መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ፣ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት
የቀድሞ የአየር ኃይል አብራሪ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ በቡና ዘርፍ ላይ ለ40 ዓመታት ሠርተዋል፡፡
በእነዚህ ጊዜያት የቡና ገበያ ውጣ ውረዶችን፣ በየወቅቱ የሚከሰቱ ተለዋዋጭ ባህርያትንና መገለጫዎቹን ሲያስረዱ፣ በፓውንድ 39 የአሜሪካ ሳንቲም ይሸጥ የነበረው ቡና በአንድ ቀን ልዩነት ሦስት ዶላር ከ70 ሳንቲም የተሸጠበትን ክስተት ያስታውሳሉ፡፡ ቡና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚጫወተው ሚና ጉልህ ከመሆኑ አንፃር አገሪቱ ከውጭ ንግድ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው የግብርና ምርቶች ግንባር ቀደም ነው፡፡ የ
ኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት መቶ አለቃ ፈቃደ፣ በተለያዩ ጊዜያት የቡና ዋጋ መዋዠቅ የሚፈጠረው በተፅዕኖ ፈጣሪዋ ብራዚል ላይ በደረሰ የቡና ውርጭ ምክንያት አቅርቦቱ በመቀነሱ እንደሆነ ገልጸው፣ የቡና ገበያ ግን በየሰከንዱ የሚለዋወጥ በመሆኑ ትናንት የተገኘው ወይም የተሸጠው ቡና ዛሬ ላይሸጥ እንደሚችል ያብራራሉ፡፡ ወቅታዊውን የቡና ንግድ በተመለከተ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞን ብርሃኑ ፈቃደ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የቡና ዘርፍ የአገሪቱ ዋና የገቢ ምንጭና የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ሆኖ ለዓመታት ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚታዩት ክስተቶች ይህንን የበላይነቱን ጠብቆ እንዲዘልቅ ያስችሉታል?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- የቡና ንግድ በባሕሪው በየሰከንዱ የዋጋ መለዋወጥ የሚታይበት ነው፡፡ የቡና ገበያን የሚመሩ ሁለት የገበያ ማዕከላት አሉ፡፡ አንዱ የኒውዮርክ ገበያ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ዓይነት የዓረቢካ ቡና የሚገበያይበት ነው፡፡ የሮቡስታ ቡና ደግሞ በለንደኑ ገበያ ማዕከል ይቀርባል፡፡ በእነዚህ ገበያዎች በየሰከንዱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚለዋወጥ ግብይት ይንፀባረቃል፡፡ በቡና ንግድ ላለፉት አርባ ዓመታት ቆይቻለሁ፡፡ የቡና ዋጋ በፓውንድ ከ39 የአሜሪካ ሳንቲም እስከ ሦስት ዶላር ከ70 ሳንቲም የዋዠቀበት ጊዜ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ በአንድ ጊዜ የሆነ ነበር?