Thursday, May 23rd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የሰሞኑ የገበያ ውዥንብር

E-mail Print PDF
User Rating: / 11
PoorBest 

አንዋር ሙሰማ በሃያዎቹ ዕድሜ ክልል ላይ የሚገኝ በሸቀጣ ሸቀጥ ችርቻሮ ንግድ ላይ የተሠማራ ወጣት ነው፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 52 በተለምዶ ሰንጋ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ስድስት ካሬ ሜትር የሚገመተው መደብሩ በተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች ተሞልቷል፡፡

 

አንዋር ሰሞኑን ከመንግሥት በተሰጠው መመሪያ መሠረት የሚሸጣቸውን ዕቃዎች የዋጋ ዝርዝር ለእይታ አመቺ በሆነ ሥፍራ ለጥፏል፡፡ ከአንዋር መደብር በቅርብ ርቀት የሚገኙ ሁለት ሱቆች ታሽገዋል፡፡ የመታሸጋቸው ምክንያት ነው ተብሎ በማሸጊያው ወረቀት ላይ የሚታየው፣ ‹‹የዋጋ ተመን በተነገረው መሠረት ባለመለጠፋቸው›› የሚል ነው፡፡

መንግሥት ከገና ዋዜማ ጀምሮ ተግባራዊ ባደረገው መመሪያ መሠረት አንዋር፣ እንደ የምግብ ዘይት፣ ሳሙና፣ ስኳርና የመሳሰሉ ዕቃዎችን በአዲሱ የዋጋ ተመን መሠረት እየሸጠ ነው፡፡ በመደብሩ በርከት ያሉ የተለያዩ የታሸጉ የምግብ ዘይት ምርቶችም ይታያሉ፡፡

እንደ አንዋር ገለጻ፣ እነዚህን የተለያዩ የዘይት ምርቶች አንዱን ሊትር ከ25 እስከ 27 ብር በላይ በሆነ ዋጋ የገዛቸው ናቸው፡፡ መንግሥት አንዱን ሊትር ዘይት በ16.50 ብር ሽጡ በማለቱ ከእያንዳንዱ ሊትር ከአስር ብር በላይ በመክሰር እየሸጠ ነው፡፡

ከመመሪያው በፊት አንዱን ሊትር እንደ ዘይቱ ዓይነት 31 ብር እና 32 ብር ይሸጥ እንደነበር የሚገልጸው አንዋር፣ በአዲሱ የዋጋ ትመና መሠረት ከዘይት ብቻ ከ1,200 ብር በላይ እከስራለሁ ይላል፡፡

ቦምብ ተራ
መርካቶ ውስጥ በተለምዶ ቦምብ ተራ የሚባለው አካባቢ የሸቀጣ ሸቀጦች ዋነኛ መገበያያ ሥፍራ ነው፡፡ በዚህ አካባቢም ሸቀጦችን ከውጪ የሚያስመጡ፣ በጅምላ የሚያካፋፍሉና በችርቻሮ የሚሸጡ ነጋዴዎች አሉ፡፡ ሪፖርተር በአካባቢው ውዥንብር የተሞላበትን የግብይት ሥርዓት ትናንትና ሥፍራውን በቃኘበት ወቅት አስተውሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ታህሳስ 28 ቀን 2003 ዓ.ም. በአገሪቷ ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ ናቸው የተባሉ 584 ነጋዴዎችን በጽሕፈት ቤታቸው ጠርተው አነጋግረዋቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለኅብረተሰቡ በጣም አስፈላጊ ናቸው ያሏቸውን 16 ምርቶች የሚሸጡባቸውን ዋጋ አሳውቀዋል፡፡ በእለቱ አብዛኛዎቹ ነጋዴዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅሬታቸውንም ሆነ ጥያቄዎቻቸውን ለማሰማት ፈርተው ነበር፡፡ የዋጋ ጣሪያ ከወጣላቸው 16 ምርቶች ከነጋዴዎች ጥያቄ ያስነሳው ብቸኛ ምርት የምግብ ዘይት ነበር፡፡ በወቅቱም መንግሥት የምግብ ዘይት ዋጋን በድጋሜ እንደሚያስተካክል አስታውቆ ነበር፡፡

የመንግሥትን ዕርምጃ ተከትሎ ይህ ነው የማይባል ውዥንብር በአገሪቱ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ተፈጥሯል፡፡ በቦምብ ተራ ውስጥ ሸቀጣ ሸቀጦችን ከአስመጪዎች እየገዛች በመደብሯ ለቸርቻሪዎች የምትሸጠው አሚና መሐመድ፣ የመንግሥትን ዕርምጃ ትደግፈዋለች፡፡ እንደ አሚና ገለጻ፣ መንግሥት አሁን ያለውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ለሸቀጦች የዋጋ ጣሪያ ማውጣቱ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም ትላለች አሚና፣ መንግሥት ለዚህ ዕርምጃው ለነጋዴው የዝግጅት የጊዜ ገደብ ማስመቀጥ ይገባው ነበር፡፡ ስለሆነም ዕርምጃው ለሁላችንም ዱብዕዳ ነው የሆነብን ብላለች፡፡

