ዳኛው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ካስተናገዳቸው ጉዳዮች መካከል የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በአንድ የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኛ ላይ የቀረበውን የዲስፕሊን ክስ መርምሮ በጉዳዩ ላይ የሰጠውን ውሳኔ ተመልክቶ ማጽደቅ (በዚያ ላይ ውሳኔ መስጠት) ነበር፡፡ ምክር ቤቱ በእለቱ ያፀደቀውን ዳኛው ከሥራቸው እንዲሰናበቱ የተሰጠውን የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ሙሉ ውሳኔ አቅርበነዋል፡፡
የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ
ስብሰባ ቃለ ጉባዔ
የዲሲፒሊን ክስ የቀረበባቸው ዳኛ፡- አቶ መሐመድ አህመድ ሽሬ
ኃላፊነት፡- የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ድሬዳዋ ምድብ ችሎት ዳኛ
ውሣኔ
በዳኛው ላይ ለጉባዔው የቀረቡት ክሶች 6 ሲሆኑ ጉባዔው የቀረቡትን ክሶች መርምሯል፡፡ ጉባዔው የቀረቡትን ክሶች የሚያጣራ አጣሪ ኮሚቴ ሰይሞ የቀረቡትን ክሶች በአግባቡ ያጣራ ሲሆን ዳኛው መልስ እንዲሰጡባቸው ከተደረገ በኋላ የቀረበውን ክስ፣ መልስና የአጣሪውን ውጤት ከሃገሪቱ ሕገ መንግሥት፣ የዳኞች ሥነ ምግባር ደንብ እና ልዩ ልዩ ህጎች አገናዝቦ መርምሯል፡፡
1. በወ/መ/ቁ. 19485
ዳኛው በዚህ መዝገብ ላይ ከሳሽ ዐ/ሕግ በተከሳሽ ላይ የወንጀል ክስ ከመሰረተ በኋላ ተከሣሽዋ አድራሻዋን በመቀያየር የማትገኝ በመሆኑ ፍ/ቤት በሰጠው ቀጠሮ የማትቀርብ ስለሆነ የዋስትና መብት እንድትከለከል ወይም ከፍ ያለ ዋስትና እንድትጠራ ይደረግ በማለት ዐ/ሕግ ያመለከተውን ዳኛው ተቀብለው ዋስትና ተከልክሎ ማ/ቤት ሆና ጉዳይዋን እንድትከታተል ትዕዛዝ ከተሰጠና ዐ/ሕግ ከችሎት ከወጣ በኋላ የተከሣሽዋ የዋስ መብት ተከብሮ እንድትለቀቅ በማድረግ ክሱ በተገቢው ጊዜ እልባት እንዳያገኝ አድርገዋል የሚል ነው፡፡
ዳኛው ለዚህ ክስ የሰጡት መልስ የተከሣሽዋን የቤተሰብ ሁኔታ አባታቸው የሞተባቸው ህፃናት ልጆች አሳዳጊና ሞግዚት ነኝ በማለት ያቀረበችው አቤቱታ የተሰጠው ትእዛዝ የችሎት ሥራ ሳይጠናቀቅ እንደገና እንዳይ አድርጎኝ እንጂ ዐ/ሕግ እንደሚለው አይደለም የሚል ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ክስ የተመሰረተበትን መዝገብ በአጣሪ ኮሚቴው አማካኝነት እንዲጣራ እንደተደረገው እንዲሁም በተከሣሽ ከተሰጠው መልስ ለመረዳት እንደተቻለው በተከሣሽ ላይ ዋስትናን አስመልክቶ የተሰጠው ትእዛዝ በዳኛው ተነስቷል፡፡ በክሱ ላይ እንደተመለከተው ትእዛዝ የተነገረው ዐ/ሕግ ከችሎት ከወጣ በኋላ ይሁን ዐ/ሕግ በችሎት እንዳለ ለማረጋገጥ ማስረጃ ባይገኝም፣
1. የዐ/ሕግ ዋስትና ይከልከልልኝ /በሕጉ ዋስትና ይሰጥልኝ ጥያቄ ቀርቦ ትእዛዝ ከተሰጠበት በኋላ በሥር ተከሣሽ ያቀረበችው የዋስትና ይፈቀድልኝ /የቤተሰብ ኃላፊ ስለሆንኩ በማለት/ ጥያቄ በአግባቡ ሳይመዘግቡ ዋስትናውን በመፍቀድ ትዕዛዝ የሰጡ በመሆኑ፣
2. የመጀመሪያውን ትዕዛዝ የቀየረው ትእዛዝ የተሰጠው በዕለቱ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ የዐ/ሕግ አስተያየት ተጠይቆ ያልተሰማና ያልተመዘገበ በመሆኑ፣ ዳኛው ዐ/ሕግ ከችሎት ከወጣ በኋላ ትእዛዙን ቀይረዋል የሚለውን ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ ባይቻል እንኳን ተከራካሪ ወገኖችን በእኩል ዓይን በመመልከት ያላስተናግዱ፣ለተከራካሪ ወገኖች ክርክር እና አቤቱታ እኩል ክብደት ያልሰጡ፣ ተከራካሪ ወገኖች ያላቸውን የመስማት መብት ያጣበቡ፣ አስተያየቱም በግልፅ ችሎት ያላስቻሉ ወይንም ለተከራካሪ ወገኖች ግልፅ በሆነ አግባብ ክርክርን ያልመዘገቡ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ይህም ከፍ ያለ የሥነ - ምግባር ጉድለት ስለሆነ ጉባዔው ጥፋተኛ ናቸው ብሏል፡፡
2. የወ/መ/ቁ. 23445
በዚህ የወንጀል መዝገብ ላይ በዳኛው ላይ የቀረበው ክስ በርካታ ገንዘብ የያዙ እና 2 ኪሎ ግራም ወርቅ ጉዳይ ያለበት የጉምሩክ መዝገብ በቀረበው መቃወሚያ መነሻ ዐ/ሕግ ክሱን ላሻሽል ብሎ ቢያመለክትም ውድቅ በማድረግ ተከሣሽን በነፃ እንዲለቀቁ አድርገዋል የሚል ነው፡፡
ዳኛው ለዚህ ክስ የሰጡት መልስ ዐ/ሕግ በክስ አመሰራረት በኩል ችግር ያለበት በመሆኑ በአብዛኛው ጉዳይ የሚረታ መሆኑን፣ ዐ/ሕግ በዚህ መዝገብ ላይ የተከሣሽ ተቃውሞ ትክክል ነው እያለ እንደገና ክስ አሻሽላለሁ ማለቱ አግባብ አለመሆኑ በብይኑ ላይ ተነስቷል፤ የዐ/ሕግ የችሎታ ማነስ እንጂ፣ የዳኛው ችግር አይደለም የሚል ነው፡፡
ጉባዔው ይህንን ክስም በአግባቡ አጣርቷል፡፡ ዳኛውም ይህ ድርጊት አልተፈፀመም በማለት ክደው አልተከራከሩም፡፡ ያቀረቡት ክርክር የዐ/ሕግን የክስ አመሰራረት እና የክርክር አካሄድ ችግር የሚዘረዝር ብቻ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ለዚህ ክስ ያስረዳልኛል በማለት ያቀረቡት ማስረጃ በዐ/ሕግ ክስ አስረጅነት የተቆጠረው መዝገብ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም፡-
1. ዳኛው በክሱ እና በተጠቀሰው የህግ ቁጥር መሀከል ያለመናበብ ችግር ሲያጋጥማቸው ክሱ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ማዘዝና ተስተካክሎ እንዲቀርብና ክርክሩ እንዲቀጥል ማድረግ ሲገባቸው እንዲቋረጥ ማድረጋቸው፣
2. ይህ ታልፎ እንኳን ክሱን እንዲሻሻል በተከራካሪ ወገን እንዲሁም በዐ/ሕግ ጥያቄው ሲቀርብ ጉዳዩን ከተከሣሽ የመከላከል መብት ማጥበብ /ማስፋት አንፃር ተመልክተው ክሱ ሊሻሻል ይገባዋል ወይ አይገባውም በማለት ብቻ ትእዛዝ መስጠት ሲገባቸው ይህን ባለማድረጋቸው፣
3. ክሱ ሊሻሻል አይገባውም ቢባል እንኳን በቀረበው ክሱና ክርክሩ መቀጠል ሲገባው ከሳሽ እና ተከሣሽ በሥነ - ስርዓት ሕግ መሠረት ተከራክረው እምነት ክህደት ተጠይቆና በሕገ - መንግሥቱ መሠረት ማስረጃ ተመርምሮ ውሳኔ መስጠት ሲገባው በሥር የወንጀል ተከሣሹ ከሥነ - ስርዓት ውጪ በነፃ እንዲሰናበት ማድረጋቸው
4. ለዚህም ትእዛዝ መሠረት አድርገው የጠቀሱት የህግ ቁጥር የወ/መ/ሥ/ሥ/ቁ. 131 /2/ ሲሆን ይህ የህግ ቁጥር በመቃወሚያው ላይ ውሳኔ ለመስጠት እን..ቻል ከሚገልጽ በቀር እንዲሁም የቀረበው መቃወሚያ በክሱ /መሻሻል/ አለመሻሻል ላይ ትእዛዝ ሊያሰጥ ሲገባው በተራ ቁጥር 3 ስር የተዘረዘሩት የማስረጃ እና የክርክር ስርዓቶች በማለፍ ተከሣሹን በነፃ ለመልቀቅ የሚያስችል የህግ ድንጋጌ ባለመሆኑ፣ ዳኛው ከፍ ያለ የሥነ ምግባር ጉድለት ፈፅመዋል እንዲሁም የሙያ ብቃት /ሰቄቂቅስ..ስቃሰስ/ ማነስ አሳይተዋል ብለናል፡፡
3. የወ/መ/ቁጥር 23958 እና 24364ን በተመለከተ
ዳኛው በእነዚህ ሁለት መዝገቦች የቀረበባቸው ክስ በተከሣሽ በኩል የቀረበው መቃወሚያ ለዐ/ሕግ ሳይደርስና አስተያየት ሳይሰጥበት እንደዚሁም በሌላ ችሎት እየታየ ያለን መዝገብ ከመዝገብ ቤት በማስቀረብ ያለምንም የህግ መሠረት ሁለቱ መዝገቦች እንዲዘጉ አድርገዋል የሚል ነው፡፡
ዳኛው ለዚህ የዲስፒሊን ክስ የሰጡት መልስ በዐ/ሕግ በኩል የሚቀርቡ ክሶች የተለያዩ ችግር ያለባቸው ናቸው፣ ክስና ዝርዝሩ አይጣጣምም፣ በአንዳንድ ተከሣሾች ላይ ከአንድ ጊዜ በላይ ክስ የቀረበውን የወንጀል ዝርዝር አይደለም፣ የሚል ሲሆን መዝገቦችን በተመለከተም በተከሣሾች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን እንግልትና ማሰቃየት እንዲሁም ከብሶታቸው የተነሳ በችሎት እንዲሁም በመንግሥትና በአጠቃላይ በፍትህ ስርዓት ላይ ሊያደርስባቸው የሚችሉት አመለካከት ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ በመገመት ለተቋሙም ሆነ የፍትህ ስርዓቱን ለመጠበቅ፣ የተነሳው ነጥብና ለችግሩ ታሳቢነት ያለው ህግ አግባብነት የሌለው መሆኑን ግንዛቤ በመውሰድ ዳኝነት ሰጥቻለሁ እንጂ አንዱን ለመጥቀም አንዱን ለመጉዳት የተሰጠ ዳኝነት አይደለም የሚል ነው፡፡
ጉባዔው በክሱ የቀረበውን ዝርዝር ጥፋት በተከሣሽ የተሰጠውን መልስ ከመዝገቡ ጋር በማገናዘብ ሲመረምር፣
1. ከፍ ሲል የተጠቀሱት ሁለት መዝገቦች እምነት ክህደት ተጠይቆባቸው በሁለቱም መዝገብ ተከሣሽ የቀረበበትን የዛቻ ወንጀል ክዶ በመከራከሩ ማስረጃ ለመስማት የተቀጠረ በመሆኑ፣
2. አንደኛው መዝገብ ለአሁኑ ዳኛ /ችሎት/ የተመራ ሳይሆን ለሌላ ዳኛ /ችሎት/ የተመራ ሆኖ እያለ ማስረጃ ለመስማት ከተቀጠረበት እለት ቀድሞ ተከሣሹ በተመሳሳይ ቦታ፣ ሰዓትና ጊዜ ተፈፀመ ለተባለ ወንጀል ሁለት ክስ ሊመሰረትብኝ አይገባም በማለት ያቀረበውን ተቃውሞ ተቀብለው ያስተናገዱ በመሆናቸው፣
3. በሁለቱም መዝገቦች አቤቱታውን ሲቀበሉ ተቃውሞ ለማቅረብ እምነት ክህደት ከመስጠቱ በፊት ያለው ጊዜ ያለፈ በመሆኑ፣ አቤቱታው ከህግና ስነ - ሥርዓት ውጪ የቀረበ ቢሆንም ዐ/ሕግ መልስ ሳይሰጥበት ሁለቱንም መዝገብ በመዝጋት ተከሣሽን በነፃ ያሰናበቱ በመሆናቸው፣
4. አንደኛው መዝገብ የሌላ ችሎት ሆኖ እያለ በምን አግባብ ቀጠሮ ሰብረውና አቤቱታውን ተቀብለው እንዳስተናገዱ ያልገለፁ፣ በክሱ ላይ የተቀመጠውን ነጥብም በግልፅ ያላስተባበሉ በመሆናቸው፣
5. ክርክር በአግባቡ ሳይካሄድ ግራ ቀኙ ማስረጃ የማቅረብ መብታቸው ሳይጠበቅና በህጉ መሠረት ሳይመዘን በቀረበው አቤቱታ ብቻ ከወንጀል ክስ በነፃ ለማሰናበት የሚያስችል ምንም ዓይነት የህግ መሠረት የሌለ በመሆኑ፣
6. ውሣኔ ለመስጠት የተጠቀመበት የህግ ቁጥር የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 132 /2/ሠ/ ሲሆን ይህም ክስን ለማቅረብ ፈቃድ ማስፈለግን ከመግለፅ በቀር ተከሣሽን በነፃ ለማሰናበት የሚያስችል ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው የህግ ቁጥር በመሆኑ፣
ዳኛው ከፍ ያለ የሥነ ምግባር እና የብቃት ችግር ተገኝቶባቸዋል ብለናል፡፡
ከፍ ሲል እንደተዘረዘረው ዳኛው በቀረበባቸው ክስ በ4 መዝገብ ላይ ጥፋት ፈፅመዋል፡፡ ጥፋት ከመፈፀሙ ደግሞ ተመጣጣኝ ቅጣት መስጠቱ ተገቢ ነው፡፡ ዳኛው በፈፀሙት ጥፋት ተከራካሪ ወገኖች ማስረጃ የማቅረብ ህገ - መንግሥታዊ መብትን የመጣስ፣ በችሎት ሥራ በህገ - መንግስቱ ድንጋጌ መሠረት ግልፅ ትእዛዝ ያለመስጠት ወይም ግልፅ የችሎት አመራርን ያመለክታል፣ ባላቸው የሥራ ልምድ እና የት/ት ዝግጅት ሊፈፀም የማይገባው ጉልህ የሆነ ብቃት ማነስ እንዲሁም በህገ - መንግስቱ ላይ የተጣለውን የዳኛ ግዴታ በመጣስ ከህግ በላይ ሆኖ የመሥራት ጥፋት ፈፅመው ተገኝተዋል፡፡ እነዚህ ጥፋቶች በህገ - መንግሥቱ አንቀጽ 79/4/ሀ/መሠረት ከሥራ የሚያሰናብቱ በመሆናቸው፤ ጉባኤው በፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 24/1988 አንቀጽ 5/5 በተሰጠው ሥልጣን ዳኛው በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዳኞች የሥነ ምግባር ደንብ አንቀጽ 4፣ አንቀጽ 5፣ አንቀጽ 12 እና አንቀጽ 13 የተደነገጉትን ድንጋጌዎች ተላልፈው በመገኘታቸው፤ በሥራ ላይ ቢቆዩ የፍ/ቤቱን መልካም ሥምና ገፅታ የሚያጎድፉ፣ ፍ/ቤቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ተዓማኒነቱንና ተገማችነቱን የሚያበላሹ፤ ለኅብረተሰቡም ጠቃሚ አገልገሎት ሊሰጡ የማይችሉ መሆናቸውን በማመኑ ለፈፀሙት ጥፋት ከዳኝነት ሥራቸው ሊነሱ ይገባል በማለት ጉባዔው ወስኗል፡፡ ውሣኔው በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እስከሚፀድቅ ድረስ ከ21/02/2002 ዓ.ም. ጀምሮ ከሥራና ከደመወዝ እንዲታገዱ ተወስኗል፡፡
ለሚመለከተው ይፃፍ፡፡
ይህ ውሣኔ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመጨረሻ ውሳኔ ይተላለፍ፡፡
የዲስፒሊን ኮሚቴ


