የኩባው ፕሬዚዳንት ራኦል ካስትሮ ከ14 ዓመት በኋላ የመጀመሪያውን የገዢውን ኮሚዩኒስት ፓርቲ ኮንግረንስ መጥራታቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡
የፓርቲው ኮንግረንስ በየአምስት ዓመቱ ስብሰባ ማድረግ የነበረበት ቢሆንም፣ ሁሌም ጊዜው ሲደርስ ስለሚራዘም የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ሆኗል፡፡ ይህ የፓርቲ ስብሰባ የሚያተኩረው የኢኮኖሚውን ችግር በመፍታት ዙሪያ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ መሠረታዊ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ዙሪያና በፓርቲያው ፖሊሲ ዙሪያ እንደሚሆን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም የኩባ ሕዝብ ለዚሁ ጉባዔ ዝግጅት እንዲያደርግ ፕሬዚዳንቱ ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ ማስተላለፋቸውን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡
* * * *
የማይናማር ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለስ ጀመሩ
በአገሪቱ መንግሥትና በታጣቂዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት አገራቸውን ለቀው ወደ ታይላንድ ተሰድደው የነበሩ ማይናማራውያን (በርማውያን) በፈቃደኝነት ወደ አገራቸው በመመለስ ላይ መሆናቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ ቁጥራቸው ከ20 ሺሕ በላይ የሆኑት እነዚሁ ስደተኞች በመመለስ ላይ ያሉት በሁለቱ ቡድኖች መካከል የሚደረገው ጦርነት በመቀዛቀዝ ላይ በመሆኑ እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል፡፡ ግጭቱ ተፈጥሮ የነበረው በቅርቡ በአገሪቱ በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ወቅት ገዢው ፓርቲ ሁሉም ሕዝብ እንዲመርጥ በማስገደዱና ዲኬቢኤ የተባለው አማጺ ቡድን ደግሞ መንግሥት በዜጎች ላይ እየወሰደው ያለው ዕርምጃ ተገቢ አይደለም በማለት በተፈጠረ ግጭት ነው፡፡ የአገሪቱ ዜጎች በአሁኑ ወቅት ለሁለት የተከፈሉ ሲሆን፣ እነሱም ወታደራዊውን መንግሥት የሚደግፉና የተቃዋሚዎች ደጋፊዎች እንደሆኑ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
* * * *
ተመድ ሰላም ለማስፈን የ29 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አገኘ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከግዞትና ከጦርነት ተላቅቀው ሰላምን የማስፈን ጥረት ለሚያደርጉ አገሮች ድጋፍ የሚሆን የ29 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ቃል የተገባለት መሆኑ ተገለጸ፡፡ በርካታ የድርጅቱ አባል አገሮች ድጋፉን ለማድረግ ቃል የገቡት ሰላም የማስከበር ባለድርሻ አካላት ባለፈው ሳምንት ኒውዮርክ ውስጥ ባካሄዱት ስብሰባ ላይ መሆኑን የተለያዩ የዜና አውታሮች በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡ ተቋሙ እስካሁን ድረስ በ18 አገሮች ውስጥ በ15 ድርጅቶች አማካይነት ለሚካሄዱ 150 ፕሮጀክቶች ድጋፍ በመስጠት ላይ ሲሆን፣ ወደፊትም ይህን ድጋፍ ለሃያ አገሮች የማዳረስ ዓላማ እንዳለው ተገልጿል፡፡
* * * *
በሃይቲ ዋና ከተማ ኮሌራ መግባቱ ተረጋገጠ
በሃይቲ ዋና ከተማ ፖርቶ ፕሪንስ በ120 ሰዎች ላይ በተደረገ ምርመራ ኮሌራ መግባቱ መረጋገጡን የአገሪቱ የጤና ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ ይኸው ውኃ ወለድ በሽታ ከአገሪቱ 10 ክልሎች ግማሽ ያህሉን ሲያጠቃ፣ የተጨናነቀ ሕዝብ በሚኖርባት ዋና ከተማዋ ፖርቶ ፕሪንስ እንዳይዘመት ተፈርቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ እንደ አገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ በአገሪቱ በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የ554 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ከስምንት ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በሕክምና ተቋማት ውስጥ ክትትል በማድረግ ላይ ናቸው፡፡