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- በአንድ ጊዜ የተከሰተ ነው፡፡ የብራዚል ምርት ምንጊዜም በዋጋ ለውጥ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው፡፡ መጠኑ በበዛና ባነሰ ቁጥር የዋጋው ሁኔታም ከፍና ዝቅ ይላል፡፡ ስለዚህ ፓራና በሚባለው ግዛታቸው ውስጥ ከፍተኛ ውርጭ ደርሶ ስለነበር የቡና ዋጋው ወዲያው በማግስቱ ከ39 ሳንቲም ተነስቶ ሦስት ዶላር ከ70 ሳንቲም ሊገባ ችሏል፡፡ ቡና በባህሪው በአንድ ዋጋ ላይ ተረጋግቶ አይቆይም፡፡ ምናልባት እንኳ ቢቆይ ከ12 እስከ 18 ወራት ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ቡናም ስንመጣ የዓለም ገበያን ተከታዮች እንጂ ተፅዕኖ አሳዳሪዎች ባለመሆናችን ምንም እንኳ የቡና ምርት መጠናችን ቢጨምር፣ የብራዚልና የቬትናምም አብሮ ስለጨመረ በገበያው ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር አልቻልንም፡፡ ገና ነን፡፡ ምናልባት ወደፊት እናሳድር ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ዘንድሮ ምንድን ነው የተከሰተው?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ትልቁ ነገር እርሱ ነው፡፡ የተከሰቱትን ሁኔታዎች በሁለት ከፍለን ብናያቸው ጥሩ ይሆናል፡፡ አንደኛው የውጭ ተፅዕኖዎችና ሁኔታዎች ናቸው፡፡ የአውሮፓ፣ የአሜሪካ፣ የጃፓንና የትልልቅ አገሮች ኢኮኖሚ መናጋት በሸቀጥ ምርቶች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ የሰው ገቢ በቀነሰ ቁጥር፣ ሥራ ያለው ሰውም በቀነሰ ቁጥር፣ ወጪውን ይቀንሳል፡፡ በፊት በቀን ሦስት ስኒ ቡና ይጠጣ የነበረ ሰው አሁን ወደ አንድ ስኒ ሊያወርደው ይችላል፡፡ የእነዚህ አገሮች ኢኮኖሚ ችግር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ቡና ገበያ ላይ ተፅዕኖ አምጥቷል፡፡ ሌላው የዶላር ደካማ እየሆነ መምጣት በንግዱ ላይ ተጽዕኖ አለው፡፡ በኒውዮርክ ገበያ ማዕከል ቡናን ጨምሮ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሸቀጦች ይነገዳሉ፡፡ ስኳር፣ ካካዎ፣ ዘይት፣ ወዘተ ማለት ነው፡፡ የጡረታ ፈንድ ሳይቀር ግብይት ይፈጸምበታል፡፡ ስለዚህ በገንዘቡ የሚነግዱ ድርጅቶች ቡና የሚጠቅም መስሎ ካልታያቸው ቡና ላይ ኢንቨስት ከማድረግ ይልቅ ወደ ሌላው ሸቀጥ ይሄዳሉ፡፡ ያን ጊዜ የቡና ንግድ ተዳከመ ማለት ነው፡፡ የመገበያያው መዳከምም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው፡፡ የተዳከመው የአሜሪካ መገበያያ ከሆነ ኢንቨስተሩ ከዚያ ይወጣና ሌላ ዓይነት ንግድ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ እንዲህ ያሉ በርካታ ተፅዕኖ ፈጣሪ ጉዳዮች ቡናው ላይ አሉታዊ ጫና አሳድረዋል፡፡
ይህ በአጠቃላይ በኢንዱስትሪው ላይ የሚታይ ነው፡፡ ሌላው ትልቁ ተፅዕኖ የሚባለው በሚቀጥለው ወር ከፍተኛ የብራዚል ምርት ወደ ገበያው የሚገባ መሆኑ ነው፡፡ የሚጠበቀው ከ50 ሚሊዮን በላይ ከረጢት በብራዚል እንደሚመረት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት 40 ሚሊዮን ያህል ነበር፡፡ ይኼ የአረቢካ ቡና ነው፡፡ የቬትናም የሮቡስታ ምርትም ዘንድሮ ወደ 23 ሚሊዮን ከረጢት ከፍ ብሏል፡፡ ባለፉት ዓመታት 17 ሚሊዮን ላይ የቆየ ነበር፡፡ ሁለቱ ብቻቸውን የዓለምን ከ75 በመቶ በላይ ምርት ማቅረብ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ የመካከለኛው አሜሪካ ግዛቶች፣ የኮሎምቢያና የአፍሪካ ሲጨማመርበት አቅርቦቱ ከፍላጎት በላይ ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡ በቀላሉ ቡና ቆይዎች ለረጅም ጊዜ የሚሆናቸውን ግዥ አያከናውኑም ማለት ነው፡፡ የሚያሳስባቸው ነገር ስለሌለ የየዕለት ፍላጎታቸውን ብቻ እየገዙ ይሠራሉ፡፡ እነኚህ ሁሉ በቡና ዋጋ ላይ ትልቁን ተፅዕኖ እያሳደሩ ያሉ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ነጋዴዎች ሲናገሩ የሚደመጠው የኢትዮጵያ ቡና ለማጣፈጫነቱ ሲባል የሚፈለግ በመሆኑና የሚላከውም መጠን አነስተኛ በመሆኑ፣ በገበያው ላይ ዋጋው አይቀንስም ነው፡፡
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- የኢትዮጵያን ቡና ለብቻው የሚፈልጉ ቡና ቆይዎች አሉ፡፡ እነኚህ ግን የሚቆሉት የቡና መጠን በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ከበርካታ ደንበኞቼ አንዱ በዓመት ሁለት ኮንቴነር ብቻ እየገዛ ጥሩ ዋጋ የሚከፍል አለ፡፡ ሌላው ቡና የግድ ትልልቆቹ ዘንድ መሄድ አለበት፡፡ ያ ሲሆን ደግሞ የኢትዮጵያን ብቻ አይደለም የሚሸጡት፡፡ ያደባልቁታል፡፡ አምስቱን እጅ የኢትዮጵያ ካደረጉ፣ ከብራዚል 30 በመቶውን፣ ከኮሎምቢያ የሆነውን መቶኛ አድርገው ይሸጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ ጥሩ ቢሆንም የዓለምን የፍጆታ ሁኔታ የሚያስቀይር ተፅዕኖ የሚፈጥር አይደለም፡፡ የአገር ውስጥ ተፅዕኖም አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ችግርም እንደ ጥቅምም የምወስደው ነገር አለ፡፡ መንግሥት ካበረታታን ቡናችንን ለመሸጥ የውጭ ገበያ አያስፈልገንም፡፡ በጠቅላላው የኢትዮጵያን ቡና እዚሁ መጠጣት የምንችልበት ሰፊ ገበያ አለን፡፡ በአፍሪካ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲን ይዘን እስከ ኮትዲቯር ድረስ ብንሄድ ቡናቸውን አይጠጡም፡፡ ገበያ የወደቀ ቀን ለቡና ማከማቻ መጋዘን ፍለጋ ነው የሚሯሯጡት፡፡
እኛ ግን ሌሎች አገሮች እንደሚቀኑብን ሕዝባችን ቡና ጠጪ መሆኑ ሰፊ ገበያ ፈጥሮልናል፡፡ የዓለም ገበያ ቢጠፋብን ዶላሩ ይቀራል እንጂ ቡና ማከማቸት አይደለም ችግራችን፡፡ ለዚህ መንግሥት ወደፊት በአምስት ዓመት የቡናን ምርት በእጥፍ አሳድጋለሁ ስላለና ያን ጊዜ ምናልባት የሕዝቡ ቁጥር ያንን ያህል ካልጨመረ ለአገር ውስጥ ፍጆታ በበቂ ይቀርብና ሚዛናዊ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ገበያ ዶላርን ከሚያስገኘው ገበያ ጋር ተወዳዳሪ ነው፡፡ ለምሳሌ ገበሬው ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ዋጋ አግኝቷል፡፡ ያንኑ ዋጋም ዘንድሮ ነጋዴውም ጭምር አብረው ይጠብቃሉ፡፡ የዓለም ገበያ ያንን ባይከፍለው የአገር ውስጥ ገበያው በጭለማም ይሁን በማጭበርበር ወይም በሌላ መንገድ ብቻ ቡናው አቆራርጦ መርካቶ ይገባና ተመልሶ ቡና ወደማያመርቱ አካባቢዎች ይሄዳል፡፡ ጥሩ ዋጋ ያስገኛል፡፡ የአገር ውስጥ ገበያው በኪሎ ከመቶ ብር በላይ ሲከፍል ሕጋዊ ገበያው ወይም ደግሞ ዓለም አቀፍ ገበያው ይህንን ማድረግ አለመቻሉ አንዱ ተፅዕኖ ነው፡፡ ሁለቱ ገበያዎች እርስ በርሳቸው ስለሚወዳደሩ ዶላር የሚያስገኘው ገበያ በቀዘቀዘ ቁጥር ቡናው ወደ ጥቁር ገበያው፣ ወደ ሕገወጡ ይሄዳል፡፡
ሪፖርተር፡- በምርት ገበያው ዋጋና በዓለም ገበያ ዋጋ መካከል የሚታይ ክፍተት መኖሩ አንዱ ማነቆ እንደሆነም ይነገራል፡፡
