Saturday, May 25th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

በዓል በኮንዶሚኒየም

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በምዕራፍ ብርሃኔ

‹‹ዓምና ገናን ያከበርኩት ከምወዳቸውና ቢያንስ ለ30 ዓመታት አብሬአቸው ከኖርኩት ጎረቤቶቼና ጓደኞቼ ጋር ነበር፤›› ያሉን የ65 ዓመቷ ወ/ሮ አበራሽ ሰይፈ ሚካኤል ናቸው፡፡

ወ/ሮ አበራሽ በልደታ የመልሶ ማልማት እቅድ መሠረት ከተነሡት የቀበሌ ቤቶች ነዋሪ የነበሩ ሲሆን፣ ባሁኑ ወቅት ጎተራ ከሚገኘው ኮንዶሚኒየም ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የአራት ልጆች እናቷ በኮንዶሚኒየም መኖር ከጀመሩ ከአንድ ዓመት በላይ ሲሆናቸው፣ በኮንዶሚኒየም ቤታቸው ሦስት በዓላትን አሳልፈዋል፡፡ ይሁንና አሁን የሚኖሩበት ባለሁለት መኝታ ቤት ኮንዶሚኒየም ሰፋ ያለና ለኑሮ የተመቸ ቢሆንም፣ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር ዕለቱን ብቻቸውን የማሳለፋቸውን ነገር ሲያስቡት ደስተኛ እንዳልሆኑ ይናገራሉ፡፡

‹‹ሰው መቼም ፍላጐቱ አይቋረጥም፡፡ የተሻለ መኖርያ ቤት ማግኘቴን ባልጠላውም፣ የነበረኝ ማኅበራዊ ሕይወት ግን ስለተቋረጠ አሳዝኖኛል፤›› ያሉት ወ/ሮ አበራሽ፣ ልደታ በነበሩበት ጊዜ ዶሮም ይሁን በግ ቢያርዱ ምሳ አንዳቸው ቤት፣ ራት ሌላኛዋ ጎረቤት እየሔዱ መብላትና ቡናውንና ጠላውን መጣጣቱ እጅግ እንደሚናፍቃቸው ገልጸዋል፡፡

የወ/ሮ አበራሽ ጓደኞችና ጎረቤቶች ከልደታ ሲነሡ ዕጣ እንደወጣላቸው በየቦታው ስለተበታተኑ አልፎ አልፎ በስልክ እንጂ በምንም እንደማይገናኙ ወ/ሮ አበራሽ ተናግረዋል፡፡

‹‹ኑሮን በኮንዶሚኒየም ከጀመርኩ በኋላ ከጎኔ ያለውን ስቱዲዮ ተከራይተው የሚኖሩ ሁለት ወጣት ሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ልጆች በየፊናቸው ተበታትነው የዕለት ጉርሳቸውን ለማሟላት ጧት ወጥተው ማታ የሚገቡ ናቸው፡፡ ሁለት ዓመት በዓሎች ላይ ሁለቴ በቤቴ ራት እንዲበሉ ብጋብዛቸውም፣ ሴቶቹ ግን በዓልን በየቤተሰቦቻቸው ስለሚያሳልፉ ሊገኙልኝ አልቻሉም፤›› ያሉት ወ/ሮ አበራሽ፣ ወጣቶቹ የእርሳቸውን ቤት የዓመት በዓል ፀበል ጸዲቅ ባለመቋደሳቸው ደስተኛ አይደሉም፡፡ ቢሆንም ግን ከሌላ መንደር የመጡ አንዲት የዕድሜ አቻቸው ጋር ቀን ቀን ቡና ስለሚጠጡ ከእርሳቸው ጋር በዓሎቹን በጉርብትና እንዳሳለፉ አስታውሰዋል፡፡

የ15 ዓመቷ የወ/ሮ አበራሽ ልጅ ሰላማዊት መንገሻ በበኩሏ፣ ‹‹ልደታ በነበርንበት ጊዜ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር ከሰፈር ጓደኞቼ ጋር ስንደሰት እንውል ነበር፤›› ብላለች፡፡ ሰላማዊት አባቷ በሞት ከተለዩዋት ጊዜ ጀምሮ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር እህቶቿን በመያዝ በየጓደኞቿ ቤት በመዞር የአባቷን ያለመኖር ክፍተት ትሞላ ነበር፡፡ አሁን ግን ያ ሁሉ ግርግር ቀርቶ በዓልን በቤታቸው ብቻ እንዲያሳልፉ እንደተገደዱ ገልጻለች፡፡

የሰላማዊት እናት የኑሮውን ቀዳዳ ለመድፈን የጎረቤቶቻቸውን ልብስ በማጠብና ጎረቤቶቻቸው የሚፈልጓቸውን ቅመማ ቅመም በማዘጋጀት ይኖራሉ፡፡ ልጆቻቸውም ለኮንዶሚኒየም ጎረቤቶቻቸው እንጀራ፣ ዳቦ፣ ወተትና ቲማቲም፣ ሲጋራም ለመግዛትና ቆሻሻን ለመድፋት ከተላኩ በኋላ፣ ለብስኩት መግዢያ የሚሰጣቸውን ሳንቲም እያጠራቀሙ ደብተር፣ እርሳስና እስክሪቢቶ ይገዙበታል፡፡

