Thu05172012

Go to :English Edition

Back ዜና ዜና በቡድን በመደራጀትና ወንጀል በመፈጸም ተጠርጥረው ከታሰሩት “የ24 ቀበሌ ልጆች” አንዱ አመለጠ

በቡድን በመደራጀትና ወንጀል በመፈጸም ተጠርጥረው ከታሰሩት “የ24 ቀበሌ ልጆች” አንዱ አመለጠ

  • PDF

-    ማረሚያ ቤት ለፍርድ ቤት የጻፈው ደበዳቤ አሳማኝ አይደለም ተባለ
-    ‹‹ምስክሮቻችን ታፍነው ስለሚወሰዱ በዝግ ይታይልን›› የተከሳሾች ጠበቃ ‹‹ስለመታፈን የተሰማ ነገር ቢኖርም የተረጋገጠ ነገር የለም›› ፍርድ ቤቱ
በቡድን ተደራጅተው ‹‹የ24 ቀበሌ ልጆች ነን›› በማለት የተለያዩ ወንጀሎችን በመፈጸምና ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ፣ ክስ ከተመሠረተባቸው አምስት ተጠርጣሪዎች መካከል ዋሲሁን መኮንን ቢያርጐ የተባለው ተጠርጣሪ፣ ታህሳስ 3 ቀን 2004 ዓ.ም. በአጃቢ ከማረሚያ ቤት ከወጣ በኋላ ማምለጡን ተከትሎ፣ ፍርድ ቤት ጥር 18 ቀን 2004 ዓ.ም. ለማረሚያ ቤቱ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡

የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሰባተኛ ወንጀል ችሎት ከጥር 18 ቀን 2004 ዓ.ም. በፊት ባስዋለው ችሎት፣ ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ተከሳሹ ችሎት ያልቀረበበትንና ከማረሚያ ቤት ጠፍቷል ስለተባለበት ጉዳይ የሚመለከተው አካል ቀርቦ እንዲያስረዳ ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሠረት፣ ማረሚያ ቤቱ ደብዳቤ መጻፉን ፍርድ ቤት ለችሎቱ በንባብ አሰምቷል፡፡

ማረሚያ ቤቱ ጥር 2 ቀን 2004 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ስለጠፋው ተከሳሽ እንደገለጸው፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሰባተኛ ወንጀል ችሎት ለተከሳሹ በሰጠው ፈቃድ መሠረት፣ ተከሳሹ ታህሳስ 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ከማረሚያ ቤት በአጃቢዎች ጋር በመሆን የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን እንዲገዛና በድርጅቱ ውስጥ እንዲያስገጥም መፍቀዱን ገልጾ ተከሳሹ ግን ወደ ማረሚያ ቤት ሳይመለስ መቅረቱን በደብዳቤው ማሳወቁን ፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው አቤቱታ፣ ተከሳሹ በቀረበበት ክስ የዋስ መብቱ ተነፍጐ በማረሚያ ቤት እንዲሆንና ክሱን እንዲከታተል የተደረገው ይጠፋል በሚል ፍራቻ መሆኑን አስረድቶ፣ ማረሚያ ቤቱ አደራ የተሰጠውን እስረኛ አለመጠበቁ የሕግ ጥሰት መሆኑን ገልጿል፡፡ ተከሳሹ በዓቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ፣ ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች ላይ ሲከራከርና ‹‹ተከላከል›› እስከሚባል ቆይቶ ዕቃ ለመግዛት በሚል ምክንያት ቢጠፋም፣ እንደተከራከረ ተቆጥሮ የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን አስመልክቶ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ተከሳሹ ተከላከል ከተባለ በኋላ ሥራ ለመሥራት በሚል ከማረሚያ ቤት ወጥቶ ሳይመለስ እንደቀረ ተደርጐ የተሰጠው ምላሽ አሳማኝ አለመሆኑን አስታውቆ፣ ተከሳሹን አጅበው በወጡ አጃቢዎች ላይ የተወሰደ ዕርምጃና በቂ ማስረጃ ካለ ገልጾ እንዲጽፍና የሚመለከተው ኃላፊ ቀርቦ እንዲያስረዳ አዟል፡፡

