ከፊታችን የመኪኖች ግጭት አለ፡፡ ትራፊኮቹ እየተሯሯጡ ናቸው፡፡ ወደ ኋላ መዞርም አንችልም፤ መዓት መኪና አለ፡፡ ትንሽ ብንጠብቅ ይሻላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
የመኪናው አለቃ እንግዲህ አንተ ነህ እሺ እንጠብቅ፤ ለሦስት ሰዓቱ ስብሰባ ግን የግድ መድረስ አለብኝ፡፡ አንተ እንዴ እዚች ጋ ትንሽ ዳቦ መሸጫ አልነበረችም ወይ?
አዎን ነበረች፤ ሴትየዋ ዘጋቻት፤ ሴትየዋ ኢሕአዴግን አትወድም፤ አውቃ ዘጋቻት፡፡
ኢሕአዴግን ብትጠላ ገንዘብ አትጠላ፡፡
(ጥበቃው) ምክንያቱ እሱ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፣ ኢሕአዴግ መጥላት መውደድ ምን አመጣው፡፡ ሁለት ሺሕ ብር ግብር እከፍል የነበረው ሠላሳ ሺሕ አደረጉብኝ እያለች ታለቅስ ነበር፡፡ ኋላ መክፈል ካልቻልኩስ ልታሰር ነው እያለች ትጨነቅ ነበር፡፡ ፈርታና ደንግጣ ዘጋችው፡፡
(ሾፌሩ) አውቃታለሁ ፀረ ኢሕአዴግ ናት፡፡ እሷ ዳቦ ቤቱን ከዘጋች ሕዝብ ዳቦ አጥቶ ያምጻል ብላ ተስፋ አድርጋ ነው፡፡ ዓይነተኛ ኪራይ ሰብሳቢ ማለት እሷ ናት፡፡
(ጥበቃው) አንተ ነህ የኢሕአዴግ ጠላት፡፡
(ሾፌሩ) ምን?! በላ ተናገር የኢሕአዴግ ጠላት የኢሕአዴግ ሚኒስትር ሾፌር ሆነ በለኛ!
ምነው ምነው ተጯጯኋችሁ፡0፡
ክቡር ሚኒስትር ይህች ምስኪን ሴትዮ ለመዝጋት ስትወስን ተሳስታ ልትሆን ትችላለች እንጂ ጠላት አይደለችም፡፡ እንደዚህ እየፈረጅን ነው ሰዉን ያሸሸነው፡፡
ገባኝ፤ መጠንቀቁ ጥሩ ነው፡፡ እኔኮ ዳቦ ቤቱ አጠገብ የነበረው ማስታወቂያ ሁሌ ስለሚያስቀኝ እሱን ለማየት ዞር ስል ዳቦ ቤቱ ተዘግቶ አይቼ ነው፡፡
(ሾፌሩ) አንዳንዶቹ ጠላቶች ዳቦ ቤት ሲዘጉ፣ ሐቀኛ የኢሕአዴግ ወዳጆች ደግሞ ለልማት ቀንና ሌሊት እየተሯሯጡ ናቸው፡፡ ያቺን የቆርቆሮ አጥር አይዋት ክቡር ሚኒስትር ያቺ?
አዎን አየኋት፡፡
አንድ የማውቀው ደላላ ነው ለኢሕአዴግ ሕይወቱን የሚሰጥ ደላላ ነው አሁን አጥሮ ቤት ሊሠራበት ነው፡፡ እንዴት ኢሕአዴግ አልሙ እያለ ቦታ ባዶውን ይቀራል ብሎ ሁሌ ይቆጨው ነበር፡፡
(ጥበቃው) አይ ያንተ ነገር፡፡ ክቡር ሚኒስትር አደራ የሚሰሙት ሁሉ እውነት እንዳይመስልዎት፡፡ የራሱ ካርታ ሳይኖረው ማዘጋጃ ቤት ሳይፈቅድለትና ሳያውቀው ነው አጥር ልገንባ ያለው፡፡
የቀበሌው ሰውዬ ፈቅዶለታል፡፡ ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ባለፈው ሳምንት ውጭ እያሉ ቡና ልጠጣ ወደዚህ አካባቢ ስመጣ ሰዎች ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡ ደላላውንም አግኝቼው ነበር፡፡ የቀበሌው ሰውዬ ፈቅዶለታል፡፡ (ሾፌሩ)
ለቀበሌው ሰውዬ ጉቦ ሰጥቶ ከሆነስ? (ጥበቃው)
ክቡር ሚኒስትር ይህ ደላላ ልማታዊ ደላላ ነው፡፡ ኢሕአዴግን በጣም በጣም ይወዳል፡፡ እርስዎን እንደሚጠራዎት ያውቃሉ? ‹‹አባቴ›› ነው የሚለው፤ አባቴ ደህና ናቸው ወይ? አባቴ ምን ይፈልጋሉ ይለኛል፡፡ ከእኔ ዕድሜ ተቀንሶ ለእሳቸው ቢሰጥ ነው የሚለው፡፡ ከደደቢት ጀምሮ እስከ አዲስ አበባ ያለውን የኢሕአዴግ ታሪክ በቃሉ ያውቀዋል፡፡
ጓድ ጥበቃ ምነው ዝም አልክ?