በጀሞ ሳይት በሚገኙት ኮንዶሚኒየሞች ደግሞ ከየቦታው በመልሶ ማልማት ስም የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ይገኛሉ፡፡ ከአራት ኪሎ ተፈናቅለው ከመጡት ውስጥ ያነጋገርናቸው ዕድሜያቸው በሠላሳዎቹ መጨረሻ አካባቢ የሚገኙትን ባልና ሚስት ጽጌረዳ መልካሙና ተመስገን ጌታቸውን ነበር፡፡

ተመስገን በዓል ሲመጣ ከጎረቤቶቹ ጋር በመጠራራት ይደሰት ነበር፡፡ በቀድሞ መኖርያው በግም ይሁን ዶሮ የሚያርድበት ቦታ ነበረው፡፡ አሁን ግን መኖርያው ከሆነው ከሁለተኛ ፎቅ ወደ ምድር በመውረድ ዶሮንም ሆነ በግን ቢያርድም፣ እንደበፊቱ ቤቱ ግን ምቹ እንዳልሆነ ይገልጻል፡፡

‹‹ከባለቤቴ ጋር እዚህ መኖር ከጀመርን ይኼ ሁለተኛ ዓመት በዓላችን ነው፡፡ የገና በዓልን በተሻለ የምናሳልፍ ሲሆን፣ የ2003 ዓ.ም. የዘመን መለወጫን ግን ፍጹም ደስ በማይል ስሜት አሳልፈናል፤›› ያለው ተመስገን፣ በእንቁጣጣሽ ጊዜ አብዛኛው የኮንዶሚኒየም ነዋሪ ባለመግባቱ በብቸኝነት ከባለቤቱ ጋር ብቻ እንዳሳለፈ ገልጿል፡፡ በአሁኑ የገና በዓል ግን እነ ተመስገን አዳዲስ ጎረቤቶችን ስላፈሩ ከዱሮ ወዳጆቻቸው ጋር በስልክ መልካም ምኞትን በመለዋወጥ የበዓል ምግቡንና ፀበል ፀዲቁን ደግሞ ከአዳዲሶቹ ጎረቤቶቻቸው ጋር እንደሚያሳልፉ ገልጿል፡፡

‹‹የኮንዶሚኒም ኑሮ ዘመናዊነትን ይጠይቃል፡፡ በአበሻ የኑሮ ዘዬም እጅግ ከባድ ነው፤›› ያለችው ጽጌረዳ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ዶሮ ከታረደ በኋላ የሚገዛው በግና የቅርጫ ሥጋ አሁን እንደማይኖር ገልጻለች፡፡ እነ ጽጌረዳ በፊት በኩሽናቸው ውስጥ የቅርጫው ሥጋ ተዘልዝሎ ቋንጣ ይደረግ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን እንኳን ቋንጣን ዘልዝሎ ለማድረቂያ ልብስ ማስጫም በቅጡ እንደሌላቸው ትናገራለች፡፡

‹‹የሚያዋጣው የብሉልኝ፣ ጠጡልኝና እዩልኝ ዓይነት የተንቦረቀቀ የኑሮ ሒደትን ሰብስብ አድርጎ ወደ ትንሽ የኮንዶሚኒየም ጓዳ ማምጣት ነው፤›› ያለችው ጽጌረዳ፣ ኑሮን ሰብሰብ ባለ መልኩ ማስኬድን ኮንዶሚኒየም እንዳስተማራቸው ገልጻለች፡፡

‹‹በዓል ሲመጣ ከቄጤማ መጎዝጎዝ ጀምሮ በርከት ያሉ የምግብ ዓይነቶች በቤታችን ውስጥ ሲኖር ደስ ይለኛል፡፡ በፊት ከደጃፋችን ወጣ ስንል የችርቻሮ ከሰልም ሆነ ቄጤማው ይገኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ቄጤማም ሆነ ከሰል ለመግዛት ቀድሞ ማሰብና መዘጋጀትን ይፈልጋል፤›› ስትል ጽጌረዳ ገልጻለች፡፡

የኮንዶሚኒየም ኑሮ ማኅበራዊ ሕይወቱ ቀዝቃዛ እንደሆነ በኮንዶሚኒየም የሚኖሩ ግለሰቦች ይናገራሉ፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ ግላዊ ሕይወትን መምራት ራስን ካላስፈላጊ ወጪ መገላገል ነው ብለው የሚያምኑም አይታጡም፡፡ ይሁንና በአንድ መንደር ተሰባስበው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ተበታትነው በየኮንዶሚኒየሙ መኖር ሲጀምሩ፣ የታመመን መጠየቅ፣ የወለደን ማረስ፣ የደከመን መደገፍ፣ ችግር ሲፈጠር መረባረብና የመሳሰሉትን የአኗኗር ዘይቤዎችን እንደሚናፍቃቸው ይናገራሉ፡፡ ከዚያም በላይ ደግሞ ኑሮን ለማሸነፍ ትንሽም ይሁን ትልቅ የሥራ ዓይነትን በመሥራት ይኖሩ የነበሩት፣ ‹‹አሁን ኑሮውን ለማሸነፍ ሳይሆን፣ ከኑሮ ጋር ግብግብ ፈጥረናል፤›› በማለት የኮንዶሚኒየም ኑሮን ሲያማርሩ ይደመጣሉ፡፡