ፍርድ ቤቱ ቀደም ባሉት የችሎት ጊዜያት የሁሉንም ተጠርጣሪዎች የመከላከያ ምስክሮች አድምጦ፣ የአምስተኛ ተከሳሽ ሳምሶን ግዛቸው ወልደ ሰማያት ቅጽል ስም ሳሚ ፋየር መከላከያ ምስክሮች መስማት ቢሆንም፣ ተከላካይ ጠበቃው ችሎቱ ዝግ ሆኖ መከላከያ ምስክሮቻቸውን እንዲያሰሙ ያቀረቡት አቤቱታ ክርክር አስነስቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ ለጠበቃው ሲያቀርብ፣ ቀደም ብሎ የተሰሙት የመከላከያ ምስክሮችና የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በዝግ ስለተሰሙ፣ የእሳቸው ደንበኛ መከላከያ ምስክሮችም ለደኅንነታቸው ሲባል በዝግ እንዲሰሙላቸው መሆኑን አስረዱ፡፡ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው አስተያየት፣ ‹‹ዓቃቤ ሕግ በዝግ ስላስመሰከረ እኔም በዝግ ላስመስክር›› ሳይሆን፣ ተከሳሹና ምስክሮቹ ከጀርባቸው ያለው ስጋት ምን እንደሆነ በግልጽ እንዲያስረዱ ጠየቀ፡፡

ጠበቃው ስጋታቸውን ለፍርድ ቤቱ ሲገልጹ፣ በሌሎች ምስክሮች ላይ የተፈጸመው በእሳቸው ምስክሮችም ላይ አንዳይፈጸም መሆኑን ተናገሩ፡፡ ፍርድ ቤቱ ‹‹ምንድነው የተፈጸመው?›› የሚል ጥያቄ ሲያነሳላቸው፣ ‹‹መስክረው ሲወጡ ታፍነው የተወሰዱና የታሰሩ ነበሩ፤›› ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ግልጽ ማድረጉንና የመከላከያ ምስክሮች መታሰራቸውን መስማታቸውንም አክለዋል፡፡ የእሳቸውም መከላከያ ምስክሮች ቀድሞ የተፈጸመውን በመስማታቸው ‹‹ፖሊሶቹን እንፈራለን›› በማለት ባሉበት ቦታ ሆነው ስጋታቸውን መግለጻቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በዕለቱም የቀረቡትን የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ወደ ፍርድ ቤት ያቀረቧቸው ደብቀው መሆኑንና ችሎቱ ሥራ ጀምሮ እስከሚጠራቸው ተደብቀው መቀመጣቸውን ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ፣ ቀደም ብሎ ተፈጸመ የተባለው ነገር አለመረጋገጡን፣ ችግር የደረሰበት ግለሰብ ራሱ ፍርድ ቤት ቀርቦ መታሰሩን ካላረጋገጠ በስተቀር በግምት መናገር ትክክል አለመሆኑን አስታውቆ፣ በወቅቱ ወስዳችኋል የተባሉት ፖሊሶች ቀርበው ‹‹አልወሰድንም›› ማለታቸውን ተናግሯል፡፡ ማስረጃ ባለመቅረቡ ፍርድ ቤቱ በማንም ላይ የማስጠንቀቂያ ትዕዛዝ አለመስጠቱንም አክሏል፡፡ በወቅቱ ተሰይመው የነበሩት ዳኛም በመዝገቡ ላይ የመዘገቡት ነገር እንደሌለ ገልጾ ‹‹ነገር ግን የተሰማ ነገር ነበር›› ብሏል፡፡

