ከሁለት ዓመት በፊት በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት አቅራቢያ በደረሰበት ድንገተኛ አደጋ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ላይ ሲካሄድ የነበረው የአደጋ ምርመራ የመጨረሻ ሪፖርት፣ በትናንትናው ዕለት በሊባኖስ ሥራና ትራንስፖርት ሚኒስቴር ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ አየር መንገዱ አውሮፕላኑ አየር ላይ ነው የፈነዳው በማለት ሪፖርቱን ተቃውሞታል፡፡ በሊባኖስ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ይፋ የተደረገው የመጨረሻ የአደጋ ምርመራ ሪፖርት እንደተጠበቀው፣ ‹‹የአብራሪዎቹ ስህተት›› እንደሆነ አድርጎ አቅርቦታል፡፡ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ሪፖርቱ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊዎች ትናንት በአዲስ አበባ ሒልተን በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የምርመራው ሒደት በግጭት ተጀምሮ በግጭት እንዳለቀ በከፍተኛ የሐዘን ስሜት ገልጸው፣ ሪፖርቱ ያልተሟላ፣ እርስ በርሱ የሚጋጭና በተሳሳቱ መረጃዎች የተሞላ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አውሮፕላኑ በአየር ላይ እንደፈነዳም አስረድተዋል፡፡
አደጋው ከደረሰ ጊዜ ጀምሮ የሊባኖስ ባለሥልጣናት የአደጋው መንስዔ ምን እንደሆነ በተለያየ ጊዜያት የተለያዩ መላምቶች ሲሰጡ የከረሙ ቢሆንም፣ በተቃራኒው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊዎች የሊባኖስ ባለሥልጣናት ኃላፊነት ከጎደለው ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ከማሳሰብ አልፈው፣ የአደጋው መንስዔ ምን ሊሆን እንደሚችል አልተነበዩም ነበር፡፡ ለዚህም የሰጡት ምክንያት ይህን እንዳናደርግ ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ድንጋጌ ይከለክለናል የሚል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ክልከላ በትናንትናው ዕለት ተነስቷል፡፡ የሊባኖስ የሥራና ትራንስፖርት ሚኒስትር ሚስተር ጋዚ አሪዲ በቤይሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ፣ በእኩል ሰዓት በአዲስ አበባ ሒልተን የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናት ላለፉት ሁለት ዓመታት በሆዳቸው አምቀው የያዙትን ጉድ በሙሉ አውጥተው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም የምርመራው ሒደት በአሳዛኝ ሁኔታ ያለስምምነት ማለቁን ገልጸው፣ ሒደቱ እጅግ አስቸጋሪና የተወሳሰበ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ “ማንኛውም የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ሒደት ሦስት ክፍሎች አሉት፡፡ እነርሱም የመረጃ ስብስባ፣ ትንተናና ድምዳሜ ናቸው፡፡ የተሰበሰቡት መረጃዎች ትክክለኛነት መረጋገጥ አለበት፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች መረጃ መለዋወጥ ይገባቸዋል፡፡ ማንኛውም ወገን የተጠየቀውን መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት፤” ያሉት አቶ ተወልደ፣ የሊባኖስ ባለሥልጣናት ለዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ሕግ ተገዢ አልሆኑም ብለዋል፡፡
