Monday, May 20th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የቅኔ ውበት

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

የድንቁርና ሌት ጨለማ አለፈ፡
የማስተዋል ንጋት ብርሃን ተነጠፈ፡
ድካምና ሙያ ዕውቀትና ጥበብ፡

ወጣ እንደ ጨረቃ ተዘራ እንደ ኮከብ፡፡
ካራቱ ማዕዘን እየለየ ቦታ፡
በምሥራቅ በምዕራብ ተገኘ ብልጭታ፡፡
ደመናውን ቀዶ ማስተዋል ፈለቀ፡
ትምህርት ተፋፋመ ተስፋፋ ደመቀ፡፡
ሆሜር አንዣበበ ከሁሉም በለጠ፡
ቦድሌር አፈዘዘ ፑሽኪን አናወጠ፡፡
ቪክቶር ሂጐ ላቀ ሼክስፒር ገነነ፡
ቪርዢል መምህር ሆኖ ተሾመ ተካነ፡
ገት አንጸባረቀ ኮርኔይ ትልቅ ሆነ፡፡
ቪለር ተከበረ ሶፎክል አስተጋባ፡
ዳንቴ ተመረቀ ለታስም ተቀባ፡፡
ሰዎች የፈጸሙት ተግባርና ሥራ፡
ክብደቱ ግምቱ ተሰፍሮ ሲጣራ፡
ማዕርግ ሲሰጠው ሲደለደል ቦታ፡
ቅኔ ተቀመጠች አክሊል ተቀዳጅታ፡፡
በጥበብ አዳራሽ በዕውቀት መኖሪያ ቤት፡
ሁሉን የምታስንቅ ቅኔ ነች እመቤት፡፡
ዘለዓለም ውብ ነች ሁልጊዜ ሙሽራ፡
መጎናጸፊያዋ ብርሃንና ጮራ፡
አብረቅራቂነቷ ነዲድ ነው እንደ እቶን፡
እሷን ደጅ ጠንተዋል ዳዊትም ሰሎሞን፡
ያካሏ ህላዌ እሳታዊ ብርሃን፡
ዙሪያዋ በሙሉ ፋና ነው ውጋጋን፡፡
እውቀት ቢፎካከር መጽሐፍ ቢወዳደር፡
ሁልጊዜ ቅኔ ነች የድርሰቱ ጀንበር፡፡

(ከበደ ሚካኤል፤ የቅኔ ውበት፣ 1999)

**********


መጻሕፍቱ እንዲህ አሉ

ደራስያን በተለያዩ ዘመናትና ሁኔታዎች ውስጥ ያጋጠማቸውን የማኅበረሰቡን የሮሮም ሆነ የፍስሐ መንፈስ በመገምገምና አስመስለው በመቅረጽ ሥነ ቃልን ይጠቀማሉ፡፡ ለመልዕክቶቻቸው ማጉያ በማድረግ በሚፈጥሯቸው ገፀ ባሕርያት አማካይነት በልዩ ልዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸው ውስጥ ሲጠቅሷቸውም እናስተውላለን፡፡ በጣም ጥቂቶቹን ብናይ፡-

- እግዚአብሔር ሲፈጥረኝ ጥንቱን በዚህ መሬት
ሳለቅስ ተወልጄ ሳለቅስ ኖሬበት
ሳለቅስ እንድሔድ ወደ ማልቀርበት
መከራን ጠግቤ ደስታን ምራብበት
ሌሎች የበሉትን እዳ ልከፍልበት፡፡

(ፍቅር እስከ መቃብር)
-  ከዚያች የተራራ ሥር መንደሬ
ከጨፈቃ ጎጆዬ ስገባ
ሆዴ ባባ
(ቤተሰቦቼን) ወገኖቼን ላጣ፡፡

(ጽጌረዳ ብዕር)
- ያም ሞተ ያም ሔደ ባዶ ሆነ ሀገሩ
አምናና ካቻምና (ስንቶች ተቀበሩ?)
-  አንተም ተው አንተም ተው የሚላቸው ጠፍቶ
(ወጣቱ ምሁሩ ለስደት ተገፍቶ)
(ግማሹ) ተቀብሮ ሌላው ጫካ ገብቶ
-   ተጋዳይ ተጋዳይ ተጋዳይ አርበኛ
ሳያመልጥህ ያዘው ያገርህን ደመኛ
(አስተዳደር በዳይ የወገን ቀበኛ)

(ቀሪን ገረመው)
- የሰው ያለህ አለች
(ሀገሬን) ሰላሟን ስላጣች

ጽጌረዳ ብዕር
*****************

-     ቦታ የለም አሉኝ ሁሉም ተያዘና
(እዚህ ቀዬ መኖር) ሰው በሰው ሆነና
ሁሉንም አይቼ ዝም ብያለሁ
ሰው በሰው ተሆነ ምን አደርጋለሁ?

