Wednesday, Jun 19th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

«ማነው ወያላው?»

E-mail Print PDF
User Rating: / 3
PoorBest 

ለመሆኑ ጨዋ ሾፌር ወይም ጨዋ ወያላ አለ እንዴ? አንዳንዶቹ፣ «የለም፣ ሊኖርም አይችልም» የሚል ክርክር አነሱ፡፡ አንድ ሰው ተናገረ፣ «ምነው እናንተ ሾፌሮችና ወያላዎች ሁሉ ከአንድ እናት የሚወለዱ አስመሰላችኋቸው?» አለ፡፡ ሌላኛው በተራው መልስ ሰጠ፣ «ከአንድ እናት ባይወለዱም ከአንድ ዓይነት አፈር ተጠፍጥፈው የተሠሩ ነው የሚመስሉት፤» ይገርማል፡፡ አንዲት ሴት ስትናገር የጭውውቱ ዙር ከረረ፣ «ወያላ ጨዋ ሆነ ከማለት ሰይጣን መነኮሰ ቢባል ይቀላል፤» አለች፡፡

ከሞላ ጐደል አብዛኛዎቹ አንድ ዓይነት መሆናቸው ሲነገር በእርግጥም ከአንድ «ኮሌጅ» የተመረቁ ነው የሚመስሉት፡፡ ለምሳሌ ትንሽ መሸትሸት ሲል ከቦሌ ድልድይ ስቴዲዮም የሚጠራ ታክሲ ማግኘት ዘበት ነው፡፡ የሚገርመው ከመገናኛ የመጡ፣ ከሃያ ሁለት የመጡ፣ ከገርጂም ቢሆን የመጡት፣ የት ተገናኝተው እንደተነጋገሩ ሳናውቀው ሸዋ ዳቦ፣ ሜክሲኮ እያሉ ይጠራሉ፡፡ ስቴዲዮም ለመሄድ የግድ የሜክሲኮን ሒሳብ መክፈል ይኖርብናል፡፡ ወይም ከዚያው ሳንርቅ ወደ ገርጂ ለመሄድ ቢታሰብ ሁሉም በአንድ ድምፅ «በአፓርታማ ገርጂ» ሲሉ፣ አንድ ላይ ተገናኝተው የሚመክሩበት ጉባዔ አላቸው ወይ ያሰኛል፡፡

የታክሲ ሾፌሮችና ወያላዎች የሚያስቀናው አንድነታቸው ብቻ ነው፡፡ አንድነት ላይ የሚያክላቸው የለም፡፡ የሚያናድደው ግን አብዛኛውን ጊዜ ለደህና ነገር ወይም ሕዝብን ለማገልገል አንድ ሲሆኑ አይታዩም፡፡ ዝናብ ሲዘንብ ወይም ጫት ቤት ሲመሽጉ አዲስ አበባችን ጭር ብላ ኦና ቤት ትመስላለች፡፡ አንዳንዴማ ምነው ኢትዮጵያውያን እንደባለታክሲዎች እንዲህ አንድ ቢሆኑ ያሰኛል፡፡ ምነው የፖለቲካ ፓርቲዎችም መከፋፈላቸውን ትተው እንደዚህ አንድ ቢሆኑ? በየጊዜው መከፋፈላቸውንና አዲስ ስም እየለጠፉ መንቀሳቀሳቸውን ትተው አንድ የማይናወጥ ነገር ይዘው ፀንተው ቢያፀኑን እንላለን፡፡ ሾፌርና ወያላ ግን አንድነታቸው የሚጐዳው እኛን ምስኪን ተሳፋሪዎችን ነው፡፡

መቼም ገዢው ፓርቲ ያለፈውን ምርጫ መቶ በመቶ ምንም ባልቀረው ውጤት ሲያሸንፍ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግፎት ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ግና ገና በሁለት እግራቸው መቆም ካልቻሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንጻር ይህ ውጤት ይሻላል ያለ ይመስላል፡፡ የታክሲ ሾፌርና ወያላ ግን ያለምንም ከልካይ መቶ በመቶ እንዳሸነፉን አሉ፡፡ ምነው ስንላቸው፣ «ታክሲ ውስጥ መጨቃጨቅ ከአሸባሪነት አይተናነስም» እያሉ ያስፈራሩናል፡፡

ኢትዮጵያችንም ብትሆን አንድ ሆና እስከ ዓለም ፍጻሜ ስትዘልቅ ማየት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጥማትና ረሃብ ነው፡፡ በሐሳቤ ይኼ ሁሉ ነገር መጥቶ ከሄደ በኋላ አንድ ነገር በጣም አስገረመኝ፡፡ መጀመሪያ ስለወያላዎችና ሾፌሮች ከሌሎች ተሳፋሪ አጋሮቼ ጋር ሆነን ስንቦጭቅ የታክሲያችን ወያላና ሾፌር ምንም መልስ አልሰጡንም፡፡ ይህ ለእኔ ከግርምትም በላይ ትንግርት ሆነብኝ፡፡

