ካዛንቺስ የቆመው የታክሲ ወያላ "በአቋራጭ መገናኛ" እያለ ጉሮሮው እስኪሰነጠቅ ይጮኻል፡፡ አብዛኛው ሰው በአቋራጭ ወይም በአድዋ ድልድይ በኩል መሔድ አይፈልግም፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚቀርበው ከመገናኛ በፊት የሚወርዱ ተሳፋሪዎች ስላሉ ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ መገናኛ ውስጥ መግባት የማይፈልጉ ተሳፋሪዎች ናቸው፡፡
ምክንያታቸውም ወደ ሲኤምሲና ወደ ኮተቤ ለመቀጠል ስለማይመች ነው፡፡ ለታክሲው ግን በጣም አጭርና ከትራፊክ ነፃ የሆነ በረራ ነው፡፡
እኔ ግን በአቋራጭም ይሒድ በፈለገው መገናኛ የምትለዋን ቃልና ዋጋው አለመጨመሩን አረጋግጬ ነው የገባሁት፡፡ ከእኔ ጋር ሁለት ሰዎች አሉ፡፡ ሌሎች በርከት ያሉ ሰዎች በቁጣ ወያላው አቅጣጫውን እንዲቀይር በንግግራቸውና በዓይናቸው ይጐተጉቱታል፡፡ እሱ ግን የሚገላምጡትን ዓይኖች ንቆ ሰው እየጐተተ ያስገባል፡፡
ወዲያው አንዲት ሴት በቁጣ "ቆይ፣ቆይ እንደፈለጋቸው የሚጭኑትን ታክሲዎች ሕግ ፊት ነው የምንከሰው"" አለች፡፡ የእሷን ተከትሎ ብዙ የማይሰሙ ድምፆች አብረው አጉተመተሙ፡፡ ሾፌሩ ተቆጣ፣ "በቃ እንዲያውም እነዚህንም አውርዳቸውና ወደ ሌላ ቦታ እንሒድ፤" አለ፡፡ ወያላው አልተቀበለውም፡፡ "ለምንድንነው ሌላ ቦታ የምንሔደው? ተዋቸው ይጩኹ፣ የሚሰማቸው የለም፤" ተቃውሞውን አቀረበ፡፡ አነጋገሩ ደፋር ፖለቲከኛ አስመስሎታል፡፡
የወያላው ንግግር በሁለቱ ጆሮዎቼ መካከል ሲያልፍ ሁለት ትርጉም ይዞ መጣ፡፡ አንደኛው "የሚሰማቸው የለም" ሲል፣ ሴትዮዋ "የት ሔደን ነው የምንከሰው?" ላለችው መልስ መስጠቱ ነው፡፡ ሴቶች የትም ብትሔዱ የሚሰማችሁ የለም ያለ መሰለኝ፤ ለጥቆም እዚህ የተሰበሰቡት ተሳፋሪዎች ቢጮኹ ማንም የሚሰማቸው የለም፣ የሚሰማ ቢያገኙ እንኳን የትም አይደርሱም እንዳለ ገባኝ፡፡
ሙሉ ለሙሉ የመናገርና የመደመጥ መብት አለን ብለን አናስብም፤ በተሰጠችን ትንሽ የመናገር መብት እንኳን ተጠቅመን የምንናገራት ነገር አትሰማም ወይም የሚሰማን የለም፡፡ ዘኪዎስ የሚባል አንድ ቀረጥ ሰብሳቢ ኢየሱስ ክርስቶስ በመንገድ ያልፋል ሲባል ሰምቶ ሊገናኘው በጣም ጓጓ፤ የቁመቱ አጭር መሆን ከእነዛ ሁሉ ሰዎች ጋር ተጋፍቶ ያሰበውን እንዲያደርግ አላስቻለውም፡፡ በመጨረሻ ግን አንድ ውሳኔን ወሰነ፡፡
ኢየሱስ በሚያልፍበት መንገድ ቀድሞ ሔዶ ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ኢየሱስም ተመለከተው ድምፁንም ሰማው፤ እንዲያውም ዛሬ በቤትህ እራት እበላለሁ አለው፡፡ እኛ ግን እንናገራለን እንጂ፣ እንጮኻለን እንጂ፣ የሚሰማን የለም፡፡ እኛስ ምን ላይ ወጥተን እንጩኽ?
