በአፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶች በርካታ መንስዔዎች የሚኖሩዋቸው ቢሆንም፣ በአብዛኛው በድንበር ውዝግብ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በሁለት አገሮች ድንበር አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶች መነሻቸው፣ ሁለትና ከዚያ በላይ ማኅበረሰቦች ለሁለት ተከፍለው መኖራቸው መሆኑን የግጭት ተመራማሪዎች ያመለክታሉ፡፡
አብዛኛው በቅኝ ግዛት ዘመን በተደረገው የደመ ነፍስ የድንበር ማካለል ነው፡፡
እነዚህ ማኅበረሰባዊ ግጭቶች እየተበራከቱ በሄዱ ቁጥር ሌላ መልክ ይዘውና ገዝፈው በአገሮች መካከል ወደሚደረጉ አውዳሚ ጦርነቶች ይሸጋገራሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ግጭቶችን ለማስቀረት እየተንቀሳቀሰ ያለው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የክልሉን ሰላምና ደኅንነትን ለመጠበቅ ኃላፊነት ወስዶ እየሠራ ይገኛል፡፡ የድርጅቱ አባል አገሮች በክልሉ በተለይ ደግሞ በሶማሊያና በሱዳን ስለሚታዩ ግጭቶችና ደኅንነት አልባ ሁኔታዎች እየተገናኙ የሚመክሩ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚከሰቱ የሽብርተኝነት አደጋዎችን ለመከላከልም ይሠራሉ፡፡ የኤርትራ መንግሥት በሶማሊያ የሚያደረገውን ጣልቃ ገብነትና ከአሸባሪዎች ጋር ያለውን ትስስር፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ሊፈጸም የታሰበው የሽብር አደጋ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ለመጣራት የበቃው ሪፖርቱ በኢጋድ ተጠናቅሮ ከቀረበ በኋላ ነው፡፡ ስለ አኅጉሩ ደኅንነትና ፀጥታ በኃላፊነት የሚሠራው የአፍሪካ ኅብረትም በተመድ የቀረበለትን አቋምና ሪፖርት ተቀብሎ ሲያስተናግድ ተስተውሏል፡፡
ታሞ ከመማቀቅ…
የተለመደው የግጭት አፈታትና መከላከል በአፍሪካ በሁሉም አካባቢያዊ ማኅበረሰቦች የሚደረግ ዓይነት ቢሆንም፣ ኢጋድ የሚከተለው አንድ የተለየ የግጭት አፈታት ዘዴ አለው፡፡ አሁን አሁን ይኼ ዘዴ በሌሎቹ አኅጉራዊና ክልላዊ ድርጅቶችም እየተለመደ መጥቷል፡፡ በተለይ በድንበር አካባቢ በሚገኙ ማኅበረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ባህላዊ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት ቀድሞ የማስጠንቀቅ ሥርዓትን በመገንባት ግጭትን ለማስቀረት ያለመ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ2002 ለዚሁ ዓላማ የተቋቋመው ንዑስ ድርጅት የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ሥርዓት (Conflict Early Warning and Response Mechanism - CEWARN) በመባል የሚታወቀው ሲሆን፣ ዋና ጽሕፈት ቤቱን እዚሁ አዲስ አበባ በማድረግ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዓላማዎች ይዞ የተነሳው ኢጋድ፣ ይኼው ስልቱ ግጭቶችን በማስቀረት የጋራ ልማትን ማስፋፋት የሚለው ዋነኛው ዓላማውን ለማሳካት የነደፈው ሥርዓት መሆኑን የተቋቋመባቸው መርሆዎች ያመላክታሉ፡፡ ተቋሙ በድንበር አካባቢ በሚገኙና ኑራቸውን በመዘዋወርና ቋሚ ባልሆነ ሥፍራ በመሠረቱ አርብቶ አደሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ይሠራል፡፡ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ለራሳቸውና ለከብቶቻቸው ወቅትን እየተከተሉ ቀለብን ፍለጋ ሲንቀሳቀሱ በሚያደርጉት ፉክክርና የጥቅም ግጭትን ተከትሎ የሚከሰቱ አለመግባባቶች ወደ ከፍተኛ አገራዊና ክልላዊ ግጭቶች እንዳያድጉ ይከላከላል፡፡
የኢጋድ አባል አገር የሆኑት ጂቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ኡጋንዳ በተስማሙበት መሠረት ላለፉት አሥር ዓመታት በክልሉ ሲንቀሳቀስ የቆየው ይኸው ድርጅት፣ በእያንዳንዱ አባል አገር ከሚገኙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ የግጭት ተቋማት ጋር በመተባበር የሚሠራ ሲሆን፣ ብሔራዊ የጥናት ተቋማትን (National Research Institute) እና የመስክ ተቆጣጣሪ (Field Monitors) ቡድኖችን በግብዓትነት ይጠቀማል፡፡ ከዚህም ውጪ በእያንዳንዱ አገርና አካባቢ አስተዳድሮች ካሉ የደኅንነትና የግጭት ተቋማትም ጋር በቀጥታ መረጃን በመለዋወጥና በመመጋገብ ይንቀሳቀሳል፡፡ ድርጅቱ በክልሉ በሦስት በተመረጡ አካባቢዎች ለይቶ የሚሠራ ሲሆን፣ አካባቢዎቹን ‹‹ክላስተር›› ይላቸዋል፡፡ እነሱም ካራሞጃ ክላስተር በመባል የሚታወቀው (በኬንያ፣ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በኡጋንዳ ድንበር ተሻጋሪ ማኅበረሰቦችን የሚያጠቃልል)፣ ሶማሌ ክላስተር (በሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ የሚገኘውን አካባቢ የሚሸፍን) እና ድኼል ክላስተር (በጂቡቲና በኢትዮጵያ መካከል የሚገኘውን የጋራ ድንበር የሚያጠቃልል) የሚሸፍኑ ናቸው፡፡
እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየተንቀሳቀሰ ያለው ሴዋርን፣ ሰሞኑን ራሱን የገመገመበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከትናንት በስቲያ በስዮናት ሆቴል ባካሄደው ስብሰባ እንደተገለጸው፣ ድርጅቱ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ወደ ከፍተኛ የግጭት ደረጃዎች ተሸጋግረው አጎራባች አገሮች ወደ ጦርነት እንዲያመሩ የሚያስገድዱ ግጭቶችን በማስቀረት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፤ በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቱ፡፡
የኢጋድ አባል አገሮች ተወካዮች በተገኙበት በዚሁ ስብሰባ በድርጅቱ የምላሽ መስጫ ክፍል አስተባባሪ አቶ አብዱራሻድ ዋርሰኖ የቀረበው የግምገማ (ጥናታዊ) ጽሑፍ እንደሚያመለክተው፣ በእያንዳንዱ አባል አገር የጋራ ድንበር የሚገኙ የሰላም ፕሮጀክቶች ውጤት እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ በምሳሌነት የተነሳውና ብዙ ጊዜ ለአካባቢ ማኅበረሰቦች ግጭት ሰላም የነፈጉ የእርስ በርስ ግጭቶች በሚነሱባቸው በኬንያ፣ በደቡብ ሱዳንና በኢትዮጵያ አዋሳኝ ቱርካና ንያጋቶም - ቶፓዛ አገናኝ በሆነው ሥፍራ የተደረጉትን የሰላም ድርድርና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን አመላክተዋል፡፡
ዲሎ - ተልታል - ተስታል ዱካና በተባሉት አካባቢዎች የተደረጉ የሰላም ምክክሮችና ንግግሮች እንደ ስኬት ተነስተዋል፡፡ በጅቡቲ አካባቢ የነበረው ተመሳሳይ የሰላም ሒደትም በአግባቡ መጠናቀቅ መቻሉ ተወስቷል፡፡ እንደ ጽሑፍ አቅራቢው አባባል፣ በአብዛኛው የሰላም ግንባታ ሒደቶች ወጣትና ሴቶች የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማማከር ትልቅ ሥራ ሊሠራ ችሏል፡፡
ጽሑፍ አቅራቢው እነዚህና ሌሎች የሰላም ሒደቶች እንደ ድርጅቱ ስኬት አድርገው ያቀረቡ ሲሆን፣ አጋጠሙ ያሉዋቸውን አንዳንድ ፈተናዎችም ጠቃቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያንና የኬንያን ድንበር አዋሳኝ (ሞያሌ) አካባቢ ቦረናና ገብራ በተባሉ ማኅበረሰቦች መካከል በቅርቡ የተፈጠረው ግጭት፣ በአካባቢው ተጀምሮ የነበረውን የሰላም ሒደት እንቅፋት እንደሆነበት ተናግረዋል፡፡ በአንዳንድ አባል አገሮች በኩል እንዲሀ ዓይነት ግጭትን ለማስቀረት በሚደረገው ጥረት ቀልጣፋና በአነስተኛ ወጪ ሊሰጥ የሚገባ ከፍተኛ የማስተዳደር ብቃት ማነስ አጋጥሟል፡፡ አጥኚው የሰላም ግንባታ ሒደቶችን የገመገሙት የስብሰባው ዋነኛ ርዕስ ጉዳይ የነበረውን ‹‹ራፒድ ሪስፖንስ ፈንድ›› (RPF) አፈጻጸምን መሠረት አድርገው ሲሆን፣ በተለይ በጂቡቲ፣ በኢትዮጵያና በኡጋንዳ ያሉትን የሰላም ሒደት ፕሮጀክቶች በመከለስ ነበር፡፡
ሒደቶቹ ከገጠሙዋቸው አጠቃላይ ፈተናዎች መካከል ቀዳሚውና ዋነኛው፣ ድንበር ተሻጋሪ ግጭቶችን ለማስቀረት በአብዛኛው በጋራ ድንበር ሰላም መፍጠር የሚያስችል መዋቅር አለመኖሩ ተጠቁሟል፡፡ ኢትዮጵያና ኬንያን በሚያዋስነው የድንበር አካባቢ በተደጋጋሚ ግጭት የሚከሰት ሲሆን፣ የሁለቱም አገሮች መሪዎች ችግሩን ለመፍታት የጋራ ኮሚቴ አዋቅረው ሲንቀሳቀሱ መስተዋላቸው የሚታወስ ነው፡፡
አጥኚው እስካሁን ከተደረገው እንቅስቃሴ የተገኙትን ትምህርቶችንና አቅጣጫዎችን የጠቃቀሱ ሲሆን፣ ድርቅና ረሃብ፣ ስደትና የአካባቢው አየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ማጥናትና ዘላቂና የአጭር ጊዜ የሰላም ግንባታ ሒደቶች ትስስር የመፍጠር አስፈላጊነትን አስገንዝበዋል፡፡
ድርጅቱ ለይቶ የሚንቀሳቀስባቸውን ሦስቱን ክላስተሮች አጠቃልለው ምን መደረግ እንዳለበት የመፍትሔ ሐሳቦች ሲጠቁሙ፣ አብዛኛዎቹ የግጭት መፍታት እንቅስቃሴዎች ከልማት ኃይሎች ጋር መናበብ እንዳለባቸው፣ በእያንዳንዱ የጋራ ድንበር አካባቢ የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎችንና ባህላዊ የሰላም ከሚቴዎችን ማጠናከር፣ እነዚህን ለማጠናከርና በአካባቢያቸው ለሚነሱ ግጭቶች በራሳቸው መንገድ መፍትሔ ይሰጡ ዘንድ በገንዘብና በቴክኒክ ማገዝ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የተገኙት የኢጋድ የሽብርተኝነት ዓቅም ግንባታ ኃላፊ ኮማንደር አበበ ሙሉነህ እንዳሉት፣ አካባቢን ለግጭቶች ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል በአርብቶ አደሮች መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ድርጅቱ ይህንን ለማስቀረት ከፍተኛ ሥራዎች አከናውኗል፡፡ ከመንግሥታቱ ጋር ቀጥተኛ ትብብር በማድረግ፡፡ ኢጋድ ሽብርተኝነትንና ሌሎች የደኅንነት ጠንቅ የሆኑትን በጋራ ለመዋጋት የጋራ መድረክ በመፍጠር ላይ መሆናቸውንም ይፋ አድርገዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከጋዜጠኞች አንዳንድ ጥያቄዎች ተቀብለው ምላሽ የሰጡት የሴዋርን ኢጋድ ዳይሬክተር ዶ/ር ማርቲን ከማኒ በበኩላቸው፣ በአንድ አካባቢ ግጭት እንዳይከሰት ማስጠንቀቅና መጠቆም አንድ ዕርምጃ ሆኖ ለችግሩ ምላሽ መስጠት ደግሞ፣ የመንግሥትና የሲቪክ ማኅበረሰቡ ሚና መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የድርጅቱ ጥረት ውጤት የሚኖረውም፣ የግጭቶች መነሻ በአብዛኛው የውኃና የግጦሽ ሀብት ፉክክር በመሆኑ በአብዛኛው ለአርብቶ አደሩ አዋጪ ፖሊሲ በመቅረፅ መፍታት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ በበላይነት የሚመሩት ይኸው ድርጅት በአካባቢው ሲከሰቱ የነበሩና ለበርካቶች ሞትና እልቂት ምክንያት የነበሩትን ግጭቶች በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ይናገራሉ፡፡ ሴዋርን ይህንን የቅድመ ማስጠንቀቅያ ሥርዓት በመንደፍ በአፍሪካ ቀዳሚ ሲሆን፣ በአፍሪካ ኅብረት ደረጃ ተቀባይነት አግኝቶ በአኅጉር ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በእያንዳንዱ አባል አገር ከፍተኛ አመራር የሚመራ ከድርጅቱ ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለው ቡድን መቋቋሙንና ቡድኑም ከአካባቢ ማኅበረሰቦችና አስተዳደሮች ጋር በትብብር የሚሠራ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በድርጅቱ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ለሚቀርቡ ጥቆማዎች ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እንዲቻል ፈንድ እያሰባሰበ የሚገኘው ሴዋርን፣ በዚሁ አማካይነት ወደ 21 አካባቢ የሚጠጉ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረግ ችሏል፡፡
እነዚህን የሰላም ሒደቶችና ግንባታዎች ለማካሄድ የተነደፉ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ወደ 700,000 ዶላር ወጪ የተደረገባቸው መሆኑን ኦስትሪያ፣ ስዊድን፣ ቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ ጣልያንና እንግሊዝ ለፕሮጀክቶቹ ድጋፍ ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡