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ይህ እውነት ነው፡፡ ምርት ገበያ ቡናዎችን በደረጃቸው ነው የሚያገበያያው፡፡ የሆነው ነገር ምንድን ነው? ለምሳሌ ዘንድሮ የታጠበ የሲዳማ ቡና የተፈለገውን ያህል አልታጠበም፡፡ ምክንያቱም እሸት ቡና የሚባለውና መታጠብ የሚገባው ቡና በሚቀርብበት ጊዜ በኪሎ 17 ብር ስለደረሰ በርካታ ማጠቢያ ቦታዎች ቡናውን አላጠቡም፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ቡናው ካልታጠበ በደረቅ መልኩ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ በደረቅ ቡናነት በሚቀርብበት ጊዜ ገበያው ከመዳከሙ በፊት በጥሩ ዋጋ የሚገዙ ኤክስፖርተሮች አሁን የቀረበውን ያንን ጥቂት ቡና በከፍተኛ ዋጋ ገዙት፡፡ ምርት ገበያው ደግሞ አማካዩን ዋጋ ነው በነገው ዋጋ ላይ የሚያስቀምጠው፡፡ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ያሳያል፡፡ ሆኖም ነገ ስትሄድ በአንድ በኩል የኒውዮርክ ዋጋ ወድቆብሃል፣ ገዢህም የሚሰጥህ ዋጋ ካለፈው ወርና ሁለት ወር ያነሰ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ሦስት ዶላር ከ20 ሳንቲም ሲሸጥ የነበረ የሲዳማ ደረቅ ቡና አሁን ሁለት ዶላር ከ12 ሳንቲም ወርዷል፡፡ ስለዚህ ለደንበኛህ በሁለት ዶላር ከ12 ሳንቲም እሸጣለሁ ብለህ ስትገባ፣ ገበያው ግን የሚያወራው አስቀድሞ የሸጠውን ሰውዬ ዋጋ ነው፡፡ ይኼ ችግር አለ፡፡ በዚህ ምክንያት በ2.12 ዶላር የሲዳማን እንሽጥ የሚሉ ሰዎች የዚያኛው ዋጋ ገና ስላልወረደ ሊሸጡ አልቻሉም ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህ ሁሉ ችግሮች እያሉ ከቡና የወጪ ንግድ የሚጠበቀው የዘንድሮ ገቢ አንድ ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ እስካሁን የተገኘው ግን 300 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ዱሮ በመስከረምና በጥቅምት ወር የታጠበ ቡና ህዳር ላይ ለገበያ ይቀርብ ነበር፡፡ ዘንድሮ አልቀረበም፡፡ ያልቀረበን ቡና ደግሞ አትሸጥም፡፡ እኔ አልሸጥም፡፡ የዓመቱ የመጀመርያ ምርት ናሙናው ተወስዶ ለገዢዎች ይላካል፡፡ አሁን ይህ ሁሉ ሳይመጣ በጨለማ መሸጥ የሚሆን አይደለም፡፡ እርግጥ የሚሠሩ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ አብዛኛው ባይሠራም፡፡ ስለዚህ ቡናው ራሱ በወቅቱ አልደረሰም፡፡
ሪፖርተር፡- እጃችሁ አልገባም ማለት ነው?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ማጠቢያ ጣቢያውም ላይ ዘግይቷል፡፡ የአየሩ ሁኔታ፣ የዝናብ ጉዳይ ወይም ሌሎች ምክንያቶች ለመዘግየቱ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ሲደርስም ገበሬው ሠፈር የነበረው ዋጋ ሲታይ የገበሬው ወደ ላይ እየወጣ፣ ዓለም አቀፉ ወደታች እየወረደ ስለነበር ብዙ ማጠቢያ ጣቢያዎች ልንከስር ነው ብለው እጃቸውን ሰብስበዋል፡፡ ሌላው ቡና በብትን በኮንቴነር ይላክ ተብሎ የነበረበት ምክንያት ብዙም ባይሆን አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ነገር ግን እርሱ እስከዚህም