አደጋው በደረሰ ማግስትና ገና ምንም ዓይነት መረጃ ባልተሰበሰበበት ወቅት የሊባኖስ ባለሥልጣናት የአደጋውን መንስዔ አስመልክተው ያሻቸውን ሲናገሩ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተወልደ፣ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ብናስብም ልናስቆማቸው አልቻልንም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና ያላቸውን የመንገደኞች ግለታሪክ፣ አደጋው በደረሰ ዕለት በቤይሩት ራፊቅ ሃሪሪ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኙ ደኅንነት ካሜራዎች የተቀረፁ ፊልሞች፣ በሻንጣ መፈተሻ መሣርያዎች የተነሱ ፊልሞች፣ እንዲሁም የአስከሬን ምርመራ ውጤት እንዲሰጧቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም፣ የሊባኖስ ባለሥልጣናት በእንቢተኝነታቸው እንደፀኑ አቶ ተወልደ ገልጸዋል፡፡ አስከሬናቸው ሳይታይና ሳይመረመር የተቀበሩ መንገደኞች እንዳሉና ይህ ሆን ተብሎ የተፈጸመ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ከአውሮፕላኑ ስብርባሪ ውስጥ ከባህር የወጣው ስምንት በመቶ ሲሆን፣ 92 በመቶ ባህር ውስጥ ቀርቷል፡፡ የሊባኖስ ባለሥልጣናት ቀሪውንና ዋናውን የአውሮፕላን አካል ከባህር ለመውጣት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ለዚህም የሰጡት ምክንያት ከአደጋው ጋር ተያያዥነት የለውም የሚል ነበር፡፡ እኛ በራሳችን ወጪ የአውሮፕላኑን ዋና አካል ከባህር እናውጣ ብለን ስንጠይቅ ብታወጡትም በምርመራው ሒደት አናካትተውም ብለዋል፤” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በርካታ ወሳኝ የሆኑ መረጃዎች ሆን ተብለው በምርመራ ሒደቱ እንዳይካተቱ እንደተደረገ የገለጹት አቶ ተወልደ፣ አደጋውን የተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ የዓይን ምስክሮች በተለይ ተረኛ የአየር ትራፊክ መኮንኖች በምርመራ ሒደቱ ላይ ቀርበው ቃል እንዳይሰጡ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ተረኛ መኮንኖቹ አውሮፕላኑ ከመውደቁ በፊት በአየር ላይ ሲፈነዳና ወደ ቡርትካናማ እሳትነት ሲለወጥ እንደተመለከቱ በዕለታዊ ሪፖርታቸው ላይ ከነፊርማቸው ማሳረፋቸውን የገለጹት አቶ ተወልደ፣ ዕለታዊውን ሪፖርት በስላይድ ለጋዜጠኞች አሳይተዋል፡፡ “አውሮፕላን ከመሬት ተነስቶ ወደ ድቡልቡል እሳትነት አይለወጥም፡፡ የውጪ ኃይል ጣልቃ ገብነት ከሌለ በስተቀር፤” ያሉት አቶ ተወልደ፣ የአየር መንገዱ ባለሙያዎች ባሰባሰቧቸው መረጃዎች ተንተርሰው አውሮፕላኑ በአየር ላይ ፈንድቷል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡
አደጋው ከደረሰ በኋላ የተጀመረው የምርመራ ሒደት ለአንድ ዓመት ያህል ተጓትቶ እንደነበር ገልጸው፣ ሒደቱን ለማስተካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የሊባኖስ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናትና ቦይንግ ኩባንያ ምርመራው በምን አኳኋን መቀጠል እንዳለበትና ማንኛውንም ለምርመራ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ስምምነት ተፈርሞ እንደነበር አውስተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የቦይንግና የናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም የአደጋ መርማሪ ቡድኑ አባላት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የጠየቋቸው መረጃዎች በሙሉ የተሰጧቸው ሲሆን፣ የአየር መንገድ አብራሪዎችን፣ ቴክኒሻኖችን፣ የበረራ ቁጥር 409 አብራሪዎች ጓደኞችን፣ ቤተሰቦችንና መምህራንን በሙሉ ቃለ መጠይቅ አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ትምህርት ቤት የአሠለጣጠን ዘዴዎችን በአጠቃላይ የአየር መንገዱን እንቅስቃሴ መርምረው ባዩት ነገር መደሰታቸውን ገልጸዋል ብለዋል፡፡
