Thu02232012

Go to :English Edition

Back ዜና ዜና በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች የሚፈጸም ውርጃ አሳሳቢ ሆኗል

በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች የሚፈጸም ውርጃ አሳሳቢ ሆኗል

  • PDF

•  የኤችአይቪ ቫይረስ ሥርጭት ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየጨመረ ነው

በአስፋው ብርሃኑ፣ ልዩ ዘጋቢ ከሐዋሳ

በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሁለቱም ካምፓሶች ልቅ ወሲባዊ ግንኙነት በመበራከቱ ውርጃ የሚፈጽሙ ሴት ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተመለከተ፡፡ ጥንቃቄ በጐደለው ወሲባዊ ግንኙነት የተነሳ ከእርግዝና በተጨማሪ ለኤችአይቪና ለአባላዘር በሽታዎች ተጋላጭ የሆኑ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑንና አንዳንድ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ሕፃናት እንደሚጣሉ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አባይነህ ኡናሾ እንደገለጹት፣ በዩኒቨርሲቲው የመዝናኛ አገልግሎት አለመኖር፣ በየካምፓሶቹ መኖር የሚገባው የተማሪዎች ቁጥጥር ዝቅተኛ መሆንና በዲላ ከተማ ያሉ ወጣት ባለሀብቶች ከሴት ተማሪዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት መስፋፋት ለእርግዝናውና በተያያዥ ለሚፈጸመው ውርጃ፣ እንዲሁም ለቫይረሱ ሥርጭት መንስዔ መሆናቸውን በተደረገ ጥናት መረጋገጡን አብራርተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲ የብሩህ ተስፋ የፀረ ኤችአይቪ ክበብ ሰብሳቢ ተማሪ ደመላሽ ታሪኩ እንደሚለው፣ የሴት ተማሪዎችን ስልክና ፎቶዎች በባጃጅ ታክሲ አሽከርካሪዎች እጅ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ምንም ዓይነት የባህሪይ ለውጥ ማየት ወደማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል በማለት፣ እርግዝናና ውርጃ ብቻ ሳይሆን የኤችአይቪ ቫይረስ ሥርጭት አሳሳቢ መሆኑን ይናገራል፡፡ እንደ ተማሪ ደመላሽ ገለጻ ከሆነ፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በ2,400 ተማሪዎች ላይ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ምርመራ ተደርጐ 380 ተማሪዎች ቫይረሱ በደማቸው ተገኝቶባቸዋል፡፡ ‹‹የከተማዋ አንዳንድ ክሊኒኮች ሴት ተማሪዎች የሚፈጽሙትን ውርጃ ማስተናገድ ዋነኛ ሥራቸው አድርገውታል፤›› በማለት ሁኔታውን አስረድቷል፡፡

በግቢው የተማሪዎች አገልግሎት አለመኖር፣ ወጣት ባለሀብቶች የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችን በገንዘብ ማማለልና የባህሪይ ለውጥ አለመኖሩ ችግሩን ማባባሱን የምትገልጸው ተማሪ ቃልኪዳን ታደሰ፣ ‹‹በከተማውና በየክሊኒኩ ስለሴት ተማሪዎቻችን ውርጃ የሚነገረውን እኔም እሰማዋለሁ፤ የከተማዋ ሴት ፈላጊ ወንዶች እንደፈለጉ ግቢ ገብተው ሴት ይዘው ይሄዳሉ፡፡ በግቢ ውስጥም ልቅ የሆነ ወሲባዊ ግንኙነት ስላለ የሚባለው ነገር ምንም አይገርምም፤›› ስትል በግቢው ያለው ቁጥጥር ልል መሆኑ ዋነኛ የችግሩ መነሻ እንደሆነ ጠቁማለች፡፡

በከተማው ቫይረስ እንዳለበት የሚታወቅ አንድ ሰው በሞተር ሳይክል እየመጣ ሴት ፍሬሽ ተማሪዎችን እንደሚወስድና ቁጥጥር ካልተደረገ የቫይረሱን ሥርጭትም ሆነ ያልተፈለ እርግዝና መቀነስ አስቸጋሪ እንደሚሆን ሌላዋ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሐያት ኢብራሂም ትናገራለች፡፡

በተመሳሳይ ግርማው አሸብር የተባለ ሌላ ተማሪም፣ በግቢው መዝናኛ ባለመኖሩና ፕሮጀክት ቀርጸው በዩኒቨርሲቲው ቢሮ የከፈቱ ግብረ ሰናይ ተቋማት ኩኪስና ሻይ ቡና አቅርበው ከመሄድ ባለፈ ችግሩን የሚቀርፍ ተግባር አለማሳየታቸውን ይናገራል፡፡ ሴት ተማሪዎች ለመዝናኛ ስፖንሰር እየፈለጉ በተለምዶ ‹‹ሹገር ዳዲ›› ከሚባሉት ጋር መሄዳቸው የተለመደ እንደሆነም ያስረዳል፡፡

ችግሩን በተመለከተ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሻግሬ ተሾመ ተጠይቀው፣ የተማሪዎች አገልግሎት ችግር እንደማንኛውም አዲስ ዩኒቨርሲቲ ያለ ቢሆንም በዋናነት የግንባታ መጓተት ችግር እንደሆነ ገልጸው፣ የሴት ተማሪዎችን እርግዝናና የቫይረሱን ሥርጭት በተመለከተ ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ተማሪዎች ቢያንስ ለአቅመ አዳምና ሄዋን የደረሱና ብዙ ነገሮችን የሚያውቁ ናቸው ብለዋል፡፡

መዝናኛ የለም ብሎ ሕይወትን ለአደጋ ማጋለጥ አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ነገሮች ተጋነው ሊወሩ ይችላሉ ብለው፣ በከተማው ውስጥ ስለሚወራው ነገር እሳቸውም መስማታቸውን አቶ አሻግሬ አክለው ገልጸዋል፡፡