በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆና በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣ ከነገ በስቲያ ሁለት ወር የሚሞላው የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣውን አዋጅ ለማስፈጸም፣ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አማካይነት የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ዛሬ ውይይት ይደረግበታል፡፡ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ አስተዳደር የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሊዝ አዋጁን ለማስፈጸም በወጣው ረቂቅ ደንብ ውይይት ላይ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ በዋናነት የሚሳተፍ ሲሆን፣ ከየክፍላተ ከተሞቹ ሕዝቡን የሚወክሉ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበር ምክር ቤት አዋጁን ተከትሎ በወጣው የማስፈጸሚያ ረቂቅ ደንብ ዙርያ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባደረገው ውይይት፣ በርካታና የተለያዩ ሐሳቦች በመነሳታቸው፣ ምክር ቤቱ ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና ለንግድ ሚኒስቴር የንግዱ ማኅበረሰቡ አባላት ያነሱዋቸውን ጥያቄዎችና አስተያየታቸውን እንዲያቀርብ ጠይቆ እንደተፈቀደለትና ውይይቱ ዛሬ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡ ለዚህ ውይይት አባላት በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉና ሊነሱ ይገባቸዋል የሚሉዋቸውን ጥያቄዎች እንዲልኩለት መልዕክት አስተላልፎ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
በውይይቱ ላይ ለመገኘት ፈቃደኛነታቸውን ያሳወቁት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌና በቅርቡ የንግድ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ከበደ ጫኔ የንግዱ ማኅበረሰብ የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎችና አስተያየቶች ያደምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ኅብረተሰቡ አዋጁን ካለመረዳት፣ ያስፈጽማሉ በተባሉ የወረዳ፣ የክፍላተ ከተሞችና የማዕከል ኃላፊዎችን ቢጠይቁም ተጠያቂዎቹም አለማወቃቸውን ተከትሎ፣ ውዥንብርና የውስጥ ለውስጥ ተቃውሞ በመፈጠሩ፣ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ከየወረዳውና ከክፍላተ ከተሞች የተውጣጡና ኅብረተሰቡን ይወክላሉ የተባሉ ተወካዮችን በአዋጁ ዙርያ ታህሳስ 21 ቀን 2004 ዓ.ም. አወያይተው ያለምንም ተቃውሞ ውይይቱ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡
በሳምንቱ ታህሳስ 26 ቀን 2004 ዓ.ም. የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮችንና የከተማ ነዋሪዎች ተወካዮችን ሲያወያዩ፣ አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች ሕዝቡ ሳይወያይበት አዋጁ በፍጥነትና በድብቅ መውጣቱን ተቃውመው፣ ‹‹አዋጁ ከወጣ በኋላ የምታወያዩን ለይስሙላ ነው›› በማለት ውይይቱ ዋጋ እንደሌለው መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ስብሰባውን ይመሩ የነበሩት ከንቲባ ኩማ ደመቅሳና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ ‹‹እናንተን ማወያየት የፈለግነው አዋጁን ለማስፈጸም በሚወጡ ደንቦችና መመርያዎች ውስጥ ጠቃሚ ሐሳቦችን ለማካተት ነው፤›› ባሉት መሠረት በዛሬው ረቂቅ ደንብ ላይ የተወሰነ ማሻሻያ ተደርጐበት ለውይይት መቅረቡ ታውቋል፡፡
ረቂቅ ደንቡን የተመለከቱና ከስብሰባው በፊት ይዘቱን ለመግለጽ ፈቃደኛ ያልሆኑ የሪፖርተር ምንጮች፣ ረቂቅ ደንቡ በአብዛኛው የአዋጁን አንቀጾች የሚደግፍ በመሆኑ፣ በውይይትና በተለያዩ ስብሰባዎች ጊዜ ማጥፋቱ ትርጉም እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በዛሬው ውይይትና በተለያዩ መድረኮች የሚነሱ ሐሳቦች ለረቂቅ ደንቡ እንደ ግብዓት ሊወሰዱ ይችሉ ይሆናል ሲሉ ግምታቸውን አስረድተዋል፡፡


