ባይናገር ቃል አውጥቶ
ባይተነፍስ ድምፅ አሰምቶ
ባይሰጥ ምላሽ ቃል አሳክቶ
ለጥያቄው ጥያቄ አንሥቶ
ባይሟገት ባይከሰስ ከማንም ጋር
መጽሐፍ ነው አይዘንጋ
የያዘውን የማይረሳ ያለው ዋጋ
ጊዜው ቢሔድ ቢረጋጋ
ለተጠየቀው ለሚጠየቀው
ምላሽ ' ሚሰጥ ባላደራው
ምላሽ ' ማያጥፍ ለተናገረው
በተናገረው ባሰፈረው ቃል
በያዘው ሁሉ የሚረታ አካል
ማንም ቢመጣ ማን ቢጠይቀው
በጽሑፍ ያለ ' ሚመልሰው
እማያፍርበት ' ሚኮራበት
እሱ ነው መጽሐፍ መልሱ ያለበት
እሱ ነው መጽሐፍ መልሱ ያለበት
(ቀለሟ መኮንን፤ፈለገ ጥበብ፣ግንቦት 2002)
- የፕሬዚዳንቱ ጸሎት
ከ1953-1961 የዩናይትድ ስቴትስ 34ኛ ፕሬዚዳንት የነበሩት ድዋይት አይዘንሀወር በየዕለቱ እንዲህ ይጸልዩ ነበር፡-
‹‹እግዚአብሔር ሆይ፣
በሆነ ምክንያት እኔ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳነት ነኝ፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ለመሆን ብዙ ማወቅ ይኖርብሃል፡፡ ያን ያህል አለማወቄን አልደብቅም፡፡ ግን ጌታ ሆይ፣ አንድ እርግጥ የሆነ ነገር አለ፡፡ አንተ እዚህ ዋሽንግተን ካለ ከዬትኛውም ፖለቲከኛ ይልቅ ምን መደረግ እንዳለበት ታውቃለህ፡፡ ስለዚህ ብትመራኝ ደስ ይለኛል፡፡ እኔ ቀኑን ሙሉ የምችለውን ሁሉ በተሻለ እሠራለሁ፡፡››
ሲመሽ ወዳልጋዬ ስሄድ ቀን የሠራሁዋቸውን ስህተቶች ከማሰብ ፈንታ እንዲህ እጸልያለሁ፡፡
‹‹ዛሬ ስለነበሩኝ ስኬቶች ላመሰግንህ እፈልጋለሁ፡፡ የስኬቴ ምስጢር አንተን መስማቴ ነው፡፡ በዕለቱ ስለነበሩኝ ውድቀቶች ይቅር እንድትለኝ እፈልጋለሁ፡፡ ያ የሆነው ድዋይት አይዘንሀወርን በመስማቴ ነው፡፡ አሁን ጌታ ሆይ፣ ወደ እንቅልፍ መሄድ እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህም ዩናይትድ ስቴትስን መንግሥት እስከ ነገ ጠዋት 12 ሰዓት ድረስ አስረክብሃለሁ፡፡ በሌሊቱ የምትችለውን ሁሉ አድርግ፡፡››
(ኃይል ከበደ፤የፓንዶራ ሙዳይ፣2002)
* * * * * *
ዳሞታ
የዳሞት ተራራ የተፈጠረው ጥንት ጊዜ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሳይሆን እንዳልቀረ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የተራራውን ስያሜ በተመለከተ በመካከለኛው ዘመን ገናና ከነበረው ከዳሞት መንግሥት ጋር ትስስር እንደነበረው አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ዳሞት በወላይታ እምብርት የሚገኝ ትልቁ ተራራ ሲሆን፣ ለሁሉም አካባቢዎች ማዕከል ሆኖ ያገለግላል፡፡ የተራራው የላይኛው ጫፍና ምሥራቃዊ የታችኛው ክፍል ከጥንታዊ የወላይታ መንግሥት መናገሻዎች አንዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ከወጥ ድንጋይ ተፈልፍለው ባማረ ባህላዊ ምህንድስና ተጠርበው የተተከሉ የጥንታዊ ሥልጣኔ አሻራ ገላጭ የሆኑ ድንጋዮች ክምችት ወይም ሶዱዋ በዳሞታ ምዕራባዊ ጎን ይገኛል፡፡
