በጥበበሥላሴ ጥጋቡ
በቴዎድሮስ ተሾመ ተጽፎ፣ ዳይሬክት እና ፕሮዲውስ የተደረገው ‹‹ዓባይ ወይስ ቬጋስ›› ፊልም ከሁለት ሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ባሉ 18 ሲኒማ ቤቶች ሲመረቅ የተመልካቹ ስሜት የተቀላቀለ ነበር፡፡
ከዚህ በፊት በቀይ ስህተት፣ በቀዝቃዛ ወላፈን እና በመሳሰሉት ፊልሞቹ የሚታወቀው ቴዎድሮስ ተሾመ፣ ይሄንን ፊልም ለመሥራት ለሬድዋን ካሜራ 1.2 ሚሊዮን ብር፣ ለማስታወቂያም 300 ሺህ ብር አካባቢ አውጥቶበታል፡፡
ከአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች እንደተገኘው መረጃ በገቢ እና በተመልካች ብዛት አንደኛ የሆነው ይኸው ፊልም፤ በአንድ ሳምንት ውስጥ በሲኒማ አምፒር 49,060 ብር በአምባሳደር ሲኒማ 78,080 ብር ማስገባት ችሏል፡፡
ከመለቀቁ በፊት ብዙ የተባለለት ይህ ፊልም ሰሎሞን ቦጋለ፣ ግሩም ኤርሚያስ እና የመሳሰሉ ታዋቂ ተዋናዮችን ይዟል፡፡
መቼቱ በባሕር ዳር በተለይም ጢስ ዓባይ እና በአሜሪካዋ ቬጋስ ላይ የሚያጠነጥነው ይኸው ፊልም ፍቅርን፣ የአገር መውደድንና የመሳሰሉትን ነገሮች ይዳሰሳል፡፡ ጭብጡንም መና በምትባለው ገፀ ባሕርይ አማካኝነት ያስተላልፋል፡፡ መና በባሕርዳር ውስጥ የምትኖር ከተሜ ልጅ ስትሆን ወደ ውጭ ሀገር ለመሔድ ጉጉት ያላት ተደርጋ ተሥላለች፡፡ ሕልሟንም ለማሳካት ስትጣጣር ቴዎድሮስ ተሾመ ወክሎ የሚጫወተውን ገፀ ባሕርይ ሣልሳዊን ታገኘዋለች፡፡ በሌላ መልኩ ሣልሳዊ ቬጋስ ውስጥ የሚኖር ሀብታም ሲሆን፣ ሴት ከሴት እያማረጠ በቁማር ጊዜውን የሚያሳልፍ ነው፡፡
ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰበት ምክንያትም ሚስት አግብቶ ለመመለስ እንደሆነ ፊልሙ ያሳያል፡፡ አጋጣሚውም ወደ ውጭ ለመሔድ የምትፈልገውን መናን አስተዋወቀው፡፡ ይኸው ባለሀብት ከትውውቃቸው ሦስት ቀናት በኋላ ወደ ውጭ ሀገር ሲመለስ እንደሚያገባትና ውጭ ሀገር እንደሚወስዳት ቃል ገብቶላት ይሔዳል፡፡
በዚህም መካከል መና ከሴት ጓደኛዋ ጋር ወደ ጢስ ዓባይ ስትሔድ በአጋጣሚው አገሩን ወዳድና ታታሪ ከሆነ ገበሬ ጋር ትተዋወቃለች፡፡ በመጀመርያ ንቀትና ጥላቻ ያሳየችው ቢሆንም በኋላ ግን በፍቅሩ ወጥመድ ውስጥ ትገባለች፡፡ ፊልሙም እንደዚህ እያለ ይቀጥላል፡፡
በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች በመታየት ላይ ስላለው ስለዚህ ፊልም ሪፖርተር የተለያዩ ተመልካቾችንና በፊልሙ ላይ ያሉ አንዳንድ ባለሙያዎችን አናግሯል፡፡ ባለሙያዎቹ ማንነታቸው እንዲገለጹ ስላልፈለጉ ስማቸው አልተጠቀሰም፡፡
አንድ ተመልካች፣ መና ገበሬውን መውደዷ ከእውነት የራቀና ሕልምን ብቻ የሚያሳይ ብሎ ገልጾታል፡፡
