Thu05172012

Go to :English Edition

Back ዜና ዜና በኦፕቲካል ፋይበር ብልሽት የቦሌ ጉምሩክ 50 ሚሊዮን ብር ያህል ገቢ አጣ

በኦፕቲካል ፋይበር ብልሽት የቦሌ ጉምሩክ 50 ሚሊዮን ብር ያህል ገቢ አጣ

  • PDF

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የቦሌ ጉምሩክ ጣቢያ በኦፕቲካል ፋይበር ብልሽት ምክንያት ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ብር ገቢ ማጣቱን አስታወቀ፡፡ የቦሌ ጉምሩክ ጣቢያ ኦፕቲካል ፋይበር ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ ብልሽት ስላጋጠመው ለሦስት ቀናት ደንበኞችን አላስተናገደም፡፡ በዚህ ምክንያት ከውጭ አገር በአውሮፕላን ያስገቡትን ዕቃ ከጣቢያው ማውጣት ያልቻሉ ነጋዴዎች ጣቢያውን ሲያማርሩ ሰንብተዋል፡፡

ነጋዴዎችና የጉምሩክ አስተላላፊዎች በአስቸኳይ ወደ አገር ውስጥ ያስገቡትን ዕቃ ማውጣት ባለመቻላቸው፣ ከደንበኞቻቸው ጋር ከፍተኛ ችግር ውስጥ ከመግባታቸውም በላይ ላልጠበቁት ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የቦሌ ጉምሩክ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክብሩ ላቀው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፈው ረቡዕ የኦፕቲካል ፋይበር ችግር በመፈጠሩ ችግሩ በአፋጣኝ እንዲፈታ ኢትዮ ቴሌኮም ይሄዳሉ፡፡ ከዚያም ኢትዮ ቴሌኮም ጨርቆስ አካባቢ ነው ችግሩ ያለው ይላል፡፡ ይሁንና ጨርቆስ አይደለም ተብለው ንፋስ ስልክ ሲሄዱም እዚያም አይደለም ይባላሉ፡፡ በመጨረሻ ሌላ የቴክኒክ ችግር ነው ተብሎ በመጨረሻ ባለፈው ዓርብ ምሽት ላይ ተሠርቷል መባላቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ጣቢያው በሦስት ቀናት ጊዜ ውስጥ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ብር ገቢ ማጣቱን አቶ ክብሩ ገልጸዋል፡፡ የቦሌ ጉምሩክ ጣቢያ የአየር ወደብ በመሆኑ የመንገደኞች፣ የፓስታና የጭነት መተላለፊያ መስመርም ነው፡፡ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን መርምሮ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ ችግር በማጋጠሙ፣ በተለይ ገቢ ዕቃዎችን ከአውሮፕላን ማረፊያ ለማስወጣት ከፍተኛ ችግር አጋጥሟል ተብሏል፡፡

ጣቢያው ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጊዜያት ብልሽት የሚገጥመው በመሆኑ፣ በርካታ ነጋዴዎችና የጉምሩክ አስተላላፊዎች ሲያማርሩ ይደመጣሉ፡፡ ለሦስት ቀናት ያህል ኢትዮ ቴሌኮም ብልሽቱን ማስተካከል ባለመቻሉ ነጋዴዎቹ ለከፍተኛ ወጪዎች መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በቴክኒክ ብልሽቱ ምክንያት ጣቢያው መደበኛ ሥራዎችን ማካሄድ ባለመቻሉ በአብዛኛው ሥራ ቆሞ የሳምንቱ አጋማሽ ተጠናቋል፡፡ ቅሬታቸውን ለሪፖርተር የገለጹ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ አንድ ቴክኖሎጂ ብልሽት ሲያጋጥመው እንዴት ሌላ አማራጭ አይኖርም ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹ቢያንስ ቴክኖሎጂው ቀርቶ ለምን በወረቀት (በማንዋል) አይሠራም?›› ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ አስመጪ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ክብሩ በበኩላቸው፣ ሁሉንም ዕቃዎች በማንዋል ማስተናገድ ከባድ ነው ይላሉ፡፡ የሚበላሹ ዕቃዎችን ግን በማንዋል ለማስተናገድ እየሞከሩ መሆኑን ገልጸው፣ ሁሉንም በማንዋል ለማድረግ ግን በገንዘብ አሰባሰብ በኩል ችግር ይፈጠራል ብለዋል፡፡

እንዲህ ዓይነቱን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳተላይት የመጠቀም አማራጭ መታየት እንደሚኖርበት አቶ ክብሩ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮ ቴሌኮምን ኔትወርክ በመተው በቀጥታ በሳተላይት እንደሚጠቀም ይታወቃል፡፡

ይህንን አሠራር ለመተግበር ተጨማሪ ጥናት አድርጎ ማየት፣ ከዚህ በተጨማሪም ሽቦ አልባ (ዋየርለስ) ቴክኖሎጂን እንደ ተጨማሪ ግብዓት መጠቀም ያስፈልጋል የሚሉ አሉ፡፡ ይሁንና አቶ ክብሩ እንደሚሉት፣ ዋየርለስም ቢሆን የሚተማመኑበት ቴክኖሎጂ ባለመሆኑ ነበር ኦፕቲካል ፋይበርን መጠቀም የጀመሩት፡፡