ዳንኤል አበራና ፍሬ ሕይወት አንገሶ የተባሉ የመከላከያ ምስክሮች ታፍነው ተወስደው ለአንድ ሳምንት ከቆዩ በኋላ መለቀቃቸውን ጠበቃው ሲገልጹ፣ ‹‹በምን ምክንያት እንደታሰሩ ያውቃሉ?›› የሚል ጥያቄ ፍርድ ቤቱ አቅርቦ፣ ፍሬ ሕይወት አንገሶ የታሰረችው ለዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆና ከቀረበች በኋላ፣ በድጋሚ የመከላከያ ምስክር ሆና በመቅረቧ መሆኑንና በሕግ አግባብ እንደማይቻል በማስረዳት፣ የታሰረችው በአግባቡ ስለመሰከረች አለመሆኑን አስታውቋል፡፡ ተከላካይ ጠበቃው ያቀረቡት ምክንያት ስጋት በመሆኑ በቂ ምክንያት ሊሆን ስለማይችል ችሎቱ በዝግ ሳይሆን በግልጽ መታየት እንዳለበት ብይን ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ብይን እንደሰጠ አንደኛ ተከሳሽ ፍራኦል አብዲሳ ኢተቻ የተባለው ተጠርጣሪ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው አቤቱታ፣ በርካታ ንብረቱ ጅቡቲ ላይ እንደተዘረፈበት በመግለጽ በቂ ዋስትና አስይዞ ወጥቶ ንብረቱን እንዲሰበስብ እንዲፈቀድለት ጠየቀ፡፡ በማረሚያ ቤት ፖሊሶች እየታጀበ ወጥቶ እንዳይሠራ እስረኞች እየጠፉ ስላስቸገሩ ማረሚያ ቤቱ እንደከለከለው ገልጾ፣ ‹‹በልጅነት ያፈራሁት ንብረቴ ከንቱ እየሆነብኝ ነው፤›› በማለት እያለቀሰ ፍርድ ቤቱን ለምኗል፡፡

ክስ ሲመሠረትበት የዋስትና መብቱን እንደተከለከለ ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ በዋስትና እንዲወጣ መጠየቅ ያለበት ቀደም ብሎ የተከለከለውን ዋስትና በይግባኝ ማሻር ችሎ ቢሆን እንደነበርና አሁን ግን ዋስትና መፍቀድ እንደማይቻል አሳውቆታል፡፡

ፍርድ ቤቱ በአምስተኛ ተከሳሽ ሳምሶን ግዛቸው ላይ የቀረቡትን አራት የመከላከያ ምስክሮች ምስክርነት ሰምቷል፡፡ በእስር ላይ የሚገኙት ሁለቱ የመከላከያ ምስክሮች ቢሆኑም ሁለተኛ ተከሳሽ የሆነው አንለይ ገብሬ ወልደ እዝጊ የሰጠው ምስክርነት ብቻ እንደሚበቃው ጠበቃው በመግለጻቸው፣ ሦስተኛ ተከሳሽ ዳንኤል ጥላሁን ማሞ ሳይሰማ ቀርቷል፡፡

ምስክሮቹ ከመሰማታቸው በፊት ተከሳሹ ሳምሶን ግዛቸው በሰጠው የተከሳሽነት ቃል የራሱን ሥራ እንደሚሠራ፣ አባቱ ጡረተኛ ሲሆኑ እናቱ የነርቭ ሕመምተኛ መሆናቸውን፣ እህትና ወንድሞቹን እንደሚያስተዳድር ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ ‹‹መከበር ያለበት የሴቶች ክብር ብቻ ሳይሆን የወንዶችም ክብር ሊሆን ይገባል፤›› ካለ በኋላ፣ መኪና እንደሚያከራይና ቀሪ ጊዜውን በቤቱና በቤተ ክርስቲያን እንደሚያሳልፍ ገልጿል፡፡

አንለይ ገብሬ የተባለው መከላያ ምስክር በሰጠው የምስክርነት ቃል፣ ሳምሶን ምንም ዓይነት መጠጥ እንደማይጠጣና ጊዜውን በቤቱና በቤተ ክርስቲያን እንደሚያሳልፍ፣ ከኢምፔሪያል ሆቴል ጭፈራ ቤት ርብቃ ካሳሁን የተባለች ሴት አስገድዶ በመውሰድ ደፍሯል የሚባለው ሐሰት መሆኑንና እሱ ኢምፔሪያል ሆቴል ጭፈራ ቤት ገብቶ እንደማያውቅ አስረድቷል፡፡ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚተዋወቁም ተናግሯል፡፡

ሌላዋ መከላከያ ምስክር የተከሳሹ የሳምሶን እጮኛ መሆኗን የገለጸችው ሜሮን አሰፋ ስትሆን ስለምትፈራ አድራሻዋን ላለመግለጽ ብትሞክርም፣ ፍርድ ቤቱ ዋስትና ሰጥቷት አድራሻዋን በማስመዝገብ መስክራለች፡፡ ከመስከረም 16 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ መተዋወቃቸውን፣ ከጳጉሜ 5 ቀን 2002 ዓ.ም. በኋላ እስከታሰረበት ዕለት ድረስ አብረው መኖር መጀመራቸውንና ጋብቻ ለመፈጸም በመንገድ ላይ እንደነበሩ መስክራለች፡፡ እንደማያመሽ፣ ከምሽቱ 12፡30 ሰዓት ላይ እየተገናኘች አብረው አምሽተው ወደቤታቸው እንደሚገቡ በመናገር፣ ፈጸመ የተባለውን ወንጀል እንዳልፈጸመ መስክራለች፡፡

የመጨረሻው ምስክር ብርሃኑ መብራቱ መሆኑን ተናግሮ የሳምሶን የቅርብ ጓደኛ መሆኑን፣ ሳምሶን ደፈራት የተባለችው ነቢያት መሐመድ፣ ሳምሶን እጮኛዋ እንዲሆን ንገርልኝ ትለው እንደነበር፣ ለሳምሶን ሲነግረው ‹‹ባለ ትዳር ነኝ እረፊ በላት›› እንደሚለውና በ2003 ዓ.ም. ሲጠፋባት ጠይቃው ትዳር መያዙን ሲነግራት፣ ‹‹ቆይ እሠራለታለሁ›› ማለቷን መስክሯል፡፡

ብርሃኑ ምስክርነቱን ሲጨርስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው አቤቱታ፣ ‹‹የመጣሁት የሕግ መጥሪያ ስለደረሰኝ ነው፤ ከዚህ ስወጣ ግን እያዛለሁ፡፡ የፍርድ ቤቱ ፖሊስ ታክሲ እንዲያሲዘኝ ይታዘዝልኝ፤ እቤቴ ከገባሁ በኋላ አልወጣም፤›› በማለት እያለቀሰ ፍርድ ቤቱን ለምኗል፡፡

ፍርድ ቤቱ መስክሮ ስለወጣ ማንም እንደማይነካው ገልጾ፣ በሕግ በሚመራ አገር ውስጥ የሚያስፈራው ነገር እንደሌለና ማንም ሊያስረው እንደማይችል ዋስትና ሰጥቶት፣ ‹‹ብትታሰር ቤተሰቦችህ መጥተው ያመልክቱ ፍርድ ቤቱ ዋስትና ሰጥቷል፤›› ሲለው፣ ዓቃቤ ሕጉ ‹‹እኔ ይዤው እወጣለሁ፤ ካስፈለገም እቤቱ አደርሰዋለሁ፤›› ቢሉም፣ ፍርድ ቤቱ ማንም እንደማይነካው በማረጋገጥ ብቻውን እንዲሄድ አድርጐታል፡፡ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ለየካቲት 29 ቀን 2004 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