እንደዚህ ዓይነቱ አመለካከት ገደል እንዳይከተን ብቻ፡፡
ለምን?
ክቡር ሚኒስትር ሚስኪኗን ሴትዮ ‹‹ጠላት›› ተባለች፤ አጭበርባሪው ደላላ ልዩ ወዳጅ አልነው፤ ወዳጅም ጠላትም መለየት አቅቶናል፡፡
[ቢሮ ደረሱ፤ መንገድ ላይ ጊዜ ስላጠፉ ጸሐፊያቸውን በአስቸኳይ ተሰብሳቢዎችን እንድትጠራ አዘዙና ስብሰባ ጀመሩ]
እንግዲህ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ብለን ሥራ ከጀመርን አንድ ዓመት ሆኗል፡፡ ከምርጫው በኋላ ማለት ነው፡፡ በዚህ ዙርያ እንቅስቃሴያችሁን ገምግሙና ሪፖርት አቅርቡ ተብለናል፡፡ ሁሉም መሥርያ ቤት ተብሏል፡፡ የሚኒስቴሩ መሥርያ ቤት የአመራር አባላት የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፡፡ አጀንዳውን ቀደም ብዬ አሳውቄያለሁ፡፡ ጊዜ ስለሌለን በቀጥታ ወደ አጀንዳው እንግባ፤ ሐሳባችሁን በግልጽና በመረጃ እያስደገፋችሁ ሰንዝሩ፡፡
ክቡር ሚኒስትር የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከተጠበቀው በላይ እየሔደ ስለመሆኑ የሚያሳየን ባለሀብቱ እየገዛው ያለው ቦንድ ነው፡፡ በቀደም አንድ ግለሰብ የሠላሳ ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛቱን ስሰማ እንባ ነው የተናነቀኝ፡፡ አንዱ አስር ሚሊዮን፣ አንዱ ስምንት ሚሊዮን ሌላው አስራ አምስት ሚሊዮን እያሉ እየተረባረቡ ቦንድ ሲገዙ ማየት ኢትዮጵያ ምን ያህል ትራንስፎርም እንደሆነች ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡ እንኳን ይህን ሳላይ አልሞትኩ ነው ያልኩት፡፡ በነገራችን ላይ እንደዚህ የተሰማኝ እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡ ሁሉም ሕዝብ ‹‹ተደሰተ››፣ በአገራችንም በኢትዮጵያም በመላው ዓለምም ‹‹ተደነቀ››፣ ‹‹አበረታች›› የመጀመርያ ዓመት ነበር፡፡
[ሌላ የዘርፍ ኃላፊ] ክቡር ሚኒስትር የምንሰጠው አስተያየት በጥንቃቄና በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ የቦንድ ግዢና የኢንዱስትሪው መጠናከር እንዳይምታታብን እንጠንቀቅ፡፡ ቦንድ እየተገዛ ነው? አዎን እየተገዛ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ቦንድ የገዛው ሁሉ የዚህ ዓመት እንቅስቃሴው አመቺ አትራፊና አስደሳች ነበር ማለት አይደለም፡፡ ከነበረው ገንዘብ ሰጥቶ ይሆናል፡፡ በዚህ ዓመት ግን ችግር አጋጥሞት ሊሆን ይችላል፡፡ ቦንድ ግዢ ሌላ፣ የዓመት እንቅስቃሴ ሌላ፡፡
