ሰባት ሰዓት ከሰላሳ አካባቢ ላይ ነበር፡፡ የወያላው አፍ አሁንም አሁንም እየተከፈተ ይዘጋል፡፡ «ኧረ ሰዓት ደርሷል» ይለዋል ሾፌሩን፤ ሾፌሩ ግን አውቆ እንዳላወቀ በሚመስል ስሜት «የምን ሰዓት?» ይለዋል፡፡ «የምሳ ሰዓት እንድልህ ነው?» አለው ወያላው መልሶ፡፡
«ምሳማ አሁን በላን አይደል እንዴ?» ሾፌሩ በስቲኪኒ ጥርሱን እየጎረጎረ ወያላውን ሆን ብሎ ያስለፈልፈዋል፡፡ ወያላው የፈለገው ነገር ግን እኛን ሳይቀር ገብቶናል፡፡
አሁንም በምሬትና በተቆራረጡ ቃላት «ሰዓት ደርሷል» አለው እንደመቆጣት ብሎ፤ «የምን ሰዓት ነው የምትለኝ? ከሠራህ አርፈህ ሥራህን ሥራ፣ ካልሠራህ ደግሞ መተው ትችላለህ፤» አለው፡፡ ወያላው ቃላቶች እያጠሩት ተንተባትቦc «ዓረብ ልጁን የገደለበት ሰዓት ደረሰ፤» አለ፡፡ በድጋሚ «አቦ የዓይሬ ሰዓት ነው በናትህ ፍታኝ አለው፤» ስለመፈታት ሲያወራ ስለመታሰር ማሰብ ጀመርኩ፤ መቼም የታሰረ ነገር ነው የሚፈታው፡፡ ማን ይሆን ያሰረው ብዬ ጠየቅኩ፡፡ አፉ ታስሯል፣ ፊቱ ታስሯል፣ ሥራውንም በፍጥነት መሥራት ተስኖት ነበር፡፡ ሱሱ ይሆን ያሰረው ብዬም አሰብኩ፡፡
ወዲያው ሾፌሩ መዝፈን ጀመረ «ሱሴ፣ ሱሴ . . .» እያለ፡፡ ሾፌሩ መናገር ጀመረ፣ «ሱስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?» አለው፡፡ «አላውቅም ምንድነው?» አለው ወያላው፡፡ «ወደው የሚገቡበት እስር ቤት ነው፤» አለው ሾፌሩ፡፡ ቀጥሎም፣ «ወዶ መግባት እንጂ ወዶ መውጣት የሚባል ነገር አይታሰብም፤» አለው፡፡
ወያላው እንደመበሳጨት ብሎ «እኔ’ኮ ሱስ የለብኝም ለሙድ ብዬ ነው የምቅመው፤» አለ፡፡ ሾፌሩ መለሰ፣ «አየንህ እኮ ሙድህ ጠፍቶ፣ ፊትህ የተረበሸ ከተማ የመሰለው እንዲሁ ለሙድ ስለምትቅም ነው፤ አይደለም?» ብሎ የባሰ አቆሰለው፡፡
ወያላው ግን ትናንትና ሲቅም አብሮ ምላሱን ውጧት ነው መሰለኝ ለሾፌሩ መልስ መስጠት አልቻለም፡፡ ከተሳፋሪ ጋር ባለው ግንኙነትም ቢሆን ሒሳብ የተቀበለውን ሰው እንደገና ይጠይቃል፣ በድጋሚ መልስ ይሰጣል፣ ከመጠን በላይ ያነጫንጨዋል፤ በዚያ ላይ ሾፌሩ ጥምድ አድርጎ ይዞ አላላውስ ብሎታል፡፡ በዚህ ላይ አልቃመም፡፡ ዓይኖቹ ጋዝ እንዳለቀባቸው ኩራዝ ሊጠፉ ጭል፣ ጭል ይላሉ፡፡
ከክፍለ አገር የመጡ የሚመስሉ ሰዎች ከኋላ አራተኛውን ወንበር ሞልተውታል፡፡ ከመካከላቸው አንደኛው ሒሳብ ሊከፍል አስቦ፣ «ማነህ አስተናጋጅ?» ብሎ ተጣራ፡፡ ወያላው ሰምቶ አሁንም ተበሳጭቶ ዝም አለ፡፡ ሾፌሩ ሰምቶ ወዲያው ቀበል አድርጎ፣ «አስተናጋጅ ምን ነክቶህ ነው? አስተናግዳቸው እንጂ፤ አትፍዘዝ በቃ አሁን ጫቱን እንገዛለን፤» አለው፡፡ ወዲያው መልሶ፣ «ቆይ እኔ ነዳጅ ልሙላ ወይስ ያንተን ሱስ ልሙላ?» ካለ በኋላ፣ ጫት እንዲገዛ ፈቀደለት፡፡ ወያላው ደስታው ወሰን አጣ፡፡ ጫት ቤቶቹ ደግሞ ልክ እንደባስ ፌርማታ በየአሥር ሜትሩ ተደርድረው ደንበኞቻቸውን ይጠባበቃሉ፡፡
