‹‹ያሳለፍነው ዓመት ከባድ ነበር፡፡ የአፍሪካ መርከብ በማዕበል ውስጥ ነበረች፤›› ያሉት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዣን ፒንግ ሰሞኑን እየተካሄደ ያለውን የአፍሪካ ኅብረት 18ኛ ጉባዔ ባለፈው ሰኞ ሲከፍቱ ነው፡፡
እንደ ሊቀመንበሩ አባባል፣ የአፍሪካ የዴሞክራሲ ሒደት መንፈስ እንዳይደበዝዝ ሕብረታቸው ዓመቱን ሲሠራ አሳልፏል፡፡
የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት ሰብሰባ እየተካሄደ ያለው አኅጉሪቱ ሁለት ወሳኝ ክስተቶችን ያስተናገደችበት ዓመት ከተጠናቀቀ በኋላ ነው፡፡ በአንድ በኩል በቱኒዝያ የተለኮሰው የዓረብ አብዮት ሰሜን አፍሪካን አናግቶ ሦስት ዕድሜ ጠገብ መሪዎች ከሥልጣናቸው የተሽቀነጠሩ ሲሆን፣ ከሰሃራ በታች ያለው የተቀረው የአፍሪካ ክፍል ደግሞ አንዳንድ ደም አፋሳሽ የሆኑ የይምሰል ምርጫዎች የተካሄዱበት ሆኖ አልፏል፡፡
የይስሙላ ምርጫ ማካሄድና የሕዝብን አመኔታ አግኝቻለሁ በማለት ሥልጣን ላይ መቆየት፣ አለበለዚያም ከነአካቴው ምርጫ አያስፈልግም በሚል ሥልጣንን ከነቤተሰብ በዘር ተቆራኝተው እዚያው መክረም የሚመርጡ የአፍሪካ መሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ የአፍሪካ የፖለቲካ ተመራማሪዎች ዘንድሮ በሰሜን አፍሪካ ውስጥ ከተፈጠረው ክስተት የማይማር መሪ አይኖርም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ከእነዚህ ክስተቶች የማይማሩና ‹‹የሥልጣን ባለቤትነት የሕዝብ ነው የሚለውን›› በቃል ብቻ የሚቀበሉ የአፍሪካ መሪዎች አሁንም አይጠፉም፡፡ የሊቢያን፣ የቱኒዚያንና የግብፅን አቻዎቻቸውን ያጡት የአፍሪካ መሪዎች በሚቀጥለው 19ኛው የኅብረቱ ስብሰባ እንደሚሳተፉ እርግጠኛ ይሆናሉ ማለት አይቻልም፡፡
የይምሰል ምርጫ እስከመቼ?
በሚቀጥለው ዓመት ራሳቸውን ለሁለተኛ ጊዜ ለምርጫ ውድድር ለማቅረብ በዝግጅት ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በወቅቱ ምርጫ ማሸናፈቸውን ተከትሎ፣ ወደ አፍሪካ በተጓዙበት ወቅት ለጉብኝት የመረጧት ብቸኛ አገር ጋና ነበረች፡፡ በአንፃራዊነት የዴሞክራሲ ጭላንጭል ከታየባቸው በጣት ከሚቆጠሩ የአፍሪካ አገሮች አንዷ በሆነችው ጋና ዋና ከተማ አክራ ላይ ሆነው ባደረጉት ንግግር፣ የአፍሪካ ሕዝቦች ለዴሞክራሲ የሚያደርጉትን ትግል ከመደገፍ ውጪ ሕዝቦቹንና መሪዎቹን በመተካት ዴሞክራሲ ለማስፈን የሚደረግ ጥረት እንደማይኖር ፖሊሲያቸውን ግልጽ አድርገው ነበር፡፡ የአፍሪካ ዴሞክራሲ አቀንቃኝ የነበሩ ሌሎች የምዕራብ መሪዎችም ይህንኑ የኦባማ ንግግር የተቀበሉ ይመስል፣ ለአፍሪካ ዴሞክራሲ የሚያደርጉትን የድጋፍ እንቅስቃሴ ከቀነሱ ውለው አድረዋል፡፡
አንዳንዶቹ ደግሞ ከአምባገነን መሪዎች ጋር ተሞዳምደው መሥራት መርጠዋል፡፡ ሕዝቡ በእነዚሁ መሪዎች ላይ ባመፀበት ወቅትም፣ አንዳንዶቹ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ለዴሞክራሲ የሚታገሉ ተቃዋሚዎችን ከመደገፍ ይልቅ ከአምባገነኖቹ ጋር ሲተባበሩና ሲንቀሳቀሱ የተስተዋሉበትም ጊዜ ነበር፡፡ ከአብዛኛዎቹ የዓለም መሪዎች ጋር ትንቅንቅ ውስጥ ገብተው የነበሩትን ጋዳፊን ለመጣል ደግሞ ምዕራባዊያኑ የአፍሪካ ኅብረት ‹‹ካርድም›› ሳያስፈልጋቸው በፈቃዳቸው ገብተው፣ ጋዳፊን በጦር ኃይል ከሥልጣን እስከማስወገድ ደርሰዋል፡፡
በሰሜን አፍሪካ በተከሰተው ዓመፅ እምብዛም ያልተነኩና በይምሰል ምርጫ ሥልጣን ላይ ቁጢጥ ብለው የሚገኙ የአፍሪካ መሪዎችም ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው ምን እንደሚሆን መገመት ባይቻልም፣ በተጭበረበረ ምርጫ የመጡትን ዕውቅና ለመንፈግ አልደፈሩም፤ ምዕራባዊያኑ፡፡ ሒውማን ራይትስ ዎች ባለፈው እሑድ ያወጣው የ2012 የዓለም ሪፖርትም የሚያትተው ይኼንኑ ነው፡፡ ‹‹ምዕራባዊያን አፍሪካንና መካከለኛው ምሥራቅን ችላ ብለዋል›› በማለት፡፡
