Thursday, Jun 20th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የአሳማ ጉንፋን በ160 ሃገራት ተሰራጭቷል

E-mail Print PDF
User Rating: / 34
PoorBest 

የአሳማ ጉንፋን ቫይረስ በ160 ሃገራት እንደተሰራጨና በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ያህል ሰዎች በበሽታው ሊያዙ እንደሚችሉ የዓለም ጤና ድርጅት ሰሞኑን አስታወቀ፡፡ ይህም የዓለምን የሕዝብ ቁጥር አንድ ሦስተኛ ማለት ነው፡፡
ከይጄ ፍኩዳ የተባሉ የድርጅቱ አንድ ባለሥልጣን እንዳሉት ቫይረሱ ከአሳማ ወደ ሰው፣ እንዲሁም ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ ከጀመረ በኋላ 800 ያህል ሰዎችን ገድሏል፡፡ ይህም በላብራቶሪ የተረጋገጠው ቁጥር ብቻ ስለሆነ የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ኩፍዳ ገልፀዋል፡፡

የመድሃነት አምራቾች የሃ1ሐ1 በመባል የሚታወቀውን የአሳማ ጉንፋን ለመከላከል የሚረዳ ክትባት እየሰሩ ሲሆን ሂደቱን እንዴት ማፍጠን እንደሚችሉ ጥናት እያደረጉ መሆናቸውን አሰታውቀዋል፡፡ ክትባቱ የሚደርስበት ጊዜ ቢዘገይም ውጤታማነቱ ግን የማያጠራጥር እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

ፈጣን ድረ ገፅ ለምሥራቅ አፍሪካ

በምሥራቅ አፍሪካ ድረ ገፆችን ፈጣን የሚያደርግ አዲስ ኬብል ሊዘረጋ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአፍሪካ በባህር ስር የሚቀበረው አዲሱ ኬብል የምሥራቅ አፍሪካ ነዋሪዎች ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡

የፋይበር ኦፕቲክ ኬብሉ የሚሰራው የአፍሪካ ካምፓኒ በሆነው ሲኮም ሲሆን ደቡብ አፍሪካን፣ ታንዛኒያን፣ ኬንያን፣ ኡጋንዳን፣ ሞዛምቢክን፣ አውሮፓንና እስያን እንደሚያገናኝ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

እንደ ሲኮም አባባል የኬብሉ መዘርጋት የምሥራቅ አፍሪካን ኢንዱስትሪና የንግድ ግንኙነት እንደሚያስፋፋ ይረዳል፡፡

ኬብሉ 17 ሺህ ኪ.ሜ የሚሸፍን ሲሆን የዝርጋታ ሥራውን ለመጨረስ ሁለት ዓመት ይፈጃል፡፡ 650 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያስወጣም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የኬብሉ መዘርጋት ይፋ በሆነበት ወቅት "በአፍሪካና በሌላው ዓለም መካከል አዲስ የተግባቦት ክፍለ ዘመን ሊፈጠር ነው" ሲል ሲኮም ገል"ል፡፡

ድሆች ለስኳር በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው

በእንግሊዝ በድህነት የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለስኳር የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ አንድ ጥናትን ጠቅሶ ኤም ኤስ ኤን ቢሲ ድረ ገፅ ዘግቧል፡፡ እንደ ጥናቱ ከሆነ በድህነት የሚኖሩት በሚመገቧቸው የምግብ ዓይነቶች የተነሳ አብዛኞቹ ከልክ በላይ የመወፈር እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ከልክ በላይ መወፈር ደግሞ ለሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ያጋልጣል፡፡

ለስኳር ከሚያጋልጡ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ከልክ በላይ መወፈር፣ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና ሲጋራ ማጨስ ይጠቀሳሉ፡፡

ጥናቱ እንደሚያሳየው ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በእንግሊዝ የስኳር በሽተኞች ቁጥር 2.5 ሚሊዮን ይደርስ ነበር፡፡ ከመካከላቸው ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙትም የገቢ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑት ነበሩ፡፡ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑት ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ድረ ገፁ ዘግቦ አሁን ባለው ሁኔታ ግን በእንግሊዝ የስኳር በሽተኞች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ከአኗኗር ዘይቤ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አለው፡፡ "የመነሻ ምንጩ ቆሽት በቂ ኢንሱሊን ማመንጨት አለመቻሉ ወይንም የመነጨው ኢንሱሊን ተገቢውን ተግባር መፈፀም አለመቻሉ አይደለም፡፡ ይልቁንም በሰውነት የክብደት ሁኔታና በአመጋገብ የሚመጣ ነው"

ጥናቱ እንደሚጠቁመው በእንግሊዝ እቤታቸው የሚውሉና ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሴቶች ከሌሎቹ ይልቅ በስኳር በሽታ የመያዝ እድላቸው በአራት እጥፍ ከፍ ያለ ነው፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች ለስኳር በሽታ ከመጋለጣቸው በተጨማሪ በበሽታው ምክንያት ለሚከሰቱ ተጓዳኝ በሽታዎችም በብዛት የተጋለጡ እንደሆኑ ድረ ገፁ ጥናቱን በመጥቀስ አብራርቷል፡፡ ጥናቱ እንደሚጠቁመው የስኳር በሽታ ያለባቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች የጤና ክትትል የማድረግ እድላቸው አናሳ ነው፡፡ በመሆኑም ለልብ ህመም፣ ለምት (ስትሮክ"፣ ለኩላሊት ህመም፣ ለአይነ ስውርነትና ለሌሎም በሽታዎች እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል፡፡

የተጎዳ ልብን ለመጠገን አዲስ ዘዴ

የተጎዳ ልብ ለመጠገን አዲስ ዘዴ እንዳገኙ ሳይንቲስቶች አስታወቁ፡፡ ሳይንቲስቶቹ እንደሚሉት አንድ የልብ ሴል በበሽታ ምክንያት ከተጎዳ ራሱን መተካት ያቆማል፡፡ ይሁንና የአሜሪካ የሳይንቲስቶች ቡድን የተጎዳውን ሴል ለመተካት የሚያስችል አዳዲስና ጤነኛ ሴሎች የሚፈጠሩበትን ዘዴ እንዳገኙ ገልፀዋል፡፡

ሳይንቲስቶቹ እንደሚሉት በአይጦችና በድመቶች ላይ የተደረገው ጥናት በበሽታ የተጎዳ ልባቸውን ለመጠገን ኤን አር ጂ1 የተሰኘ ንጥረ ነገር በመስጠት የልብ ሴሎቻቸው አዳዲስ ሴሎችን እንዲተኩ ማድረግ መቻሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

እንደ ዘገባው ከሆነ ዘዴው ከዚሁ በፊት ልብን ለመጠገን የተሻለ ዘዴ ነው የሚባልለትንና በሰፊው ሙከራ ያልተደረገበትን የስቲም ሴል ህክምና (ስቲም ሴል ቴራፒ) የሚያስንቅ ነው፡፡ ተጓዳኝ ችግርም እንደማያስከትል ሳይንቲስቶች ገልፀዋል፡፡

ኤን አር ጂ1 የተሰኘው ንጥረ ነገር አዳዲስ ሴሎች እንዲፈጠሩ በማድረግ የተጎዳው የልብ ጡንቻ እንዲጠገንና አጠቃላዩ የልብ ክፍል ወደተፈጥሯዊ ሥራው እንዲመለስ ያደርጋል ያሉት ሳይንቲስቶች ንጥረ ነገሩን በመርፌ መልክ በወሰዱ አይጦችና ድመቶች መረጋገጡን አብራርተዋል፡፡