- የነዳጅ ማደያዎችን የልኬት መሣርያዎች ትክክለኛነት መፈተሽ ጀመረ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ተሰብስቦ የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የሚያቀርብለትን አዲስ የንግድ አሠራር የለውጥ (ሪፎርም) ፕሮግራም ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የንግድ ሪፎርሙ ንግድን በሚመለከት ስምንት ንዑስ ፕሮግራሞች ይኖሩታል ተብሏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ማንም የንግዱ ማኅበረሰብ አባል የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ዕደሳ ለማድረግ ወደ ቢሮው ሲመጣ፣ ሸቀጣ ሸቀጥ የሚለኩባቸው የልኬት መሣርያዎች ትክክለኛ መሆናቸውን የሚገልጽ ሠርቲፊኬት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
ሸማቾች የሚደርሱባቸውን ችግሮች የሚፈታ የዳኝነት አካል ይቋቋማል፡፡ የሸማቾች መብት እንዲያስጠብቅ በፌዴራል ደረጃ ከተቋቋመው ባለሥልጣን መሥርያ ቤት በተጨማሪ፣ የከተማ አስተዳደሩም ተመሳሳይ ሥልጣን ያለው መሥርያ ቤት የሚያቋቁሙበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡
ከእነዚህ ማሻሻያዎች በተጨማሪም የገበያ ልማት ማሻሻያና የገበያ ውድድር ማሻሻያ ፕሮግራሞችን አካቷል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታዬ ጫላ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ እነዚህን ጉዳዮች ያካተተው ፕሮግራም በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ለካቢኔ ቀርቦ ይፀድቃል፡፡
ይሁንና ኅብረተሰቡ በነዳጅ ማደያዎች ላይ ተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀረበ በመሆኑ፣ ቢሮው ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅን ለማስፈጸም ከወዲሁ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ የንግድ አሠራር ሪፎርሙ መነሻ አዋጅ ቁጥር 685/2000 መሆኑ ታውቋል፡፡
በዚህ መሠረት ጥር 15 ቀን 2004 ዓ.ም. በከተማው በሚገኙ 200 የነዳጅ ማደያዎች ላይ የልኬት መሣርያዎች ፍተሻ ማካሄድ ተጀምሯል፡፡ አቶ ታዬ ማክሰኞ ከሰዓት በፊት በስምንት የነዳጅ ማደያዎች ላይ በተካሄደ ፍተሻ፣ ሊታረሙ የሚችሉ ክፍተቶች መኖራቸውን አስረድተው፣ መሥርያ ቤታቸውም ክፍተቶቹ እንዲታረሙ እያደረገ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ቢሮው ባካሄደው የአሠራር ለውጥ 1,600 ባለሙያዎችን ቀጥሯል፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች በክፍላተ ከተሞችና በ116 ወረዳዎች ውስጥ ተደልድለዋል፡፡ ባለሙያዎቹ በየጊዜው ድንገተኛ ፍተሻና ክትትል በማድረግ የሸማቾችን መብቶች ለማስከበር ይሠራሉ ተብሏል፡፡ በእስካሁኑ ሒደት ቢሮው በዳቦ ቤቶች፣ በአትክልት መሸጫዎችና በእህል መሸጫ መደብሮች ሸቀጦች በሚሸጡባቸው ሚዛኖች ላይ ፍተሻ አካሂዷል፡፡
አግባብነት የሌለው ተግባር ፈጽመዋል ባላቸው ላይም ዕርምጃ መውሰዱን አቶ ታዬ ገልጸዋል፡፡ ከትናንት ጀምሮም ለተከታታይ 15 ቀናት የሚቆይ የነዳጅ ማደያዎች የልኬት ፍተሻ ለማካሄድ ሥራውን ጀምሯል፡፡
የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነዳጅን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጦችን በሚሸምቱበት ወቅት የሚዛን ማጭበርበር እንደሚገጥማቸው በተለያዩ መድረኮች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
ፍተሻው በስኬት የመጠናቀቁ ጉዳይም ምናልባት በቢሮው ሠራተኞችና በንግዱ ኅብረተሰብ መካከል ሊፈጠሩ በሚችሉ የጥቅም ግንኙነቶች ምክንያት፣ ዘመቻው የመክሸፍ ስጋት ሊገጥመው ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው ሸማቾች አልታጡም፡፡
አቶ ታዬ ለዚህ ስጋት ሲመልሱ፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች ፍተሻው የሚካሄድበት አሠራር በመኖሩ ችግሩ እንደማይከሰት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡


