Wednesday, Jun 19th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

‹‹በጡረታ ፈንድ ውስጥ የእኔ የሚባል ገንዘብ የለም››

E-mail Print PDF
User Rating: / 1
PoorBest 

 

ሰሞኑን ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን የግል ድርጅቶች የጡረታ ፈንድ ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ከተቃዋሚ ፓርቲ ብቸኛው የፓርላማ አባል ከሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ጋር ባለፈው ሳምንት እትማችን ቆይታ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡

አቶ ግርማ በዚያ ቃለ ምልልሳቸው የአዋጁ መውጣት ለግል ድርጅት ሠራተኞች ዋስትና የሚሰጥ ቢሆንም፣ ከአሥር ዓመት በታች ያገለገሉ ሠራተኞች ያዋጡት የጡረታ አበል እንዳይከፈል መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት ይህንን ማድረጉም ሠራተኞች ያጠራቀሙትን ሀብት ከመውረስ የማይተናነስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህንን ቃለ ምልልስ የተመለከተው የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በበኩሉ የምክር ቤቱ አባል አዋጁን አስመልክተው የተናገሩት ስህተት መሆኑን ገልጿል፡፡ ኃይሌ ሙሉ በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ከማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጋሻው ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን ለተወካዮች ምክር ቤት የቀበረው የግል ድርጅቶች ጡረታ ፈንድ ችግር እንዳለበት እየተገለጸ ነው? ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ይህንን አስተያየት እንዴት ያየዋል?

አቶ ተስፋዬ፡- ሁለት የተደባለቁ ነገሮች አሉ፡፡ የመንግሥት ማኅበራዊ ዋስትናን የግል ድርጅት ማኅበራዊ ዋስትናን የማደባለቅ ነገር አለ፡፡ በተወሰነ ደረጃ የአሠራር ልዩነት አላቸው፡፡ የመንግሥቱ ላይ ያለውን ነገር ወደ ግሉ በመውሰድ እንደዚህ ሊሆን ይችላል ብሎ ያልበሰለ አስተያየት የመስጠት ሁኔታ ታይቷል፡፡ ለምሳሌ አዋጁ በአጠቃላይ የመውረስ መንፈስ ያለበት ነው የሚል አንድ ነጥብ ተነስቷል፡፡ ከአሥር ዓመት በታች ሲሠሩ ቆይተው መሥሪያ ቤት የሚቀያይሩ ሠራተኞች ካሉ ወይም ከአሥር እስከ ሃያ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሠሩ ቆይተው መሥሪያ ቤት የሚለቁ ሠራተኞች የመዋጮ ተመላሽ የሚደረግላቸው ሠራተኞች ከተቻለ ያዋጡትን ካልተቻለ ደግሞ ከነወለዱ ሊመለስላቸው ይገባል የሚል ነገር ተነስቷል፡፡ ይህ ጥያቄ ከመደበኛ ባለመብቶችም ብዙ ጊዜ ይነሳል፡፡ ይኼንን ለመመለስ እንግዲህ የማኅበራዊ ዋስትናን መርህ ማወቅ ወሳኝ ነው፡፡ የማኅበራዊ ዋስትና የተለያዩ አሠራሮች አሉት፡፡ በእኛ አገር የምንከተለው አሠራር የማኅበራዊ መድኅን (Social insurance) የምንለው ነው፡፡ ማኅበራዊ መድህን ደግሞ የሚመራባቸው ዓለም አቀፍ መርሆዎች አሉ፡፡ ከነዚህ መርሆዎች አንዱ የመረዳዳት (Solidarity) መርህ የምንለው ነው፡፡ ስለሆነም ከአሥር ዓመት በታች ያገለገሉ ሠራተኞች ለምንድን ነው የጡረታ አበል የማይመለስላቸው? ብለን ስንጠይቅ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው መርህ እነዚህ ሰዎች አንድ መሥርያ ቤት ሲሰሩ ቆይተው ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት ሲቀይሩ በመርህ ደረጃ እነዚህ ሰዎች የተሻለ ነገር አግኝተው ነው የሄዱት ተብሎ ይታሰባል፡፡ በፊት ከነበሩበት የተሻለ ዕድል አግኝተው ነው የሄዱት፡፡ ስለሆነም ከአንድ እስከ አሥር ዓመት የጡረታ አበል ሲያዋጡ የኖሩ ሠራተኞች ግል ድርጅት ሊሆን ይችላል ወይም በሌላ መሥሪያ ቤት ሊሆን ይችላል ሲሰሩ ቆይተው ሲመጡ ቀደም ሲል የሰጡት አገልግሎት ይያዝላቸዋል፡፡ ነገር ግን ገንዘቡ ቀጥታ ወደ ጡረታ ፈንድ የሚገባበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- የጡረታ ፈንድ ምንጮች ምንድን ናቸው?


አቶ ተስፋዬ፡- የጡረታ ፈንድ ምንጮች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው የጡረታ መዋጮ፣ ሁለተኛው ደግሞ የኢንቨስትመንት ሥራ ነው፡፡ የጡረታ መዋጮዎች በየወሩ ቢኖርም በየወሩ ደግሞ የጡረታ ክፍያ አለ፡፡ የአበል ክፍያ አለ፡፡ ከዚህ አንፃር በየወሩ ከሚከፈለው ገንዘብ የተረፈው የጡረታ መዋጮ ወደ ጡረታ ፈንድ ይሄዳል፡፡ በጡረታ ፈንድ ውስጥ ያለው ገንዘብ ነው እንግዲህ ተሰልቶ አዋጭ በሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ኢንቨስት የሚደረገው፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ አሠራር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያለ አይደለም፡፡ በአንዳንድ አገሮች እንዲያውም የጡረታ ተመላሽ የሚባል ነገር የለም፡፡ ምናልባት የጡረታ አበል ከሚመልሱ በጣም ጥቂት አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡ ምክንያቱም በጡረታ ፈንድ ውስጥ የእኔ የሚባል ገንዘብ የለም፡፡ ወደ ቋቱ ሲገባ የግለሰቡ ሳይሆን የሁሉም የዐቅዱ አባላት ሀብት ነው፡፡ የባለመብቶች ሁሉ ገንዘብ እንጂ የእኔ የሚባል ነገር የለም፡፡ ከዚህ አንፃር ከአሥር ዓመት በታች አገልግለው መሥሪያ ቤት ሲቀይሩ ገንዘባቸው ሳይመለስላችው በዚያው ወደ ጡረታ ፈንድ የሚገባበት ዋነኛ ምክንያት የመረዳዳት መርህ (Solidarity principle) ስለምንከተል ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የሆነ ሰፈር እድር ቢገባ እዚያ ሰፈር የሚኖር ከሆነና እክል ከደረሰበት ከእድሩ ፈንድ ይጠቀማል፡፡ ነገር ግን ቤት ገዝቶ ወይም ቤት ሰርቶ ሰፈር ቢቀይር እክል እስካልደረሰበት ድረስ ሳዋጣ ስለኖርኩ ብሬን መልሱልኝ ብሎ አይጠይቅም፡፡ እንዲያውም እክል ስላልደረሰበት ደስ ብሎት ነው የሚሔደው፡፡ ሐሳቡ (Assumption) እዚያ ያለው የቀረው ሰው ይጠቀምበት የሚል ነው፡፡ መረዳዳት (Solidarity) የምንለው ይህንን ነው፡፡ ይህ መርህ ነው በጡረታ ፈንድ መርህ ውስጥ በትልቁ የምናየው፡፡ ከአሥር እስከ ሃያ ዓመት አገልግለውም የራሳቸው መዋጮ የሚመለስላቸውን ባለመብቶች በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ቅድም እንደገለጽኩት የጡረታ አበል የሚመልሱ አገሮች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉ አጠቃላይ ሂደት ውስጥ ግን ሠራተኞች የትም ሲሠሩ ኖረው ተመልሰው ወደ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም በግል ድርጅት ከተቀጠሩ አገልግሎታቸው ይያዝላቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ለማኅበራዊ ዋስትና የሚቀረው ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ ይሆናል?

አቶ ተስፋዬ፡- በመሠረቱ በአንድ አገር ውስጥ ከመንግሥት ውጪ የሆነ ገንዘብ ሊኖር አይችልም፡፡ ነገር ግን ቅድም እንደገለጽኩት ነፃ የሆነ የጡረታ ፈንድ አለ፡፡ እነዚህ ሰዎች ገንዘባቸው ሳይመለስላቸው ሲቀር ገንዘቡ ወደ ፈንዱ ነው ገቢ የሚሆነው፡፡ ከመንግሥት ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ አለው፡፡ ገንዘቡን መንግሥት ያጠፋዋል የሚል ሐሳብ አለ፡፡ ይህ በእውነተኛ ሐሳብ ላይ ያልተመሰረተ መሆኑ መታወቅ መቻል አለበት፡፡ የጡረታ ፈንድ አለ፡፡ የጡረታ ፈንድ የሚተዳደርባቸው አግባቦች አሉ፡፡ በነገራችን ላይ የጡረታ ፈንድ በመንግሥት አይደጎምም፡፡ ራሱን የቻለ ፈንድ ነው፡፡ የፈንዱ ምክር ቤትም ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የጡረታ መዋጮና ኢንቨስትመንት ናቸው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ ፈንዱ የግምጃ ቤት ሰነድ ከመግዛት ውጪ በምንም ዓይነት ኢንቨስትመንት እንደማይሰማራ ነው የሚነገረው፡፡

አቶ ተስፋዬ፡- የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተጠንተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ እንግዲህ የጡረታ ፈንድ ኢንቨስትመንት የሚመራባቸው ራሳቸውን የቻሉ መርሆዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ጥቅምንም ችግርንም በጋራ መጋራት (Risk pulling and benefit sharing) የምንለው አንዱ መርህ ነው፡፡ ለምሳሌ ፈንዱ በግሽበት ቢመታ እያንዳንዱ ሰው ነው የሚካፈለው እንጂ ግለሰቦች ብቻ አይጎዱም፡፡ ሰውዬው በየወሩ የሚያገኘውን ጡረታ አያጣም፡፡ እንደዚሁ ሁሉ በኢንቨስትመንትም የምንከተላቸው መርሆዎች አሉ፡፡ አንደኛው ኪሳራን በማይቀበሉ አስተማማኝ የኢንቨስትመንት መስኮች በምንላቸው ላይ ነው ኢንቨስት የሚደረገው፡፡ ምክንያቱም ጡረታ ፈንድ ኢንቨስት ሲደረግ አደጋው ዜሮ መሆን አለበት፡፡ የሕዝብ ሀብት ስለሆነ አስተማማኝ ባልሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች መሳተፍ የሚችልበት ሁኔታ የለም፡፡ ነገር ግን በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ አስተማማኝ ሊባሉ የሚችሉ ወይም የመክሰር አደጋው ወደ ዜሮ የተጠጉ የኢንቨስትመንት መስኮች የትኞቹ ናቸው ተብለው የተጠኑ የኢንቨስትመንት መስኮች አሉ፡፡ ለምሳሌ በቦንድ፣ በመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ፣ በአክሲዮንና በጊዜ ገደብ ተቀማጭ ላይ ባለፉት ዓመታት ኢንቨስት አድርገናል፡፡ ከዚህም ውጪ አንድ ሰባት የሚሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች ተጠንተዋል፡፡ ያዋጭነት ጥናት እየታየ እንደአስፈላጊነቱ በሥራ ላይ የሚውል ይሆናል፡፡ በዋነኛነት ግን መታወቅ ያለበት ነገር ፈንዱ ኢንቨስት የሚያደረገው አስተማማኝ በሆነና ኪሳራ ሊቀበሉ በማይችሉ የኢንቨስትመንት መስኮች መሆኑን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአሥር ዓመት በታች ያገለገለ የግል ድርጅት ሠራተኛ ከሥራ ሲለቅ ራሱና ድርጅቱ ያጠራቀመለትን ገንዘብ እንዳይወስድ መከልከሉ ሥራ ፈጠራን እንዳያበረታታ ያደርጋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡

አቶ ተስፋዬ፡- ሥራ ፈጣሪነትን አያበረታታም የሚለውን እኔ በግልባጩ ነው የማየው፡፡ የማኅበራዊ ዋስትና ማግኘት ሥራ ፈጣሪነትን ያበረታታል፡፡ ይኼ ደግሞ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን የሌሎች አገሮች ተሞክሮዎችንም መውሰድ ይቻላል፡፡ በተለምዶ የሠራተኞች ዋስትና ማግኘቱ ምርታማነትን ይጨምራል፡፡ በነገራችን ላይ የዓለም ሥራ ድርጅት (ILO) በኮንቬንሽኑ ካስቀመጣቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ የዜጎች ማኅበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት ነው፡፡ የማኅበራዊ ዋስትና መነሻው ራሱ ከኢንዱስትሪያል አብዮት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ሠራተኞች በውጤታማነታቸው ዘመን ሲሰሩ ቆይተው ውጤታማ በማይሆኑበት ዘመን የማኅበራዊ ዋስትናቸው ካልተረጋገጠ ማኅበራዊ ቀውስ ከመፈጠሩ ጋር ተያይዞ የተነሳ ሐሳብ ነው፡፡ ስለዚህ የማኅበራዊ ዋስትናን ማግኘት ይበልጥ ያበረታታል፡፡ ምክንያቱም ሠራተኛው ዋስትና አለው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሥራ የሚለቅ ሰው ለሥራ ፈጠራ የሚረዳው መነሻ ካፒታል ከሌለው ሥራ ፈጣሪ ሊሆን አይችልም የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ፡፡

አቶ ተስፋዬ፡- በግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ውስጥ ከታዩ ነገሮች ውስጥ አንዱ ይኼ ነው፡፡ የራሳቸውን ሥራ የሚፈጥሩ (Self employed) የሚሆኑ ዜጎችም የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች የማኅበራዊ ኤጀንሲ አለ፣ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ አለ፡፡ በግል ድርጅቶች ማኅበራዊ ዋስትና ውስጥ በግላቸው የሚተዳደሩ (Self employed) የምንላቸው ሰዎች በፍላጎታቸው የዋስትናው ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በግላቸውም ቢሰሩ የዋስትናው አባል ከመሆን የሚከለክላቸው የለም፡፡ ስለዚህ ከመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም ከግል ድርጅት እስከወጡበት ድረስ ያዋጡት ገንዘብ በራሳቸውም ቢዝነስ ቢጀምሩ ሽፋኑ ይቀጥልላቸዋል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ለሠራተኛው ያዋጣውን መዋጮ ለምንድነው የጡረታ ፈንድ የሚወስደው?

አቶ ተስፋዬ፡- ለፈንዱ የሚቀረው በመረዳዳት (Solidarity) መርህ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ የሚቀረው እዚያ ለቀሩትና የማኅበራዊ ዋስትና ዕቅድ አባል የሆኑ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ነው፡፡ ብዙ ሠራተኞች በሥራ ላይ በነበርንበት ዘመን ያዋጣነው ገንዘብ ሽፋኑን ባገኘንበት ጊዜ ተመልሶ ይሰጠናል የሚል አስተሳሰብ አላቸው፡፡ ይኼ በጣም የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው፡፡ አንድ ሰው የመንግሥት ወይም የግል ድርጅት ሠራተኛ በነበረበት ወቅት ያዋጣው መዋጮ ብቻ ቢሰላ ለሰውዬው ሊከፍል የሚችለው ከሰባት እስከ አስር ዓመት ያለውን የጡረታ ሽፋን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው በዕድሜ መግፋት ብቻ በ60 ዓመቱ ጡረታ ቢወጣ 90 ዓመት ወይም 120 ዓመት ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ በዚህ ስሌት ያዋጣው ገንዘብ ምን ያህል ይከፈለዋል ብለን ብናስብ በጣም ጥቂት ነው የሚሆነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጡረታ ከወጡ በኋላ ሀምሳ ዓመትም ስልሳ ዓመትም ይኖራሉ፡፡ በመረዳዳት ጽንሰ ሐሳብ ፈንዱን ካላሳደግከው ረጅም ዓመት የሚኖሩ እነኚህ ሰዎች ቀሪውን ሀምሳ ዓመት ምንድነው የሚበሉት? ከየት ነው የሚከፈለው?   