ባለፈው ዓመት በአፍሪካ 20 ምርጫዎች የተካሄዱ ቢሆንም፣ የተደረገው የፓርቲ ወይም የሥልጣን ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ባለፈው ዓመት ከተካሄዱት ደም አፋሳሽ ምርጫዎች መካከል የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አንዱ ሲሆን፣ ከበፊቱ (እ.ኤ.አ 2006) ምርጫ በጥራቱ የወረደና ብዙ ዓለም አቀፍ ትችት ያስተናገደ ነበር፡፡ አገሪቱም እጅግ እንድትከፋፈል ምክንያት ሆኗል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት በበኩሉ በምርጫ ሳቢያ የተከሰቱ ቀውሶችንና ግጭቶችን መቆጣጠር ተችሏል በሚል ራሱን እያንቆለጳጰሰ ነው፡፡ የኮትዲቯር፣ የላይቤሪያ፣ የናጄሪያ፣ የዛምቢያና የሴራሊዮን ምርጫዎች በመጠኑም ቢሆን በአወንታዊ መልኩ የሚነሱ ናቸው፡፡
ከጥቂቶቹ በስተቀር በአፍሪካ የተካሄደ ምርጫዎች ከሞላ ጎደል ቅጥፈት፣ ውሸትና ማጭበርበር የሚታይባቸው በመሆናቸው፣ የሕዝቡ እውነተኛ ፍላጎት የተንፀባረቀባቸውና የሕዝቡን የሥልጣን ባለቤትነት ያረጋገጡ ነበሩ ማለት አይቻልም፡፡
ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነውን ሒውማን ራይተስ ዎች በ676 ገጽ ሪፖርቱ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በዓለም ላይ ተፈጸሙ ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያካተተ ሲሆን፣ በተናጠልም የ90 አገሮችን የሰብዓዊ መብት ከዘላቂ ጥቅምና መርህ አያያዝ አንፃር አካቶ ይዟል፡፡ የመግቢያው ዋነኛ አካል አድርጎ ባቀረበው ሪፖርቱም በወቅቱ በመካሄድ ላይ ያለውን የሰሜን አፍሪካንና የዓረብ አብዮትን መደገፍ ያስፈልጋል የሚል አቋም ይዟል፡፡
‹‹መንግሥትን ለሚቃወሙትና ለሠልፈኞቹ የማይቋረጥና የማይዛነፍ አለም ዓቀፍ ድጋፍ ማድረግ በአካባቢው ያሉ አምባገነኖችን ለማስወገድና መሠረታዊ የሰው ልጅ ነፃነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ ዋነኛ ጫና የማሳደርያ መንገድ ነው፤›› ብሏል፡፡
‹‹እ.ኤ.አ. በ2011 ዓመት በአፍሪካ የተካሄዱት ምርጫዎች ዴሞክራሲያዊ አመራር ለመስጠት የሚያስችል ቁርጠኝነት መኖሩን ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱ ይሆናሉ፡፡ ሆኖም መሪዎቹ በምርጫዎቹ ወቅትም ሆነ በምርጫዎቹ ማግስት ብጥብጥ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆነዋል፤ መብቶችንም ረግጠዋል፤›› ሲል ኮንኗል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል በቀለ፣ ‹‹ባለፈው ዓመት አፍሪካዊያን መሪዎቻቸውን ለመምረጥ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ሆኖም በሚያሳዝን ሁኔታ ድምፃቸው በመንግሥት አልተከበረም፡፡ የወታደርና የፖሊስ ወከባም በዝቷል፡፡ ግጭቶችም ተቀስቅሰዋል፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ችግሮች ካልተወገዱ በስተቀር አፍሪካዊያን በመጪዎቹ ምርጫዎችም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው የሚገጥማቸው፤›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
በመጪው ዓመትም ሌሎች 25 የአፍሪካ አገሮች ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጁ ቢሆንም፣ አፍሪካ ኅብረት እንደ ድርጅት ዲሞክራሲን አበክሮ መደገፍ ተስኖታል ሲል ሒውማን ራይትስ ዎች ይተቻል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ከምርጫና ከሕገ መንግሥታዊ መንገድ ውጪ ወደ ሥልጣን ለሚመጣ አካል ዕውቅና ባይሰጥም፣ የሚካሄዱት ምርጫዎች ግን ዲሞክራሲያዊ አለመሆናቸውን ሲያሳይ አይስተዋልም፡፡ ለአብነት በአውሮፓ ኅብረትና በአሜሪካ መንግሥት ትችት የቀረበበትን የኢትዮጵያ የ2002 ምርጫ ከማናቸውም አካል በበለጠ ‹‹ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ›› በማለት ነበር ድጋፉን የሰጠው፡፡ ይህም ለከፍተኛ ትችት ዳርጎታል፡፡