ታክሲው በትክክል ዳር ይዞ አልቆመም ነበር፡፡ አንድ የከተማ አውቶቡስ በአጠገባችን ለማለፍ ሲንደረደር ወያላው በፍጥነት ለሾፌሩ መልዕክት አስተላለፈ፣ "ዳር አሲዝ፣ ዳር አሲዝ እንደልቡ መጣ፤" አለ፡፡ እንደልቡ በእርግጥም ጥሩምባውን ድብልቅልቅ አድርጐት በአጠገባችን ሽው ብሎ አለፈ፡፡
ረዳቱን ጠየቅኩት፤ ለምን እንደልቡ እንዳለው፤ የመለሰልኝ የአውቶቡስ ሾፌሮች ሲነዱ እንደፈለጉ ነው፤ ብዙ ጊዜ አደጋ ሲደርስ ተጠያቂ የሚሆነው ግን ታክሲ ነው፡፡ በሌላ ተሽከርካሪ ጥፋት የደረሰ አደጋ ቢኖር እንኳን በአደጋው ውስጥ ታክሲ ካለ፣ በቃ ሁሉም ታክሲው ላይ ያላክካል፡፡ አውቶቡሱ የፈለገውን ያህል ነው የሚጭነው፤ ለዚያ ነው እንደልቡ የተባሉት አለኝ፡፡
"እኛ አናጠፋም፣ በጣም ጠንቃቃ ነን ለማለት ፈልገህ ነው?" አልኩት፡፡ "አንዳንዶች ምን እንደሚሉ ታውቃለህ?" አልኩ እንደገና፤ "ምን አሉ?" አለኝ፡፡ "ከእያንዳንዱ ውጤታማ ወንድ በስተጀርባ ጠንካራ ሴት እንዳለች ሁሉ፤" ትንፋሼን በረዥሙ ሰበሰብኩ፡፡ "እሺ እባክህ?" አለኝ እያሾፈ፡፡ "ከእያንዳንዱ አደጋ በስተጀርባ ታክሲ አለ፤" አልተቀበለውም፤ ለማሳመን ጥረት ማድረግ ጀመረ፡፡ "አንፈጥንም ለማለት አልደፍርም፣ እንፈጥናለን፣ የምንፈጥነው ግን አደጋ ለማድረስ ብለን ሳይሆን ጊዜን ለመቅደም ነው፡፡ በዚያ መሐል አደጋ ሊፈጠር ይችላል፡፡ አሁን በአቋራጭ መጫን የመረጥንበት ዋነኛው ምክንያት ጊዜን ለመቆጠብና አደጋን ለመቀነስ ነው፤" እያለ መፈላሰፍ ጀመረ፡፡
"ለእኔስ እንደልቡ ማለት እናንተ ናችሁ፤" አልኩት፡፡ "ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ሳታስፈቅድ ትሳደባለህ እንዴ? ማን የሰየመህ እንባ ጠባቂ ነህ?" ሌላም ሌላም ነገር ተናገረ፡፡ እኔም በደንብ ሐሳቤን አጠናከርኩለት፡፡ "እንደልባችሁ ብትሆኑም አይደል እንዴ በምትፈልጉበት አቅጣጫ ብቻ የምትጭኑት? እንደልባችሁ ብትሆኑም አይደል እንዴ ያላግባብ ታሪፍ እየጨመራችሁ ሰውን የምታንገላቱት? እንደልባችሁ ብትሆኑም አይደል እንዴ ሰው በሰው ላይ ደራርባችሁ የምትጭኑት? እነዚያ ሁሉ ድርጊቶቻችሁ ምን የሚያሳዩ ይመስላችኋል?" ባልፈራው ኖሮ ሌላም ሌላም ነገር ልለው አስቤ ነበር፡፡ ዘንድሮ ምን የማይፈራ አለ፡፡ ጉልበተኛ በዝቷል፡፡ ከሕግ ውጪ በጉልበቱ የሚያድር በየቦታው ይቀፈቀፋል፡፡ እነ ጉልቤ ማሰብ ሲያቅታቸው ዱላ ይመዛሉ፡፡
"የባስ ሾፌር ነበርክ እንዴ?" አለኝ ለማሾፍ እየሞከረ፤ መናደድ አልፈለኩም፣ እኔ ግን ላናድደው ተነሳሁ፡፡ "አአይ ወያላ ግን አልነበርኩም፤" አልኩት፡፡
የረሳሁት ነገር ትዝ አለኝ፣ የሳንቲም መልስ ነበረኝ፡፡ በቁጣ "መልሴን ስጠኝ" አልኩት፡፡ "ስንት ነበር የሰጠኸኝ?" ለአሥር ሳንቲም ነው ብሎ ከመወርወር በማይተናነስ ሁኔታ አቀበለኝ፡፡ የእኔም አቀባበል ለነገሩ ከመመንጨቅ አይተናነስም ነበር፡፡ ሰው ሁሉ ለአሥር ሳንቲም ያደረኩትን ግብ ግብ አይቶ ምን እንዳሰበ አላውቅም፡፡ አንዳንዶቹ የማነው ገብጋባ ያሉኝ መሰለኝ፤ አንዳንዶቹም "ጋቭሮቭ" ያሉኝ መሰለኝ፤ አንዳንዶቹ ግን ልክ ነህ እንዳሉኝ ያረጋገጥኩት፣ "የኛንም መልስ አምጣ" ብለው ሲቀበሉት ነው፡፡
