጊዜ በዚህ የሚያጣው ጥቅም የለም፡፡
ሪፖርተር፡- አዋጁ ግንባታን አቀዛቅዟል እየተባለ ነው እኮ?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- በግሌ ከዚህ አዋጅ በኋላ መሬቱን አብረን እናልማ እያለ ጥያቄ የሚያቀርብ ሰው ነው የበዛብኝ፡፡ እድሮች፣ ማኅበራት፣ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች ሰፋፊ ቦታዎች አሉንና አካባቢው የሚጠይቀውን የግንባታ ዓይነት በተናጠል መገንባት ስለማንችል፣ በጋራ ከእናንተ ጋር እንገንባ የሚሉ ጥያቄዎች በዝተውብኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ ለግንባታ ሥራዎች የሊዝ አዋጁ መልካም ነው እያሉኝ ነው?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- ያስኬዳል፡፡ ግን አሁንም ቢሆን እኛ ገንብተን የምንሸጠው ንብረቱን መልሼ እሸጠዋለሁ ብሎ ለሚፈልግ ሰው ነው፡፡ እሸጣለሁ ብሎ የሚገባ ሰው አዋጁን በቅጡ ካልተረዳው የሚገዛን ሰው መቀነሱ አይቀርም፡፡ ለዚህ ነው ሰዎች አዋጁን በደንብ ማየት አለባቸው የምለው፡፡
ሪፖርተር፡- የሚገዛችሁ ሰው ላይመጣ የሚችልበት ምክንያት ምንድነው?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- አዋጁን ያለማንበብ ችግር ስላለ ነው፡፡ በአዋጁ ይዞታን ስለማስተላለፍ በተቀመጠው አንቀጽ ውስጥ በጉልህ ስላልተቀመጠ ነው፡፡ ምክንያቱም መሬት በሊዝ ውስጥ መታቀፉ የሚጠይቀው የገንዘብ ፍላጐት በጣም አነስተኛ ስለሆነ፣ ብዙ ሰዎች በዚህ ምክንያት ነው የሚወያዩበት ብዬ ለመድፈር አይመቸኝም፡፡ እኔ የሚመስለኝ አንድ ሰው ንብረቱ በሚሸጥበት ጊዜ ከንብረቱ ሽያጭ የሚያገኘው ገንዘብ 95 በመቶ ይወሰድብኛል የሚለው ነው፡፡ 95 በመቶው የሚወሰደው በባዶ መሬት ላይ በሚገኝ ጥቅም ላይ ነው፡፡ በባዶ መሬት ብቻ በሚገኝ ጥቅምና በመሬቱ ላይ ንብረት ባልተገነባበት፣ እንዲሁም ተገንብቶ ባላለቀበት ጊዜ በሚገኝ ጥቅም ላይ የሚመሠረት ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ኅብረተሰቡ እስኪረዳው ድረስ ብዥታ ሊኖር ይችላል፡፡
ለምሳሌ የእኛ የሪል ስቴት ደንበኞች 50 በመቶው ዲያስፖራ ናቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ናቸው፡፡ ሁሉም የሚገዙት ሽያጭ ይኖራል ብለው ነው፡፡ ምክንያቱም ሀብት አለኝ የምለው ገበያ ላይ በሚያወጣው ዋጋ መሠረት ስለሆነ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሪል ስቴት ገበያ ቀንሷል ይባላል፡፡ ይህን ደግሞ ከአዲሱ የሊዝ አዋጅ ጋር ያያያዙትም አሉ፡፡
ኢንጂነር ፀደቀ፡- የሪል ስቴት ገበያን በሚመለከት ለምሳሌ እኛ ዘንድ መቀዝቀዝ ይታያል፡፡ ይህ ማለት ሁሌም ከዘመን መለወጫ በኋላ ባሉት ጥቂት ወራት (እስከ ገና ድረስ) ይቀዘቅዛል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ተመልሶ ወደላይ የሚወጣው፡፡
ሪፖርተር፡- በእነዚህ ወራት ገበያው የሚቀዘቅዘው ለምንድነው?