ነፋሻማ አየር ያዘለው የዳሞታ ተራራ ሰንሰለት ሶዶ ከተማን በደቡቡ፣ በደቡብ ምሥራቅና በደቡብ ምዕራብ በኩል ቁልቁል የሚያይ ሲሆን በ1887 ዓ.ም. ጥንታዊ የቅድመ ሶዶ ማዕከል /ዳልቦ/ የተቆረቆረችውም በዚህ ተራራ ምሥራቃዊ ክፍል ነበር፡፡
(ፍቅሩ ዳታ ደጋጋ፤የንጋት ኮከብ፣2000)
* * * * * *
አማልክቱ
የወላይታ ብሔር የበላይ አምላክ ጦሳ ሲሆን መንፈሱ ‹‹አያና›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ‹‹ጦሳ›› ሁሉን ፈጣሪና የበላይ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ምርቃትና መሐላ በ‹‹ጦሳ›› ስም ይደረጋሉ ባህላዊ ‹‹የጉተራ›› ሥነ ሥርዓት ‹‹ጦሳን›› በመጋበዝ ይከናወናል፡፡ ‹‹ጦሳ›› ያልተጠራበት ሥርዓት ሁሉ ከንቱ እንደሆነ ተደርጐ ይወሰዳል፡፡ ስለሆነም ጦሳ ልዑልና ክቡር ነው፡፡
ጦሳ በሰማይ ላይ አለ ተብሎ ይመለካል፡፡ ጦሳንና አምላኪዎችን የሚያገኛኝ መንፈስ አያና ይባላል፡፡ ይህ መንፈስ በሁሉም አማልክት ውስጥ ቢኖርም፣ የመንፈሱ ብርታት ከአማልክት ወደ አማልክት ይለያያል፡፡ አማልክቱ ሊያኖርና ሊያጠፋ፣ ሊያሳካና ላያሳካ ይችላል ተብሎ ስለሚታመን በየአድባራቱ መስዋዕት ይደረግለታል፡፡ አማልክቱ ይገኛሉ ተብሎ የሚገመተው በተራራዎች፣ በወንዞች፣ በታላላቅ ደኖች፣ በጫካዎችና በቤት ምሶሶ እንዲሁም በደብሮች አካባቢ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ መስዋዕቱ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ይቀርባል፡፡
(ፍቅሩ ዳታ ደጋጋ፤የንጋት ክከብ፣2000)
* * * * * *
የሀሮማያ ሐይቅ የት ገባ?
ዛሬ በሃያዎቹ መጨረሻ የሚገኝ አንድ የሀሮማያ ወጣት ከጥቂት ዓመታት በፊት የሀሮማያን ሀይቅ ዋኝቶበታል፡፡ እንዳይጠልቅ እየፈራ ሶቶ ገብቶበታል፡፡ ህጻናት ሲዋኙ እንዳይሰምጡ ወላጆች ተጨንቀዋል፡፡ ከአዲስ አበባ በ480 ኪሎ ሜትር በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ከሐረር ከተማ ምዕራባዊ አቅጣጫ ደግሞ በ21 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የሀሮማያ ሀይቅ እየተጨለፈ ይጠጣል፤ እድፍ ያጸዳል፤ ጓሮ ያለማል፤ በ1960 ዓ.ም. በተደረገው ጥናት አማካይነት ጥልቀቱ 8 ሜትር ገደማ ነበር፡፡
የዋኙበት፣ ፎቶ የተነሡበትም፣ ከሐይቁ ዳርቻ ንፋስ እየተቀበሉ አሻግረው አድማስን የተመለከቱትም ዛሬ ሀሮማያ ሐይቅን ቢያዩት የሚያውቁት ሰው በሞት እንዳጡት ክው ይላሉ፡፡ የትናንቱን ሀሮማያ ዛሬ በሥፍራው ሲያጡት አገር የተሳሳቱ እስኪመስላቸው ደርቀው ይቀራሉ፡፡
‹‹የሰው የለው ሞኝ
የሰው የለው ሞኝ
ከሀገሩ ከቦታው
ከሥፍራው ሲገኝ
የሰው የለው ሞኝ››
‹‹የሰው የለው ብልጥ
የሰው የለው ብልጥ
ሀይቁ ከሥፍራው ጠፍቶ ሲለወጥ
የሰው የለው ብልጥ››
ሀሮማያ ሐይቅ የት ገባ? እውነት ተፈጥሮ ሰውን እንዲህ ትከዳለች? እነኛ የሐይቁን ውኃ የመጠጡት ፓምፖች ትፉ ቢባሉ ሐይቅ መትፋት ይችላሉ? የአንድ ጎረምሳ እድሜን ያክል ጊዜ ሳይሰጥ የትናንትናው ሐይቅ ዛሬ የብስ ሆነ፤ እናት ብታምጥ ሐይቅ አትወልድም፡፡ ተፈጥሮ ከመከነች ምን ተስፋ አለን?
