የደቡብ ኮሪያ የጦር መርከብ ከዓሣ አጥማጅ መርከብ ጋር ተጋጭታ በመስጠሟ አንድ ሰው ሲሞት ሁለት ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም፡፡
እንደ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ 150 ቶን ክብደት ያላት የጦር መርከብ በአካባቢው ቅኝት አድርጋ ስትመለስ 270 ቶን ክብደት ካላት የዓሣ አጥማጅ መርከብ ጋር ተጋጭታ ልትሰጥም ችላለች፡፡ በአደጋው በመርከቧ ውስጥ ከነበሩት 31 ሰዎች መካከል የተረፉት 28 ሰዎች በአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ጥረት በሰላም ሊወጡ ችለዋል፡፡ የጦር መርከቦችና ሔሊኮፕተሮች ግጭቱ በደረሰበት ስፍራ የጠፉትን ሁለት ሰዎች በመፈለግ ላይ መሆናቸውን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል፡፡
******************************************
እንግሊዝ በአደንዛዥ ዕፅ መናኸሪያነት ቀዳሚ እንደሆነች ተገለጸ
በቅርቡ የወጣ አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት እንዳመለከተው እንግሊዝ በቅርብ ጊዜ የዓለማችን የአደገኛ ዕፅ ዋና መናኸሪያ ልትሆን ትችላለች፡፡ በአሁኑ ጊዜም ከአውሮፓ ቀዳሚዋ አገር እንደሆነች ተገልጿል፡፡ ዘ ኢኮኖሚክ ታይምስ ጥናቱን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በአምስት ዓመት ውስጥ ብቻ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶች ቁጥር ሃምሳ በመቶ ጨምሯል፡፡ በእንግሊዝ አደገኛ ዕፅ ተጠቃሚ የሆኑ ታዳጊዎችና ጐልማሶች ብቅ ማለት የጀመሩት እ.ኤ.አ. ከ1990 ጀምሮ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ አንድ ጥቅል ዕፅ ከሁለት ፓውንድ ባልበለጠ ዋጋ መሸጡ ደግሞ የተጠቀሰውን የተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ አድርጐታል፡፡ ይኼው የአውሮፓ ኅብረት የአደገኛ ዕፅ ቁጥጥር ኤጀንሲ ጥናት እንዳመለከተው፣ እንግሊዝ ካናቢስ፣ ኤክስታሲና አምፌታሚን በተባሉት ዕፆች ተጠቃሚዎች ቁጥር ብዛት ከአውሮፓ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛለች፡፡
******************************************
በሱዳን የአውሮፕላን አደጋ አንድ ሰው ሞተ
በሱዳን አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን ላይ በደረሰ አደጋ አንዲት ሴት ስትሞት፣ በስድስቱ ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ መድረሱን የሂንዱ ታይምስ ዘገባ አመልክቷል፡፡ የአውሮፕላኑን ሠራተኞች ጨምሮ 36 ሰዎችን ጭኖ የነበረው አንቶኖቭ 26 የተባለው አውሮፕላን ከምዕራብ ዳርፉር ወደ ዛሊንጌ ከተማ የአገር ውስጥ በረራ በማድረግ ላይ ነበር፡፡ አደጋው ሊደርስ የቻለው የአውሮፕላኑ የኋላ ጐማ ፈንድቶ በእሳት በመቀጣጠሉ እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል፡፡ ከመንገደኞቹ መካከል አራት ሕፃናት ይገኙበት እንደበር ዘገባው ሲያመለክት፣ የአውሮፕላን ማረፊያው አሸዋማ በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱን አውሮፕላን ለማሳረፍ እንደማይችል ሌሎች ዘገባዎች አስታውቀዋል፡፡
******************************************
በኢንዶኔዥያ ተቋርጦ የነበረው የበረራ አገልግሎት ተጀመረ
በኢንዶኔዥያ ባለፈው ሳምንት በፈነዳው እሳተ ገሞራ የተነሳ በተፈጠረው የብናኝ አመድ ደመና ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የአየር በረራ አገልግሎት መጀመሩን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ባለፈው ሳምንት 191 ሰዎችን ለሞት የዳረገው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ብናኝ አመድ ምክንያት ሊቋረጥ የቻለው ዓለም አቀፍ በረራ ቢጀምርም፣ አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ግን ተገልጿል፡፡ በጃቫ ደሴት ውስጥ በሜራፒ ተራራ ላይ ሳይታሰብ የፈነዳው እሳተ ገሞራ ስድስት ኪሎ ሜትር ያህል ከፍታ ብናኝ አመድ በማስነሳቱ እስከ አሁን እንዳልተቋረጠ ዘገባው ጠቁሞ፣ ነገር ግን ብናኙ ለበረራ ስጋት እንደማይፈጥር ጠቁሟል፡፡ በአደጋው ምክንያት በአካባቢው የሚኖሩ ከ350 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ዘገባው አክሎ አመልክቷል፡፡


