Thu02232012

Go to :English Edition

Back ዜና ዜና መድን ድርጅት ለካንጋሮ ፕላስት 21.1 ሚሊዮን ብር ካሳ ከፈለ

መድን ድርጅት ለካንጋሮ ፕላስት 21.1 ሚሊዮን ብር ካሳ ከፈለ

  • PDF

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከአሥር ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ትልቁን የካሳ ክፍያ 21.1 ሚሊዮን ብር ባለፈው መስከረም ወር በእሳት ለወደመው ካንጋሮ ፕላስት ፋብሪካ መክፈሉን አስታወቀ፡፡ መድን ድርጅት ለካንጋሮ የከፈለው ይህ ክፍያ ከአሥር ዓመት በፊት አደጋ ደርሶባቸው ለነበሩት ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ፈጽሞ ከነበረው ክፍያ ቀጥሎ ትልቁ ነው ተብሏል፡፡

ክፍያው የተፈጸመው ጥር 7 ቀን 2004 ዓ.ም. ሲሆን፣ የመድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ የወንድወሰን ኢተፋ ለካንጋሮ ፕላስት የፋይናንስ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ማሙሸት አፈወርቅ ገንዘቡን አስረክበዋል፡፡

ካንጋሮ ፎም መስከረም 30 ቀን 2004 ዓ.ም. በእሳት ቃጠሎ መውደሙ ይታወሳል፡፡ ይህንን እሳት ለመቆጣጠር የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት ድርጅት 143 አባላት ያሉት እሳት አጥፊ ብርጌድ ያሳተፈ ሲሆን፣ ብርጌዱ ከሰባት ሰዓታት በኋላ እሳቱን መቆጣጠር ቢችልም፣ በፋብሪካው ላይ ጉዳት ደርሶ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከሦስት ወራት በኋላ ለወደመው ንብረት ካሳ የሚሆን ገንዘብ በአንድ ቼክ ክፍያ ፈጽሟል፡፡ አቶ ማሙሸት የካሳውን ክፍያ በተቀበሉበት ወቅት እንደገለጹት፣ ይህንን ከፍተኛ ገንዘብ በአንድ ጊዜና በፍጥነት መክፈል በመቻሉ ከመድን ድርጅት ጋር አብሮ ለመሥራት እምነት የሚጣልበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በአሁኑ ወቅት ከ45 በላይ የተለያዩ ፖሊሲዎችን ቀርጾ በሕይወትና በንብረት ላይ የሚደርስን ጉዳት፣ እንዲሁም በሕጋዊ ኃላፊነት የተነሳ የሚደርስ ተጠያቂነትን በመሸፈን ላይ ይገኛል፡፡

ድርጅቱ ባለፈው ዓመት 233.3 ሚሊዮን ብር ለሞተር መድን ካሳ የከፈለ ሲሆን፣ በዚያው ዓመት በቃጠሎ ለደረሰ ውድመት 6.7 ሚሊዮን ብር ክፍያ ፈጽሟል፡፡ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት የተገኘ መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ለሞተር መድን የተከፈለው ገንዘብ ሊበዛ የቻለው የሞተር አደጋ የመድረስ አጋጣሚው በርካታ በመሆኑ ነው፡፡