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- ይህንን በሚመለከት ለሦስት ዓመታት የተለያዩ መረጃዎችን ሰብስበናል፡፡ ከዚህ መረጃ መገንዘብ የተቻለውና የእኔም ግምት የኢትዮጵያ ገበያ ከግብርና ምርት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ነው፡፡ የግብርና ምርቱ ገበያ ሲጨምር ገንዘብ ይኖራል፡፡ አዲስ የእህል ምርት ወደ ገበያ ሲገባ፣ የወጪ ንግዱ ሲጨምርና የንግድ መጠኑ እያደገ በሚመጣበት ጊዜ ቤት ሊገዙ የሚችሉ ሰዎች ገንዘብ ይኖራቸዋል፡፡ ሌላው ደግሞ መደበኛ ያልሆኑ ግብይቶች ነበሩ፡፡ መደበኛ ያልሆኑት ወይም ኢንፎርማል ያልሆኑ ክስተቶችም ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የንግድ ሥርዓቱን ከማስተካከል ጋር የተሠራው ሥራ ይጠቀሳል፡፡ ችርቻሮን በችርቻሮ፣ ጅምላንም በጅምላ ግብይት እንዲሠራ፣ ቫት መክፈል ያለበት እንዲከፈል የማድረግ ሥራዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ደግሞ የንግድ እንቅስቃሴ መቀነሱ ስለማይቀርና ይህም ስለታየ በእኛ ገበያ ላይ መቀዛቀዝ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ሌሎች የግንባታ ሥራዎችም እየተቀዛቀዙ ነው፡፡ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በሚታየው ፍጥነት ያህል የኮንስትራክሽን ሥራ እየተጓዘ አለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- የግንባታ ከፍ ማለትና መቀዛቀዝ ከመንግሥት ግዥ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ገበያው ሲኖር ዋጋው ይወጣል፤ ገበያው ሲቀዘቅዝ ዋጋም ይቀንሳል፡፡ ግዥና ግንባታ ደግሞ ይያያዛሉ፡፡ አሁን እንዳየነው የሲሚንቶ ፍላጐት ሲወርድ ገበያው ወርዷል፡፡ በአንድ ወቅት ብረት በጣም በመወደዱ ምክንያት ሲሚንቶ ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ቀንሶ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የብረት ዋጋ ራሱ እየወረደ ነው ያለው፡፡
ስለዚህ ግንባታ እየቀዘቀዘ ያለበት ምክንያት ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር አካባቢ መንግሥት ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር በተያያዘ ወጪውንና ኢንቨስትመንቱን የማቀናጀት ሥራ እየሠራ ስለነበር ነው፡፡ ይህ በየቦታው የሚታይ ነው፡፡ ይህ የዝግጅት ሥራ እስከሚያልቅ ድረስ የግንባታ ሥራዎች ጋብ ብለዋል ሊባል ይችላል፡፡ ይህ እስኪስተካከል ድረስ በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በክልል መንግሥታት የግንባታ ሥራዎች ትንሽ ቀዝቀዝ ያሉ ይመስለኛል፡፡ አሁን ግን ተቀዛቅዘው የነበሩት ግንባታዎች እንደገና በጣም እየመጡ መሆኑን እያየን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ትልቁን ግንባታ የሚያከናውነው መንግሥት ነውና መንግሥት የግንባታ ጨረታዎችን ቀንሶ ነበር ማለት ይቻላል?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- አዎ! ጨረታዎች ቀንሰው ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- በአንድ ወቅት አልቀመስ ብሎ የነበረው የሲሚንቶ ዋጋ አሁን በመቀነሱ ክስተቱ ምን ያመለክታል?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- ቀደም ብሎ ከጠቀስኩት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ፍላጐቱ ሲቀንስ ዋጋውም ቀንሷል፡፡ ሲሚንቶ ሊበላሽ የሚችል ምርት ነው፡፡ ከሦስት ወር በላይ አስቀምጠህ ልታቆየው የምትችለው ምርት አይደለም፡፡ እርጥበት ያበላሸዋል፡፡ በተጠራቀመ ቁጥር ችግር ሊኖረው ይችላል፡፡ ፋብሪካዎቹ የማከማቻ ቦታ ስለሌላቸው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከቆየባቸው የሚያከማቹት ሲሚንቶ ይበላሻል፡፡ የግድ ዋጋውን ዝቅ አድርገው መሸጥ አለባቸው፡፡ አሁንም ቢሆን አልሸጥ ካላቸው በቅናሽ ካወጡት ዋጋ አሁንም ዝቅ አድርገው መሸጥ አለባቸው፡፡ ሌላ ምርጫ የላቸውም፡፡