ተፅዕኖ ያለው አይመስለኝም፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች ከጥቅምት እስከ ታህሳስ አጋማሽ ድረስ መሸጥ የሚገባንን ቡና አልሸጥንም፡፡ ገዢዎቻችን የታህሳስ መጨረሻው ላይ ወይም በእነርሱ ዲሴምበር ማብቂያ፣ አዲሱ ዓመትና የገና በዓላቸው ስለመጣ እኛም ሳንሸጥ እነርሱም ሳይገዙ እረፍት ወጥተዋል፡፡ ብንሸጥ ኖሮ ጥርና የካቲት ላይ የቡናውን ጭነት እናጧጡፍ ነበር፡፡ አልሸጥንም፡፡ ምርቱ በወቅቱ አልቀረበም፡፡ ሲቀርብም ግብይቱ ትክክል አልነበረም፡፡ እነኚህ ሁኔታዎች ተደማምረው አሁን ያለንበትን ቀውስ ፈጥረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ አሁን የመንግሥት አቋም ምን ሊሆን ይችላል?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- አሁን የዓለም አቀፍ ገበያው ዋጋ እንደ አምናው በከፍተኛ ደረጃ ላይ አይቆይም፡፡ ወደታች ይወርዳል፡፡ ይህንን የቡና ዋጋ መቀነስን መንግሥት እንደ መደበኛ ክስተት መውሰድ አለበት፡፡ የወጣ ይወርዳል፤ የወረደም ይወጣልና፡፡ ትናንት ጥሩ ገበያ አግኝተናል፤ ዛሬ ደግሞ ገበያው ወርዶብናል፡፡ ገበያው ከወረደብን ማድረግ ያለብን ጥርሳችንን ነክሰን መጠኑን መጨመርና የዋጋ ጉድለቱን ማካካስ ነው፡፡ ግብርና ሚኒስቴር፣ ንግድ ሚኒስቴር፣ ክልሎች ሁሉ መሥራት ያለባቸውና ላኪውም ማድረግ ያለበት፣ አሁን ጥሩ ዋጋ ማግኘት አለብኝ ሳይሆን ባለው ዋጋ ለመሸጥ መሞከር ነው፡፡
የዓለም ዋጋ ተከታዮች እንደመሆናችን በመጠን ያጣነውን በመጠን ማካካስ፣ በዋጋ ያጣነውን እንደገና ተጨማሪ መጠን አቅርበን ማሟላት ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢሊባቦር፣ የከፋ፣ የወለጋና የሲዳማ ምርት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ በመሆኑ ምርቱ መምጣት አለበት፡፡ ፈተናው ግን ምንድን ነው ከተባለ ገበሬው የዶላሩን ጉዳይ አለማየቱ ነው፡፡ እንዳለፈው ጊዜ መቶ ብር ክፈለኝ ቡናውን እሰጥሃለሁ ይላል፡፡ ነጋዴው ደግሞ አልችልም 70 ብር እከፍልሃለሁ ሲለው፣ ተወው 100 ብር የሚከፍል የአገር ውስጥ ገበያ ስላለኝ ብሎ በጨለማ ወደዚያ ይወስደዋል፡፡ ወደ ሕገወጡ ገበያ ይልከዋል፡፡ ስለዚህ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በሙሉ በአገር ውስጥ የቡና ንግድ ላይ በቂ ቁጥጥር ማድረግ አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ቡና ላኪው የአገር ውስጡን በሕጋዊ ገበያው ሊወዳደረው አይችልም፡፡ ካልቻለ ደግሞ የውጭው ገበያ መቅለጡ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በነበራችሁ በብትን አላላክ ውይይት ላይ ይህንን ተከትሎ አንዳንድ ገዢዎች ሸሽተዋል የሚል መከራከሪያ ተነስቶ ነበር፡፡
