Thursday, May 23rd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

በረራ ET 409 - የመጨረሻዎቹ ሁለት ደቂቃዎች

E-mail Print PDF
User Rating: / 48
PoorBest 

ፈልጎ የማዳን ጥረቱ ዛሬም ይቀጥላል
(በጋዜጣው ሪፖርተር)

የበረራ ቁጥር ET 409 ለአንድ ሰዓት ያህል በቤይሩት ራፊቅ ሃሪሪ አለም አቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ ከቆየ በኋላ፣ 90 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ አዲስ አበባ ለማቅናት ሰኞ ከንጋቱ 9፡35 ላይ ተነሳ፡፡

በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ይበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 አውሮፕላን ግን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከራዳር ዕይታ መጥፋቱን የቤይሩት አውሮፕላን ማረፊያ በረራ ተቆጣጣሪዎች ያሳውቃሉ፡፡

አስቸጋሪ ነበር በተባለው የአየር ሁኔታ ከማረፊያው ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ የበረረው የዚህ አውሮፕላን አሰቃቂ ዕጣ የታወቀው የአይን ምስክሮች ከአካባቢው ሰማይ ከፍተኛ የእሳት ብልጭታ ወደ ሜዲትራኒያን ባህል እየተምዘገዘገ ሲወርድ ማየታቸውን ካሳወቁ በኋላ ነበር፡፡

አንዳንድ ዘገባዎች ኢትዮጵያውያኑ አብራሪዎች የመጀመሪያዎቹን ሁለት ደቂቃዎች ከቤይሩት ማረፊያ ከሚገኘው የአየር መቆጣጠሪያ በተደረገላቸው እገዛ ያበሩ እንደነበር ይገልፃሉ፡፡

የቤይሩት የአየር መንገድ ባለሥልጣናት፣ ዝናብና መብረቅ በቀላቀለ ተመሳሳይ የአየር ሁኔታ ወቅት የሚደረግ የተለመደ አሰራር መሆኑንም ለዜና አውታሮች አሳውቀዋል፡፡

አደጋው ከተከሰተ ጀምሮ እየተደረገ ባለ የፍለጋ ሥራ እስከ ትናንት ማታ 25 አስከሬን የተገኘ ቢሆንም፣ የአካባቢው የአየር ሁኔታ የፍለጋ ሥራውን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ከተገኙት ውስጥ 6 ኢትዮጵያውያንና 8 ሊባኖሳውያን መሆናቸውም ታውቋል፡፡

ከፍለጋ ሥራው አዳጋችነት የተነሳ የሊባኖስ መንግሥት የአሜሪካ የባህር ኃይል በፍለጋው ሥራ እገዛ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የሚመራ የኢትዮጵያ አጣሪ ቡድንን  ጨምሮ አንድ የእንግሊዝ የአደጋ ጊዜ ፍለጋ ሥራ ላይ የተሰማራ ብሌክ ኢመርጀንሲ ሰርቪስስ (Blake Emergency Services) የተባለ ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታትም እንደሚገኙበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ግርማ ዋቄ ሰኞ እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቀዋል፡፡

ካፒቴን ደስታ ዘርኡ የአየር መንገዱ በረራ ኦፕሬሽንስ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ማዘዣ ዋና ዳይሬክተር ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ አየር መንገዱ ከእንግሊዙ ድርጅት ጋር ከተወሰነ ጊዜ በፊት ስምምነት መግባቱን እና በአደጋ ጊዜ ምላሽ እና በተለያዩ የፎረንዚክስ እና የዲኤንኤ ምርመራዎች ላይ የካበተ ልምድ እንዳለው አሳውቀዋል፡፡

ከዚሁ ድርጅት እና ከኢትዮጵያ ሰኞ እለት ከበረሩት ቡድኖች በተጨማሪ፣ በትናንትናው እለት በርካታ አባላት ያሉት ቡድን ከብሌክ ኢመርጀንሲ ሰርቪስስ እና ከኢትዮጵያ፣ የተለያዩ የሕክምና እና የምርመራ መሣሪያዎችን ይዞ ወደ ቤይሩት አቅንቷዋል፡፡