(ዮሐንስ አድማሱ)   
****************

የዝምታ ውይይት

አሌክሳንደር ስሚዝ የተባለው የስኮትላንድ ባለ ቅኔ ሲናገር ‹‹አትክልት በሚገኝበት መስክ ላይ ቀናትን አሳልፋለሁ፡፡ ሌሊቶችን ደግሞ በመጻሕፍት ቤቴ አሳልፋለሁ ብሏል፡፡

ፍላጎቶቼ በአበቦቼና በመጽሐፎቼ መሀል የተከፈሉ ናቸው፡፡ አበቦቼ ያሁኑን ጊዜ ሲያስታውሱኝ፣ መጽሐፎቼ ደግሞ ያለፈውን ጊዜ ያስታውሱኛል፡፡

ወደ መጻሕፍት ቤቴ ስገባ ታሪኮች በመላ እፊቱ ይከሠታሉ፡፡ የዓለምን የንጋት አየር እተነፍሳለሁ፡፡ የገነት ጽጌሬዳዎች ሽታ ተበርዞበታል፡፡ የመጀመርያዎቹ የንጋት ወፎች ዜማም ከእናታችን ከሔዋን ሳቅ ጋር ተደባልቆ ይሰማናል፡፡ ፒራሚዶች ሲሠሩ እመለከታለሁ፡፡ የታላቁ እስክንድር ሠራዊት ሲንጫጫ አዳምጣለሁ፡፡ በካምቢዜስ ሠራዊት ግስገሳ የመሬቱ አዋራ ሲነሣ ይታየኛል፡፡

በአንድ ቴአትር ቤት እንደተቀመጠ እሆናለሁ፡፡ የቴአትሩ ሰገነት ጊዜ ነው፡፡ ቴአትሩም የዓለም ታሪክ ነው፡፡ ትዕይንቱ በጣም አስገራሚነት አለው፡፡

ታላቅ ግርማ….. ኤልቆ መሳፍርት የሆነ ሰልፍ የከተማዎች ቃጠሎ ጭስ…. ከሠረገላዎች ኋላ ኋላ ድል አድራጊዎቻቸውን ተከትለው የሚሮጡ ምርኮኞች በቅደም ተከተል በፊቴ ያልፋሉ፡፡……. ሆሜርን አነሣና ኤሺልን……. በጦር ሜዳው ላይ እንዳለ በርታ እለዋለሁ፡፡ ሕዝብ ያልሰፈረባቸው የሶርያ ሜዳዎች ዝምታ፣ የፓትርያርኮች መምጣት እና መሔድ አብርሃምና እስማኤል ይስሐቅም በመስኩ ላይ ሳለ…… ርብቃ ውሃ ስትቀዳ ……..ኤሳው በምድረ በዳው ፀሐይ ዓይኖቹ ቀልተው…… እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች በብሉይ ኪዳን ውስጥ አገኛቸዋለሁ፡፡……. ግሩም ድንቅ ነው፡፡…… ብሏል፡፡

እውነትም ሥነ ጽሑፍ ማለት እውነትንና ውበትን መተርጐም ማለት ነው፡፡ ሰውን አዋቂና ጨዋ ያደርጉታል፡፡ ለማሰብ እስኪያቅተው ድረስ ከፍተኛ ድካም ሲሰማው አንድ መልካም መጽሐፍ አንሥቶ የመጽሐፉ ደራሲ የኖረበትን ዓለምና የአዕምሮውን አስተሳሰብ ወደ አዕምሮው በማስገባት ቀደም ሲል ያደከመውን ጉዳይ ጠርጎ ያስወጣል፡፡

ውበትን ድምፅ የሌላት የተፈጥሮ ዜማ ናት እንደምንል ሁሉ፣ በመጽሐፍ ታትሞ የተላለፈ መልዕክትም የዝምታ ውይይት በዓል ነው ይባላል፡፡
(ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ፤ ዓለም የሠራተኞች ናት)

