Thursday, May 23rd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የእሳት ተራራው በተፋው እሳት በርካቶች ሞቱ

E-mail Print PDF
User Rating: / 2
PoorBest 

በኢንዶኔዢያ ‹‹የእሳት ተራራ›› (ማውንት ሜራፒ) በሚል ስያሜ ከሚጠራው ተራራ በተነሳ እሳተ ገሞራ ከ100 በላይ ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ቆሰሉ፡፡ አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው 750 ዲግሪ ሴልሺየስ በሚተፋው እሳተ ጐመራ የተጐዱ ሰዎች በርካታ በመሆናቸው የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ በድንገት የተነሳው እሳተ ገሞራ በርካታ ቤቶችን አፈራርሶና ከተገመተው በላይ ተስፋፍቶ በመቀጠሉ፣ ከተራራው በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው የብሮንጋንግ መንደር ሳይቀር በርካታ ወታደሮችና ነዋሪዎች በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ አስገድዷል፡፡ አንድ የኢንዶኔዢያ የእሳተ ገሞራ ባለሙያ ለዜና አውታሩ እንዳስረዱት፣ የማውንት ሜራፒ የአደጋ ክልል 20 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ በዚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ማናቸውም ነገሮች የአደጋው ሰለባ እንደሚሆኑም አስጠንቀቀዋል፡፡ ባለፈው ወር መፈንዳት የጀመረው ይህ እሳተ ገሞራ ባለፈው ዓርብ ከነበረው መጠን ጋር ሲነጻጸር በስድስት እጥፍ መጨመሩንና በአቅራቢያው የነበሩ በርካታ ሕፃናትና ሴቶችን በከባድ ተሽከርካሪዎች ለማሸሽ የተሞከረ ሲሆን፣ ፍንዳታው በፈጠረው የአቧራ ጭጋግ ከተሸፈነችው ብሮንጋንግ መንደር 80 ቤተሰቦችን ለማሸሽ ተችሏል፡፡ የእሳት ተራራው ለበርካታ ጊዜያት በተደጋጋሚ በመፈንዳቱ የሚታወስ መሆኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡

*******************************
የዚምባቡዌ የአልማዝ ማዕድን ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
የዚምባቡዌ ፖሊስ የሁለት የአልማዝ ማዕድን አውጪ ኩባንያ ስድስት ኃላፊዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ኃላፊዎቹ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኘው ማራንጅ በተባለው አካባቢ ማዕድን ለማውጣት የሚያስችላቸውን ፈቃድ በተጭበረበረ ሁኔታ ለማግኘት በመሞከራቸው ነው፡፡ አካባቢው በመብት ጉዳዮችና በታጣቂዎች ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ያልተረጋጋ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡ መርማሪዎች አካባቢው ደም አፋሳሽ መሆኑን በማረጋገጣቸው ከቦታው የሚወጣ አልማዝ ለገበያ እንዳይቀርብ እገዳ ተጥሎበት እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡ የዚምባቡዌ ማይኒንግ ዴቨሎፕመንት ኮርፖሬሽንና ዚምባቡዌና ደቡብ አፍሪካ በጣምራ የያዙት ካናዳይል ማይነርስ የተባሉት ኩባንያዎች ኃላፊዎች ለፈጸሙት ወንጀል፣ ከበድ ያለ ቅጣት ሊጠብቃቸው እንደሚችል ዘገባው አክሎ አመልክቷል፡፡

*******************************
በፓኪስታን መስጊድ አጥፍቶ ጠፊዎች ባደረሱት ጥቃት 40 ሰዎች ተገደሉ
በሰሜን ምዕራብ ፓኪስታን በሚገኝ አንድ መስጊድ ላይ አጥፍቶ ጠፊዎች ባደረሱት የቦምብ አደጋ ከ40 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ70 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡ አደጋው የደረሰው ዓርብ ዕለት ምዕመናኑ ጸሎት አድርገው በመውጣት ላይ እንዳሉ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ጥቃቱ ያነጣጠረው የአካባቢው ነዋሪዎች የታሊባንን ዕርምጃ እንዲቃወሙ በሚመክሩ የጐሳ መሪ ላይ ሳይሆን እንዳልቀረ ያመለከተው ዘገባው፣ መሪው የጥቃቱ ሰለባ ስለመሆናቸው ግን ይፋ የወጣ ነገር አለመኖሩን ዘገባው አመልክቷል፡፡  

*******************************
በኩባ 68 ሰዎችን ያሳፈረ አውሮፕላን ተከሰከሰ
ንብረትነቱ የኩባ አየር መንገድ የሆነው አውሮፕላን ባለፈው ሐሙስ ሌሊት ተከሰከሰ፡፡ በውስጡ ካሳፈራቸው 68 ሰዎች በሕይወት የተረፈ ሰው ለጊዜው አለመገኘቱን ዴይሊ ቴሌግራፍ የኩባ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ አውሮፕላኑ ሳንቲያጐ ደኩባ ከተባለው ቦታ ተነስቶ ወደ ዋና ከተማዋ ሀቫና በመጓዝ ላይ ሳለ መከስከሱን የዘገበው የዜና አውታሩ፣ አውሮፕላኑ የካናዳ ዜጐችን አሳፍሮ ይጓዝ እንደነበር ለማጣራት ሙከራ እየተደረገ መሆኑን፣ በኩባ የካናዳ ልዑካን ጋር የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በጋራ እየሠራ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