ሪፖርተር፡- አገር ውስጥ የሚመረት ሲሚንቶ አልበቃ ብሎ በውጭ ምንዛሪ ከውጭ ተገዝቶ እንዳልተሠራ ሁሉ፣ የሲሚንቶ ዋጋ መቀነስና መትረፍረፍ ከግንባታ መቀዛቀዝ ጋር የተያያዘ ነው ልንል እንችላለን?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- አዎ! ግን ከውጭ የሚመጣ ሲሚንቶ እኮ ዛሬ አዝዘህ ወዲያው የሚመጣ አይደለም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ከ150 እስከ 180 ቀናት ያስፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ የዛሬውንና የዛሬ ስድስት ወር ሊሆን የሚችለውን ነገር ገምተህ ነው የምታደርገው፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆንም ዛሬ ግንባታ ተቀዛቀዘ ማለት ከአንድና ከሁለት ወራት በኋላ እንዲሁ ይቆያል ማለት ስላልሆነ፣ የሚመጣው ሲሚንቶ ይጠቅማል እንጂ አይጐዳም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሲሚንቶ ዋጋ አሁን ባለበት ሁኔታ ከማምረቻ ዋጋው ከ80 እስከ 120 በመቶ ብልጫ እየተሸጠ ነው፡፡ ስለዚህ የሲሚንቶ ዋጋ አሁን ከሚሸጥበትም በታች መውረድ አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ሲሚንቶ አሁን ቀንሶ ከሚሸጥበት ዋጋ በታች ሊወርድ ይገባዋል ብለው ያምናሉ?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- አዎ! ከዚህ በታች ዋጋው ወርዶ ቢሸጥ ያዋጣል፡፡ መውረድም ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ግን ዋጋውን በዋነኝነት የሚያወርደው ፍላጐቱ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሲሚንቶ የዚህን ያህል ዋጋው ወርዶ መሸጥ የሚቻልና አትራፊ ከሆነ፣ ለምን ይህንን ያህል ጊዜ የትርፍ መጠኑ እንዲለጠጥ ተደረገ? ለምንስ ተወደደ?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- ሲሚንቶ ዋጋው እየጨመረ የቆየው ከፍተኛ ፍላጐት ስለነበረ ነው፡፡ በ20 ብር ስኳር ገዝተው የሚጠቀሙ አሉ አይደል? በአራት መቶ ብር ኩንታል ሲሚንቶ የሚገዙ እስካሉ ድረስ ይሸጣል፡፡ ፍላጐቱ ከጨመረ ዋጋው መውጣቱ አይቀርም፡፡
ሪፖርተር፡- የሲሚንቶና የብረት ዋጋ ቀንሷል፡፡ እንደሚባለውም የመሬት ሊዝ ዋጋም ቀደም ብሎ በጨረታ ይሸጥበት ከነበረው ዋጋ ሊቀንስ ከቻለ፣ የቤት መሥርያ ዋጋ እስካሁን ይወጣ ከነበረው ዋጋ ሊቀንስ ይችላል?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- የቤት ዋጋ ሊቀንስ ይችላል፡፡ ቅናሹ የሚወሰነው በመግዛት አቅሙ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ መሬትና የመገንባት አቅም የሚገናኙበት ጉዳይ አለ፡፡ ዋናው ነገር አሁን ባልከው ሁኔታ የሕግ ማዕቀፉ፣ የኢንቨስትመንት ፖሊሲው፣ የባለሀብቶቹና የሰው ፍላጐት ሲታይ ቤት ይበዛል፡፡ በነገራችን ላይ የሊዝ አዋጁ መንፈስ ሰዎች እንዳይሸጡ መከልከል ሳይሆን፣ ዋናው የአዋጁ ዓላማ የከተማውም የገጠሩም ነዋሪ እንዳይፈናቀል ነው፡፡ በገንዘብ ኃይል ወዶም ሆነ ተገድዶ ከይዞታው እንዳይነቀል ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ እዚያው ባለበት አቅሙን ያገናዘበ አገልግሎት የሚያገኝበት ጊዜ እየመጣ ነው ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የሊዝ አዋጁ ሲሠራበት የነበረው የመሬት ሊዝ ዋጋ የካሬ ሜትር መነሻው እንደሚከለስ ይጠበቃል፡፡ የመነሻ ዋጋው ቀድሞ ከነበረው ዋጋ ከፍ ይላልም ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ የሊዝ ዋጋውን ሊያንረው አይችልም?