“የእኛ ጥረት እውነቱን ለማወቅ ብቻ ነው፡፡ የመግባቢያ ሰነዱ ከተፈረመ በኋላ እንኳ የከለከሉንን መረጃዎች እንዲሰጡን ጠይቀን በድጋሚ ከልክለውናል፡፡ በአደጋው አሻጥር (Sabotage) የሌለ በመሆኑ እናንተ የምትጠይቁት መረጃ አስፈላጊ አይደለም በማለት በእንቢተኝነት ፀንተዋል፡፡ ከሁሉም በላይ የሊባኖሳዊያኑ ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ምስክርነት እጅግ በጣም ወሳኝ ነበር፤” በማለት አስረድተዋል፡፡
‹‹ባለፈው መስከረም የአደጋ ምርመራው ሪፖርት በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንደሌለው ተገልጾ ለሊባኖስ ባለሥልጣናት ተመልሶ ተልኳል፡፡ ከዚህም በኋላ በፓሪስ በተካሄደ ስብሰባ ኢትዮጵያ በሪፖርቱ ላይ ያላትን ተቃውሞ ለሊባኖሱ ተወካይ ልዑክ ያሳወቁ ሲሆን፣ የሊባኖሱ ልዑክ የቀረበውን ቅሬታ ተቀብሎ በሪፖርቱ ላይ ለውጥ እንደሚደረግ ገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ በስተመጨረሻ ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን “የመጨረሻ ሪፖርት” ተብሎ የተላከው ምንም ዓይነት ማሻሻያ ያልተደረገበት የበረራ ቁጥር 409 አብራሪዎችን የሚኮንን ዘገባ ነበር፤›› ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ክፍል ኃላፊ ካፒቴን ደስታ ዘሩ፣ የበረራ ቁጥር 409 ከቤይሩት አውሮፕላን ማረፊያ ሊነሳ ሲዘጋጅ ከበረራ መቆጣጣሪያ ማማ የተምታታ መረጃ እንደተሰጠውና የበረራ ተቆጣጣሪዎቹ የተሳሳተ መረጃ ለአብራሪዎቹ በመስጠት ወደ ነጎድጓድ እንደመሯቸው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ሊነሳ ሲል በዚያው ወቅት ለማረፍ ተቃርቦ የነበረ የኢትሃድ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 533 አውሮፕላን በተሰጠው የተሳሳቱ መረጃዎች ለግጭት ተቃርበው እንደነበር፣ ይህም ሊሆን የቻለው በበረራ ተቆጣጣሪዎቹ ስህተት እንደሆነ የገለጹት ካፒቴን ደስታ፣ የበረራ ተቆጣጣሪዎቹ ያለ እረፍት ለ24 ሰዓት በመሥራታቸው የሠሩት ስህተት ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡
“ከበረራ መረጃ መቅጃ (FDR) እና ከበረራ ክፍል መቅረፀ ድምጽ (CVR) ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ሁለቱም መሣርያዎች መቅዳት ያቆሙት በ1300 ጫማ ከፍታ ላይ ነው፡፡ በበረራ ክፍሉ መቅረፀ ድምፅ የመጨረሻ ክፍል ቅጂ የሚሰማው ከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ ነው፤” ያሉት ካፒቴን ደስታ፣ “ይህ ሁሉ የሚጠቁመው አውሮፕላኑ በአየር ላይ በፍንዳታ ኃይል ምክንያት መበታተኑን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው አውሮፕላኑ ከውጪ በመሣርያ ሲመታ፣ በአሻጥር እንዲፈነዳ ሲደረግ ወይም በመብረቅ ነጎድጓድ የተመታ እንደሆነ ነው፤” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በወቅቱ በራፊቅ ሃረሪ አየር ማረፊያ ለማረፍ ተቃርበው የነበሩ የኢትሃድና የግሪኩ ኦሊምፒክስ አየር መንገድ አብራሪዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በእሳት ሲጋይ መመልከታቸውን እንደተናገሩ ካፒቴን ደስታ ገልጸዋል፡፡ በተለይ የኢትሃዱ ካፒቴን ባየው ነገር በጣም ተረብሾ ሽቅብ እንዳለው ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ካፒቴን ከመርማሪው ቡድን ፊት ቀርቦ ቃል እንዳይሰጥ ተደርጓል፡፡ የኦሎምፒክስ ካፒቴን ግን ቃሉን አስፍሮ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች መስጠቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ በደረሰ ማግስት በስፍራው ተገኝተው ያነጋገሯቸው የዓይን ምስክሮች ደብዛ እንዲጠፋ ተደርጓል፡፡ በአደጋው ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች አስከሬኖችና የአውሮፕላኑ ስብርባሪ ከባህር ሲወጣ የኢትዮጵያ ልዑክ እንዳይመለከት ተከልክሏል፡፡ የሊባኖስ ባለሥልጣናት የተወሰኑ አስከሬኖችም ሳይመረመሩ እንዲቀበሩ መደረጉ ተገልጿል፡፡
