Thu05172012

Go to :English Edition

Back ኪንና ባህል ኪንና ባህል የምሥራቅ አፍሪካን ‹‹ጎስፕል›› ያሸነፈው ሙዚቀኛ ዳዊት ጌታቸው

የምሥራቅ አፍሪካን ‹‹ጎስፕል›› ያሸነፈው ሙዚቀኛ ዳዊት ጌታቸው

  • PDF

ዕድሜው ገና 24 እንኳን ባይሞላም ብዙዎች በጣም ጐበዝ ሙዚቀኛ እንደሆነ ይናገሩለታል፡፡

ዳዊት ጌታቸው ባለፈው ወር በተካሔደው የምሥራቅ አፍሪካ ሙዚቃ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ ‹‹ጐስፕል›› (መንፈሳዊ) በተባለው ዘርፍ ‹‹ከአድማስ ባሻገር›› በተሰኘ ሥራው ሊያሸንፍ ችሏል፡፡ በመካነ ኢየሱስ የጃዝ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ፒያኖ ከማስተማሩም በተጨማሪ ብዙ መዝሙሮችን አቀናብሯል፡፡ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የመዝሙር ዲቪዲ ሠርቶ አጠናቅቋል፡፡

ዲቪዲው ከ40 በላይ ሙዚቀኞችን በማሳተፍ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተቀረፀ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ እየቀረ የመጣውን ‹‹ቢግባንድ›› አሁን ያለውን የሙዚቃ አካሔድን ሊቀይር እንደሚችል ማኔጀሩ ታደሰ ታጠቅ በሙሉ ልብ ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያን ስም ያስጠራበት ሽልማቱን እና መጪው ሥራዎቹን በተመለከተ ዳዊት ጌታቸው ከጥበበሥላሴ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኛውን ጊዜ መዝሙር ለውድድር ማቅረብ የተለመደ አይደለም አንተ እዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ እንዴት አሰብክ?

ዳዊት
፡- ይሔ ነገር የመጣው ለገና በዓል በዚህ ዓመት ካደረግነው ኮንሰርት በኋላ ነው፡፡ በእዚህ ኮንሰርት ላይ የኛን ዝግጅት ሊያይ የመጣ ሲሳይ የሚባል ሰው ነበር፡፡ ያደረግነውን ካየ በኋላ በጣም ተደስቶ እሱ አልበሜን ለውድድር ላከው፡፡ ብዙ ጊዜ መዝሙር ሲዘመር ዓላማው ለውድድር ወይም ለመሸለም ሳይሆን ለሌላ ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ነበሩ? አሸንፋለሁ ብለህስ አስበህ ነበር?

ዳዊት
፡-አምስት ያህል ነበርን፡፡ በጐስፕል ዘርፍ የተወዳደርነው ናቲማን፣ ኢዮብ መኮንን፣ ኢትዮ ከለር፣ መቅረዝ የሚባል ቡድን እና እኔ ነው፤ ከዚህ ስሔድ እጩ እንደነበርኩ አውቄያለሁ፡፡ በጣም ደስ ይላል፡፡ አዳራሹ ውስጥ ስሜ ሲጠራ ብዙ ሰዎች አላወቁኝም፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ግንኙነታቸው በጣም ጠንካራ ነው፡፡ የሩዋንዳ፣ የኬንያ አርቲስት ሲጠራ አዳራሹ ውስጥ ያለ ሰው በሙሉ ያጨበጭባል፡፡ እኔን ግን ማንም አላወቀኝም ነበር፡፡ ከ6,000 ያህል ተወዳዳሪዎች አራት ተወዳዳሪዎች ተመረጡ፤ ከዚያም እኔ አሸነፍኩ፡፡

ሪፖርተር፡- በማሸነፍህ ምን አገኘህ?

ዳዊት
፡- የገንዘብ ሽልማት አልነበረውም፡፡ የነበረብኝን ወጪ ሁሉ ግን ሸፍነውልኛል፡፡ የእነሱን ዘፈኖች ካየሁ በኋላ የኛን ሙዚቃ ጥራቱ በጣም ደካማ እንደሆነ ነው የተረዳሁት፤ እናም ከሌሎች አርቲስቶች ጋር መሥራት እንደምችል አሳይቶኛል፡፡ እቦታው ላይ ስደርስ ያሰብኩት በቃ አንድ ተወዳዳሪ ነኝ ብዬ ነበር፡፡ ምክንያቱም ባየኋቸው ሥራዎች እነሱ በጣም ሌላ ደረጃ ላይ እንዳሉ አሳይቶኛል፡፡ ፕሮዳክሽናቸው የሚገርም ጥራት አለው፡፡ እኔ በድምፅ ብዙ ባልሳተፍም እደርሳለሁ፡፡ ከዚያ በተጨማሪ አቀናብራለሁ፤ በሁሉም ነገር እግዚአብሔር ረድቶኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ያሸነፍክበትን አልበም መቼ ነው የሠራኸው?