የሊባኖስ የአየር ጥቆማ መስሪያ ቤትና የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣኑ፣ ከፍተኛ ማዕበል፣ እስከ 18 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስ ቅዝቃዜ እንዲሁም ድቅድቅ ጭጋግ ቀጣይ የፍለጋ ሥራውን አስቸጋሪ ያደርጋል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡

እስካሁን በፍለጋው የተገኙ አስከሬኖችን ማንነት ለማጣራት የዲ.ኤን.ኤ (DNA) ምርመራ እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል፡፡ 

51 ሊባኖሳውያን፣ 23 ኢትዮጵያውያን፣ አንድ እንግሊዛዊ፣ አንዲት ፈረንሳዊት፣ አንድ ሶሪያዊ፣ አንድ ቱርካዊ እና አንድ ኢራቃዊ ተሳፋሪዎች፤ እንዲሁም ከሁለቱ አብራሪዎች ጋር አምስት የበረራ አስተናጋጆችን እና አንድ ኢትዮጵያዊ የበረራ ደህንነት አባልን ይዞ መጓዝ የጀመረው ቦይንግ አውሮፕላን ላይ ለደረሰው አደጋ መንስኤው ገና በውል አልታወቀም ብለዋል አቶ ግርማ ዋቄ፡፡

አደጋው መድረሱን ተከትሎ ይሰጥ የነበረው ግምት፣ ምናልባት አውሮፕላኑ በመብረቅ ተመትቶ ይሆናል የሚል ቢሆንም፣ አቶ ግርማን ጨምሮ ስለአቪዬሽን ዕውቀት ያላቸው ግን ማጣራቱ ሳይጠናቀቅ በፊት እርግጠኛ መሆን አይቻልም ይላሉ፡፡

አንዳንድ ከአየር በረራ ሥራ ጋር ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን አስተያየት ሰጪዎች የአይን ምስክሮቹ እንዳሉት "አውሮፕላኑ በአየር ላይ ፍንዳታ ደርሶበት ከሆነ በመብረቅ የመመታቱ ነገር አጠራጣሪ ይሆናል" ብለዋል፡፡

አውሮፕላኑ በሜዲትራኒያን ከተከሰከሰ ከሰዓታት በኋላ ከባሕሩ ዳርቻ የአውሮፕላኑ ስብርባሪና በውስጡ የነበሩ የሕጻናት አሻንጉሊቶች፣ ሻንጣዎች እና የመድሃኒት ብልቃጦችን የመሳሰሉ ቁሳቁሶች ተገኝተዋል፡፡

በበረራ ቁጥር ET 409 ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩት ውስጥ የ3 ዓመትና የ4 ዓመት ሊባኖሳውያን ህፃናት ይገኙበት እንደነበር ይፋ የተደረገ የተሣፋሪዎች ስም ዝርዝር ያሳያል፡፡

አደጋው ከመድረሱ በፊት ስለነበረው ሁኔታ የተለያዩ ምስክሮችና አስተያየቶች እየተሰጡ ሲሆን፣ አንዳንድ ዘገባዎች የሊባኖስን የጦር ኃይል ዋቢ በማድረግ አውሮፕላኑ አኮብኩቦ ከተነሳ በኋላ በእሳት መያያዙን ይጠቁማሉ፡፡

ሌሎች ደግሞ እስከ ጭራሹ የአይን ምስክሮቹ አየነው ያሉት ከፍተኛ የእሳት ብልጭታ ጭምር እንደሚያጠራጥራቸው ይናገራሉ፡፡

"በአውሮፕላን አደጋ ወቅት የአይን ምስክር ነን የሚሉ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ፍንዳታ ስለመስማታቸው ወይም ኃይለኛ ወላፈን ስለማየታቸው ይመሰክራሉ" ሲል በአሜሪካ የሚገኘው የበረራ ደህንነት ፋውንዴሽን ጥርጣሬውን ገልጿል፡፡