‹‹እንዳላረካህን እንዳልጠጣንብህ
አወይ ሀሮማያ አንተን ጥም ገደለህ››
ማንጐራጐር መፍትሔ ነው? እከሌ ነበረ ሞተ ይባላል፡፡ አቢጃታ እንደ ሀሮማያ ስጋት ወሮታል፡፡ የሐይቁ መጠን እየቀነሰ ነው፡፡ ፈሰሰም ተነነም፣ ለአቢጃታ ካልተረባረብን አእዋፋት አይዋኙበትም፡፡ ይልቁንስ ሜዳ ይሆናል፡፡ መልከ ጥፉ ሜዳ ተፈጥሮ እንደተቀበረችበት የሚያሳብቅ ምድር ሆኖ ያርፋል፡፡
በየ10 ዓመቱ ጥልቀቱ በግማሽ የሚቀንሰው እና ከዛሬ 60 ዓመት በፊት ድንቅ ሰፊና ይልቅ የነበረው አቢጃታ ዛሬ ታሟል፡፡ መቼ ይሆን ተፈጥሮን ስለማከም የምንጨነቀው? የግል ንጽህናን አለመጠበቅ ደስ አይልም፡፡ የአካባቢን ንጽህናን አለመጠበቅም በሽታን ያመጣል፡፡ የተፈጥሮ ሚዛንን አለመጠበቅ ግን ሞት ነው! ሊያውም ድንተገኛ ሞት፡፡
(ሀገሬ ሚዲያ፤ቱባ፣የካቲት 2002)
* * * * * *
ገ ራ ገ ር
በመኝታ ክፍሉ ውስጥ ዓለምን ለመዞር የተዘጋጀው ጐልማሳ
የአቪየሽን አድናቂ የሆነው ጐልማሳ ከመኝታ ክፍሉ ሳይወጣ ዓለምን ለሰባት ቀን ለመዞር ማቀዱን ኦሬንጅ ኒውስ ዘግቧል፡፡ የ50 ዓመቱ ጆን ዴቪስ ቦይንግ 747 የመለማመጃ አውሮፕላን እንዳለው ተገልጿል፡፡ ይኸው የመለማመጃ አውሮፕላን የሌለን ነገር ያለ በማስመሰል ስሜቱን እንደሚሰጥ ተገልጾ ይህም ግለሰቡ ከቤቱ ሳይወጣ ዓለምን እየዞረ እደሆነ እንዲሰማው እንደሚያደርግ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ዴቪስ ይኸውን አርቲፊሻል አውሮፕላን ለመሥራት 18 ሺሕ ፓውንድ እንዳወጣ ጠቁሞ በአሁኑ ጉዞውም ለበጎ አድራጎት ሥራ ገንዘብ እንደሚያሰባስብበት ጠቁሟል፡፡ በወጣትነት ዕድሜው ፓይለት የመሆን ህልም እንደነበረውና በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ማምጣት ባለመቻሉ እንዳልተሳካላት የሚናገረው ዴቪ፤ የአሁኑን ሥራውን በአማራጭነት እንደሠራው አብራርቷል፡፡ እሱን ጨምሮ ስምንት የአውሮፕላኑ ሠራተኞችም አብረውት እንደሚበሩ ዘገባው አመልክቷል፡፡
* * * * * *
ከሰባተኛ ፎቅ ተወርውራ የተረፈችው የ15 ወር ሕፃን
ከተማ ከሚገኝ አንድ አፓርትመንት ሰባተኛ ፎቅ ላይ የ15 ወር ዕድሜ ብቻ ያላት ሕፃን በፓሪስ ተወርውራ መትረፏን ሮይተርስ በድንቃ ድንቅ ወሬዎቹ አስፍሮታል፡፡ ሕፃኗ ከአራት ዓመት እህቷ ጋር በመጫወት ላይ እንዳለች በድንገት በመስኮት በኩል ልትወረወር ችላለች፡፡ ከሕንፃው ስር ያለ ካፌ ዣንጥላ ላይ ከነጠረች በኋላ መንገደኛ የሕፃኗን በፍጥነት መውረድ በመመልከት ከምድር ሆኖ በእጆቹ ተቀብሏታል፡፡ ሕፃኗ በአካሏ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ያልደረሰባት ሲሆን ለጠቅላላ ምርመራ ግን አቅራቢያ ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወስዳለች፡፡ የካፌው ባለቤት እንደተናገረው ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የሕንፃው ነዋሪዎች የሲጋራ ትርኳሽ ከላይ ወደ ታች ስለሚወረወሩ ጥላውን ይሰበስበው እንደነበር ገልጾ ልጅቷ በተረፈችበት ቀን በአጋጣሚ እንደዘረጋውና የመልካም ነገር ምልክት በመሆኑ ጥላውን እንደማያጥፈው አብራርቷል፡፡ የአካባቢው ፖሊስ የሕፃናቱ ወላጆች በአካባቢው ባለመኖራቸው የአደጋውን መንስዔ ለማጣራት እንደተቸገረ መግለጹን ዘገባው አመልክቷል፡፡


