የኩባንያው ማርኬቲንግ ዲፓርትመንት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ኃይለ ሚካኤል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዲዲቲ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ እንዳይውል በመደረጉ ኩባንያው ከ450 ቶን በላይ ክምችት ለመያዝ ተገዷል፡፡ ኃላፊው ጨምረው እንደገለጹት፣ የተቀረውን ክምችት ለመሸጥ የሚተባበራቸው አካል ካለ አብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አዳሚ ቱሉ ይህንን ኬሚካል ለመሸጥ የተስማማው አንዱን ኪሎ በ4.50 ዶላር ሲሆን፣ አቶ ተስፋዬ ዋጋው ጥሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ላለፉት ዘመናት ኢትዮጵያ ወባን ለማጥፋት ዲዲቲ ስትጠቀም ቆይታለች፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዲዲቲ ጥቅም ላይ እንዳይውል ዕገዳ ቢጣልበትም፣ የዓለም የጤና ድርጅት እንዲያውቀው ተደርጎ ወባን ለማጥፋት ብቻ የተወሰኑ አገሮች እንዲጠቀሙ ተፈቅዶላቸዋል፡፡
ከእነዚህ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ በመሆኗ ነው ወባን ለማጥፋት ዲዲቲ ስትጠቀም የቆየችው፡፡ ይሁንና ኬሚካሉ በሰው ጤናና በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑና ይህንኑ ከግንዛቤ በማስገባት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በ2001 ዓ.ም. ዲዲቲ ጨርሶ ጥቅም ላይ እንዳይውል አግዷል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በአገሪቱ ያለው የዲዲቲ ክምችት ኤክስፖርት ይደረጋል እንጂ፣ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ አይውልም ሲሉ በወቅቱ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡
ከሁለት ዓመታት በላይ ከቆየ በኋላ ነው ኩባንያው ገዢ አግኝቶ በአሁኑ ወቅት ወደ ቦትስዋና ለመላክ ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኘው፡፡ ወባን ለመከላከል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዕውቅና የሰጠው አዳሚ ቱሉ ለሚያመርተው ዴልታ ሜትሮን የተሰኘ ኬሚካል ነው፡፡
ይህ ኬሚካል ከዲዲቲ ጋር ሲነጻጸር ጎጂነቱ አነስተኛ ቢሆንም፣ ወባን የምታስተላልፈው የወባ ትንኝ እየተቋቋመችው መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህም በመሆኑ ኩባንያው አዲስ ፀረ ወባ ኬሚካል ለማምረት በዝግጅት ላይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ በ2007 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ ወባን የመቆጣጠር ዕቅድ ነድፋለች፡፡ እስካሁን ባገኘችው ውጤትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝታለች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ 15 ሚሊዮን ቤቶች ይኖራሉ ተብሎ ሲገመት፣ ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ 10 ሚሊዮን የሚሆኑት የወባ ትንኝ ይጎበኛቸዋል የሚል ግምት አለ፡፡


