(በዮሴፍ ጌታቸው፣የሕግ ጥናት፣ ማርቀቅ፣ ትምህርት፣ ሥልጠና እና ምክር ባለሙያ)
የፍ/ሕ/ቁ 1 በአንደኛ መጽሐፍ ስለሰውና ስለሰዎች መብት በሚደነግገው ክፍል፤ ሰው ከተወለደበት ቀን አንስቶ እስከ እለተ ሞት ቀኑ ድረስ የሕግ መብት እንዳለው ያመለክታል፡፡
በሌላ ሁኔታም ቢሆን አንድ ሰው የጠፋና ከሁለት አመት ወዲህ ወሬውን ያልሰጠ እንደሆነ ማንኛውም ባለጉዳይ ቢሆን የሰውዬው መጥፋት በዳኞች እንዲነገርለት ለመጠየቅ እንደሚችል የፍ/ሕ/ቁ 154(1) ያስረዳል፡፡ በዳኞች የሚሰጠው የመጥፋት ውሣኔ የቀረቡት አስረጂዎች የጠፋው ሰው የሞተ ለመሆኑ እንደ እርግጠኛ አይነት ሆኖ ሊቆጠር የሚችል መሆኑ ሲረጋገጥ፤ ለመጥፋቱ ውሣኔ እንዲሰጥበት ጥያቄ የቀረበለት ፍርድ ቤት የጠፋውን ሰው የሞት ማስታወቂያ ፍርድ ለመስጠት እንደሚችል የፍ/ሕ/ቁ 161 ይገልጻል፡፡ እንግዲ ሰው ከዚህ አለም በአፀደ ስጋ በመለየቱ ወይም በፍርድ ቤት የመጥፋት ውሣኔ በመሰጠቱ ምክንያት የሟች ወይም በጠፋው ሰው መሞት የሚገኙ መብቶችና ግዴታዎች በሟች መሞት ምክንያት አብረው ቀሪ እስካልሆኑ ድረስ በሕግ ወይም በኑዛዜ በመብቶቻቸው ሊጠቀሙባቸው ለሚችሉ በሕይወት ወዳሉ ሰዎች የሚተላለፉ ይሆናሉ፡፡
በአጠቃላይ አገላለጽ ማንኛውም መብትና ግዴታ ለወራሾች ሊተላለፍ የሚችለው መብትና ግዴታዎቹ ተፈጥሮአዊ ያልሆኑና በሟች ሞት ምክንያት አብረው ቀሪ የማይሆኑ ሲሆኑ እንደሆነ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በቀላል ምሳሌ ለመግለጽ በፍ/ሕ/ቁ 828 መሠረት በሞት ምክንያት ለሟቹ ዘመዶች ወይም ባል ወይም ሚስት የሚሰጡ ጡረታዎች ወይም ካሳዎች የውርስ ሀብት ክፍል እንደማይሆኑ፤ በፍ/ሕ/ቁ 827 መሠረት ስለ ሕይወት የሚደረግ ኢንሹራንስ ሟቹ ተጠቃሚውን የወሰነ እንደሆነ ተጠቃሚነታቸው ከተወሰኑ ሰዎች ውጪና ሟቹ በፈረመው ስለ ሕይወት ኢንሹራንስ ውል ላይ ስማቸው ባይጠቀስም እንኳ በንግድ ሕግ ቁጥር 701(2) መሠረት ከባል ወይም ከሚስት ወይም ከልጆች በስተቀር ለሌሎች ሰዎች የሚከፈሉ ገንዘቦችን የውርስ ንብረት ክፍል እንዲሆን መጠየቅ እንደማይችሉ በምሳሌነት መመልከቱ ተገቢ ይሆናል፡፡
ከፍ/ሕ/ቁ 826(2) አጠቃላይ አነጋገር እንደምንረዳው በሟች መሞት ምክንያት የሚቀሩ ካልሆኑ በቀር የውርስ ሕግን በሚመለከቱ ደንቦች መሠረት በውርስ ውስጥ የሚገኙት የሟቹ መብቶችና ግዴታዎች ያለኑዛዜ ወራሾችና በኑዛዜ ወይም በከፊል ያለ ኑዛዜና በከፊል በኑዛዜ ወራሾች ለሆኑ ባለመብቶች ሊተላለፉ ይችላሉ፡፡ እነኚህን መብትና ግዴታዎች ወራሽ ሆኖ ለመቀበል በሕይወት ያለ መሆንና ለወራሽነት ያልተገባ አለመሆን አስፈላጊ ችሎታዎች እንደሆኑ ከፍ/ሕ/ቁ 830 እና ተከታዮቹ የሕግ ቁጥሮች መረዳት ይቻላል፡፡ በሕይወት ያለ መሆን ማለት ሟች በሞተበት ቀን ወራሽ የሚሆነው ሰው ምትክ ሆኖ መውረስን የተመለከቱ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው በሕይወት መኖር እንደሚጠበቅበት ሲያመለክት፤ በሌላ በኩል በሰዎች መካከል በጾታ፣ በእድሜና በዜግነት ልዩነት ሳይደረግ በወራሽነት መብቶች ለመስራት እንደሚቻል የፍ/ሕ/ቁ 837 ይደነግጋል፡፡ ለወራሽነት ያልተገባ አለመሆን ማለት ደግሞ በፍ/ሕ/ቁ 838 መሠረት ሟችን ወይም የሟችን ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጅ ወይም ወደላይ የሚቆጠሩ ወላጆች አንዱን ወይም የሟቹን ባል ወይም ሚስት አስቦ በመግደል የተፈረደበት አለመሆንና ተያያዥ የወንጀል ድርጊቶችን ፈጽሞ ቅጣት ያልተወሰነበትና ሌሎች ከኑዛዜ ጋር የተያያዙ ሟች ከመሞቱ በፊት በኑዛዜው እንዳይሰራ የማሰናከል ተግባር ያልፈጸመ ሊሆን ይገባል፡፡
ቀደም ሲል እንደተገለጸው የውርስ ሀብት በኑዛዜ ወይም ያለኑዛዜ ለወራሾች የሚተላለፍ ሆኖ፤ በፍ/ሕ/ቁ 826(1) መሠረት የሟች ዋናው መኖሪያው በሆነበት ቦታ ውርሱ የሚከፈት ይሆናል፡፡ ያለኑዛዜ የሚተላለፍ ውርስ በፍ/ሕ/ቁ 842(1) መሠረት የሟች ልጆች የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾች ሲሆኑ፤ ተወላጆች በሌሉ ጊዜ በተከታዮቹ የሕግ ቁጥሮች በተመለከተው የዝምድና ደረጃ መሠረት ተፈፃሚ የሚሆን ነው፡፡
ወራሽ ማንነው? የሟች ውርስ የት ይከፈታል? ወራሽ ለመሆኑ የሚያበቁ መብቶችና ገደቦች ምንድን ናቸው? የሚሉትን ነጥቦች በአጭር አገላለጽ ለግንዛቤ ያህል ካየን በኋላ እነኚህን የውርስ ንብረቶች ለመውረስና ግዴታዎችን ለመወጣት የውርስ ሀብት አጣሪ ምን ማድረግ እንደሚገባው/ት/ ቀጥሎ ለማየት እንሞክራለን፡፡
ሟች በሕይወት ዘመኑ ያፈራቸውንና በእሱ ባለቤትነት ስር የነበሩ ሀብትና ንብረቶችን በተገቢው ሁኔታ ጠብቆ ለወራሾች ለማስተላለፍ፣ እንዲሁም ሟች ግዴታውን ሳይወጣ ለገንዘብ ጠያቂዎች ገንዘባቸውን ሳይከፍል ያለፈ እንደሆነ ይህንኑ ዕዳ ለመክፈልና ባለዕዳዎችም የሚፈለግባቸውን ክፍያ በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል በፍ/ሕ/ቁ 946 እና ተከታዮች የሕግ ቁጥሮች መሠረት ያለ ኑዛዜ ወይም የኑዛዜ የሆነ ውርስ አጣሪ በሚባሉ በአንድ ወይም በብዙ ሰዎች እንደአግባቡ ውርስ የሚጣራ ይሆናል፡፡
በፍ/ሕ.ቁ 947 መሰረት ያለ ኑዛዜ ወራሽ የሆኑ ሰዎች ያለአንዳች ፎርማሊቲ በሕግ መሠረት የውርስ አጣሪነት መብት እንዳላቸው፣ በፍ/ሕ/ቁ 948(1) መሠረት ሟቹ አንድ ኑዛዜ የተወ እንደሆነ በዚሁ ኑዛዜ ውስጥ የኑዛዜው አስፈፃሚ እንዲሆን የመረጠው ሰው የአጣሪነት መብት እንዳለው እና በፍ/ሕ/ቁ 950(1) መሠረት ወራሾች የማይታወቁ የሆነ እንደሆነ ወይም ያለኑዛዜ ወራሽ የሚሆኑት ሰዎች ሁሉም ውርሱን ለማጣራት የማይፈቅዱ መሆናቸውን ገልጸው ያስታወቁ እንደሆነ፣ ማናቸውም ባለጉዳይ በሚያቀርበው ጥያቄ መሰረት ዳኞች አንድ አጣሪ ሊሾሙ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡
በሌላ በኩል በፍ/ሕ/ቁ 852 መሠረት ሟች ዘመዶች የሌሉት እንደሆነ እና በፍ/ሕ/ቁ 950(2) መሠረት ተናዛዡ ወራሾች ያልተወና ውርሱም መንግስት የሚወርሰው የሆነ እንደሆነ፣ ዳኞች አንድ አጣሪ የመሾምና በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ በፍ/ሕ/ቁ 951 መሠረት ከማናቸውም ባለጉዳይ በሚቀርብ ጥያቄ መሠረት የተመረጡ አጣሪዎችን ለመተካት አንድ ውል ለመዋዋል ስልጣን የተሰጠውን ሰው ወይም ማናቸውንም ሌላ ሰው ዳኞች ለመምረጥ እንደሚችሉ ሕጉ ሰፊ ሥልጣን ይሰጣል፡፡
ሟች በሕይወት ዘመኑ ያፈራው ሀብትና ንብረት መብት ላለው/ት/ ወራሽ ከመተላለፉ በፊት ሀብትና ንብረቱ ተጠብቆ ለወራሾች ለማስተላለፍ እንዲቻል የውርስ ሀብት አጣሪ ማን ነዉ? የሚለው ከተለየ በኋላ አጣሪው ስለሚፈጽመው ሥራ ከውርስ ሕጉ አንፃር ማየቱ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ የሚሰጠንን አግባብነት ያለውን የፍ/ሕ/ቁ 944 መመልከቱ ተገቢነት አለው፡፡ አጣሪው የማጣራቱን ስራ ሲያከናውን የሚከተሉትን፡-
ሀ. የውርሱ ተቀባይ እነማን እንደሆኑ መወሰንን፣
ለ. የውርሱ ሀብት ምን መሆኑን መወሰን፣
ሐ. ለውርሱ የሚከፈለውን ገንዘብ መቀበል፣ ለመክፈል አስገዳጅ የሆነ እዳን
መክፈል እና
መ. ሟቹ በኑዛዜው ስጦታ ላደረገላቸው ሰዎች የሰጣቸውን ውርስ መክፈል እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ስለ ውርስ አስተዳደር የሚደነግገው የፍ/ሕ/ቁ 1003 እና ተከታዮቹ የሕግ ቁጥሮችም አጣሪው ከተመረጠበት ቀን ጀምሮ የወራሽነት ባለመብት የሆኑ ሰዎች ድርሻቸውን ወይም የሚደርሷቸውን ንብረቶች እስከሚቀበሉ ድረስ የሟች ንብረቶችን እንደ መልካም የቤተሰብ አስተዳዳሪ ሆኖ ማስተዳደር እንዳለበት ያመለክታል፡፡
የውርስ አጣሪው እነኚህን ሥራዎች በፍ/ሕ/ቁ 956 መሰረት ካከናወነ በኋላ የሥራውን ክንውን ጉዳይ የሚያመለክት ሪፖርት ለወራሾችና ለፍ/ቤት ማቅረብ እንዳለበት የፍ/ሕ/ቁ 960 ይደነግጋል፡፡ ሆኖም የውርስ አጣሪው በወራሾች መካከል ክርክር ቢነሳ አግባብነት ያላቸውን ማስረጃዎች በማጠናቀር ሪፖርት ከማቅረብ በዘለለ ሁኔታ በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ የውርስ አጣሪው መርምሮ በፍርድ የመወሰን ሥልጣን የለውም፡፡ ምክንያቱም በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 37(1) መሰረት ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሣኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት ያለው በመሆኑ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79(1) መሠረት በፌዴራልም ሆነ በክልል የዳኝነት ስልጣን የተሰጣቸው ለፍርድ ቤቶች ብቻ በመሆኑ የውርስ አጣሪው በወራሾች መካከል የሚቀረቡትን ክርክሮች ለፍርድ ሰጪው አካል ሪፖርት ከማቅረብ ውጪ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ሀብት የእገሌ ነው ወይም አይደለም በማለት ፍርድ ለመስጠት እንደማይችል በሕጉ ተመልክቷል፤ ሆኖም በልማድ እነዚህ ስራዎች በሰፊው እየተሰራባቸው እንደሆነ ይታያል፡፡ በመሆኑም የልምድ አሰራሩ የሕግ መሠረት የሌለውና ለሕግ ተቃራኒ የሆነ ስራ በመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መ/ቁ/23322 ሰኔ 19 ቀን 2000 ዓ/ም የሰጠው ፍርድ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን እንደገና ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(1) መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ሊከተሉት እንደሚገባ ስለሚደነግግ የተሰጠው ፍርድ ከተያዘው ጉዳይ ጋር አግባብነት ያለው በመሆኑ ለግንዛቤ እንዲረዳ ሙሉ ውሳኔው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የሰ/መ/ቁ. 23322
ሰኔ 19 ቀን 2000 ዓ/ም
ዳኞች፡- አቶ አብዱልቃድር መሐመድ
አቶ ታፈሰ ይርጋ
አቶ መድሕን ኪሮስ
አቶ አሊ መሐመድ
አቶ ሱልጣን አባተማም
አመልካች፡- ወ/ሮ አዳነች ወርዶፋ ቀረቡ
ተጠሪዎች፡- እነ ወ/ሮ አስናቀች ወርዶፋ ቀረቡ
መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡
ፍ ር ድ
ጉዳዩ የተጀመረው በፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ሲሆን፣ አመጣጡም የአሁንዋ አመልካች ህዳር 10 ቀን 1997 ዓ/ም ጽፈው ባቀረቡት ማመልከቻ የውርስ አጣሪው በ16/2/97 ዓ/ም ያቀረቡት ሪፖርት በአግባቡ የቀረበ አይደለም፡፡ አጣሪው ሊጸድቅ የማይገባውን የስጦታ ውል መነሻ በማድረግ ውሣኔ ሰጥተዋል፡፡ በውርስ እዳነት መመዝገብ የማይገባውን እዳ መዝግበዋል፡፡ ያቀርብኳቸውን ማስረጃዎች በአግባቡ አልመረመረም፡፡ ወራሾች ሳንስማማበት የውርስ ንብረት ለወራሾች እንዲከፋፈል ወስነዋል፡፡ በመሆኑም የውርስ አጣሪው ሪፖርት መጽደቅ የለበትም በማለት አመልክተዋል፡፡
ፍ/ቤቱም የውርስ አጣሪው የሟች የኑዛዜና ያለኑዛዜ ወራሾች እነማን እንደሆኑ፣ የሟች የውርስ ሀብት ምን እንደሆነ ከውርስ ሀብት ላይ ሊከፈል የሚገባውን እዳ ምንነትና በኑዛዜ የተሰጠ ስጦታ ለተቀባዩ መከፈልን በተመለከተ የግራ ቀኙን አቤቱታና ማስረጃ መርምረው ያቀረቡት ሪፖርት የሚነቀፍበት ምክንያት የለም፡፡ አመልካች አለኝ የሚሉት መብት ካላቸው ዳኝነት ከፍለው በክስ ከሚጠይቁ በስተቀር የውርስ አጣሪውን ሪፖርት ባለማጽደቅ በዚህ መዝገብ ሊጠይቁ የሚችሉበት ሁኔታ የለም በማለት አቤቱታውን ባለመቀበል ሪፖርቱን አጽድቆታል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤትም ከአመልካች የቀረበለትን ይግባኝ በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 337 መሠረት ሰርዞታል፡፡ አመልካች ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ያቀረቡትም የስር ፍ/ቤቶች የሰጡትን ትዕዛዝ በመቃወም ነው፡፡ በአቤቱታው ውስጥ የተጠቀሱት ቅሬታዎችም የውርስ አጣሪው የሟችን ሀብት በአግባቡ አላጣሩም፡፡ በሕግ መፍረስ የሚገባውን የስጦታ ውል አጽድቀዋል፡፡ የቆጠርኳቸውን ማስረጃዎች ባለመስማት መብቴን አጣብበውብኛል፡፡
ያለአግባብ የውርስ ንብረቶችን ወራሾች እንድንከፋፈል ወስነዋል፡፡ የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤትም የውርስ አጣሪው ያቀረቡትን ሪፖርት እንዳያጸድቅ፣ የውርስ ማጣራቱ ሥራ እንደገና እንዲካሄድ እንዲያደርግልኝ ያቀረብኩትን ጥያቄ ባለመቀበል ሪፖርቱን ማጽደቁ በአግባቡ አይደለም፡፡ በመሆኑም የስር ፍ/ቤቶች የሰጡት ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ ትዕዛዙ ሊሻርልኝ ይገባል የሚሉ ናቸው፡፡
1ኛ ተጠሪ ሐምሌ 30 ቀን 1999 ዓ/ም ጽፈው ባቀረቡት መልስ የውርስ አጣሪው በኑዛዜ ስጦታው ላይ ያሉትን ምስክሮች አስቀርበው በመስማት የኑዛዜ ስጦታው የሕግ ስህተት የሌለበት መሆኑን አጣርተው የአሁንዋ አመልካችንና ሌሎቹን ወራሾች በዝርዝር መዝግበው ባደረጉት ማጣራት መሰረት ሪፖርታቸውን ለፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ማቅረባቸው በአግባቡ ነው፡፡ የሥር ፍ/ቤቶቹ ሪፖርቱን ለማጽደቅ የሰጡት ትዕዛዝም መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም፡፡ በመሆኑም ትዕዛዙ ሊጸድቅልን ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡
2ኛ ተጠሪ ደግሞ ሐምሌ 30 ቀን 1999 ዓ/ም ጽፈው በሰጡት መልስ ውርስ አጣሪው የውርስ ንብረቱን በአግባቡ አላጣሩም የ1ኛ ተጠሪን ቤት በውርስ ንብረት ውስጥ ማካተት ሲኖርባቸው በስጦታ ያገኙት ነው በማለት መወሰናቸው ተቀባይነት የለውም፡፡ አዋጅ ቁጥር 47/67 ከመውጣቱ በፊት ሟች ለእኔ የሰጡኝን ቁጥሩ 432 የሆነውን ቤት በውርስ ንብረት ውስጥ ያለማካተታቸው ግን በአግባቡ ነው፡፡ በመሆኑም የውርስ አጣሪው ሪፖርት ባለበት ሁኔታ እንዲፀድቅ መደረጉ ተቀባይነት የለውም በማለት ተከራክረዋል፡፡
በበኩላችን ደግሞ የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት የውርስ ንብረት አጣሪውን ሪፖርት ምንም ጉድለት አላገኘሁበትም በማለት ያፀደቀው በአግባቡ ነው ወይም አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ መዝገቡን መርምረናል፡፡