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያውያን የዕድሜ ጣሪያ በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ከስልሳ ዓመት በላይ ኖሮ ጡረታ የመቀበል እድል ያለው ሰው ቁጥር በጣም ጥቂት እንደሆነ ይነገራል፡፡

አቶ ተስፋዬ፡- የዕድሜ ጣሪያን በተመለከተ አንደኛው ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ጉዳይ የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን የሚሰጠው በዕድሜ ጣሪያ ብቻ አይደለም፡፡ የማኅበራዊ ዋስትና አነስተኛ መመዘኛዎች ዘጠኝ ናቸው፡፡ እነኚህ መመዘኛዎች በዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) ተቀባይነት አግኝተው ሥራ ላይ የዋሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በእኛ ተቋም ብቻ ወደ አራት የሽፋን ዓይነቶች ይሰጣሉ፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ደግሞ ሁለቱ ብቻ ይሰጣሉ፡፡ አሁን ደግሞ ማኅበራዊ ዋስትና በጤና ጥበቃ ይሰጣል፡፡ ስለዚህ  በአጠቃላይ ጡረታ ሊገኝባቸው የሚችሉ ወደ ሰባት ዓይነት መስኮች አሉ፡፡ የእድሜ መግፋት ከእነዚህ መመዘኛዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች አሉ፡፡ የሥራ ላይ ጉዳት፣ የህመም፣ የተተኪዎች አበል የምንላቸው አሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ሲያረጅ ብቻ አይደልም የማኅበራዊ ዋስትና የሚያገኘው፡፡ ለምሳሌ አንድ የፋብሪካ ሠራተኛ ያንን ሥራ ለመሥራት የሚያስችለው አካሉ ቢጎድል የዕድሜ ልክ የማኅበራዊ ዋስትና ሊያገኝ ይችላል፡፡ ወይም ሊድን የማይችል በሽታ መሆኑ በሦስት የሕክምና ባለሙያዎች ከተረጋገጠ የዕድሜ ልክ የማኅበራዊ ዋስትና ሊያገኝ ይችላል፡፡ ሰውዬው በሞት ቢለይ የተተኪዎች አበል የምንለው አለ፡፡ በሰውዬው ላይ ጥገኛ ሆነው የሚተዳደሩ ልጆቹ፣ ባለቤቱ፣ እናት ወይም አባት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በአጠቃላይ እነዚህ መስኮች ናቸው የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን የሚሰጣቸው፡፡ የዕድሜ ብቻ አይደለም፡፡ ያም ሆኖ በቅርቡ የወጡ መረጃዎች የዕድሜ ጣሪያ (Life expectancy) ኢትዮጵያ ውስጥ እየጨመረ እንደመጣ ነው የሚያመላክቱት፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ የጡረታ ገንዘብ ለመንግሥት ወጪ ይውላል፤ ይባክናል፡፡ የሚለውንስ እንዴት ያዩታል?

