Thu05172012

Go to :English Edition

Back ዜና ዜና በአላባ ቁሊቶ ከተማ በጅምር የቀሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በጨረታ ሊሸጡ ነው

በአላባ ቁሊቶ ከተማ በጅምር የቀሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በጨረታ ሊሸጡ ነው

  • PDF

በአስፋው ብርሃኑ፤ ልዩ ዘጋቢ ከሐዋሳ

በደቡብ ክልል በአላባ ቁሊቶ ከተማ ግንባታቸው የተቋረጠ ከ250 በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባሉበት ሁኔታ በጨረታ እንዲሸጡ ተወሰነ፡፡ ከተጠናቀቁት 105 ቤቶች መካከል 82 ያህሉ ባለፈው የካቲት 6 ቀን 2004 ዓ.ም ለነዋሪዎች መተላለፋቸው ተገለጸ፡፡

በክልሉ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በአላባ ቁሊቶ ከተማ በ2000 ዓ.ም 360 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ የአብዛኞቹ ግንባታ ሳይቀጥል ተቋርጧል፡፡ በተወሰኑ ሜትሮች ከፍታ ላይ በሚገኙት ጅምር ቤቶች አናት ላይ ጉልላት መስሎ የሚታየው ፌሮ ብረት መዛጉ፣ ቤቶቹ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን አይቶ መረዳት ይቻላል የሚሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነዋሪ፣ ግንባታው ከተቋረጠ ሁለት ዓመት እንደሚሆን ለሪፖተር ገልጸዋል፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታም ጥራት ያልነበረውና ኮንትራክተሮቹን የሚከታተል ያለ አይመስልም ነበር ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ፣ አንዳንድ ብሎኮች እየፈራረሱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የአላባ ቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ቆንቻ በጅምር ስለቀሩትና ስለተጠናቀቁት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተጠይቀው፣ የ360 ቤቶች ግንባታ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም የተጠናቀቁት 105 ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከ105 የጋራ መኖሪያ ቤቶች (90 መኖሪያና 15 የንግድ) መካከል 82 ቅድመ ክፍያ ለፈጸሙ ነዋሪዎች የካቲት 6 ቀን 2004 ዓ.ም በዕጣ መተላለፉን አቶ ከድር አብራርተዋል፡፡

ፀሐይና እርጥበት የሚፈራረቅባቸው ቤቶች ግንባታቸው ለረዥም ጊዜ ለምን እንደተቋረጠ የተጠየቁት ከንቲባ አቶ ከድር፣ ‹‹የክልሉ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ከተጀመሩት 360 ግንባታዎች 105 ብቻ እንዲጠናቀቁና የቀሪዎቹ ግንባታ እንዲቋረጥ በመወሰኑ ሥራው እንዲቆም ተደርጓል፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ስለጅምር ግንባታዎች መጨረሻ በተመለከተም የክልሉ ካቢኔ በወሰነው መሠረት ባሉበት ሁኔታ እንዲሸጡ በአሁን ወቅት ጨረታ መውጣቱን ከንቲባው አስረድተዋል፡፡

በክልሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በጅምር የቀሩት በአላባ ብቻ ሳይሆን በዲላ፣ በይርጋ ዓለምና በሌሎች ከተሞችም በተመሳሳይ እንደሚገኙና አንዳንዶቹ እየፈራረሱ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በይርጋ ዓለም የተጠናቀቁት ቤቶች ለሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሲሰጡ፣ በሆሳዕና ከተማ የተጠናቀቁትን የጋራ መኖሪያ ቤቶች የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ እንዲጠቀምበት ተደርጓል፡፡