መዝገቡን እንደመረመርነውም የውርስ አጣሪው ለፍ/ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ቁጥሩ 432 የሆነው ቤት አዋጅ ቁጥር 47/67 ከመውጣቱ በፊት ሟች ወ/ሮ ደጊቱ ደንጓሬ ለወ/ሮ አሰለፈች ወርዶፋ በስጦታ የሰጡዋቸው በመሆኑ የውርስ ሀብት አይደለም በማለት ወስኛለሁ፣ ቁጥሩ 431 የሆነው ቤትም የወ/ሮ አስናቀች ወርዶፋ የኑዛዜ ድርሻ ነው፣ አመልካች ስጦታዎቹ ፈራሽ ናቸው በማለት ቢከራከሩም የሚፈርስበትን ምክንያት አልገለጹም፡፡ ስጦታው እንዲፈርስ በፍርድ ቤት ጠይቀው ያስፈረሱበትን የፍ/ቤት ውሣኔ አላቀረቡም በማለት ያሰፈሩዋቸው ድምዳሜዎች ንብረቶቹን የማከፋፈል ዓይነት ስራ ያከናወኑ መሆኑን እንደሚጠቁሙ ለመረዳት ችለናል፡፡
በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 956 እንደተደነገገው የአጣሪው ስራ ሟቹ አንድ ኑዛዜ ትቶ እንደሆነ መፈለግና በመጨረሻው ውርስ የሚደርሳቸው ሰዎች እነማን እንደሆኑ ማረጋገጥ፣ የውርሱን ሀብት ማስተዳደር፣ መክፈያቸው የደረሰውን የውርስ እዳዎች መክፈልና ሟቹ በኑዛዜ ያደረጋቸውን ስጦታዎች መክፈልና የኑዛዜውን ቃል ለመፈፀም ማንኛቸውም ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎች ማድረግ ነው፡፡ እነዚህ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት በሚያከናውንበት ጊዜ ደግሞ በኑዛዜው የውርስ ንብረት መሆናቸው ተጠቅሶ የክፍፍል ስርዓትም የተቀመጠላቸውና ወራሾች በሙሉ የተስማሙባቸው ንብረቶችና መክፈያቸው የደረሰው የውርስ እዳዎች ሲኖሩ በወራሾቹ ስምምነት መሰረት ንብረቶቹን ሊያከፋፍልና እዳዎቹንም ሊከፍል ይችላል፡፡ በኑዛዜው ላይ በተጠቀሱትና ባልተጠቀሱት ንብረቶች የውርስ ሀብት መሆን ያለመሆን ላይ ወራሾቹ ያልተስማሙና ክርክር ያነሱ ከሆነ ግን የአጣሪው ሥራና ኃላፊነት ወራሾች የተስማሙባቸውን ንብረቶችና እዳዎች ካሉ ደግሞ ማስረጃ በመስማት ማስረጃው ምን እንደሚያስረዳ ሪፖርቱ ላይ በማስፈር እንዲያጣራ ላዘዘው ፍ/ቤት ማቅረብ እንጂ ንብረት አጣሪው ይህ ንብረት የውርስ ሀብት መሆኑን ስለተገነዘብኩኝ ንብረቱ የውርስ ሀብት ነው በማለት ወስኛለሁ ወይም ደግሞ ማስረጃውን እንደተመለከትኩት ንብረቱ የውርስ ሀብት ያለመሆኑን ስላረጋገጥኩኝ የውርስ ሀብት አይደለም በማለት ወስኛለሁ ለማለት የሚያስችለው ሥልጣን የለውም፡፡
በዚህ ጉዳይ የውርስ አጣሪው ያደረጉትን የማጣራት ሥራ ስንመለከተው ወራሾቹ የውርስ ሀብት ናቸው በሚሉዋቸው ሁለቱም ቤቶች ላይ ገና ከጅምሩ አንስቶ ያልተስማሙና ክርክር ያነሱ በመሆኑ አጣሪው ማስረጃ መስማታቸው በአግባቡ ነው፡፡ ሆኖም አጣሪ በወራሾች መካከል የተደረገው ክርክር ምን እንደነበረ፣ የኑዛዜ ወራሾችና የሕግ ወራሾች እነማን እንደሆኑ፣ የግራ ቀኙ ማስረጃ ምን እንደሚመስል፣ እንዲሁም ወራሾች የተማመኑባቸውና