[ሌላ] አሁን የተባለው አባባል ትክክል ነው አናምታታው፡፡ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሠማሩት በኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ የማምረት ሒደታቸው እየተስተጓጐለ ነው፡፡ የግሽበቱ ሁኔታም የሚገዙት ሁሉ ውድ ሆኗል፡፡ ጥሬ ዕቃና ማሽን መለወጫ ተወደዋል፡፡ በአዲሱ የባንክ አሠራርም ብድር ማግኘት ተቸግረዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች በባለሀብቱ ላይ አለመረጋጋት ፈጥረዋል፡፡ ብዙዎችም የማምረት ሒደታቸው እየመነመነ ነው፡፡ በዚህ ዓመት የተከሠቱት ችግሮች ስለሆኑም በዚህ ዙርያ የነበረን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንዳሰብነው ግቡን እየመታ አይደለም፡፡ ይህ ችግር እያለ ለሚሌኒየሙ ግድብ ቦንድ መግዛቱ ባለሀብቱን ያስመሰግነዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ሥራው የተሳካ ነበር ማለት ግን አይደለም፡፡ ክቡር ሚኒስትር እየተጠነቀቅን እንገምግም፡፡ መንግሥትን እንዳያሳስት፡፡
ሆን ብለህ መንግሥትን እያሳስትክ ነህ እያላችሁኝ ነው? የዓባይ ግድብ ለማሳካት ቦንድ ግዢ ያለው ሚና አይገባችሁም ማለት ነው? ወይስ የተሰበሰብኩት ከግብፅ ኃላፊዎች ጋር ነው?
[ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው] እንዴ፣ እንዴ፣ እንዴት እንደዚህ ትላለህ? አጀንዳውኮ ስለቦንድ አይደለም፡፡ የቦንድ ግዢውንኮ የተቃወመ የለም፡፡ እየገመገምን ያለነውኮ መሥርያ ቤታችን ከሚመለከተው የኢንዱስትሪ ሥራ አንጻር ሒደቱ ምን ይመስል እንደነበር ነው፡፡
ባለሀብቱ ለዓባይ፣ ለግድቤ! እያለ ቼኩን በደስታና በፈገግታ ላጥ አድርጐ ሲሰጥ ኃላፊዎች ግን ከመደሰት ይልቅ ሲሰጉና ሲተክዙ ሳይ ገርሞኝ ነዋ!
አንዳንድ ስታቲክስ ስናይ ለምን ብለን እንድንጠየቅ እንገደዳለን፡፡ ለኢንዱስትሪ ብለው መሬት ወስደው 60 ከመቶ የሚሆኑት ሥራ አልጀመሩም፡፡ የመሬት ቢሮክራሲ አደናቀፈን የሚሉ አሉ፤ ኤሌክትሪክ አጣን ያሉም አሉ፤ ይሠራል የተባለው መንገድ አልተሠራም ያሉም በርካታ ናቸው፡፡ የባንክ ብድር ተዘጋብን፤ ጥሬ ዕቃ ማስገባት አቃተን የሚሉም አሉ፡፡ ይህንኑ ችግር ማየትና ማሰብ ተገቢ ነው፡፡
[ሌላ] ክቡር ሚኒስትር አሁን ያሉት ትክክል ነው፡፡ በቦንድ መደበቅ ማለት ያለውን ችግር ማድበስበስ ማለት አይደለም፡፡ የችግሩን አስከፊነት መረዳት ደግሞ ፀረ ግድብ መሆን ማለት አይደለም፡፡ እኔ ወዳጅ ነኝ ሌላ ጠላት ነው የሚል አመለካከት በመሃላችን መሰማቱ ግን አሳፋሪ ነው፡፡ አጉል ብልጣ ብልጥነት ነው፡፡
[የስብሰባው መንፈስ ስላላስደሰታቸው ረጋ ብለው አስበውና ተመካክረው ለመቀጠል ለሚቀጥለው ቀን አስተላለፉት፤ አሁንም ከሾፌሩና ጥበቃው ጋር እያወሩ ወደ ቤት ሔዱ]
በክፍለ ከተማ ኃይለኛ ግምገማ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡ (ሾፌሩ)
ውጤቱስ?