አንደኛው የፊልም ባለሙያ፣ ከዚህ ፊልም ብዙ ጠብቆ እንደነበር ይናገራል፡፡ በተለይም አሁን አለ በሚባል ሬድ ዋን ካሜራ የተሠራ ቢሆንም ፊልሙ ግን እንደጠበቀው ጥሩ አልነበረም ብሏል፡፡ እንደርሱ አገላለጽም፣ ‹‹ፊልሙ ላይ መስተካከል የሚችሉ ቀላል ቴክኒካል ስህተቶች ነበሩበት፡፡ ለምሳሌ በንግግሮች መሀከል የሚሰማ የጄኔሬተር ድምፅ ዓይነት ጉልህ የድምፅ ችግር፣ እንኳን ‹የውጭ አገር የድምፅ ኢንጂነር› በተሳተፈበት ፊልም ላይ ቀርቶ ፊልም ሠርቶ የማያውቅ ሰው እንኳን በቀላሉ ሊያገኘው የሚችለው ነገር ነው፡፡ በምስሎቹ ላይ ያልተመጣጠነ ከለር (ቀለም) ታይቶበታል፡፡››
የፊልሙን ዋና ገፀ ባሕህርይ ሰሎሞን ቦጋለ በደንብ ተጫውቶታል የሚለው ደግሞ ዐቢይ ከበደ የሚባል ተመልካች ነው፡፡ እርሱ እንደሚለውም፣ ‹‹ለኔ ሰሎሞን ቦጋለ ባይኖር ኖሮ ፊልሙ ጥሩ አይሆንም ነበር፡፡ እርሱ በመኖሩ ምክንያት ፊልሙን አይቼ እንድጨርስ አድርጎኛል፡፡››
የታሪኩ ፍሰት እና የገፀ ባሕርያቱ አቀራረጽ ትክክል አይደለም የሚለው ደግሞ የፊልም ባለሙያ፣ ታሪኩን ቴዎድሮስ መጻፍ አልነበረበትም ብሎ ያምናል፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም በነበሩት ፊልሞች ላይ ቴዎድሮስን አይተነዋል፡፡ ምንም እንኳን ገበያ ላይ ቢሳካለትም፣ በጥበቡ ላይ ስንመጣ ጥሩ አልነበረም፡፡ ያሁኑ ፊልምም ላይ ያንን ነው የደገመው ታሪኩ አልተያያዘም፡፡ በተጨማሪ ደግሞ አንዳንድ የማያስፈልጉ ገፀ ባሕሪያት በፊልሙ ውስጥ ተካትተዋል፡፡ ለምሳሌ የመና ጓደኛ እና መጨረሻዋን ያላወቅንላት በሣልሳዊ የተፈቀረችው እና ፍቃዱ ተክለ ማርያም ወክሎ የሚጫወተው ገፀ ባሕርያት ይጠቀሳሉ፡፡ ይሄ ባለሙያ ቴዎድሮስ ለጥቃቅን ነገሮች ትኩረት እንዳልሰጠ ያስረዳል፡፡ ምሳሌም የሚያደርገው ሣልሳዊ ሀብታም መሆኑን ሲናገር የገንዘብ ምንጩ አለመጠቀሱ አንዱ ነው፡፡ ሰላም ከበደ የተባለች ተመልካች ደግሞ፣ ፊልሙን እንደወደደችውና የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪዎች ከዚህ ፊልም ሊማሩ እንደሚገባቸው ትናገራለች፡፡
‹‹ይሄ ፊልም በጣም ጥሩ ፊልም ነው፡፡ ቀለሙ፣ ምስሉ ሁሉ ነገር ያስደስታል፡፡ ሁለት ጊዜም አይቸዋለሁ››
በፊልሙ ላይ ያለው የኮንዶም ትዕይንት ግን ለሌላዋ ተመልካች ለምሥራች ዮሐንስ አልተዋጠላትም፡፡
‹‹አንድ ገበሬና ወሲብ ፈጽማ የማታውቅ ልጅ እንዴት ኮንዶም ይዘው እንደሚዘዋወሩ አልገባኝም፡፡ ሌላው ነገር ደግሞ በፊልሙ ላይ አገራዊ ለማስመሰል የሚሰጡት ሌክቸሮች የ6ኛ ክፍልን ትምህርት ያስታውሰኛል፡፡›› ብላለች፡፡
አንድ የፊልም ድርሰት ጸሐፊም የሚለው ነጥብ አለው፡፡ ‹‹ቴዎድሮስ በራሱ ብዙ ነገሮች ይሞክራል፡፡ ለተተኪ ፊልም ሠሪዎችም ያሳያል፡፡ ይሄ ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡ ነገር ግን ፊልም ሲሠራ ከንግድ በላይ ማስተማርያና ታሪክ መንገርያ ነው፡፡ በተለይም ጥበብ ነው፤ ያንን እንዴት መናገር ወይም መታየት አለበት የሚለውን ሁሉም ፊልም ሠሪዎች ማወቅ አለባቸው፡፡ ቴዎድሮስ ጥበቡን አግኝቶታል ወይ? ብለን ስንጠይቅ አይመስለኝም ስለዚህ የተለያየ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ቢያሳትፍ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡››