ካፒቴን ደስታ እንደገለጹት፣ የሊባኖስ ባለሥልጣናት የበረራ መረጃ መመዝገቢያ መሣርያዎቹን ለብቻቸው እንደፈለጉት አድርገዋቸዋል፡፡ “የበረራ ክፍል መቅረፀ ድምፁ ከተቀዳው ቅጂ ውስጥ የተደመሰሰ ክፍል እንዳለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ የ21 ሰከንዶች ቅጂ ጠፍቷል፤” ያሉት ካፒቴን ደስታ፣ ከመቅረፀ ድምፁ ለመረዳት እንደተቻለው አብራሪዎቹ ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነ ኃይል አውሮፕላኑን እንደመታውና አውሮፕላኑ ከቁጥጥር ውጪ እንደሆነ ነው፡፡ ካፒቴኑ ምን እንደተፈጠረ እንዳላወቀና ይህንኑ ሲጠይቅ፣ አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ሲታገልና የረዳት አብራሪውን እገዛ ሲጠይቅ ከመቅረፀ ድምፁ እንደተደመጠ ከካፒቴን ደስታ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህንን ሰቆቃ ለጋዜጠኞች ማስደመጡ ተገቢ እንዳልሆነ ካፒቴን ደስታ ገልጸዋል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ሪፖርቱ የአደጋው መንስዔ ‹‹የአብራሪዎቹ ስህተት›› እንደሆነ ማቅረቡ ፍፁም ስህተት ወይም የፈጠራ ሐተታ እንደሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ ሪፖርቱ የበረራ ቁጥር 409 አብራሪዎች ከተሰጣቸው አቅጣጫ ውጪ እንዳበረሩና አውሮፕላኑ ከተለመደው ውጪ የበረራ እንቅስቃሴ እንዳደረገ ይገልጻል፡፡ ይህም በሆነ ጊዜ አብራሪዎቹ አውሮፕላኑን መቆጣጠር እንዳልቻሉ ሪፖርቱ ገልጿል፡፡
የካፒቴን ደስታ ጥያቄ ደግሞ አውሮፕላኑ ለምን ባልተለመደ ሁኔታ የበረራ እንቅስቃሴ አደረገ የሚል ነው፡፡ ለዚህ የእርሳቸው ምላሽ አውሮፕላኑን ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆንና እንዲፈነዳ ያደረገው ውጫዊ ኃይል (External Force) ነው፡፡ ይህም ማለት አውሮፕላኑ በመሣርያ ተመትቷል ወይም እንዲፈነዳ ተደርጓል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ አገር ሪፖርቱን እንደማትቀበል ጠቅሳ በጽሑፍ የላከችው ተቃውሞ ከሪፖርቱ ጋር ተያይዞ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ካፒቴን ደስታና አቶ ተወልደ በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ፣ ሚስጥራዊ ሰነዶችን በማውጣት የሚታወቀው “ዊኪሊክስ” የተባለው ድረ ገጽ ያወጣው መረጃ ጥርጣሬያቸውን አጠናክሮታል፡፡ አደጋው ከደረሰ ከሦስት ሳምንት በኋላ ቤይሩት ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ ዋሽንግተን የተላከው ሚስጥራዊ ሰነድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን አደጋ ሪፖርት መደምደሚያ ‹‹የአብራሪዎች ስህተት›› የሚል እንደሚሆንና በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከባድ ፈተና እንደሚገጥመው ገልጿል፡፡ አሜሪካኖቹ አደጋው በደረሰ በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ መረጃ ገና ሳይሰበሰብ፣ የመረጃ ሳጥኑ ሳይገኝ ይህን እንዴት ሊያውቁ ቻሉ የሚለው ጥያቄ አሜሪካኖቹ ‹‹የፓይለቶች ስህተት›› እንደሆነ አድርጐ ለማቅረብ የተጠነሰሰ ሴራ እንደነበር ከጅምሩ ያውቁ ነበር የሚል ጥርጣሬ ጭሯል፡፡