ጥሩ ነበር፡፡ በሙስና የተዘፈቁት ተገመገሙና ተባረሩ፡፡
(ጥበቃ) መረጃ መስጠትህ ካልቀረ በሚገባ ስጥ እንጂ፡፡
ምን አስቀረሁ?
ያ ለዚያ ወዳጅህ ልማታዊ ደላላው አለአግባብ መሬት የሸጠው የቀበሌ ሹመኛም በሙስና ተገምግሞ ተባረረ ብለህ ንገራቸው እንጂ፡፡
ተባረረ?
አዎን ክቡር ሚኒስትር ተባረረ፡፡
እንግዲያውስ ከዚህ ወንድምህ ተማር፡፡ አንተ በጭፍን ልማታዊ ስትለው የነበረው እሱ ግን ሙሰኛ ሊሆን ይችላል ይልህ ነበር፡፡ ሰውን በተግባር መዝን፤ የአፍ ነገር አሁን ሁሉም ብልጣ ብልጥ ሆኗል፡፡
(ጥበቃው) የዳቦ ቤቷ ሴትዮም አቤት ብላ የተመደበላት ተሻሽሎላት አሁን ዳቦ መሸጫውን ከፍታ ሥራዋን ቀጥላለች፡፡ እኔም ሔጄ ችግሯን ስሟት ብዬ ተናግሬ ነበር፡፡ ሰው ሲበደል አይቶ እንዳላየ ማለፍ ስለማልፈልግ፡፡
ጥሩ ጥሩ አደረግክ ጐሽ፤ ስማ ጓድ ሾፌር ያንተ ሁለቱም ግምገማዎችህና መረጃዎችህ ስህተት ነበሩ፡፡ ጠላት ስለሆነች ዘጋችው አልከኝ፡፡ ጠላት አይደለችም፡፡ ወዳጅ ያልከው ደግሞ ሙሰኛ ሆኖ ተገኘ፡፡
[በዚህ እየተሳሳቁ ቤት ደረሱ፡፡ ክቡር ሚኒስትር እንቅልፍ አልወሰዳቸውም፡፡ እኔስ ምን ያህል ነው የተሳሳተ መረጃ ተቀብዬ ውሳኔ የምሰጠው? እኔ ስንት የተሳሳተ መረጃ ለበላይ አካል ሰጥቼ የተሳሳተ ውሳኔ በበላይ አካል እንዲወሰን አድርጌያለሁ? ብለው ሲያስቡ አደሩና ጠዋት ቢሮ ገብተው የሕግ ክፍል ኃላፊውን ጠሩት]
አቤት ክቡር ሚኒስትር?
ባለፈው ዓመት አምስት አቤቱታዎች ቀርበውልን ነበር፡፡ ከኢንቬስተሮች የመጡ አቤቱታዎች ነበሩ፡፡ እስቲ እነሱን ፋይሎች ይዘህልኝ ና፤ የሰጠነውን ውሳኔ ቁጭ ብለን እንነጋገርበታለን፡፡
እሺ ክቡር ሚኒስትር እንደአጋጣሚ እኔም ስለነርሱ ከእርስዎ ጋር ለመወያየት ፈልጌ ነበር፡፡
[ፋይሎቹ መጡ] ይኸውልዎት በዚህኛው እንጀምር፡፡
ይህንን ለምን ነበር ውድቅ ያደረግነው?
ክቡር ሚኒስትር መረጃ ስናሰባስብ ሰዎቹ ኢሕአዴግን ይጠላሉ፤ ከተቃዋሚዎች ጋር ይተባበራሉ፤ የሚል ወሬ ሲደርሰን ውድቅ አደረግነው፡፡
ቢቃወሙስ መብታቸው አይደለም ወይ?
እሱ ብቻ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፤ ሐቁ ደግሞ በተቃራኒው ነው፡፡ ለእኛ መረጃ የሰጡን ሰዎች ከነሱ ጉቦ ለመውሰድ ፈልገው አንሰጥም ስላሏቸው በቂም በቀል የውሸት መረጃ ለእኛ ሲሰጠን እኛ አምነን ተቀበልናቸው፡፡
የተሳሳተ መረጃ የሰጡን የት አሉ?