ኅብረቱ እርስ በርሳቸው መተቻቸትና መተራረም ለማይሆንላቸው የአኅጉሪቱ አምባገነን መሪዎች መደበቂያ ሆኖ እያገለገለ ነው የሚሉ ትችቶችም ይደመጣሉ፡፡
አፍሪካ ኅብረት ዴሞክራሲንና ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ በርካታ ቻርተሮችን በማፅደቅ የሚታወቅ ቢታወቅም፣ ለተግባራዊነታቸው እምብዛም ነው፡፡ ይባስ ብሎ አንዳንዶቹ ወሳኝ ሰነዶች ሲጓተቱ ይስተዋላሉ፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ2007 የተረቀቀው፣ ‹‹የዴሞክራሲ፣ የምርጫና የአስተዳደር ቻርተር›› በመባል የሚታወቀው ሰነድ ከ53 አባል አገሮች 37 ብቻ የፈረሙበት ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል በፓርላማቸው ያፀደቁት 14 ብቻ ናቸው፡፡ ይኼው አምባገነንትን ለመዋጋት ይረዳል በሚል የተረቀቀው ሕግ ሆኖ እንዲወጣ በ15 አባል አገሮች ተፈርሞ መፅደቅ ይኖርበታል፡፡
ዴይሊ ማክፈክ የተባለው ሚዲያ ያነጋገራቸው መቀመጫው በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሆነ የደቡብ አፍሪካ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ናሚያ በህበር ሙለር፣ ቻርተሩ በቀጥታ ከምርጫና ከሰላም ጋር የተዛመደ መሆኑን ከገለጹ በኋላ፣ ‹‹ቻርተሩ ቀደም ሲል ከፀደቀው የሰብዓዊ መብት ቻርተር ብዙም የማይለይ ቢሆንም፣ መሪዎቹ ለመፈረም ያዳገታቸው ምን እንደሆነ አይገባኝም፤›› ይላሉ፡፡
እንደዚህ ዓይነት ወሳኝ ሰነዶች ማፅደቅና መተግበር ያቃተው የአፍሪካ ኅብረት ለዴሞክራሲ ምን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የተጠራጠሩት ሙለር፣ ዕድሜ ልካቸውን በሥልጣን ለመቆየት ከሚፈልጉ መሪዎች ስብስብ ምንም አይጠበቅም የሚል ድምዳሜ ሰጥተዋል፡፡
አመፅ እንደ አማራጭ
በአፍሪካ የሚካሄዱት ምርጫዎች በአብዛኛው በብጥብጥና በአመፅ የሚታጀቡ ናቸው፡፡ አመፆቹ የምርጫዎቹን ውጤት መቀበል ካለመቻል የሚነጩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የ1997ቱ ምርጫ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡ በግጭትና በፖለቲካ ቀውስ የሚታጀቡ ምርጫዎች ሕዝብንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተስፋ በማስቆረጥ፣ የአገሪቱን ዴሞክራሲ ወደኋላ የሚጎትቱ ናቸው፡፡ በአብዛኛው የአፍሪካ አገሮች እየተስተዋለ ያለውም ይኸው ነው፡፡
በሊቢያ፣ በግብፅና በቱኒዚያ የተከሰተውና በሶርያና በየመን እየተቀጣጠለ ያለው አመፅ ግን ከምርጫ ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ አፍሪካ ኅብረት በሰሜን አፍሪካ በተከሰተው እንዲህ ዓይነቱ ወሳኝ አመፅ የወሰደው የተለሳለሰ አቋም በብዙዎች ክፉኛ እንዲተች መንገዱን አመቻችቷል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ግን ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ አፍሪካ ኅብረት በሊቢያና በሌሎች አገሮች የያዘው አቋም ችላ ቢባልም ትክክለኛ ነበር በሚል ይሞግታሉ፡፡ ኅብረቱ በዚህ ጉዳይ ላይ የወሰደውን አቋም ክፉኛ የተቸው የሰሞኑ የሒውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ግን፣ አፍሪካ ኅብረት አሁንም በአፍሪካ ሊከሰቱ የሚችሉ ፀረ አምባገነን አመፆች የዴሞክራሲ ምንጭ መሆናቸውን ግንዛቤ ወስዶ አወንታዊ ሚና እንዲጫወት ጠይቋል፡፡ ‹‹ዓለምም የሰሜን አፍሪካና የአረብ አብዮት እንዲስፋፋ መደገፍ ይኖርበታል›› የሚል አቅም ይዟል፡፡


