በምዕራፍ ብርሃኔ
የ23 ዓመቷ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ፋክልቲ ተማሪ፣ ሁለት ብርጭቆ አልኮል ከተጎነጨች በኋላ በሕይወቷ ውስጥ የተፈጠሩትን ክሥተቶች ዘርግፋ ለጓደኞቿ ማውጋቷን ተያይዛዋለች፡፡
ቀሰም(ስሟ ተለውጧል) የእናትና የአባቷ ትዳር በጭቅጭቅ በልቅሶ የተሞላ በመሆኑ፣ የራሴ የምትለውና የምታፈቅረው ሰው እንዲኖራት ፍጹም ትታትር ነበር፡፡ ‹‹ከልብ ካለቀሱ እምባ አይገድም›› ነውና ነገሩ፣ የ16 ዓመት ወጣት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሆና አንዱን ወጣት ትተዋወቃለች፡፡ የሁለቱ ፍቅረኛሞች የፍቅር ጊዜ ግን ከሦስት ዓመት መዝለል አልቻለም፡፡ ሌላ ጓደኛ ለማግኘት ፍለጋዋን ቀጠለች፡፡ ፍላጎቷም ተሳክቶ ከመጀመርያው ጓደኛዋ ጋር በተለያየች ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ በግል የኮምፒውተር ሥልጠና ኮሌጅ ውስጥ በአስተማሪነት ከሚያገለግል ወጣት ጋር ፍቅርን ማጣጣም ጀመረች፡፡ ይሁንና ከዚህኛው ወጣት ጋርም የነበራት ግንኙነት ከሁለት ዓመት በላይ መዝለቅ አልቻለም፡፡
‹‹እኔ እኮ የሚገርመኝ ከልቤ ሳፈቅራቸው ለምን ትተውኝ እንደሚሔዱ ነው፤›› ያለችው ቀሰም፣ ሁለተኛው የፍቅር ግንኙነቷ በመቋረጡ፣ ከዚህ በኋላ ወንድ ማፍቀር ትርጉም የለሽ ስለሆነ፣ ‹‹አርፌ ስሜቴን ለምን አላስተናግድም›› በሚል ውሳኔ ፍለጋዋን አቆመች፡፡
እርሷ እንደምትለው ከሆነ፣ የተፈጠረችው ለማፍቀር እንጂ፣ ለመፈቀር አይደለም፡፡ ስለዚህ ከሁለተኛው ፍቅረኛዋ ጋር ከተለያየች በኋላ ዕድሜዋ 23 እስኪደርስ ድረስ ከ28 ወንዶች (ማስታወስ የቻለችው ብዛት) ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽማለች፡፡
‹‹ከሁለቱ ፍቅረኞቼ ጋር ግብረ ሥጋ ለመፈጸም ስናስብ በቅድሚያ ያደረግነው የኤች. አይ. ቪ ምርመራ ማድረግን ነው፡፡ ከሦስት ወራት ቆይታ በኋላም እንዳላረግዝ ብቻ እየተጠነቀቅን፣ ያለኮንዶም እንወጣ ነበር፤›› ያለችው ቀሰም፤ ከ28ቱ ወንዶች ጋር ስትወጣ ግን አንድም ቀን ኮንዶም አለመጠቀሟን አልሸሸገችም፡፡
ቀሰም ታሪኳን ለጓደኞቿ በምትናገርበት ጊዜ መናገር እስኪያቅታት ድረስ ሰክራ የነበረ ሲሆን፣ ጓደኞቿ እንዴት ሆነው ይሰሟት እንደነበረና ማንስ ሲሰማት እንደነበረ ማስተዋል ተስኗት ነበር፡፡ ከስካር ውጪ በነበረችበት ጊዜ፣ ታሪኳን በጠለስ ዐምዳችን ላይ ማስተናገድ እንደምንፈልግ ጠይቀናት እሺታዋን ከገለጸችልን በኋላ፣ ‹‹ይሄ ታሪኬ ማንን ከምን ያድን ይሆን? ስትል ጠይቃናለች፡፡