*****************
ነፍስና አንጎል

ነፍስና አንጎል አንድ ናቸው፡፡ ከአንጎል የተለየ ሐሳባችንን የምናመነጭበት ሌላ የሰውነት ክፍል የጥአሠራሩ ዓይነት መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህም በላይ በዚሁ በአንጎላችን ላይ የሚደርስብን ማናቸውም ጉዳት ሐሳባችንን እንደሚያሰናክልብን በብዙዎች ሰዎችና እንደዚሁም በእንስሳት ላይ የታየና የተረጋገጠ ነገር ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህም የሚያመለክተው ማናቸው ሐሳባችንና እውቀታችን ሁሉ የሚመነጨው ከአንጎል እንጂ፤ ከሌላ እንዳልሆነ ነው፡፡

በእውነቱ ማናቸውም የሰው ሐሳቡና የችሎታው ደረጃ በአንጎሉ ሁኔታ መጠን ወይም ክብደት ሊፈርድ ይቻላል፡፡ በእንስሳትም ላይ እንዲሁ ነው፡፡ ለምሳሌ አንጎላቸው ትንሽ የሆነ ዝቅተኞች እንስሶች የሐሳብ ችሎታቸውም በዚያው ልክ ዝቅተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከትናንሾቹ እንስሳት ወደ ትላልቆቹ እንስሳት የተሻገርን እንደ ሆነ ከበፊተኞቹ የበለጠ የአንጎል ክብደትና የተጠላለፉ የዚሁ የአንጎል የደም ሥሮች በብዙ ስለምናገኝ የሐሳባቸውም ደረጃ በዚያው መጠን ከፍ ያለ ሆኖ እንመለከታለን፡፡ ከእንስሳትም ወደ ሰዎች የተሻገርን እንደሆነ የአውሮፓውያንና የአፍሪካውያን የሐሳብ ችሎታ ልዩነት ከዚሁ የመጣ ነገር መሆኑን እንድንገነዘብ ግዴታ ይሆንብናል፡፡ ይኸውም የአፍሪካውያንን ወይም የእስያውያንን አንጎል ከአውሮፓውያን ጋራ ብናስተያየው፤ የነዚህኞቹ ከነዚያኞቹ በክብደትም ሆነ በሥሮቹ ብዛት ወይም ደግሞ ብዙ ፎስፈረስ በማቅረብ ብዙ ብልጫ እንዳለው እናገኛለን፡፡ በሁለቱም ወገኖች መካከል የሚታየው የሐሳብ ችሎታ ልዩነት ከዚሁ የተፈጠረ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ በእውነቱ የሚያመለክተው አንጎልና ነፍስ የተባሉት ሁለቱ ነገሮች ያው መሆናቸውን ነው፡፡ የምናስበውና ማናቸውንም ነገር የምናደርገው በአንጎላችን በኩል መሆኑን ማመን አለብን፡፡
(የማነ ገብረ ማርያም፤ የፍልስፍና ትምህርት፣ 1954)

*************

የፋሲልን ነፍስ ይማር

ለመንግሥታቸውና ለሕዝባቸውም በሰፊው ከማሰባቸው የተነሳ ከርሳቸው በፊት የነበሩት ነገሥታት ያልሰሩትን የዓባይን ድልድይ አንዱን በአፈረዋናት፤ አንዱን በአዳቤት ሁለት ድልድይ አሠርተውለት ከሞቱ በኋላ፣ ነጋዴውም መንገደኛውም ሲያልፍ የፋሲልን ነፍስ ይማር እያለ ያርፍ ነበር ይባላል፡፡ መሃል በጌምድርም የርብን ድልድይ፣ ከጎንደር አጠገብ የአንገረብን ድልድይ ያን ጊዜ አሠርተውት የነበረው እስከ ዛሬ ፍራሹ አለ ይባላል፡፡

በዚህ ጊዜ ወይም ከዚያ ወዲህ ዘፋኝ እንዲህ አለች ይባላል፡፡
ርብና ዓባይ መንጠቅ የለመዱ
እንደ ልማዳቸው ሰውን እንዳይገድሉ
በፋሲል ዳኝነት ተፈጥመው ሔዱ፡፡
ርብና ዓባይ ሸፍተው ሲኖሩ
አላፊ አግዳሚውን ከጎራ እያሠሩ
በትላልቅ ድንጋይ ተደብድበው ቀሩ፡፡
አብርሃም ነው ጣና እንግዳ ተቀባይ
ከቤቱ ቢመጡ ርብና ዓባይ
ሌቦች ናቸው ሳይል ግብራቸውን ሳያይ
መንገዱን መራቸው እንዳይሔዱ በላይ፡፡
የግጥሙን ምክንያት ዓባይ በጣና ባሕር ላይ ሔዶ የሚለይበት ባሕር ዳር ጊዮርጊስ ስለሆነና ርብም የሚገባው ጣና ስለሆነ ነው፡፡
(ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፤ ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ፣ 1958)
*****************

‹‹ሳላድ››

ፈርንጆቹ ‹‹ሳላድ›› ይሉታል፡፡ ከምሳና ከራት ጋር ጥሬውን ለምግብነት የሚውል ማንኛውም አትክልት ነው፡፡ በተለምዶ አጠራርም ‹‹ተከታይ አትክልት›› ይሰኛል፡፡ በነጠላም ሆነ በድብልቅ ‹‹ተከታይ አትክልትን›› ለማዘጋጀት ሎሚ አስፈላጊ ነው፡፡ ሎሚ የጨጓራን ተግባር ለማቀላጠፍና የሆድ ድርቀትን ለማስወገድም ይረዳል፡፡ ትውከትን፣ የጉሮሮ ችግሮችንና የአሲድ ብዛትንም ያስወግዳል፡፡ የሎሚን ጭማቂ ከውሃ ጋር ደባልቆ መጠጣቱ ይመረጣል፡፡ ሎሚ በተራራ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሁሉ የልብ ወዳጅ ነው፡፡ የሎሚ ጭማቂ ኢንፍሎዌንዛን፣ ወባንና ጉንፋንን ይከላከላል፡፡ ለትኩሳትም ግሩም መድኃኒት ነው፡፡ በሆድ አካባቢ ህመም ሲሰማ፣ የሎሚን ጭማቂ መጠጣቱን ለፈጣን ፈውስ ይረዳል፡፡ የጥርስንና የአጥንትን ጤና በመጠበቅ በኩልም ሎሚ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ ሎሚ ውሃ፣ ቅባት፣ ካርቦኃይድሬት፣ ካልስየም፣ ፎስፈረስ፣ ብረት፣ ቫይታሚን ሲ እና ፕሮቲን አለው፡፡
(ዓባይነህ አበራ፤ ዶክተር ለራሴ)

*************************
ገራገር

አዛውንቱ በ94 ዓመታቸው ወለዱ
ህንዳዊው ገበሬ አዛውንት በ94 ዓመታቸው ልጅ በመውለዳቸው የዓለም ሽማግሌው አባት ልባል ይገባኛል ብለዋል፡፡

እኚህ ነዋሪነታቸው በሰሜናዊቷ ህንድ የሆነው አዛውንት ራማጀት የሚባሉ ሲሆን፣ እድሜያቸው 50ዎቹ ውስጥ ከሚገኙት ባለቤታቸው ከሻኩንታላ፣ ካራሞጂት የተባለውን ወንድ ልጃቸውን ተገላግለዋል፡፡

አዛውንቱ አዲሱ ልጃቸው ሲያድግ እንደሚመለከቱና ጥቁር እባብ ካልነደፋቸው በስተቀር እንደማይሞቱ ደይሊ ሜይል በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

ሕፃኑን ያዋለዱት ሐኪሞች ከአንድ ወር በፊት ወደዚች ዓለም የተቀላቀለው ሕፃን ሙሉ ጤነኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 21ኛውን ልጃቸውን ወልደው ሽማግሌው አባት ተብለው የተሰየሙት አዛውንቱ ናሙንን በእድሜ የሚበልጧቸው የ94 ዓመቱ ራማጃት፣ ሽማግሌው አባት ተብለው በመሰየም ሪከርዱን ሊሰብሩ እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡

***********

ለሁለት ሰዓት አቅራቢያ በረዶ ውስጥ ራሱን የዘፈዘፈው

ኔዘርላንዳዊው ዊም ሆፍ ስለ አየር ንብረት ለውጥ እውቅናን ለማሰራጨትና የዓለም ሪከርድን ለመስበር  በረዶ በተቀላቀለበት የውኃ ገንዳ ውስጥ ራሱን ዘፈዘፈ፡፡
ይህ በቅጥያ ስሙ ‹‹የበረዶው ሰው›› የተባለው የ51 ዓመቱ ጎልማሳ፣ የመዋኛ ፓንት ብቻ በማድረግ በረዶ በተቀላቀለው ውኃ ውስጥ ለ1፡50 ደቂቃዎች እራሱን እንደዘፈዘፈ የዜና አውታሮች አስነብበዋል፡፡

ጎልማሳው የፈረንጆችን የአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ራሱን በውኃ ገንዳ ውስጥ በመዘፍዘፍ በዓለም ተመዝግቦ የነበረውን ሪከርድ በስምንት ደቂቃዎች አሻሽሏል፡፡
**********