አቶ ተስፋዬ፡- የእኛ አገር የጡረታ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት በኩል ጠፍቷል፡፡ የሚለው ነገር ምንም ዓይነት ማስረጃ የሌለውና ትክክለኛ ያልሆነ አስተያየት ነው፡፡ ይኼ ምናልባት ማስረጃ ቢጠየቅበት በጣም አስቸጋሪ የሚሆን ነገር ነው፡፡ በሌላው አገር ያሉ ተቋማት ኃላፊነት ባለው መንግሥት የሚመሩ መሆኑን እዚህ አገር ላይ ይኼ ግን እንደሌለ የተጠቀሰበት ሁኔታ አለ፡፡ በአጠቃላይ ይኼ አስተያየት ተቋሙ ካለበት ሁኔታ ጋር በፍጹም የማይገናኝ ነገር ነው፡፡ አዲሱ የግል ድርጅቶች ጡረታ ፈንድ ኤጀንሲ ተቋም ገና እየተቋቋመ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ከወዲሁ ሕዝቡን ብዥታ ውስጥ ሊከት የሚችል የተሳሳተ ነገር ነው የተነገረው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ረቂቁ ታስቦበት የተዘጋጀ አይደለም ለሚለው አስተያየት የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ ተስፋዬ፡- ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ካየን የማኅበራዊ ዋስትና ጉዳይ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነው፡፡ የድህነት ቅነሳ ዋነኛ ስትራቴጂዎች ከሚባሉት አንዱ የማኅበራዊ ዋስትናን ማስፋፋት ነው፡፡ ሁለተኛ የዓለም ሥራ ድርጅት አባል አገር ነን፡፡ የዓለም አቀፍ የማኅበራዊ ዋስትና አባል አገርም ነን፡፡ ስለዚህ ይህንን ነገር በጣም ማጠናከርና ማስፋፋት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ እንደውም በጣም ዘግይቷል ተብሎ ሊታይ የሚችል ነገር ነው፡፡ ማኅበራዊ ዋስትና ማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 91 ላይ አቅም በፈጠረ መንገድ ዜጎች የማኅበራዊ ዋስትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደነግጋል፡፡ በእኛ አገር የማኅበራዊ ዋስትና ወደኋላ የቀረ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ በአገራችን የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅት ሠራተኞች ፖሊስና መከላከያ ናቸው፡፡ እነዚህን ደግሞ ከአጠቃላይ ሕዝቦች ጋር ካየነው በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የሄደውን የግሉን ዘርፍ ሠራተኞች ሽፋን እንዲያገኙ ማደረግ በአሁኑ ወቅት አግባብ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የማኅበራዊ ዋስትና ረቂቅ አዋጅ በአሁኑ ወቅት ተዘጋጅቶ መቅረቡ ከትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ጋር የሚያገናኘው ነገር አለ?

አቶ ተስፋዬ፡- ሊሆን ይችላል፡፡ በመርህ ደረጃ ሊሆን አይችልም ብለን መውሰድ አንችልም፡፡ ነገር ግን አንደኛው ነገር እንደማሳያ መውሰድ የምንችለው የግል ሴክተር ማኅበራዊ ዋስትና ባይኖርና መንግሥት በዚያ በኩል ባይወስደው የትስ ባንክ ቢሆን ሊያገኘው አይችልም ወይ? የሚለው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ውስጥ ከተካተቱ ዋነኛ የትኩረት ነጥቦች አንዱ የዜጎች የማኅበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት ማረጋገጥ ነው፡፡ ዋናው ነገር ይኼ ነው፡፡ ማኅበራዊ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ በአንድ አገር ውስጥ ማኅበራዊ ቀውስን ለማስወገድ ከምንጠቀምባቸው የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂዎች አንዱና መተኪያ የሌለው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ገንዘቡ የትም ቢሆን መንግሥት አያጣውም፡፡ ሁለተኛው መንግሥት ገንዘብ ፈልጎ ከሆነ ተቋሙን እያቋቋመ ያለው መንግሥት ከካዝናው ገንዘብ አውጥቶ ነው፡፡ መንግሥት ከዚያ ገንዘብ ሊያገኝ ይቅርና ከካዝናው ገንዘብ አውጥቶ ሠራተኛ እየቀጠረ ነው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ትልቁ ትኩረት የማኅበራዊ ዋስትናን በማረጋገጥ ማኅበራዊ ቀውስን የመቀነስ ድርሻ መውሰድ ነው፡፡ ሌላው እንደማሳያ ልንወስደው የምንችለው ነገር የዚህ እቅድ አባል የሚሆኑ ድርጅቶች ወይም ሠራተኞች በፍላጎታቸው ነው የሚሆኑት፡፡ ስለዚህ ከትራንስፎርሜሽን እቅዱ ጋር ሊገናኝ የሚችልበት ምክንያት የለም፡፡ ሁላችንም እንደምንገነዘበው በአዋጁ ላይ በግልጽ የተቀመጠው ከሰኔ 2002 በጀት ዓመት በፊት የፕሮቪደንት ፈንድ አቋቁመው ሠራተኞቻቸውን የዚያ ዋስትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደረጉ ተቋማት በሙሉ በፈቃደኝነታቸው ነው የጡረታ ፈንድ አባል የሚሆኑት፡፡ ከሰኔ 2002 ዓ.ም. በፊት ተቋቁመው ነገር ግን ፕሮቪደንት ፈንድ ያላቋቋሙ ካሉ በግዴታ የጡረታ ፈንድ ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡ ዜጎች የማኅበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት ስላላቸው መንግሥት ይህንን የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰኔ 2002 በፊት የተቋቋሙ ድርጅቶች ከሰኔ 2002 በኋላ ፕሮቪደንት ፈንድ አቋቁመው ከሆነ በፕሮቪደንት ፈንዱ መቀጠል ይችላሉ?

