በሩብ የበጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ ርዕሶች ከ10.9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ማስታወቁን ዋልታ ዘገበ፡፡
ባለሥልጣኑ ገቢውን የሰበሰበው ከውጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ፣ ከአገር ውስጥ ገቢና ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የተጣራ ገቢ ነው፡፡ ከገቢው 5.7 ቢሊዮን ብር ከወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ መገኘቱንና ይህም ከሌሎች ገቢዎች የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱ ተገልጾ፤ ከአገር ውስጥ ገቢ የተሰበሰበው 5.1 ቢሊዮን ብርም ቀጣዩን ስፍራ መያዙ ተመልክቷል፡፡ የሩብ የበጀት ዓመቱ ዕቅድ 12 ቢሊዮን 17 ሚሊዮን ብር እንደነበር ያመለከተው ዘገባው፣ የዕቅዱን 91 በመቶ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ገቢው ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ3 ቢሊዮን 669 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተመልክቶ፣ በተያዘው የበጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ ርዕሶች 54.1 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን ዘገባው አስታውቋል፡፡
*******************************
የሰላምና የምክክር ጉባዔ መዋቅሩን በክልልና በዞን ሊዘረጋ ነው
የኢትዮጵያ የሃይማኖትና የእምነት ተቋማት የሰላምና የምክክር የጋራ ጉባዔ መዋቅሩን በክልልና በዞን እንደሚዘረጋ ኢዜአ ዘገበ፡፡ ጉባዔውን የመሠረቱት አምስቱ የእምነትና የሃይማኖት ተቋማት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያን ኅብረት፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችና በኢትዮጵያ የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ የሃይማኖት መሪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት የጉባዔው መዋቅር ወደ ሕዝቡ እንዲወርድና ጉባዔው በየክልሉና በየዞኑ እንዲቋቋም አሳስበዋል፡፡ በጉባዔው ላይ ከየክልሉና ከየዞኑ የተወከሉ የእምነትና የሃይማኖት ተቋማት ተጠሪዎችን ጨምሮ በሰላም ላይ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳታፊ መሆናቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
*******************************
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ጉባዔ የሥራ ኃላፊዎችን ሹመት አፀደቀ
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ባለፈው ዓርብ ባካሄደው መሥራች ጉባዔ አዲስ ከንቲባን ጨምሮ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎችን ምርጫና ሹመት ማፅደቁን ኢዜአ ዘገበ፡፡ ጉባዔው በገዥው ፓርቲ በደኢሕዴን የቀረቡትን አቶ ዘላለም ላሌን ዋና አፈ ጉባዔ፣ ወ/ሮ ገነት ጋቢሶን ደግሞ ምክትል አፈ ጉባዔ አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡ እንዲሀም በቅርቡ የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው በተሾሙት የቀድሞው ከንቲባ ምትክ አቶ ሽብቁ መገኔ አዲስ ከንቲባ ሆነው እንዲሠሩ ጉባዔው በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡ ለከተማዋ በምክትል ከንቲባነትና በንግድ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊነት እንዲሠሩ አቶ ከበደ ካያሞን መርጧቸዋል፡፡ ጉባዔው በተጨማሪም አዳዲሶችን ጨምሮ የስምንት ካቢኔዎችንና የተለያዩ መምሪያ ኃላፊዎችን ሹመት ሲያፀድቅ የስያሜ ለውጥና የተዋሃዱ መምሪያዎችን አደረጃጀትም ይፋ ማድረጉን ዘገባው አመልክቷል፡፡
*******************************
በአዳማ በኩል ከ35 ሺሕ ቶን በላይ የግብርና ምርት ለውጭ ገበያ ተላከ
በአዳማ በኩል በያዝነው የመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት ከ35 ሺሕ ቶን በላይ ጥራቱ የተጠበቀ የግብርና ምርት ለውጭ ገበያ መላኩን በግብርና ሚኒስትር የአዳማ እጽዋት ኳራንቲን ጽሕፈት ቤት መግለጹን ኢዜአ ዘገበ፡፡ ከተላከው ምርት መካከል ጥራጥሬና የቅባት እህል፣ ቅመማ ቅመም፣ አትክልትና ፍራፍሬና ሌሎችም ሰብሎች ይገኙባቸዋል፡፡ ለውጭ ገበያ የተላከው ምርት ከእቅዱ በ130 ሺሕ ኩንታል፣ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ደግሞ በ90 ሺሕ ኩንታል ብልጫ ማሳየቱ ተገልጾ፣ ምርቱ ዕድገት ያሳየው ለኢትዮጵያ ምርት የሚቀርበው የገበያ ጥያቄ እየጨመረ በመምጣቱ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ምርቱ የተላከው ወደ አውሮፓ፣ እስያ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ጂቡቲና ኬንያ እንደሆነም ዘገባው አክሎ ገልጿል፡፡


