በብርሃኑ ፈቃደ
የዘንድሮ ገበያና ዋጋ ልጓም አልባ እየሆነ፣ ከአምናና ከካቻምና ይሻል ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ እያሻቀበ አስቸግሯል፡፡
አንዳንዱ ሸቀጥ፣ መገልገያም ሆነ የፍጆታ ዕቃ ቀስ በቀስ የሚያዩት እንጂ የማይቀምሱት እስከመሆን እየዘለቀ ግራ አጋብቷል፡፡
ሌላው ቀርቶ ድንችና ጎመን እንኳ ለወትሮ ባልተለመደና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋቸው ጨምሮ ተጠቃሚን አስደንግጠዋል፡፡
በገበያው የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ከሰሞንኛ ጉዳይነት ተሻግሮ የኑሮ ውድነት ነፀብራቅ እየሆነ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙትም ይበልጡን ተስፋ እያስቆረጠ ይገኛል፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋልና ከሜክሲኮ ወደ ገርጂ በሚያቀና ታክሲ ውስጥ የተሳፈረ አንድ ወጣት ጎን ተቀምጬ በምጓዝበት ወቅት፣ ለጉዞው የከፈለውን አራት ብር ከአምሳ ሳንቲም ተንተርሶ ‹‹ከዓመት በፊት የክፍለ አገር ሒሳብ ነበር›› ሲል በቀጥታ ከኑሮ ውድነት ጋር አያይዞ መናገር ይጀምራል፡፡
‹‹ከአራት ዓመት በፊት ትዳር ስይዝ የወር ደመወዜ 450 ብር ነበር፡፡ ግን ያን ያህል አይቸግረኝም፡፡ አትክልት ተራ ሔጄ በ70 ወይም በ80 ብር ሁለት ፌስታል ሙሉ የቤት አስቤዛ እገዛ ነበር፡፡ አሁን እኰ 200 ብር ይዘህ ሔደህ የምትገዛው አንድ ፌስታል እንኳ አይሞላም. . .››
ወጣቱ ያሳሰበው ሰሞንኛው ዋጋ ብቻ አልነበረም፡፡ ‹‹ኑሮው እንዲህ ከቀጠለ ነገ የልጄ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ማሰብ ያስፈራኛል፤›› በማለት መፃኤው ጊዜ ተስፋ የማይጣልበት እንደሆነ አስረግጧል፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ማዘውተሪያዎች የስፖርት (ጂምናዚየም) አሰልጣኝ በመሆን ራሱንና ቤተሰቡን ያስተዳድራል፡፡ ዋጋ ሲጨምር፣ ኑሮ ሲወደድ የገቢ ምንጫቸው ለማይጨምር ‹‹የመንግሥት ሠራተኞች ይብላኝላቸው›› ሲልም የባሰ አታምጣ በሚል ዓይነት ድምፀት ጨዋታውን ቀጥሏል፡፡
በአገራችን የልማድ ገበያ የተንሰራፋ በመሆኑ ያለበቂ ምክንያት አጋጣሚ እየጠበቁ ዋጋ ማናር የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ በዓል እስኪጠጋ ወይም የተለየ አጋጣሚ እስኪፈጠር እየጠበቁ ዕቃ የሚደብቁ ሞልተዋል፡፡ ሐቀኞች፣ በአግባቡ ነግደው የሚያተርፉ፣ አትርፈው የሚከብሩ የሉም አንልም፡፡ በርቱ ተበራቱ እንላቸዋለን፡፡ ዋጋ ለማስወደድ፣ የማይረባ ጥቅም ለማግኘት ፋታ የሚነሱንን ግን አንድ እንዲባሉ እንፈልጋለን፡፡ እነዚህ ክስተትና አጋጣሚ እየጠበቁ ትርፍ ከሚያጋብሱባቸው ወቅቶች አንዱ ደግሞ የገና በዓል ነው፡፡
የፍጆታ ዕቃዎች በብዛት የሚሸመቱበት ይህ በዓል ‹‹ትልቅ ቢዝነስ›› የሚሠራበት ወቅት በመሆኑ፣ ከበዓሉ አስቀድሞ ዕቃዎች ከገበያ ወይ ገሸሽ ይደረጋሉ አልያም አናት ላይ የሚወጣ ዋጋ ይጫንባቸዋል፡፡
በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ የተወሰዱ አንዳንድ እርምጃዎችን ታዝበናል፡፡ ቢዘገይም ከምንም ይሻላልና ቁጥጥሩ አይከፋም፡፡ ሁልጊዜ ግን የእሳት ማጥፋት ዓይነት እርምጃ መውሰዱ ውጤታማ ያደረጋል አንልም፤ ብለንም አናምንም፡፡
ከዚህ በፊት የጋራ ዋጋ (Cartel price) እያበጁ በስምምነት ገበያውን ሲቆጣጠሩ በነበሩ ላይ እርምጃ ሲወሰድ የነበረ ቢሆንም፣ ለውጥ ያመጣ አይመስልም፡፡ ወይም የተወሰደው እርምጃ ያን ያህል አስተማሪነት ያልነበረው፣ የይስሙላ ነበር ያስብላል፡፡
ተቀናቃኝ (ተወዳዳሪ) ምርቶች በአንድ ጀምበር እኩል ዋጋ የሚጨምሩበት፣ ከውጭ በሚያስመጡት ምርት ላይ ተነጋግረው የሳንቲም ልዩነት እንኳ ሳያደርጉ ዋጋ የሚያንሩበት ክስተት እየተስተዋለ፣ በአደባባይ እየታየ ይህንን ለመከላከልና እርምጃ ለመውሰድ ይመለከተኛል የሚል መጥፋቱ ያሳስባል፡፡
በዋጋ ጉዳይ ላይ ንግድ ሚኒስቴር ድርሻ እንዳለው ይታወቃል፡፡ በየሱቁ ዋጋ እንዲለጠፍ ማሳሰቢያ ሲያወጣም ይታያል፡፡ ምን ዓይነት ዋጋ እንደተለጠፈም እንዲቆጣጠርና እንዲገልጽልን ጭምር እንፈልጋለን፡፡
የቡታጋዝ (የሲሊንደር) ዋጋ ጨመረ ሲባል አንብበናል፡፡ ያንን ያህል የዋጋ መጠን ሲጨመር ንግድ ሚኒስቴር ምነው አለመናገሩ? ስለማያውቅ ይሆን? አይመስለንም፡፡ ይህንና ይህን የመሰሉ ጉዳዮች ሲከሰቱ የሚመለከታቸው ቀድመው ቢያሳውቁና ቢነግሩን በነጋዴ ላይ በጅምላ ከመፍረድ፣ በመንግሥትም ላይ ከማማረር በገላገሉን ነበር፡፡ አሁንም በፊታችን ያለውን የገና በዓል ሰበብ እያደረጉ ገበያና ዋጋ ከሚያሳቅሉት እንዲታደጉን የሚመለከታቸውን ለማመላከት እንወዳለን፡፡