አሁንማ ሲያጭበረብሩ ተይዘው ፍርድ ቤት እስር ቤት ከቷቸዋል፡፡
እሺ ቀጥሎ ያለውስ?
የዚህ ፋይል ደግሞ በጣም ያሳዝናል፡፡ የመንግሥት ወዳጅ ነኝ የሚል አንድ ግለሰብ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ተጣልቷል፡፡ እነሱን ለማጥቃት የማያደርገው እንቅስቃሴ የለም፡፡ የውሸት ዶክሜንቶች እኛ ጋ እንዲደርስ አደረገ፡፡ እኛም በእነሱ ላይ መሠረት አድርገን ጥያቄአቸውን ውድቅ አደረግነው፡፡
ጉድ! ጉድ!
ክቡር ሚኒስትር ሌሎችም ተመሳሳይ ናቸው፡፡
ለበላይ አካል ያስተላለፍነው የተሳሳተ ነገርስ አለ ወይ?
አዎን አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡
ምን?
ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ማብራርያ ተጠይቀን በሦስት ፋይሎች ላይ የተሳሳተ መረጃ ሰጥተናል፡፡ እንዲያውም አቤት ብለው እዚያው ቀጠሮ ሲጠይቁ እኛ በሰጠነው መረጃ መሠረት የቀጠሮ ዕድል ተከልክለዋል፡፡
ሌላስ?
የእንባ ጠባቂ፣ የፀረ ሙስናና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በሁለት ፋይል መረጃ ጠይቆን የተሳሳተ መረጃ ሰጥተናል፡፡
ወንጀለኞች አይደለንም ታዲያ?
እ . . . እጅግ በጣም ከፍተኛ ስህተት ፈጽመናል፡፡ ስህተት ሳይሆን ወንጀል፡፡
ይህ አንድ ነገር ሆኖ ሌላው ማወቅ የምፈልገው ነገር ለምን እንደዚያ አደረግን የሚል ነው፡፡
እሱም ያኔ ይከብድ ይሆናል እንጂ አሁን ሳየው መልሱ ቀላል ነው፡፡
ቀላል ከሆነ አስረዳኝ፤ እስቲ ለምን እንደዚያ ዓይነት ስህተት ፈጸምን?
ደጋፊ ነን፤ ኢሕአዴግ ነን፤ እያሉ የሚቀርቡን ሰዎች መቶ በመቶ እናምናቸዋለን፡፡ ሕግን ተከትሎ የሚሠራና የማያወድሰንን ግን አናምነውም፡፡ ሰው ያለንን እንሰማለን፤ ለመታለልና ለመጭበርበር በራችን ክፍት ነው፡፡
ትክክል፡፡
እ. .
የተበደሉትን የምንክስበት መንገድ የለም? ያሳሳቱንን የሚቀጡበት መንገድ የለም?
በእውነት የመከሰስና የመቀጣት ጉዳይ የግድ መኖር አለበት፤ ግን. . .
ግን ምን?
ሌሎችን ያጠቁ እኛንም ለማጥቃት ወደ ኋላ አይሉም፡፡
እና?
ወይ አለማጥቃትና ዝም ማለት ነው፤ አሊያ ደግሞ ለሐቅና ለሕግ የበላይነት ጥቃት ለመቀበልም ዝግጁ ሆኖ መታገል ነው፡፡
የለም የለም ዝም ብለንማ ማየት የለብንም፤ ለነገ ጠዋት ፋይሎቹን ሁሉ አዘጋጅልኝ፤ ወደ መዝገብ ቤት መልሳቸውና ነገ ጠዋት ታመጣቸዋለህ፡፡
እሺ፡፡
[በነገው ጠዋት ክቡር ሚኒስትሩ የሕግ ክፍል ኃላፊው ጠሩት]
እሺ ፋይሎችን አዘጋጀህ?
ኧረ ክቡር ሚኒስትር . . .
ኧረ ምን?
ፋይሎቹ በሙሉ ጠፉ፡፡
እንዴት ጠፉ? የመዝገብ ቤት ኃላፊውን አነጋገርከው?
የመዝገብ ቤት ኃላፊውም ቢሮ አልገባም፤ ቤት ብንደውልም የለም፡፡
የት ሔደ አሉህ?
ኬንያ!
ዋና ደጋፊያችን ነው ስትለኝ አልነበረም?