ዳዊት
፡- አልበሙ የተሠራው ከዓመት በፊት ነው፡፡ የተሠራውም ስቱዲዮ ውስጥ ነው፡፡ ብዙ ጊታር አለበት፡፡ በዝቅተኛ ብር ነው ፕሮዲውስ የተደረገው ያሸነፍኩበት ሥራ  ከመድረክ የቀረበ እንዲመስል ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን አሁን ሳስበው በቀጥታ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ የቀረፅነውን ቢያዩ ኖሮ ብያለሁ፡፡ ይሄ በጣም ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ለኔ አልበሙ ጅማሪዬ ነው፡፡ ይሄንን እንድሠራ ያነሣሣኝም ይሄ አልበም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሙዚቃ መሣርያ የሚያጅቡ 40 ሰዎች እንደተሳተፉ ሰምተናል፡፡ በጠቅላላው ምን ያህል ሰዎች ነበር የተሳተፉበት?

ዳዊት
፡- በአጠቃላይ ከ100 ሰዎች በላይ ተሳትፈውበታል፡፡ በውስጤ የነበረውን የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከጃዝ ሙዚቃ ጋር አጣምረነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ይሄንን ሥራ ለመሥራት ሐሳቡ እንዴት መጣ?

ዳዊት
፡- ከዚህ በፊት ደብረ ዘይት ላይ ኮንሰርት አዘጋጅተን ነበር፡፡ ያ ኮንሰርት ሪከርድ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ለደብረ ዘይት አካባቢ ሰዎች ብቻ የተወሰነ ነበር፡፡ ስለዚህ ይሄንን ኮንሰርት አዲስ አበባ ለመድገም አሰብን፡፡ እናም የብሔራዊ
ቴአትሩ በብዙ ነገር የተሻለ ነበር፡፡ ብዙ ሰዎችም ተሳትፈውበታል፡፡ ቪዲዮ ዳይሬክተር፣ ሳውንድ ማን፣ በአጠቃላይ ብዙ ሰዎች የተሳተፉበት ሥራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት በትልቅ ባንድ የሚሠሩ ኮንሰርቶችም ይሁኑ ፕሮዳክሽኖች በጣም ውድ ናቸው፡፡ የአንተስ ልምድ እንዴት ነው?

ዳዊት
፡- በጣም ውድ ነው፡፡ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ጉልበት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛው ሙዚቃ ከየትኛው ጋር እንደሚሔድ ማወቅ በጣም ፈታኝ ነው፡፡ ወደ ወጭው ስንመጣ ለእያንዳንዱ ሰው መከፈል አለበት፡፡ ያን ሁሉ ሰው መሸከም የሚችል ሳውንድ ሲስተም ማግኘትም ከባድ ነው፡፡ ምንም እንኳን የብዙ ሰዎች ድጋፍ ባይለየንም ብዙ ውጭ ነበረብን፡፡ ለደብረ ዘይቱ ኮንሰርት 70,000 ብር እንዲሁም ብሔራዊ ቴአትር ለነበረውም 80,000 ብር አካባቢ አውጥተናል፡፡ ነገር ግን ይሄ ወጭ በመድረክ ላይ ለነበረው ሲሆን ከዚያ በኋላም ሌሎች ወጭዎች ተጨምሮበታል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት የሚሠሩ ብዙ ሥራዎች ተቀናብረው የሚያልቁት በአንድ ስቱዲዮ ውስጥ ነው፤  ይሄንን ሁኔታ እንዴት ታየዋለህ?

ዳዊት
፡- ይሄ ነገር የምርጫ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚሠሩ ሙዚቃዎች በአብዛኛው የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ቀጥታ ገብተውበት አይሠራም፡፡ ወደተለያዩ አገሮች ስንሄድ የሚሠሩት የሙዚቃ ጥራት በጣም የሚገርም ነው፡፡ እኛ አገር ይሄ ሊሆን ያልቻለበት ምክንያት አንድ ስቱዲዮ ውስጥ የተለያዩ የሙዚቃ መሣርያዎችን ድምፅ ለማምጣት ስለማይሞከር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይሄ ዲቪዲ ምን ያህል ሥራዎችን አካትቷል? ለመሥራትስ ምን ያህል ጊዜ ፈጅቷል?

ዳዊት
፡- ብዙ ነገሮችን ጨርሰናል፡፡ በኮንሰርቱ ላይ የነበሩ አሥራ አንድ መዝሙሮች  ሲካተቱበት ሌሎች ተጨማሪ ትራኮችም አሉበት፡፡ ዲቪዲውን በአንድ ላይ ለማምጣት ስምንት ወር ያህል ወስዶብናል፡፡