‹‹በሕይወቴ ለሦስተኛ ጊዜ ያወጣኝ ወንድ በእኛ ግቢ (ካምፓስ) የሚማር ሲሆን፣ ሁለታችንም አብረን መጠጣት እንፈልግ ነበር፤›› ያለችው ወጣቷ፣ ሕይወቷን ያጨለመባት አጋጣሚን ትናገራለች፡፡ ወጣቱ ተማሪ ከእርሷ በፊት የተለያዩ የሴት ጓደኞች የነበሩት ሲሆን፣ በሚማርበት ግቢ ‹‹አተራማሽ›› ተብለው ከሚጠሩት ተማሪዎች ውስጥ አንዱ ነበር፡፡
‹‹እኔ የፈለግኩት ከልጁ ጋር አብሮ ጠጥቶ መለያየትን እንጂ መውጣትን አልነበረም፡፡ ነገር ግን ከአራት ብርጭቆ አልኮል መጠጥ በኋላ፣ እጅግ ሰክሬ ስለነበር እንኳን ካንተ ጋር አልወጣም፤ ለማለት ይቅርና፣ እንድንጠቀምበት የሰጠኝን ኮንዶም ከእሽጉ ለማውጣት እንኳን ተስኖኝ ነበር፤›› ያለችው ቀሰም፣ ኮንዶሙን ከእሽጉ ለማውጣት ስላቃታት በመወርወሯ ያለ ኮንዶም ግንኙነት መፈጸማቸውን ትናገራለች፡፡
አብሯት የነበረውም ወጣት ስለ ውሳኔዋ እርግጠኛ መሆኗን ሲጠይቃት፣ እርግጠኛ እንደሆነችና ችግር እንደሌለው ነግራው ያለ ኮንዶም ከወጣቱ ጋር ወጥተዋል፡፡
ለእንደ ቀሰም ያሉ ወጣቶች ራስን ከኤች. አይ. ቪ ኤድስ ለመከላከል፣ ኮንዶም አስፈላጊ ነው ብሎ መንገሩ ሞኝ ቢያስብልም፣ ያለኮንዶም መውጣትን ሲያስቡት ግን በጭንቅላታቸው ውስጥ የሚያቃጭል ጩኸት ከሌለ፣ ኮንዶምን ከእሽጉ የማውጣት ትዕግስት በማጣት ለበሽታው የመጋለጥን እድል ያሰፋዋል፡፡
‹‹ከልጁ ጋር አድሬ በማግሥቱ ስካር በደንብ ስላልለቀቀኝ ቤቴ ሔጄ ተኛሁ፡፡ ከዚያም ወደ አመሻሹ ወደ መኝታዬ ስሔድ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ከልጁ ጋር የወጣሁት ያለኮንዶም ስለነበር፣ የነበርኩበት የወር አበባ ዑደት ደግሞ በቀላሉ እንዳረግዝ ስለሚያደርገኝ ቶሎ ብዬ የወሊድ መከላከያን እንክብል መውሰድ ነበረብኝ፤›› ያለችው ቀሰም ግንኙነት በተፈጸመ በ72 ሰዓት ውስጥ የሚወሰዱትን ሁለት የወሊድ መከላከያ እንክብሎችን በአሥራ ሁለት ሰዓታት ልዩነት ወስዳለች፡፡
‹‹ደግሞ እኮ ስህተቶቼ የሚታወሱኝ ቀስ በቀስ እያሉ ነው:: እርግዝናም እንዳይፈጠር የወሊድ መከላከያ እንክብል ስወስድ፣ ኤች. አይ. ቪ እንዳይዘኝ ደግሞ ምናባቴ ልውሰድ?›› ያለችው ወጣቷ፣ ይሄኛው ሩጫዋ ግን የዘገየ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ እንደምንም ብላ ሦስቱን ወራት ካሳለፈች በኋላ፣ የደም ምርመራ ስታካሒድ የፈራችው አልቀረም፤ የኤች. አይ. ቪ ቫይረስ በደሟ ተገኘ፡፡
‹‹ለእኔ ከዚህ በኋላ ሕይወት የለም፡፡ ፍጥረቴ በአጭሩ ለመቀጨት ስለሆነ፣ ከዚህ በኋላ 20 ዓመታትን መኖር አልፈልግም፤›› ያለችው ቀሰም፣ ቢሆንላት ኖሮ በ25 ዓመቷ መሐንዲስ ለመሆን እንደነበር ተናግራለች፡፡


