የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በአርሶ አደር ደረጃ በተበጣጠሰ መሬት ላይ የሚሠሩ አነስተኛ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ትራንክተሮችን በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያመርት መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በኮርፖሬሽኑ ሥር በተደራጁ ፋብሪካዎች በአርሶ አደር ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡ አነስተኛ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ትራክተሮች በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማሰራጨት መታቀዱን የጠቆመው ዘገባው፣ ኮርፖሬሽኑ ሙሉ በሙሉ ትራክተር ማምረት ወደሚችልበት ደረጃ ላይ ለማሸጋገር የአቅም ግንባታ ሥራ በማካሄድ ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡
* * * * *
በጎርፍ ለተጎዱ መንገዶች ጥገና 14 ሚሊዮን ብር በጀት ተያዘ
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ባለፈው ክረምት ወቅት በጎርፍ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው 25 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው መንገዶች ላይ በ14 ሚሊዮን ብር የተጠናከረ የአስፓልት ጥገና በማካሄድ ላይ መሆኑን አዲስ ዘመን ዘግቧል፡፡ የተጎዱትን መንገዶች በአስፓልት ለመሸፈንና ተጓዳኝ ሥራዎችን ለማከናወን 41.6 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 14 ሚሊዮን ብሩ ለተበላሹት መንገዶች ጥገና እንደሚውል ተገልጿል፡፡ የመንገዶቹ ጥገና ባለፈው መስከረም አጋማሽ ላይ መጀመሩንና በመጪው ታህሳስ ወር መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ ዘገባው አክሎ አመልክቷል፡፡
* * * * *
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሳምንት መከበር ጀመረ
የኢትዮጵያ አገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና ናሽናል አሶሴሽን ኦፍ ኢትዮጵያን ኢንዱስትሪስ በጋራ ያዘጋጁት 10ኛው የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሳምንት፣ ከህዳር አራት ጀምሮ ‹‹ለኢንዱስትሪ ዕድገት እንተጋለን›› በሚል መሪ ቃል መከበር መጀመሩን የአዲስ ዘመን ዘገባ አመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሳምንት መከበር ዋና ዓላማው በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዕድገት ላይ ባለኢንዱስትሪው፣ መንግሥት፣ ኅብረተሰቡና የሚመለከታቸው ሁሉ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ መሆኑ ተገልጾ፣ በተጨማሪም በአፍሪካ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ውስጥ አገሪቱ ሊኖራት የሚገባውን ደረጃ አጉልቶ ለማሳየት በብዙ መንገድ እንደሚረዳ ተገልጿል፡፡ የበዓሉ አከባበር እስከ ህዳር 11 ቀን 2003 ዓ.ም. እንደሚቆይ ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡
* * * * *
የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመረቀ
ቀደም ሲል በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ሥር ለ12 ዓመታት ሲተዳደር የቆየው የምህንድስና ኮሌጅ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሆኖ ራሱን ችሎ በማደራጀት መመረቁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከጀርመን መንግሥት ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቁ ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽ በምርምር ጥናት የተመሰረተ ሲሆን፣ ተግባርን ከቀለም ትምህርት ጋር በማዛመድ ሥልጠና የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ኢንስትቱዩቱ በቀን፣ በማታና በክረምት የትምህርት ክፍለ ጊዜያት ከ5500 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያሠለጥን ተጠቁሟል፡፡
* * * * *
በአዲስ አበባ 229 ሔክታር መሬት መልሶ እንደሚለማ ተገለጸ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 229 ሔክታር መሬት ለመልሶ ማልማት እንደሚውል አዲስ ልሳን ዘግቧል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት በባሻ ወልዴ፣ በአፍሪካ ኅብረት፣ በሸራተን፣ በመስቀል አደባባይ መግቢያና በወሎ ሰፈር አካባቢዎች የመልሶ ማልማት ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ ነባሮቹን ማረፊያዎች መልሶ መጠቀም እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለዘላቂ ማረፊያነት በአቃቂ ክፍለ ከተማ 14 ሔክታር መሬት የሚለማ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡