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ይኼ ጊዜያዊ ነው፡፡ ነገር ግን ወቅቱ የብራዚል ከፍተኛ ምርት የሚገባበት በመሆኑ ከአንተ ወይም ከኬንያ በአንድ ጊዜ አንድና ሁለት ሺሕ ቶን የሚገዙበት አይደለም፡፡ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ግዥ የሚፈጸምበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ የቡና መነሻ ናት፡፡ ለዓለም ገበያ ከ200 ሺሕ ቶን በላይ ያቀረበች፣ ከዓለም ስድስተኛ ከአፍሪካ አንደኛ አምራች አገር በመሆኗ፣ ገዢዎቹ እንዲሁ ዝም ብለው አንገዛም የሚሉበት ሁኔታ የለም፡፡ የሚሉት ምንድን ነው? ዛሬ በኮንቴነር አልገዛም ቀይር፣ በጆንያ መግዛት ነው የምፈልገው ይሉሃል፡፡ በጆንያ ስታደርግላቸው ደግሞ ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን ገዢዎች ያልመጡበት አንዱ ምክንያት የዓለም የኢኮኖሚ ጉዳይ ተጠቃሽ ነው፡፡ የአውሮፓ ኢኮኖሚ ተናግቷል፡፡ ግሪክን የሚያክል አገር ከአውሮፓ ኅብረት አባልነት ይሰረዝ እየተባለ ነው፡፡ አውሮፓን የሚያክል አኅጉር ቻይና ሄዶ እባካችሁ ኢኮኖሚው እንዳይወድቅ ቻይና ዕርዳታ መስጠት፣ ማገዝ አለበት እያለ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለ አንድ ቢሊዮን ዶላሩ የቡና የወጪ ንግድ ገቢ ዕቅድ ታዲያ ምንድን ነው ማለት የሚቻለው?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ኃላፊነት የተሰጣቸውም፣ ያልተሰጣቸውም ያለንን ቡና በሙሉ፣ ጥሩ ምርት ስላለ ሳይባክን ወደ ሕጋዊ ገበያ የሚሄድበትን መንገድ መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ ትግል ያስፈልገዋል፡፡ በአንድ በኩል የውጪው ገዢ በኢኮኖሚ ተዳከመ፡፡ በሌላ በኩል የአገር ውስጡ ገበያ ለኪሎ ከ100 ብር በላይ ከፍሎ እየጠጣ ነው፡፡ ተጨማሪም ይፈልጋል፡፡ ድንበር ጥሶ የሚሄድ ገበያ ወይም ኮንትሮባንድም እየታየ ነው፡፡ ወደ ሱዳን ድንበር ጥሶ መሄድ ጀምሯል፡፡
ሪፖርተር፡- ያለ ምርት ገበያው ዕውቅና ማለት ነው?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ያለ ማንም ዕውቅና፡፡ በኮንትሮባንድ ማለት ነው፡፡ ወደ ኤርትራም ይሄድ ይሆናል፡፡ አይታወቅም፡፡ ስለዚህ የአገር ውስጡን ሕገወጥና ድንበር ጥሶ የሚሄደውንም ለመቆጣጠር ዝግጁ መሆን ይኖርብናል፡፡ ትንሽ ቀበቷችንን አጥብቀን ከሠራን የተባለውን ገቢ የማናገኝበት ምክንያት የለም፡፡
ሪፖርተር፡- ሊገኝ ይችላል ብለው ያምናሉ?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- መሠራት አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ጊዜው ግን ቀድሞ ሄዷል፡፡
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- እርግጥ ሰባቱን ወር እንዲህ አጥተናል፡፡ ነገር ግን ያለፈውን እንዴት ማካካስ እንዳለብን ማሰብ ነው፡፡ ትናንት ያልበላነውን ቁርስ፣ ምሳ እንዲሁም ራት ዛሬ ላይ ደርቤ ልብላ ማለት መፈንዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህ እውነታ ነው፡፡ ትናንት ያልበላነውን ቁርስ ከዛሬው ጋር ደርበን መብላት ሊያስኬድ ይችል ይሆናል፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ያለፈውን ልናመጣው አንችልም፡፡ የምንችለው በቀሩን ወራት ጠንክረን መሥራት ብቻ ነው፡፡ ያለፈውን ትተን መልካሙን ለማምጣት መረባረብ ይኖርብናል፡፡ በጀት ዓመቱ መዝጊያ ድረስ ብቻ ሳይሆን፣ ሐምሌ፣ ነሐሴ፣ መስከረምም ልንሠራው እንችላለን፡፡ ዞሮ ዞሮ የአገር ገቢ ነውና፡፡ ነገር ግን ቡናው መባከን የለበትም፡፡