በተፃራራዊው፣ አንዳንድ የዜና አውታሮች፣ ከቤይሩት አውሮፕላን ማረፊያ የደህንነት ካሜራዎች የተገኘ ባሉት ፊልም አንድ አውሮፕላን በጨለማ ሲበርና ከፍተኛ የሆነ የብርሃን ብልጭታ ሲታይ በድረ ገፃቸው አቅርበዋል፡፡ የቦይንግ 737 አውሮፕላኑን መከስከስ ተከትሎ የሊባኖስ ባለስልጣናትም መግለጫዎችን እየሰጡ ይገኛል፡፡

የአገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር ለአሶሽየትድ ፕሬስ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያዊው አብራሪ ከመቆጣጠሪያ ማማው ይሰጠው የነበረውን የአቅጣጫ አመላካች መልዕክት በተፃረረ መልኩ ሌላ መስመር ይዞ መጓዙን ገልፀዋል፡፡

"ከመቆጣጠሪያ ማማው አቅጣጫውን እንዲያስተካክል መመሪያ ቢሰጠውም በጣም ፈጣንና ያልተለመደ አጠማዘዝ በማድረግ ከራዳር ዕይታ ጠፋ" ብለዋል ጋዚ አሪዲ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የሊባኖስ ባለስልጣናት አውሮፕላኑ የሽብር ጥቃት ሰለባ እንዳልነበረ ይገልፃሉ፡፡

"ሆን ተብሎ የተፈፀመ ወይም የሰዎች እጅ አለበት ብለን አናምንም" ሲሉ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሚቼል ሱሌይማን ተናግረዋል፡፡

አደጋው የደረሰበት ቦይንግ 737 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኪራይ ይጠቀምበት የነበረ ሲሆን አምራቹ ኩባንያ የራሱን መርማሪዎች የአደጋውን መንስኤ እንዲያጣሩ ወደ ሊባኖስ ልኳል፡፡

ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተሰነዘሩ ያሉትን ግምታዊ አስተያየቶች አስመልክቶ ካፒቴን ደስታ ለሪፖርተር እንደገለፁት "በአሁኑ ወቅት ግምታዊ አስተያየት ተገቢ አይደለም፡፡ ምርመራው ሳይጠናቀቅ አስተያየት መስጠት ከሙያዊ ስነምግባር ውጪ ነው፡፡"

አክለውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት ትኩረት የሚሰጠው የተሣፋሪዎችን ቤተሰቦች መንከባከብ፣ መረጃ በጊዜ እንዲያገኙ ማድረግና የሟቾችን አስከሬን በማፈላለግ የተረፉ ካሉም እነሱን ማዳን ላይ ነው ብለዋል፡፡

ሰኞ እለት ማታ ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት 10 የተሳፋሪ ቤተሰቦችን አየር መንገዱ ሙሉ ወጪ ሸፍኖ ወደ ቤይሩት እንደላካቸው ካፒቴን ደስታ ገልፀው፣ በትላንትናው ምሽት ደግሞ በአየር መንገዱ ወደ ቤይሩት መሄድ እንደሚፈልጉ ተጠይቀው ምላሽ የሰጡ በበረራው የነበሩ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ቤተሰቦች ሄደዋል፡፡

በተጨማሪም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥዩም መስፍን፣ የትራንስፖርት እና የመገናኛ ሚኒስቴሩ አቶ ዲሪባ ኩማ እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዳይሬክተር አቶ ወሰንየለህ ሁነኛው የሚመራ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ወደ ቤሩት አቅንቷል፡፡

የፍለጋ ሥራው ዛሬ ሙሉ ቀን እንደሚቀጥልም ካፒቴን ደስታ ለሪፖርተር አሳውቀዋል፡፡ ወደ ሕትመት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ የበረራው መረጃ ሳጥን (Black Box) እና ድምፅ መቅረጫው እንዳልተገኘም አክለው ገልፀዋል፡፡

ከቤይሩት ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 23 ኢትዮጵያውያን ተሣፋሪዎች በሙሉ ሴቶች ነበሩ፡፡