Thu05172012

Go to :English Edition

Back ዜና ዜና ለስኳር ልማት የሚያስፈልግ 100 ሺሕ ሔክታር ከሰው ንክኪ ነፃ ሊሆን ነው

ለስኳር ልማት የሚያስፈልግ 100 ሺሕ ሔክታር ከሰው ንክኪ ነፃ ሊሆን ነው

  • PDF

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የስኳር ልማት ኮርፖሬሽንና የፓኪስታኑ ኩባንያ አል ሐበሻ ስኳር ሊያለሙ ያቀዱትን መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት ከሰው ንክኪ ነፃ በማድረግ ሥራ ተጠምዷል፡፡ መሬቱ የሚገኘው በጂማና በምሥራቅ ወለጋ ዞኖች መካከል ከበደሌ ከተማ ወደ ነቀምት ከተማ በሚወስደው ደዴሳ ሸለቆ ውስጥ ነው፡፡

በዞኖቹ ኩታ ገጠም በሆነው ለሸንኮራ አገዳ ልማት ምቹ ቦታ ላይ 100 ሺሕ የሚጠጉ አርሶ አደሮች የሚገኙ በመሆኑ፣ ክልሉ ለአርሶ አደሮቹ ተለዋጭ ቦታ በመፈለግ ላይ ይገኛል፡፡

ይሁንና ግን ሥራውን በዋነኛነት በማካሄድ ላይ የሚገኘውን የኦሮሚያ መሬትና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ የሚመሩት አቶ ድሪቡ ጀማል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተነሺዎቹ 100 ሺሕ እንደማይሆኑና ለጊዜው ቁጥራቸውን በውል እንደማያስታውሱ አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ የሚነሱት በሰባት ወረዳዎች ሥር ከሚገኙ 49 ቀበሌዎች ነው፡፡
በሥፍራው የሚገኙ ምንጮቻችን እንደገለጹት፣ በአንድ ቀበሌ ከሦስት ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ይገኛሉ ብለው፣ እንዲያውም አርሶ አደሮቹ ከመቶ ሺሕ በላይ እንደሚሆኑ ይከራከራሉ፡፡ በሥራው ላይ የሚገኙ ምንጮቻችንም ተነሺዎቹ ከመቶ ሺሕ ይበልጡ ይሆናል እንጂ አያንሱም ብለዋል፡፡

ከቦታው ላይ መነሳታቸው ያላስደሰታቸው አርሶ አደሮች፣ ተቃውሟቸውን በተለያዩ መንገደች እየገለጹ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከተቃውሞ መካከልም ከአንድ ሳምንት በፊት በፓኪስታኑ ኩባንያ የሸንኮራ አገዳ ማሳ ላይ እሳት መለቀቁን ይጠቅሳሉ፡፡ እሳቱን ለማጥፋትም ከፍተኛ ርብርብ ከተደረገ በኋላ ከሁለት ቀን በኋላ መጥፋቱን ከሥፍራው የደረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አቶ ድሪቡ እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል ለኩባንያው የተሰጠው ከወንዝ ወዲህና ወዲያ ማዶ ነው፡፡ አሁን በአንድ ለማጠቃለል እየተሠራ ነው፡፡ ከወንዝ ወዲያ ማዶ ብቻ ከ62 ሺሕ ሔክታር መሬት በላይ ለልማት ምቹ የሆነ ቦታ መኖሩን ገልጸዋል፡፡

የፓኪስታኑ ኩባንያ አል ሐበሻ ስኳር ፋብሪካ ከሦስት ዓመታት በፊት በአካባቢው 26 ሺሕ ሔክታር መሬት በመረከብ የሸንኮራ አገዳ ልማት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በዓመት 24 ሺሕ ቶን ስኳር የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያው ከተረከበው ቦታ በተጨማሪ 26 ሺሕ ሔክታር መሬት ለማስፋፊያ የሚፈልግ በመሆኑና የተቀረውን ቦታ የስኳር ልማት ኮርፖሬሽን ለአርጀ ደዴሳ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቱ የሚፈልገው በመሆኑ፣ ቢሮው አርሶ አደሮቹን መልሶ በማስፈር ሥራ ተጠምዷል፡፡

የዚህን ቦታ የመሬት አጠቃቀም ጥናት እንዲያካሂድ የፌዴራል መንግሥት፣ ለኦሮሚያ ውኃ ሥራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ሰጥቶታል፡፡ ኢንተርፕራይዙ ይህንን ሥራ ለመሥራት 52 ሚሊዮን ብር የተከፈለው ሲሆን፣ ልማቱን ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ግድብ የዓባይ ገባር በሆነው ደዴሳ ወንዝ ላይ እንዲገነባ ደግሞ ለኦሮሚያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ሥራው ተሰጥቶታል፡፡

ኢንተርፕራይዙ ግንባታውን ለማካሄድ 1.6 ቢሊዮን ብር ተከፍሎታል፡፡