አቶ ተስፋዬ፡- ድርጅቶቹ ከሰኔ 2002 በፊት ከነበሩ ፕሮቪደንት ፈንድ ማቋቋም ነበረባቸው፡፡ ሲጀምሩ ጀምረው የዜጎችን ዋስትና የማረጋገጥ ግዴታ በሌበር ሕግም አለ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ከሰኔ 2002 በኋላ የፕሮቪደንት ፈንድ ቢያቋቁሙም ወደ ጡረታ ፈንድ የመግባት ግዴታ አለባቸው፡፡ የጡረታ ዕቅድና የፕሮቪደንት ፈንድ ልዩነቱ ግልጽ ነው፡፡ ፕሮቪደንት ፈንድ በአሠሪና ሠራተኛ ስምምነት መሠረት ለሠራተኛው የሚቀመጥ ገንዘብ ነው፡፡ ይኼ በዓለም ላይ በአሁኑ ወቅት አሜሪካን ጨምሮ በጋና እንዲሁም በሴራሊዮን እየተቀየረ ነው፡፡ የፕሮቪደንት ፈንድን እያፈረሱ ወደ ጡረታ ፈንድ የገቡበት ሁኔታ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- አገሮች የፕሮቪደንት ፈንድን ወደ ጡረታ ፈንድ የሚቀይሩበት ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ ተስፋዬ፡- ዋነኛው ምክንያት አንደኛ ፕሮቪደንት ፈንድ ለግሽበት የተጋለጠ ነው፡፡ ሁለተኛው ነገር ዜጎች በፈቀዳቸው ጊዜ ገንዘባቸውን አውጥተው አላስፈላጊ ለሆነ ወጪ ሊያባክኑት ይችላሉ፡፡ በፕሮቪደንት ፈንድ ቤት የሰሩና መኪና የገዙ አሉ ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ይኼ በተጨባጭ በኢትዮጵያ ሊሠራ ይችላል፣ አይችልም የሚለውን ፍርድ ልትሰጡ ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን በተጨባጭ ያለው እውነታ ፕሮቪደንት ፈንድ የሚያጠራቅሙ ሰዎች በፈለጉበት ጊዜ ለፈለጉት ጉዳይ አውጥተው በኋላ ለማኅበራዊ ቀውስ የሚዳረጉበት ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡  በእኛ አገር የቁጠባ ባህላችን ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መንግሥት ማኅበራዊ ቀውሱን የመከላከል ኃላፊነት አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር ዘላቂ የሆነ ዋስትና የሚያገኙበትን አቅጣጫ ነው መንግሥት እየተከተለ ያለው፡፡ ስለዚህ በዓለም ደረጃም ካየነው ፕሮቪደንት ፈንድ እየቀረ ወደ ጡረታ ዕቅድ የሚገባበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ ከተያዙ ነገሮች ውስጥ አንዱ የማኅበራዊ ዋስትና የማስፋትና የማጠናከር ስትራቴጂ ነው፡፡ በሥራ ላይ የቆየው የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የመንግሥት ሠራተኞችን ስለያዘ ይህንን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ ነው የሚታመንበት፡፡ ለማጠናከር የተሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ እስካሁን ድረስ ከሠራተኞች