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- አይችልም፡፡ በአዲሱ አዋጅ የአፈጻጸም ደንቦች መሠረት አንድ ሰው ከቦታው ሲነሳ የንብረቱ የገበያ ዋጋና የመሬቱ የሊዝ መነሻ ዋጋ ታይቶ ሁለቱ ናቸው የሚካካሱለት፡፡ ስለዚህ አንተ ለራስህ ብለህ ከፍ ብታደርገው የመንግሥት ገቢ ለማሳደግ ብሎ የከተማው አስተዳደር ከፍ ቢያደርግ፣ ለዚያ ቦታ የተተመነውን ያህል መጠን ያለው ቦታ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ እንደዚህ ከሆነ በሊዝ መነሻ ዋጋ መስጠትና ገንዘቡን መመለስ አለበት፡፡ የራሱ ይዞታ ስለሆነ ምትክ ቦታ የሚሰጠው ከሆነ ይህንን የሚመጥን ቦታ መስጠት አለበት፡፡ ሁሉም ነገሮች ላይ ፍትሐዊ ሥራዎች ከተሠሩ ገበያውን አይሰቅሉትም፡፡
ሪፖርተር፡- የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማስፈጸም እየተደረገ ባለ ዝግጅት ሳቢያ ግንባታዎች ተቀዛቅዘዋል ተብሏል፡፡ ከዚህ በኋላ እንደገና ግንባታዎች ሊያንሰራሩ ይችላሉ?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- ምንም ምርጫ የለም፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ቦታዎች የሉም፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ቦታዎች ራሳቸው አነስተኛና የጐጆ ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህን መገንባት ይጠብቀናል፡፡ የመኖሪያ ቤትም እንዲሁ፡፡ ተጠቃሚውን የሚመጥኑ ቤቶች በብዛት መሥራት አለብን፡፡ የመንግሥት ስትራቴጂ የቤቶች ልማትና የሰው ኃይልን አንድ ላይ ማድረግ ነው፡፡ ቤት በተሠራ ቁጥር ከአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች ጋር በመደጋገፍ ልክ ኮንዶሚኒየም ላይ እንደሚሠራው በሁሉም መስክ የቤት ልማት ከቅጥር ጋር እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ዘርፉ ደግሞ ብዙ የሰው ኃይል ይፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኮንስትራክሽን ግንባታዎች ለግሽበት ምክንያት ናቸው ይባላል፡፡ ይህ ዘርፍ አሁን ከታየው የግንባታ መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ በግሽበት ላይ ለውጥ አምጥቷል ማለት ይቻላል?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- ኮንስትራክሽን ለግሽበት የሚኖረው አስተዋፅኦ በተለያዩ መንገዶች ሊገለጽ ይችላል፡፡ አንደኛው የመንግሥት ኮንትራቶች ላይ ቁጥጥር ሳይደረግባቸው ሰዎች በሚጫረቱበት ጊዜ፣ ጥራትና እሴት ሳይጨምሩ ዋጋቸው ዝም ብሎ ይጨምራል፡፡ መንግሥት ዋጋው ከጨመረበት ምርጫው ተበድሮ ዕዳውን ለሥራ ተቋራጮች መክፈል ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት በመበደሩ ምክንያት የገንዘብ አቅርቦትን ይጨምራል፡፡ ይህም የመንግሥት ወጪ እንዲጨምር አድርጐ ግሽበት