በአገሪቱ ውስጥ ካሉ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት በላይ ከ36 ሺሕ በላይ አባላትን በመያዝ ቀዳሚ የሆነው የትግራይ ንግድ ምክር ቤት፣ ስለሕንፃ አጠቃቀም የሰጠውን ውሳኔ የተቃወመበትን ደብዳቤ ለብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱና ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ላይ ልኳል፡፡
የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ውሳኔ ትክክል ያልሆነና ሕጋዊ መሠረት የሌለው መሆኑን ከመግለጽ ጐን ለጐን፣ የሕንፃውን አጠቃቀም በተመለከተ መሆን ይገባው ነበር ያለውን ሐሳብ ያካተተ መሆኑን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የትግራይ ንግድ ምክር ቤት የሕንፃው ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው ሆኖ እያለ በውሳኔ አሰጣጡ ላይም ሆነ እንደ አንድ አባል ምክር ቤት ሊሰጠው የሚገባው መብት የተነፈገው በመሆኑ፣ ይህ እንዲታይለትና አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጠው መጠየቁን የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን በበኩላቸው፣ የትግራይ ንግድ ምክር ቤት ለጻፈው ደብዳቤ ቦርዱ ተወያይቶ መልስ ይሰጥበታል ብለዋል፡፡
የትግራይ ንግድ ምክር ቤት አዲሱ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቦርድ ውሳኔን የሰማው በሚዲያ መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች፣ ቢያንስ ስለሕንፃው አጠቃቀም ሐሳብ ለመስጠት ዕድል ሊሰጠው ይገባ ነበር የሚልም አቋም አለው፡፡ በተለይ በሕንፃው ጉዳይ መወሰን የነበረበት ጠቅላላ ጉባዔ እንጂ ቦርድ አይደለም በማለት በደብዳቤው ገልጿል፡፡ ወይዘሮ ሙሉ ግን ይህንን ሐሳብ አይቀበሉም፡፡ ‹‹ቦርዱ ምን መሥራት እንዳለበትና የጠቅላላ ጉባዔው ሥልጣን ደግሞ ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የሕንፃውም ጉዳይ በጽሕፈት ቤት ደረጃ ሊያልቅ ይችል ነበር፤›› ያሉት ወ/ሮ ሙሉ፣ ነገር ግን የሕንፃው ጉዳይ ለብዙ ጊዜያት ጭቅጭቅ የነበረበት ስለነበረ ቦርዱ ሊወስን መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በአዲሱ ቦርድ የተወሰነው ውሳኔ የመጨረሻ መፍትሔ ይሆናል ብለው የማያምኑ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ደግሞ፣ ሕንፃው ለአራት ምክር ቤቶች ተመለሰ የተባለበት ሰነድ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ሕንፃውን እንዲጠቀሙበት ቅድሚያ የተሰጣቸው ከአራቱ ንግድ ምክር ቤቶች ሌላ ሌሎች የብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ አባላት እንዲካተቱ ባለመደረጋቸው፣ ውሳኔው በራሱ ክፍተት ያለበት እንደሆነ ያሳያል በማለት፣ ቦርዱ ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ውጭ ሄዷል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ 18 አባል ምክር ቤቶች ሲኖሩት፣ እነዚህም አባላት የየክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች፣ አገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የአምራቾች ማኅበራትን የሚያጠቃልል ነው፡፡
ጥር 8 ቀን 2004 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው የአዲሱ ቦርድ ውሳኔ ግን በሕንፃው እንዲጠቀሙ የተደረጉት የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ አገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ናቸው፡፡
የሕንፃውን አጠቃቀም በተመለከተ በአዲሱ ቦርድ የተወሰነውን ውሳኔ በመቃወም የመጀመርያው የሆነው የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቢሆንም፣ ሌሎች የክልል ንግድ ምክር ቤቶች ተመሳሳይ ጥያቄ ሊኖራቸው ይችላል የሚል ግምትም እየተሰነዘረ ነው፡፡
ወ/ሮ ሙሉ ግን ሌሎች ጥያቄዎች ቢነሱም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ የትግራይ ንግድ ምክር ቤት ያቀረበው ጥያቄ ለብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ከመቆርቆር ይሆናል የሚል እምነት ያላቸው ቢሆንም፣ ከዚህ ውጭ ግን ሆን ተብሎ ምክር ቤቱን ሊበጠብጡ የሚችሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ የሕንፃውን አጠቃቀም በተመለከተ ቦርዱ በወሰነው ውሳኔ ላይ ግን ማንኛውንም ኃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ እንደሆኑም አስረድተዋል፡፡
በሕንፃው አጠቃቀም ላይ የተሰጠውን ውሳኔ ተከትሎ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት እስከዛሬ ሲከራከርበት የቆየውን የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳቱን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
ከ65 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ይህ ባለሰባት ፎቅ ሕንፃ በወቅቱ ዋጋ በ1.8 ሚሊዮን ብር ነበር የተገነባው፡፡ የግንባታው ወጪውም በየክልሉ ባሉ ነጋዴዎችና መንግሥት ለዚሁ ሕንፃ ብሎ እንዲሰበሰብ ካደረገው የቴምብር ሽያጭ በመሆኑ፣ ቀድሞም ቢሆን የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የሕንፃው ባለቤት ነኝ ብሎ መከራከር እንዳልነበረበት የሚናገሩ አሉ፡፡ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች ለዓመታት ሲወዛገቡበት ቆይተዋል፡፡ ይህ ሕንፃ በደርግ ዘመን ከተወረሰ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፊርማ ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ሚያዝያ 21 ቀን 2000 ዓ.ም. እንዲመለስ መወሰኑ ይታወሳል፡፡