ልክ ታክሲው ሲቆምለት ወያላው በሰከንድ ውስጥ ከአንደኛው ጫት ቤት ተወርውሮ በመግባት የተፈቀደለትን ያህል ገዝቶ ተመለሰ፡፡ አንድ ሁለቴ መታ፣ መታ እንዳደረገ የተደበቁት ዓይኖቹ ብቅ ብቅ አሉ፡፡ ቅድም ጨለምለም ብሎ የነበረው ፊት እንደ ባውዛ ማብራት ጀመረ፡፡ ዘገምተኛ ይመስል የነበረው ወያላ በቅጽበት እንደ ማሽን ይሾር ጀመረ፡፡ ተብታባ ይመስል የነበረው ሰውዬ በአንዴ ባለ ሁለት አፍ ሆነ፡፡ ንግግሮቹ አራት ነጥብ ጠፋላቸው፡፡ ቅድም ለሾፌሩ የሚመልሰው መልስ እንዳላጣ አሁን ደግሞ በተራው ሾፌሩ አፉን ያዘ፡፡
ቅድም አስተናጋጅ ብለው ወደጠሩት ሄዶ በትህትና፣ «ምን ልታዘዝ? ቦሌ፣ ሩዋንዳ፣ ስቴዲዮም፣ ሜክሲኮ» ብሎ ሜኖውን አነበበላቸው፡፡ የሚፈልጉትን መርጠው ዋጋ ተከራክረው፣ ሌሎች ተሳፋሪዎችን ጠይቀው ከፈሉ፡፡ «ዘፋኞቻችን እስከ ዛሬ ለጫት ባለመዝፈናቸው አዝንባቸዋለሁ፤» አለ ወያላው፡፡ ሾፌሩም፣ «ግጥም የሚሰጣቸው አጥተው እንጂ መቼ መዝፈን አቅቷቸው መሰለህ?» አለው፡፡ ይኼኔ ወያላው ተናገረ፣ «እኛን ቢጠይቁን እኮ የግጥም ዓይነት እናዥጎደጉድላቸው ነበር፤» ብሎ የሆነ ግጥም በቃሉ ያነበንብ ጀመር፡፡
«የቃመ ተጠቀመ፣
ያልቃመ ተለቀመ፤
ጫቱን ቅሞ ቅሞ ሐጃው ካልሰመረ፤
ፈረስ ተቀልቦ ገደል ካልዘለለ፣
ወንድ ልጅ ተወልዶ አባቱን ካልጦረ፣
ስሙ ምን ይባላል በከንቱ የቀረ፤»
የግጥም መድበል ቢያሳትም መቼም የሚገዛው አያጣም፡፡ ሲያወራ አይፎርሽም፤ ግጥሞቹ በተለይ በእርሱ አፍ ተነግረው ሲደመጡ እውነትም ቃም፣ ቃም ያሰኛሉ፡፡ ወያላው ቀጠለ፡፡
«ሐመሩን ለኛ፣
ባጃጅ ለምቀኛ፤»
ሾፌሩ፣ «በገዛ እጄ» አለ፡፡ «ምነው እንደዛው ዱዳ ሆነህ በቀረህ ይሻለኝ ነበር፤» አለው፡፡ መልሶም፣ «ቆይ ኢትዮጵያ ውስጥ ጫት ቢከለከል ምን ይውጥሀል?» አለው፡፡ «የዚያኔ ኮሽም ትቅም እንደሆን ይታይ ነበር፤» አለው፡፡ «ማንም ሊከለክለን አይችልም፤» አለ ወያላው በኩራት፡፡ መልሶም፣ «ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ከጫት ኤክስፖርት ገበያ ያገኘችው ገንዘብ ከ54 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፤ ይህ ገቢዋ ደግሞ በዚህ ዓመት ከወርቅና ከአበባ ካገኘችው የውጭ ምንዛሪ ይበልጣል፡፡ ታዲያ የጫት ምርት ይቁም የምትል ይመስልሃል? ከዚህ ሁሉ የአበባ አምራቾች ተጠራርገው ቢወጡና የወሰዱት ቦታ ሁሉ ተሰብስቦ ለጫት አምራቾች ቢሰጣቸው ይሻላል፤» ብሎ አረፈው፡፡ ይኼኔ ሾፌሩ የሚናገረው አጥቶ ጸጥ አለ፡፡ እኔ ደግሞ ዝም ማለት አልቻልኩም፡፡
«ስማ!» አልኩት ተቆጥቼ፡፡ «አገራችን ሃምሳ አራት ሚሊዮን ብር ከጫት ብታገኝም፤ በጫት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጭንቅላቶች ደንዘዋል፣ ዝገዋል፣ በአግባቡ አገልግሎት መስጠት ተስኗቸው በየጫት ቤቱ ተጎልተው ይታያሉ፡፡ ላንተ ጫት ኢትዮጵያን ምን ያህል እየገደላት እንደሆነ ገና አልተገለጠልህም፡፡ ሚሊዮን አይደለም ቢሊዮን ብር የኢትዮጵያዊያንን አዕምሮ አይተካም፡፡ ቫይረስ እንደገባበት ኮምፒዩተር 'ስታክ' እያደርክ ደግሞ ጫት ጠቀመኝ ትላለህ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ነበርክ፤» አልኩት በቁጣ ውስጥ ሆኜ፡፡
«አንድ ሁለት እንጨት ብትሞክር እንዲህ አትልም ነበር እንካ ሞክር፤» አለኝ፡፡ «እኔማ አልሞክርም፣ ጫት አንተን ምን እንዳስመሰለህ እያየሁ የምቅም ይመስልሃል? ስለጫት ጥቅም ለማወቅ አንተንና መሰሎችህን ካየሁ ይበቃኛል፤ ሌላ ምርምር መሥራት አያስፈልገኝም፤ ብልህ ከሰነፍ ይማራል፤» በማለት ቁጭቴን ሁሉ ዘረገፍኩበት፡፡ ጨምሬም «በየፋርማሲው የኩፒድን ገበያ ያደራው ምን ይመስልሃል? ኩፒድ ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ? ለነገሩ ተወው አይገባህም፡፡ ስንቱ በስንፈተ ወሲብ ምክንያት ትዳሩ እየተበተነ ነው፡፡ ብቻ ተወው፡፡ ደግሞ አታፍርም እንዴ ለጫት ምሥጋና ግጥም ታነበንባለህ፡፡» እንዲያውም መባል የነበረበት፡-
«ያልቃመ ተጠቀመ፣
የቃመ ተለቀመ . . . ፤» ሳልጨርስለት፣ «ኮፒ ራይት» አለኝ፡፡
አንድ አባት መናገር ጀመሩ፡፡ «አአዬ ልጄ እፀ በለስ በለው፤ እሱን ስንበላ ዓይናችን ይከፈታል ይላሉ፤ ሔዋን ያንን እፀ በለስ ስትበላም አይደል ዓይኗ የተከፈተው፤»አሉ፡፡ «አዎን ልክ ነዎት፣ በቃ ለነሱ ልክ እንደዛው ነው፤ ዓይናችን ተከፈተ ይበሉ እንጂ ክፉና ደጉን ለይተው አያውቁም፤» አልኳቸው፡፡
«እኔ አንድ ጎረምሳ ልጅ አለኝ ጠዋትም፣ ማታም እሱን ካላኘከ አያስቀምጠንም፡፡ መግዣ ሲያጣ ደግሞ የቤቱን ዕቃ አንድ በአንድ አውጥቶ ሸጦ አሁን ቤታችንን ብታየው እየኖርንበት ባዶ ከመሆኑ የተነሳ የተለቀቀ ቤት ይመስላል፤» በማለት አምርረው አዘኑ፡፡
አባባ ምሬታቸውን ቀጠሉ፣ «እናቱማ ጨርቋን ጥላ ልታብድ ምንም አልቀራትም፤ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ያላትን ሁሉ አሟጣ ሰጠችው፤ እሱ ግን ትምህርቱንም ሳይጨርስ ጫት መብላት ለምዶ መጣ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ራሳቸው ጫት መቃሚያ ቤት እንጂ መማሪያም አይመስሉ፤» ብለው አማረሩ፡፡ «ታዲያ የትኛው አፍ ነው ደፍሮ ጫት ጥሩ ነው ብሎ የሚናገረው›› ብለው አባት ጥያቄ ጠየቁ፡፡
ሾፌሩ ያሉትን ሰምቶ እሱም አገዛቸው፣ «የሚገርምዎት ይኼ ወያላ ያጎቴ ልጅ ነው፤ አትቃም ስለው አይሰማኝም፡፡ ባለፈው ሰሞን ጨጓራውን በጣም ታሞ ቀዶ ጥገና አድርጎ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠፍቶ የነበረ የጫት ትል ሆዱ ውስጥ ተገኘ፡፡ ከጨጓራው ውስጥም ብዙ ያልተፈጨ ጫት አወጡለት፡፡ አሁንም ገና የተሰፋው ቁስሉ ሳይደርቅ ይቅማል፡፡ ታዲያ ይኼ ልክፍት ቢሆን ነው እንጂ ሰው ከሕይወቱ የሚበልጥ ምን አለ?» ብሎ በትካዜ ታክሲውን ይነዳ ጀመር፡፡


