ትናንት በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የመሥርያ ቤታቸውን የአምስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ እንደገለጹት፣ የአገሪቱ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ፕሮግራም በቁጠባ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ለማድረግ፣ 40 በመቶ ከቤቱ ባለቤትና 60 በመቶ ከባንክ በሚገኝ ረጅም ብድር የሚገነባ ቤት አቅርቦት እንዲከናወን፣ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የቁጠባ ቤት ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ስትራቴጂና አደረጃጀት ጥናት ተጠናቋል፡፡
ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ በጥናቱ መሠረት ከብሔራዊ ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በአፈጻጸሙ ላይ ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ደሃ ተኮር የቤት ልማት ለማካሄድ ስትራቴጂ በመጠናት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከተሞችን እንደየዕድገት ደረጃቸው በሦስት በመክፈል የተለያዩ የዲዛይን አማራጮች ለማዘጋጀት የአማካሪ ቅጥር እየተካሄደ ነው፡፡
በ40 በመቶ ቁጠባና በ60 በመቶ ብድር ለሚገነቡ ቤቶች መዘጋጀት ካለባቸው አምስት ዓይነት ስታንዳርድ ዲዛይኖች ውስጥ የሁለቱ መጠናቀቁንና የሦስቱ ቶፖሎጂ ዲዛይን ዝርዝር እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ መኩሪያ አክለው ገልጸዋል፡፡
የአሥሩን አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ በተመለከተም ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው እንደገለጹት፣ በሁለተኛው ዙር ግንባታ ከደብረ ታቦርና ከአዲስ አበባ በስተቀር በአብዛኛዎቹ የአፈጻጸም ችግር ታይቷል፡፡ የፋይናንስ እጥረት፣ የኢንዱስትሪ ውጤት ከሆኑት መካከል የመስተዋት አቅርቦት መዘግየት፣ የአካባቢ ግብዓትና የጉልበት ዋጋ መናር፣ እንዲሁም የመሠረተ ልማት አቅርቦት መዘግየት ዋና ዋናዎቹ ችግሮች መሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ ከፋይናንስ እጥረት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመወያየት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ ከዋጋ ንረት ጋር የተያያዙ ችግሮችም መሠረታዊ መንስዔያቸውን ለመለየት ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም አቶ መኩሪያ አስታውቀዋል፡፡
የአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን ግንባታ በሚመለከት አስተያየት የሰጡ አንድ የፓርላማ አባል በበኩላቸው፣ የሚገነቡት ዩኒቨርሲቲዎች የዲዛይን ችግር ያለባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲዎችን ተዘዋውረው በጐበኙበት ወቅት የፀሐይ ብርሃን የማያስገባ ቤተ መጻሕፍትና የእጅ መታጠቢያ የሌለው የምግብ አዳራሽ ተመልክተዋል፡፡