ደመወዝ አራት በመቶ፣ ከአሠሪዎች ደግሞ ስድስት በመቶ በአጠቃላይ አሥር በመቶ ነው የጡረታ መዋጮ ሲሰበስብ የቆየው፡፡ ነገር ግን አሁን ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር ይህንን ይዞ መቀጠል የጡረተኞችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ ካሉ የጡረታ መዋጮዎች መካከል የእኛ መዋጮ በጣም ትንሽ ከሚባሉት የሚመደብ ነው፡፡ ለዚህ ነው የጡረታ ክፍያም የሚያንስበት ምክንያት፡፡ የእኛ ማኅበራዊ ዋስትና የሚከተለው የፈንድ ማኔጅመንት ሥርዓት Pay as you go (ትውልድ የትውልድን እዳ እየከፈለ የሚሄድበት) የሚል ነው፡፡ አሁን ያለው ሠራተኛ አሁን ላለው ጡረተኛ ይከፍላል፡፡ አሁን ያለው ሠራተኛ ጡረታ ሲወጣ ደግሞ የዚያን ጊዜ የሚኖር ሠራተኛ ይከፍላል፡፡ ይኼ በዋነኛነት የማኅበራዊ ዋስትና የፋይናንስ ማኔጅመንት መርህ ቢሆንም፣ ከፈንዱ ያለመዳበር ጋር በተያያዘ ነው ሊከሰት የሚችለው፡፡ የጡረታ ክፍያ አነሰ ይባላል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን በጣም ለጋስ ከሚባሉ የጡረታ የማስያ ስሌቶች አንዱ የእኛ አገር ነው፡፡ ይኼንን ደረጃ በደረጃ ለማጠናከር የሠራተኛውን ድርሻ ከአራት በመቶ ወደ ሰባት በመቶ የድርጀቱን ድርሻ ደግሞ ከስድስት በመቶ ወደ አስራ አንድ በመቶ በማሳደግ በአጠቃላይ በ2006 የጡረታ መዋጮውን በአሥራ ስምንት በመቶ በማሳደግ የጡረተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታቅዷል፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው አዋጅ ውስጥ የጡረታ አበል ጭማሪ ለጡረተኞች የሚደረገው በዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት እየተጠና ነው፡፡ እየተጠና አቅም በፈቀደ ሁኔታ በየአምስት ዓመቱ ለጡረተኞች ጭማሪ ይደረጋል፡፡ በአዋጅ የተቀመጠው በአምስት ዓመት አንዴ እንደሚጨመር ቢሆንም፣ መንግሥት በየሦስት ዓመቱ የጡረታ አበል ጭማሪ እያደረገ ነው፡፡ በ1999 ዓ.ም. ለጡረተኛ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ዘንድሮም ተደርጓል፡፡ ካለው ሁኔታ ጋር ነገሮችን ማስተካከል ስለሚገባ መንግሥት እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ እስካሁን ድረስ የሚታወቀው ትንሽ የጡረታ አበል 160 ነበር፤ ዘንድሮ ይህንን በ84 በመቶ በማሳደግ 294 ብር ደርሷል፡፡ አሁን በጡረታ ላይ ያሉ ዜጎች ተጠቃሚነትም በዚያው መጠን ይረጋገጣል ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አሁን የሚመጡት የግል ድርጅት ሠራተኞች በጣም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ አለ፡፡