Saturday, May 25th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የናይጄሪያ ወታደሮች ታጋቾችን አስለቀቁ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

የናይጄሪያ ወታደራዊ ኃይሎች በዚህ ወር ብቻ በኒጀር ዴልታ ታጣቂዎች ታግተው የነበሩ 19 ታጋቾችን ማስለቀቃቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ፡፡ ከታጋቾቹ ውስጥ 12 የሚሆኑት ናይጄሪያውያን ሲሆኑ ሁለቱ አሜሪካውያን፣ ሁለቱ ፈረንሳውያን፣ ሁለቱ ኢንዶኔዥያውያንና አንድ ካናዳዊ ነበሩ፡፡ የናይጄሪያ ባለሥልጣናት እንደገለጹት ታጋቾቹን የማስለቀቅ ጥረቱ የተካሄደው የምድር፣ የአየርና የባሕር ኃይልን በመጠቀም ነው፡፡ ታጋቾቹን የማስለቀቁ ጥረት ውጤታማ መሆኑን የገለጸው ቢቢሲ፣ በኒጀር ዴልታ ታጣቂዎች ከዚህ በፊት ይታገቱ የነበሩ ታጋቾች ጥቃት ይደርስባቸው እንደነበሩ አስታውሷል፡፡



ታንዛኒያዊው የጓንታናሞ እስረኛ ከተከሰሰባቸው ወንጀሎች በአንዱ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኘ

የመጀመሪያው የጓንታናሞ እስር ቤት እስረኛ የነበረው ታንዛንያዊው አህመድ ጋይላኒ ከተከሰሰባቸው 286 የሽብር ጥቃት ወንጀሎች ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1998 በኬንያና በታንዛኒያ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ፡፡ የ36 ዓመቱ አህመድ ጋይላኒ የቦምብ ጥቃት በመፈጸም የአሜሪካ ንብረትን በማውደም ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህ ወደል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው ጋይላኒ በግድያና በግድያ ሙከራ ወንጀል በርካታ የወንጀል ክሶች ተመስርተውበት ነበር፡፡ ጋይላኒ ጥፋተኛ ሆኖ በተገኘበት ወንጀል ቢያንስ 20 ዓመታት የእስር ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ በታንዛንያና በኬንያ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ከ12 ዓመታት በፊት በአሸባሪዎች በደረሰው ጥቃት 224 ሰዎች መሞታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ጋይላኒ በድርጊቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንደነበር ተጠቁሞ ጥቃቱ የአልቃይዳ ቀዳሚ ጥቃቶች ከሆኑት ውስጥ አንዱ ነው ተብሏል፡፡


ፕሬዚዳንቱ በታሪቅ አዚዝ የሞት ቅጣት ውሳኔ ላይ እንደማይፈርሙ ገለጹ

በቀድሞው የኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ታሪቅ ኢዚዝ ላይ የተላለፈው የሞት ቅጣት ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲሆን ፊርማቸውን ማኖር የሚጠበቅባቸው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጀላል ታሊባኒ፣ ፊርማቸውን እንደማያኖሩ መግለጻቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ፡፡ የ74 ዓመቱ የቀድሞ የኢራቅ ከፍተኛ ባለሥልጣን ታሪቅ አዚዝ በዘመነ ሥልጣናቸው ለሠሩት ጥፋት ባለፈው ወር የኢራቅ ፍርድ ቤት በሞት እንዲቀጡ ውሳኔ ያስተላለፈ መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው ለውሳኔው ተፈጻሚነት የፕሬዚዳንቱ ፊርማ ቢጠበቅም ፕሬዚዳንቱ ለመፈረም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ዕድሜያቸው የገፋ መሆኑንና የኢራቅ ክርስቲያን በመሆናቸው ምክንያት ተፈጻሚነት ተባባሪ የመሆን ፍላጐት እንደሌላቸው አብራርተዋል፡፡ የሞት ቅጣት በማንም ላይ መፈጸም የለበትም የሚል አቋም ያላቸው ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚህ ቀደም የሞት ቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን በሞት እንዲቀጡ ፊርማቸውን ለማኖር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በመግለጻቸው፣ በምክትላቸው አማካይነት በተፈረመ ፊርማ ውሳኔው ተፈጻሚ ሊሆን መቻሉን ዘገባው አስታውሷል፡፡


በኒውዚላንድ ማዕድን ማውጫ የፍንዳታ አደጋ ደረሰ

በኒውዚላንድ አንድ ትልቅ የከሰል ማዕድን ማውጫ ላይ በደረሰ የፍንዳታ አደጋ 30 ሰዎች መሬት ውስጥ የተቀበሩ ሲሆን፣ ከ25 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የገቡበት አለመታወቁን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ አንድ የአገሪቱ ፖሊስ እንደገለጸው፣ በስፍራው አደጋው ከመከሰቱ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት መብራት ተቋርጦ ስለነበር እንደ አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሎ ተገምቷል፡፡ አታራው በተባለች ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውና በተራሮች በተከበበው የማዕድን ማውጫ ውስጥ የተረፉ ሰዎች ካሉ ለማዳን የነፍስ አድንና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በመረባረብ ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ እስካሁን በተደረገው ጥረትም አምስት ሰዎችን ከተቀበሩበት ማውጣት መቻሉን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