ምናልባት እነዚህ አዲስ ይሆናሉ ብዬ አሰብኩ፡፡ የሾፌሩም አነዳድ ሆነ የወያላው አወያየል ለሥራው አዲስ እንዳልሆኑ በግልጽ ታየኝ፡፡ ታዲያ ምን ዘጋቸው? እንኳን እንደዚህ በግልጽ ለሚሰድባቸው አይደለም ከመሬት ተነስተው ያገኙትን ሁሉ ጥምብ እርኩሱን ነው የሚያወጡት፡፡ እነዚህኛዎቹን ምን ነካቸው? ወያላዎች አፋቸውን በስድብ የሚፈቱ ነው የሚመስለኝ፡፡ እነዚህኞቹ ግን ከመጣራትና ተሳፋሪን ከማስገባት ውጪ፣ በሰው  ሞራል ላይ ስንዝር ያህል አይራመዱም፡፡ በዚያ ላይ ወያላው ለሰው ያለውን አክብሮት ስመለከት፣ ምናልባት በፊት «ሆስተስ» ሆኖ ሠርቶ ይሆናል ብዬ አሰብኩኝ፡፡

«ከስንዴ መሀል እንክርዳድ አይጠፋም» ሲባል አምናለሁ፡፡ ከወያላዎች መሀል ግን መልካም አለ ሲባል በፍፁም አላምንም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ወያላው በትህትናው አናት አናቴን ኮረኮመኝ፡፡ እንደለመድኩት ብዙ ተሳደብኩ፣ ምንም መልስ አልሰጠኝም፤ ሌሎችንም አስተባብሬ አስሞለጭኩት፤ እሱ ከትህትናው ፍንክች አላለም፡፡ በመጨረሻ አንድ ጥያቄ አዕምሮዬን ሞገተኝ፤ ጥያቄውም፣ «ማነው ወያላው?» የሚል ነበር፡፡

እኔ አይደለሁም ለማለት ከራሴ ጋር ብዙ ተሟገትኩ፡፡ ወያላውን ሲሳደቡ የነበሩት የስድብ አጋሮቼ ናቸው በማለት ለጭንቅላቴ ላቀርብለት ሞከርኩ፤ ከህሊናዬ ሙግት ማምለጥ አልቻልኩም፣ «አንተ ነህ ወያላው» ይለኝ ነበር፡፡

«ህሊና በሰው ማንነት ውስጥ እውነቱን ለመናገርና ለማሳየት የተቀባ ነብይ ነው፤» የሚለው አባባል ታወሰኝ፡፡ ምናልባት ነብይ በአገሩና በቤተሰቡ አይከበርም ስለተባለ፤ እኛም ሁልጊዜ እውነት እውነቱን የሚነግረንን ህሊናችንን አንቀበለውም፡፡ እኔን «ለዛሬ ወያላው አንተ ነህ» ቢለኝም፣ አለመሆኔን ለማስረዳት ብዙ ማስረጃ ማዘገጃጀት ጀመርኩ፡፡ የትምህርት ማስረጃዬን ጨምሬ አሳየሁ፡፡ ህሊናዬ ግን ይባስ ብሎ «የትምህርት ማስረጃ ተብዬ ያለህ ወያላ ነህ ለዛሬ» ያለኝ መሰለኝ፡፡

በመጨረሻ ከራሴ ጋር ተስማማሁ፡፡ ሁሉንም ወያላዎች በአንድ መስፈሪያ ማየት ኃጢያት ነው፡፡ በጣም ሊበረታታ የሚገባ መልካም ምግባር ያላቸውን ወያላዎች በዓይኔ ስለተመለከትኩ፡፡ ከዚህ በኋላ የወያላ ጥሩ የለውም የሚለው የደፈና አባባል ለኔ ክህደት ነው፡፡ «ለዛሬ ወያላው አንተ ነበርክ» ባለኝ የህሊናዬ ፍርድ እየተስማማሁ፣ መልካም ሥነ ምግባር ያላቸውን ወያላዎች በመመረቅ ለምን ሐሳባችንን አንገታም? ከተስማማን እኔ እመርቃለሁ፤ እናንተ አሜን እያላችሁ ታሳርጋላችሁ፡፡

የተሳፋሪ ወያላ ከመሆን ይጠብቀን . . .  አሜን
በአንድ መስፈሪያ ትውልዱን ሁሉ ከመስፈር ይጠብቀን . . .   አሜን
አሜን አትሉም እንዴ?
የተባረኩ ወያላዎችን ያብዛልን . . . አሜን
ከወያላ ጉልበተኛ ከሾፌር ምላሰኛ ይሰውረን . . . አሜን
ከታክሲ ግፊያ ገላግሎ የራሳችንን መኪና ይስጠን . . . አሜን
ነዳጅ በውኃ ዋጋ፣ ጤፍ በጨው ዋጋ የሚሸጥበት ዘመን ያምጣልን . . . አሜን
አገራችንን ሰላም ያድርግልን . . . አሜን
አሜን!
በፀሎት ውስጥ አሜን እያለ አክሲዮን ያልገዛ ካለ ከተዘረዘሩት ውስጥ ቢያንስ አንዱ እንደማያጋጥመው ብንናገር ነውር ይኖረው እንዴ? እናንተ አሜን ያላችሁ ከተባለው ነገር አንዱንም አይጉድልባችሁ፡፡ ከታክሲው ስወርድ ጐንበስ ብዬ በትህትና ወያላውን ይቅርታ መጠየቄን አልዘነጋሁም፡፡ እሱም ቢሆን ሐሳቤ ስለገባው «ምንም ችግር የለም፣ ለሌላ ጊዜ ብቻ እንደዚህ አታድርግ፤» ብሎ በትህትና ማስተርሱን ሠራብኝ፡፡ ትህትና ይብዛላችሁ!!!