የሌሎቹን መልስ ላለመስጠት ፈልጐ ዝርዝር የለኝም በማለት መነጫነጭ ጀማምሮት ነበር፡፡ አንደኛው ተሳፋሪ ተቆጥቶ "እኛ ዝርዝር ባይኖረን በነፃ ትወስደን ነበር?" ሲል አፋጠጠው፡፡ "እወስዳለሁ ግን እንዳንተ ዓይነቱን አይደለም፤" አለው፡፡ "ከፈለግክ ሁለቱንም ብር እመልስልሀለሁ" ሲለው ሰውዬው ተበሳጨ፡፡ "ነው እንዴ? አሥር ሳንቲም ያልመለስክ ሁለት ብር ትመልሳለህ?" ሲል እንደገና አጉረጠረጠበት፡፡ "ለመሆኑ ስምህ ማነው?" አለው፡፡ ወያላው ስሙን አስተዋወቀ "መለሰ"፡፡ "አንተማ መለሰ መባል የለብህም፤ መባል ያለብህ ፣አስረሳኸን፣ ነው፣ አሥር ሳንቲሞችን እያረሳሳህ ስትዘርፍ ትውላለህ፤" አለው፡፡ ወያላው በንዴት ፊቱ ፍም መሰለ፡፡
ተሳፋሪው እንደገና "እንዲያውም እከስሀለሁ" አለው፡፡ ወዲያው ግን ዞር ብሎ "ብንከስስ ምን ዋጋ አለው? የሚሰማን የለም፤ ሦስት ምስክር አምጣ ብባል ከየት ነው የማመጣው? የምንናገረው ሳናጣ የሚያደምጠን አጥተን፣ ዝምታን መርጠን አርፈን ተቀመጥን፤" በብሶት ተናገረ፡፡ ሰውዬው ሌላ ብሶት ያለበት ነው የሚመስለው እንጂ፣ ታክሲ ውስጥ የተፈጠረው ነገር የዚያን ያህል እንዲህ ያብከነክነዋል ብዬ ማሰብ ተቸገርኩ፡፡ እውነት ነው ከሌላ ነገር ጋር ተዳምሮበት ነው፡፡ ብሶቱ ሞልቶ ይሆናል፡፡ መቼም ታክሲ ውስጥ የሚታየው የመብት ጥሰት ከመዘውተሩ የተነሳ እዚህ ገንፍሎበት ነው እንጂ፣ ሰውዬው በጣም የተነካበት ነገር በሆዱ ይዟል፡፡ እንዳነጋገሩ ከሆነ የሚሰማው አጥቶ የቁራ ጩኸት የሚጮህ ነው የሚመስለው፡፡
መገናኛ ደረስን፤ መገናኛ ያለው የታክሲና የሃይገር ባስ ትርምስ ዛሬም አልረገበም፡፡ አደባባይ ውስጥ ለመግባት ረጅም ሠልፍ ይጠይቃል፡፡ በእርግጥ በቆምንበት ቦታ ቢያወርዱንም የሚቀጥለውን ታክሲ ለመያዝ ግን ወደ ውስጥ በእግራችን መዝለቃችን አልቀረም፡፡ ከድልድዩ በስተግራ በኩል ያለው አካባቢ በሽንትና በሌላ መጥፎ ነገር ተበለሻሽቷል፡፡ በዚያ ላይ ዝናብ ጠብ ሲልበት ሽታው ሌላ ነው፡፡ "ሽንት መሽናት ክልክል ነው" ተብሎ ተጽፏል፤ ያስቀጣልም ተብሏል፡፡ አንዳንዶች ግን እዚያው ሽንት መሽናት ክልክል ነው ተብሎ የተጻፈበት ቦታ ላይ ነው የሚሸኑት፡፡
ከዚህ ሁሉ ቢያንስ እዚያ አካባቢ ላሉ ጐዳና ተዳዳሪዎች፣ ሊስትሮዎች፣ ወያላዎችና የተለጣፊ ሱቅ ባለቤቶች ተንቀሳቃሽ ሽንት ቤት ቢቀመጥላቸው፣ የሽንት መሽናት ክልክል ነው ማስታወቂያ ላያስፈልግ ይችላል፡፡ እንኳን ክልክል ነው ቀርቶ "ዴንጀር" ተብሎ ቢጻፍም በአቅራቢያው ሽንታቸውን የሚሸኑበት ካላገኙ፣ ትዕዛዙን የሚያከብር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሰውም፣ ማስታወቂያውም፣ ሁሉም ነገር አዳማጭና ሰሚ አጥቷል፡፡ እሮሮ የማይደመጥበት ኑሮ በስጨትጨት ቢያደርግም፣ ከወያላ ጋር እየተዳረቁ መኖሩ ግን መቼም ይቀጥላል፡፡