ያልተማመኑባቸው የውርስ ንብረቶችና እዳዎቹ ምን ምን እንደሆኑ በመዘርዘር ሪፖርት ማዘጋጀት ሲኖርባቸው ከዚህ አልፈው ወራሾችን አከራክረው ማስረጃ ከሰሙ በኋላ ክርክሩንና ማስረጃውን ከሕግ ጋር በማገናዘብ ይህ ንብረት የእገሌ እንጂ የእገሌ አይደለም በማለት መወሰናቸው ከተሰጣቸው የውርስ አጣሪነት ሥልጣን በላይ በመሄድ መደበኛ ፍ/ቤት በሚያከናውነው የዳኝነት ሥራ ውስጥ መግባት መሆኑንና ይህም ተገቢ ያለመሆኑን ተገንዝበናል፡፡
ውርስ አጣሪው አዘጋጅተው ያቀረቡት ሪፖርት ውሣኔም ጭምር ያዘለ በመሆኑ ሪፖርቱ በቀረበለት ፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት መጽደቁ ደግሞ በአጣሪው የተወሰነው ነገር በፍ/ቤት ተቀባይነት አግኝቶ የፀደቀ ተደርጎ ስለሚወሰድ አመልካች አዲስ ክስ አቅርበው የውርስ ድርሻቸውን ለማግኘት የሚያስችላቸውን መብት የሚያጣብብ ነው የሚሆነው፡፡ በመሆኑም የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ሪፖርቱን መርምሮ ያለበትን ጉድለት እንዲስተካከል ማድረግ ሲገባው እንዳለ ተቀብሎ ማጽደቁ ተገቢ ሆኖ አልተገኘም፡፡
ስለዚህ የውርስ ንብረት አጣሪው ያቀረቡት ሪፖርት የአጣሪንና የመደበኛ ፍ/ቤትን ሥራ አጠቃሎ የያዘ በመሆኑ ሪፖርቱ በአግባቡ የተዘጋጀ ባለመሆኑና የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ሪፖርቱን ያጸደቀበትና የፌ/ከ/ፍ/ቤት ደግሞ የቀረበለትን ይግባኝ የሰረዘበት ትዕዛዝ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሆነው ስለተገኙ የሚከተለውን ውሣኔ ሰጥተናል፡፡
ው ሳ ኔ
1.የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት በመ/ቁ. 04036 ጥር 5 ቀን 1997 ዓ/ም የሰጠው ትዕዛዝና የፌ/ከ/ፍ/ቤት በመ/ቁ. 37777 ህዳር 21 ቀን 1998 ዓ/ም የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 348/1/ መሠረት ተሽረዋል፡፡
2.የሥራ ፍ/ቤት የውርስ ማጣራት ሪፖርቱን ያፀደቀው ከነጉድለቱ ጭምር በመሆኑ መፅደቅ አልነበረበትም ብለናል፡፡ በመሆኑም የሥር ፍ/ቤት እንደገና አጣሪ ሾሞ የውርስ ማጣራቱን ሥራ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 956 መሠረት እንዲከናወን በማስደረግ ሪፖርቱ በአግባቡ የቀረበ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ በሕጉ መሠረት አስፈላጊውን እንዲፈጸም በማለት ወስነናል፡፡ ይፃፍ፡፡
3.ወጪና ኪሳራን በተመለከተ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን እንዲችሉ ብለን መዝገቡን ዘግተን ወደ መዝገብ ቤት መልሰናል፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት


