Thu05172012

Go to :English Edition

Back ዜና ዜና ለደመወዝ ጭማሪ ጥያቄው ምላሽ ያጣው የመምህራን ማኅበር አስቸኳይ ጉባዔ ሊጠራ ነው

ለደመወዝ ጭማሪ ጥያቄው ምላሽ ያጣው የመምህራን ማኅበር አስቸኳይ ጉባዔ ሊጠራ ነው

  • PDF

በመላው አገሪቱ 350 ሺሕ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር (ኢመማ) ለመንግሥት ያቀረበው የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ለመጥራት ተቃርቧል፡፡ ከጥቅምት 3 እስከ 5 ቀን 2004 ዓ.ም. የተካሄደው የኢመማ መደበኛ ምክር ቤት ስለመምህራን የደረጃ ከፍታ፣ ደመወዝና ተፈላጊ ችሎታ በሚመለከት ውይይት ካደረገ በኋላ የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ እስከ ጥር 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ ጥያቄው ምላሽ ካላገኘ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ ወስኖ ነበር፡፡

ምንጮቻችን እንደገለጹት ጉዳዩ የሚመለከተው የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ማኅበሩ ላቀረበው ጥያቄ እስከ ጥር 30 ቀን ምላሽ ካልሰጠ መደበኛ ምክር ቤቱ በወሰነው ውሳኔ መሠረት አስቸኳይ ጉባዔ ይጠራል፡፡

ማኅበሩ በወቅቱ ባወጣው ባለአሥር ነጥብ የአቋም መግለጫ መምህራን ለሚያቀርቡት የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ መጓተት በኑሯቸው ላይ እያሳደረው ያለው ተፅዕኖ በየጊዜው እየናረ የመጣው የመኖርያ ቤት ኪራይ ታክሎበት፣ በአሁኑ ጊዜ መቋቋም ከማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁሞ፣ ችግሩን ለመፍታት የተጀመረው እንቅስቃሴ እየታየበት ያለው መጓተት ተወግዶ መቋጫ የሚያገኝበትና መምህራኑን ተጠቃሚ የሚያደርግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲጀመር፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ተቋማዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቆ ነበር፡፡ ይህ የማኅበሩ አቋም መግለጫ ለሁሉም ክልል ማኅበራት ተልኮ በየትምህርት ቤቱ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ እንዲለጠፍ መደረጉን ከምንጮቻችን ለመረዳት ችለናል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ለመንግሥት ያቀረበው የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ሲጓተት ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ በጥር 2003 ዓ.ም. ለመንግሥት ሠራተኞች የተደረገው ጭማሪ ቀደም ሲል ከማኅበሩ የቀረበውን ጥናት በአግባቡ ያላገናዘበ መሆኑን በመጥቀስ፣ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር አቶ ጁነዲን ሳዶ በተገኙበት የካቲት 26 ቀን 2003 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አስቸኳይ የምክር ቤት ስብሰባ ተካሂዶ ጭማሪውን በመገምገም፣ የከፍተኛ ትምህርት መምህራንን የደረጃ ከፍታ ጨምሮ ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ ጠይቆ ነበር፡፡ ይህንኑ የማኅበሩን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ማኅበሩ የተወከለበት ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩ ሲታይ ቢቆይም ጥናቱ ተጠናቆ ሊገለጽ አልቻለም፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የማኅበሩ አመራር አባል እንደገለጹት፣ መንግሥት እስከ ጥር 30 ድረስ ለቀረበለት የደመወዝ ጭማሪ ምላሽ ካልሰጠ ማኅበሩ በሚጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ውሳኔ ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ በንቲ በበኩላቸው፣ ማኅበሩ አሁንም ከመንግሥት ጋር እየተወያየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“ጥያቄያችሁ ምላሽ ካላገኘ ምን ዓይነት ዕርምጃ ለመውሰድ አስባችኋል?” በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ “ምን ማድረግ እንዳለብን የሚወስነው ጉባዔው ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ኃላፊዎች አባል የሆኑ መምህራንን ባለፈው ቅዳሜ ሰብስበው ማነጋገራቸው ተሰምቷል፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመምህራን ማኅበሩ ያቀረበው የደመወዝ ጥያቄ ተገቢ ቢሆንም፣ “ጥያቄያችን ምላሽ ካላገኘ ከጥር 30 በኋላ ሰላማዊ ሰልፍ እናካሂዳለን፤ ሥራ እናቆማለን፤” የሚለው የተወሰኑ መምህራን አስተሳሰብ ትክክል አለመሆኑን ለባለሥልጣናቱ አሳስበዋል፡፡