ያመጣል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የገበያ ትንበያ ነው፡፡ አሁን የግል ግንባታዎች ላይ ደግሞ እሴት ሳይሆን የገነቡት ወይም የያዙት መሬት ነገ በትልቅ ዋጋ ይሸጣል ብለው በማሰብ ብቻ የሚገነቡ በመሆኑ ነው፡፡ አንድ ሺሕ ብር ያወጣ ግንባታ በኋላ አሥር ሺሕ ብር ይሸጣል በሚልና ይህንን ለመግዛት በሚፈልጉ ሰዎች የሚመጣ ግሽበት ነው፡፡ ከውጭ መጤ የሆነ ግሽበት ነው፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ ከከተማ ወደ ገጠር፣ ከውጭ አገር ተልኮ በሚገባ ዶላርም ሊመጣ ይችላል፡፡ ሦስተኛው ግሽበት የሚመጣው ደግሞ ግንባታን አጠናቅቆ ሥራ ካለመጀመር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንድ ኢንቨስትመንት ከተሠራ ለኅብረተሰቡ አቅርቦትን ስለሚጨምር ግሽበት መኖር የለበትም፡፡ ምክንያቱም አንድ ነገር ኢንቨስት ስታደርግና ኢንቨስትመንቱ አቅርቦትን ስለሚጨምር በአቅርቦት መብዛት ምክንያት ግሽበቱ ይቀንሳል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ችግሩ ግን ግንባታዎች አይጠናቀቁም፡፡ ግንባታዎች ስለማይጠናቀቁ ከፍተኛ ወጪ ይወጣል እንጂ የሚጠበቀው አቅርቦት አይገኝም፡፡ መንገዶች ይሠሩና ካልተጠናቀቁ ምርት ወደ ገበያ አይደርስም፡፡ ፋብሪካዎች ይገነቡና መጨረሻ ላይ እዚያ ውስጥ መግባት ያለበት ማሽን ወይም የኤሌክትሪክ ኃይል ሲጐድል የታሰበው የፋብሪካው አቅርቦት አይመጣም፡፡ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ነገሮች በኮንስትራክሽን ዘርፍ ግሽበትን ሊያመጡ ይችላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ግንባታዎች እንደገና እያደጉ ከመጡ አሁን ቀነሱ የምንላቸው የኮንስትራክሽን ግብዓቶች እንደገና ሊጨምሩ ይችላሉ?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- ዋጋ ይጨምራል፡፡ ነገር ግን ከዋጋ ጭማሪው ጋር ገቢ ይጨምራል፡፡
ሪፖርተር፡- ገቢ እንዴት ሊጨምር ይችላል?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- ገቢ የሚጨምረው አነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎችን ከቤቶች ልማት ጋር በማቀናጀት ነው፡፡ የከተሞች ልማት ብቻውን ፎቅ መገንባት ሳይሆን፣ ከተሞች ሲለሙ በየአካባቢው ያለው ገቢ አብሮ እንዲጨምር በማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ የሰው ኃይል ቅጥር ይጨምራል፡፡
ሪፖርተር፡- የቤቶች ግንባታ መብዛት ተቀጣሪ ሠራተኞችን ያበረክታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጭ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ አይካሄድም እየተባለ ነው፡፡ ይህ አሁን ካሉኝ ጋር አይጋጭም?
ኢንጂነር ፀደቀ፡- ይህ መባሉን አላውቅም፡፡ ግን የምገምተው የአካባቢው ገቢ ሊመጥነው የሚችለውን ቤት ነው እንጂ በስመ ኮንዶሚኒየም አይደለም መሥራት ያለብህ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየደጋገሙ እንደሚናገሩት ለጫማው እግር ነው ወይስ ለእግሩ ጫማ ነው የሚያስፈልገው እንደሚባለው ዓይነት ማለት ነው፡፡
ኮንዶሚኒየም ሠርተን ለኮንዶሚኒየም አይደለም የምናዘጋጀው፤ ለሰው የሚሆነውን ኮንዶሚኒየም ነው ማዘጋጀት ያለብን፡፡ ስለዚህ ለአካባቢው ተመጣጣኝ የሆነ ቴክኖሎጂና የቤት ዲዛይን ከመምረጥ አኳያ ይመስለኛል፡፡


