Wednesday, Jun 19th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የባህል ስፖርቶች በአዲስ አበባ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በደረጀ ጠገናው

የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ቱሪዝም ቢሮ፣ ከኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን፣ ከአዲስ አበባ የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን፣ እንዲሁም ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር ያዘጋጀው የባህል ስፖርት ፌስቲቫል ባለፈው ዓርብ ተጠናቅቋል፡

፡በውድድሩ አሥሩም ክፍለ ከተሞች፣ ልዩ ልዩ የስፖርት ተቋማትና አደረጃጀቶች የታደሙበት ሲሆን፣ እነዚህም ፈረስ ስፖርት፣ ፈረስ ሸርጥ፣ ፈረስ ጉግስ፣ የገና ጨዋታ፣ የገበጣ ውድድሮችና የትግል (ግብግብ) ውድድሮች ይገኙባቸዋል፡፡ በትግል ከ48 እስከ 52 ኪሎ ግራም፣ ከ53 እስከ 57 ኪሎ ግራም፣ ከ58 እስከ 62 ኪሎ ግራም፣ ከ63 እስከ 67 ኪሎ ግራም እና ከ68 እስከ 72 ኪሎ ግራም ካታጎሪዎች ተካሒዷል፡፡

በጃን ሜዳ ስፖርትና ትምህርት ማዕከል ከታኅሣሥ 23 እስከ 29 ቀን 2003 ዓ.ም ለተከታታይ ሰባት ቀናት በተከናወነው ፌስቲቫል፤ ከአዲስ አበባ ከ10 ክፍለ ከተሞች በተጨማሪ የመከላከያ፣ የጄኔራል ኃየሎም አርአያ እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ እና ለገጣፎ በክለብ ደረጃ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ዘመናዊና ሳይንሳዊ በሆነ መልክ ተደራጅቶና ሕግ ወጥቶላቸው እየተዘወተሩ ያሉት የባህል ስፖርቶች ስድስት ደርሰዋል፡፡

የመላው አዲስ አበባ የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል፣ የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ መስፍን ከበደ፣ የባህል ስፖርቶች በተለይም የኢትዮጵያ ባህሎች ከሌሎች አገሮች ለየት የሚሉበት መሠረታዊ ጉዳዮች እንዳለ ገልጸው፣ እነዚህን ውብና ድንቅ ባህሎች ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ በፌዴራል ደረጃ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ስፖርቱ በአዲስ አበባ ደረጃ ሲካሔድ የዘንድሮው ለ16ኛ ጊዜ መሆኑን ያስረዱት አቶ መስፍን፣ እያንዳንዱ የባህል ስፖርት የራሱ ፌዴሬሽን እንዲኖረውና ስፖርቱም የዘመናዊ ስፖርት እድገት መሠረት ስለመሆኑ፣ ቀልብን የሚስቡና የሚማርኩ ከእኛ የፈለቁ ጌጦች ስለመሆናቸው፣ በጨዋታዎቹ ለመሳተፍ ልዩ ተሰጥኦ ሳይጠይቁ ማንኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል ማካተት እንደሚቻል፣ በሀገር በቀል መሣርያዎች ያለተጨማሪ ወጪ ለመጫወት የሚያስችሉና ሁሉንም ጾታ ማሳተፍ የሚችሉ ስለመሆኑ ከፍተኛ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

ከነዚህ የባህል ስፖርቶች በተለይ የገና ውድድር፣ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ከአዲስ አበባ በተሻለ እየተዘወተረ እንደሚገኝ ያስረዱት ኃላፊው፣ በአሁኑ ወቅት በሐረር ውስጥ የተገኘውና ከአዲስ አበባ በስተቀር በፌዴራል ደረጃ ሕግና ደንብ ወጥቶለት እየተለመደ የመጣውን ሻሕና ቡብ (ዳማ የሚመስል የባህል ስፖርት) በአዲስ አበባ ደረጃ ለማስጀመር በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