የአደጋው መንስዔ አሻጥር ነው ተብሎ ከተጠረጠረ ለምን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቤይሩት የሚያደርገውን በረራ አላቋረጠም? የምርመራ ሒደቱን አቋርጣችሁ ለምን አልወጣችሁም? የሊባኖስ ባለሥልጣናትን መክሰስ አይቻልም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች ተነስተዋል፡፡ ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት አቶ ተወልደ፣ የኢቲ 409 አደጋ አንድ አሳዛኝ ክስተት መሆኑን ገልጸው፣ አየር መንገዱ በረራ እንዲያቋርጥ የሚያደርግ የደኅንነት ስጋት ባለማግኘቱ ወደ ቤይሩት የሚያደርገውን በረራ እንዲቀጥል ተደርጓል ብለዋል፡፡ እስካሁን በሚደረገው ዕለታዊ በረራ ባለፉት ሁለት ዓመታት (አደጋው ከደረሰ በኋላ) የገጠመ ችግር እንደሌለ የገለጹት አቶ ተወልደ፣ በበረራ መስመሩ ላይ የመንገደኞች ቁጥር እንደጨመረ ተናግረዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ሁሉም ወገኖች (አደጋው የደረሰበት አገር፣ የአየር መንገዱ ባለቤት አገርና አውሮፕላኑ የተመረተበት አገር) በአደጋው ምርመራ ሒደት ተባብረው መሥራት አለባቸው የሚለውን መርህ በማክበር፣ ኢትዮጵያ እስከ መጨረሻው የምርመራውን ሒደት ለማቃናት እንደታገለች አቶ ተወልደ ገልጸዋል፡፡
በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት አቶ ተፈራ መኮንን፣ ኢትዮጵያ ሪፖርቱን እንደማትቀበለው በዝርዝር በጽሑፍ ያቀረበችው ተቃውሞ ከሪፖርቱ ጋር ተያይዞ እንዲወጣ ከመደረጉም በላይ፣ ለዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ፕሬዚዳንትና ዋና ጸሐፊ ተቃውሞዋን እንዳቀረበች ገልጸዋል፡፡ በአደጋ ምርመራ ሒደት የኢትዮጵያ ልዑክ መሪ የሆኑት አቶ ተፈራ ኢትዮጵያ መርማሪ ቡድኑ የተከተለው የምርመራ ሒደት ትክክል እንዳልሆነ ለማስረዳት የተቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረጓን ገልጸው፣ ከዚህ አልፎ ሊባኖስን እንደ አገር መክሰስ የሚቻልበት መንገድ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ በሞሪታኒያ የሚገኝ ድረ ገጽ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን እንዲፈነዳ የተደረገው በእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድ ቅጥረኛ በሆኑ ሊባኖሳውያን እንደሆነና ፍንዳታው የታለመው በአውሮፕላኑ ላይ የተሳፈሩ የሂዝቦላህ ሰዎችን ለመግደል እንደሆነ ያቀረበውን ዘገባ በተመለከተ፣ አቶ ተወልደ ዘገባው የተወሰነ እውነታ እንደሚኖረው ጠቅሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናትን ጥርጣሬ የሚያጠናክር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የካሳ ክፍያን በተመለከተ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሕግ ክፍል ምክትል ኃላፊ አቶ ገናናው አሰፋ ለተወሰኑ ተጐጂ ቤተሰቦች የካሳ ክፍያ እንደተፈጸመ ገልጸው፣ ከተቀሩት ቤተሰቦችም ጋር የካሳ ክፍያ ስምምነት በቅርቡ ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ከቤይሩት ራፊክ ሃሪሪ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከአራት ደቂቃ በኋላ በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ በወደቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን አደጋ የአውሮፕላኑን ሠራተኞች ጨምሮ የ90 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ደኅንነት ታሪክ እጅጉን የተደነቀ እንደሆነ የአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር በተደጋጋሚ መግለጹም እንዲሁ ይታወሳል፡፡