ሪፖርተር፡- ላኪዎች የኢትዮጵያን ቡና መለያ ወይም ትሬድ ማርክ እያስተዋወቁ እንዲሸጡ መንግሥት ይፈልጋል፡፡ ይኼ ተጨማሪ ጫና ነው ማለት ይቻላል?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- አይደለም፡፡ ጫና አይሆንም፡፡ መንግሥት ያለው የሲዳማን በሲዳማነቱ፣ የሊሙንም በሊሙነቱ ሽጡ ነው፡፡ ነገር ግን የሚገዛው ሰውዬ ይርጋጨፌን ለራሱ በሚያመቸው መንገድ ኢትዮጵያዊነቱን አሳጥቶ እንዳይሸጠው ጥንቃቄ ይደረግ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ ግን ቀላል ይሆናል እንዴ? ጃፓን ከኢትዮጵያ የምትገዛውን ቡና ሞካ ብላ በራሷ መለያ ብትሸጠውስ?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- እነርሱ ጥሩ ሕግ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ሞካ ብለህ በምትሸጥበት ጣሳ ላይ ከለጠፍክ፣ ቢያንስ 70 በመቶው ሞካ ቡና እዚያ ውስጥ መገኘት አለበት፡፡ አለበለዚያ ያልሆነውን ሆኗል ብሎ ሸማቹን ማጭበርበር አይቻልም፡፡ ሌላው ወደ ጃፓን ሲኬድ የምንፈራው በተቃራኒው ያለውን ነው፡፡ ይርጋጨፌ ብለው እውነት የእኛን ይርጋጨፌ ብቻ ነው የሚሸጡት? በእርግጥ የጓቴማላና የሌላው አገር አይጨመርበትም ወይ? ይኼ የእኛ ስጋት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ጎረቤት አገሮች ኬንያና ኡጋንዳ በአሁኑ ጊዜ ጥሩ የቡና ገበያ እያገኙ ነው ይባላል፡፡ ለመሆኑ ከኢትዮጵያ ምን የተሻለ ነገር ሠርተው ነው?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ይኼ ነገር ምንጩ ግልጽ አይደለም፡፡ ኬንያ በዓመት የምታገኘው የምርት መጠን እኛ በወር ወይም በሁለት ወር የምንሠራውን ነው፡፡ በተለይ ወደ ሚያዝያና ግንቦት ላይ እስከ 50 ሺሕ ቶን እንሠራለን፡፡ የኬንያ እኮ ዓመታዊ የኤክስፖርት መጠን 48 ሺሕ ቶን ነው፡፡ ይህ በጣም ትንሽ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን በዚህ ስድስት ወር ከታየው የኤክስፖርት አፈጻጸም አኳያ ጥሩ ገቢ አግኝተዋል፡፡ ያላቸውንም በአግባቡ ስለመሸጣቸውም ይነገራል፡፡
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- የእነሱ ሥርዓትና የእኛው የተለያየ ነው፡፡ የእነሱ ገበያ የቡና ቦርዳቸው በሚያወጣው ጨረታ ነው የሚካሄደው፡፡ ገዢው ቡናውን ጨረታው ላይ በዶላር ይገዛል፡፡ ያ ወደ ኬንያ ሽልንግ ይቀየርና ወይም ደግሞ ሽልንጉ ወደ ዶላር ተቀይሮ በዚህን ያህል ዋጋ ተሸጠ ይባላል፡፡ ከዚያ በኋላ ቡናው ወደ ሞምባሳ ይሂድ፣ አሊያም እዚያው ይቀየጥ፣ አገር ውስጥ ይጠጣ ወደ ኋላ የሚነሳ የቁጥጥር ጥያቄ ይሆናል ማለት ነው፡፡ አንዴ ዶላሩ ከተገኘ በኋላ ነገሩ ሁሉ አክትሟል፡፡ በአጭሩ የእኛና የእነርሱ አንድ አይደለም፡፡ የእኛ ከእነሱ የተሻለ በመሆኑ እነሱን ጭምር እያስተማርናቸው ነው፡፡ የምርት ገበያው አንዳንድ ድክመቶች ያሉበት ቢሆንም፣ ከአፍሪካ አለ ሊባል የሚችለው እርሱ ነው፡፡ ከደቡብ አፍሪካው ምርት ገበያ እንደሚበልጥ ተረጋግጧል፡፡ እርግጥ በአንዳንድ ምርቶች አቅርቦት መጠን ሊበልጡን ይችላሉ፡፡ እኛ የምናገበያያቸው እንደ ሰሊጥ ያሉ ምርቶች በአፍሪካ በከፍተኛ ሁኔታ ግብይት የሚካሄድባቸው እዚሁ እኛው ዘንድ ነው፡፡ በቡና ግብይቱም ከአፍሪካ እኛ ቀዳሚ ነን፡፡



