የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ በአገሪቱ የሚገኙ ባንኮች ለሰጡት ብድር የያዙትን መያዣ (ኮላተራል) ዋጋ እንደሚያሳጣው ያሰጋው የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር፣ አዋጁ ብድር በማስመለስ በኩል የሚኖረውን ተፅዕኖ ለማወቅ በባለሙያዎች ጥናት እያስጠና መሆኑን አስታወቀ፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከተለያዩ ባንኮች በተውጣጡ ባለሙያዎች አማካይነት ጥናቱ እየተካሄደ መሆኑንና በጥናቱ የሚደረስበት መደምደሚያ ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ ባንኮች መያዣ በመያዝ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ብሮችን በብድር ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ለሚሰጡዋቸው ብድሮችም ከሚይዟቸው መያዣዎች መካከል በዋነኝነት በመሬት ላይ የተካሄዱ ግንባታዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ባንኮቹ መሬቱን በቀጥታ ለመያዣነት ባይጠቀሙበትም ግንባታው የተካሄደበት ቦታ (ሎኬሽን) ለብድሩ መጠን ግምት መውሰጃ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ አዲሱ የሊዝ አዋጅ መሬቱም ሆነ መሬቱ ያለበት ቦታ ከሚያስገኘው ዋጋ (ቫሊዩ) ተጠቃሚው መንግሥት እንደሆነ ይደነግጋል፡፡
በዚህ ምክንያት ባንኮቹ ላበደሩዋቸው ብድሮች የያዙዋቸው መያዣዎች እንደማይመጥኑ በመገመትና የሚያመጣውን ተፅዕኖ በማጥናት፣ ከመንግሥት ጋር ለመወያየት እየተዘጋጁ መሆናቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
‹‹ከመሬት ጋር የተያያዘ መያዣ ባንኮች ለሚሰጡት ብድር እስከ 40 በመቶ ድረስ ዋጋ ያስገኛል፡፡ አንድ ባንክ አምስት ቢሊዮን ብር ብድር ሰጥቷል ቢባል 40 በመቶው ግንባታው ለተካሄደበት ቦታ የተሰጠ ዋጋ ነው፤›› ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የባንክ ባለሙያ በባንኮች ላይ ሊጋረጥ ይችላል የሚባለውን አደጋ ከፍተኛነት ይገልጻሉ፡፡
እኚሁ ባለሙያ ባንኮች ከዚህ በኋላ ብድር መስጠት ያለባቸው በመያዣ ላይ ተማምነው መሆን የለበትም ሲሉ ገልጸው፣ ለሚሰጡዋቸው ብድሮች አዋጭ ናቸው በሚሏቸው የፕሮጀክት ሐሳቦች ላይ መተማመን እንዳለባቸው መክረዋል፡፡