ለወትሮ በገበያተኞች ይጨናነቅ የነበረው ይህ አካባቢ፣ የገበያተኞችን እግር ሲናፍቅ ተስተውሏል፡፡ አሚና እንደምትለው፣ ደንበኞቼ በአብዛኛው ሰፈር ውስጥ የሚቸረችሩ ሱቆች ናቸው፡፡ የመንግሥት ዕርምጃን ተከትሎ ሰኞና ማክሰኞ ወደ መደብሯ ጐራ ብለው ከመጠየቅ ውጪ ገዝቷት የሄደ ነጋዴ እንደሌለ አጫውታናለች፡፡ በመደብሯ ውስጥም መንግሥት የዋጋ ጣሪያ ካበጀላቸው ሸቀጦች መካከል የሆነው የዱቄት ወተተ በብዛት ተደርድሮ ይታያል፡፡ መንግሥት ለዱቄት ወተተ (450 ግራም) ያወጣው ዋጋ 72.50 ብር ሲሆን፣ በመደብሯ ውስጥ ያሉት ኒዶ፣ ኤስ-26፣ ፕሮሚልና ፕሮግረስ (ሁሉም 400 ግራም ናቸው) 65 ብር የሚል የዋጋ ተመን ተለጥፎባቸው አይተናል፡፡ አሚና እነዚህን የዱቄት ወተቶች በብዛት ከአስመጪዎች መግዛቷን ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡ ላለፉት ሁለት ቀናት የገዢዎች ቁጥር በጣም የቀነሰበትን ምክንያት አሚና ስታስረዳ፣ በየሰፈሩ የሚገኙ ሱቆች ሸቀጦችን አለመግዛታቸው ነው፡፡

በቦሌ አካባቢ አነስተኛ የሰፈር ሱቆችን ተዘዋውረን በጐበኘንበት ወቅትም መንግሥት ያወጣው የዋጋ ተመን በግልጽ በሚታይ ቦታ ተለጥፎ ተመልክተናል፡፡ ዘሪሁን አሸናፊ የተባለ አንድ ባለሱቅ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ መንግሥት ባወጣልን የዋጋ ጣሪያ መሠረት ከስረን እየሸጥን እንገኛለን፡፡ በሱቃችን ያለንን ዕቃ ሸጠን ገንዘብ እስካልያዝን ድረስ አሁን በወጣው አዲስ የዋጋ ተመን ከአከፋፋዮች መግዛት አንችልም፡፡ መርካቶ ከሚገኙት አከፋፋዮች በአዲሱ የዋጋ ተመን ለመግዛት አሁን በሱቄ ውስጥ ያሉትን ዕቃዎች መሸጥ አለብኝ የሚለው ዘሪሁን፣ ሰሞኑን የመርካቶ አከፋፋዮች ጋር ዋጋ ቢቀንስም፣ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሄዶ መግዛት እንዳቃተው ይናገራል፡፡

በተጻራሪው ቦምብ ተራ የሚገኘውን የአልሳም የሸቀጣ ሸቀጦች ሱቅ በጐበኝንበት ወቅት፣ በርካታ ገበያተኞች ሲስተናገዱ ተመልክተናል፡፡ ከአልሳም ሸቀጦችን ሲገዙ የነበሩት በአበዛኛው የጅምላ ሻጭ ነጋዴዎች ነበሩ፡፡ የአልሳም አንድ የሥራ ኃላፊ እንደገለጹልን፣ በፊት አንድ ነጋዴ በሳምንት ወይንም በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ አምስት ካርቶን ዕቃ ይገዛ ነበር፡፡ አሁን ግን መንግሥት ባወጣልን የዋጋ ጣሪያ መሸጥ ከጀመርን በኋላ አንዳንድ ነጋዴዎች ምናልባትም በቀን ከሦስት ጊዜ በላይ መጥተው በአንዴ ከአስር ካርቶን በላይ ይገዛሉ ብለዋል፡፡ ሪፖርተር የአልሳምን ሱቅ በጐበኘበት ወቅት ይህንን ተመሳሳይ ትዕይንት መመልከት ችሏል፡፡

መንግሥት ባወጣው የዋጋ ጣሪያ መሠረትም ሁሉም ዓይነት የዱቄት ወተት (400 ግራም) 64 ብር፣ ቢ-29 ሳሙና (200 ግራም) 4.95 ብር፣ ቢክ እስኪብርቶ 2.16 ብር የሚል የዋጋ ተመን በሱቁ ውስጥ ተለጥፎ ተመልክተናል፡፡ አልሳም በአሁኑ ወቅት ከመቶ ፐርሰንት በላይ ከስሮ እየሸጠ መሆኑንም የሥራ ኃላፊው ጨምረው ገልጸውልናል፡፡

ሆኖም ከአልሳም ኤስ-26 የተባለውን የዱቄት ወተት (400 ግራም) በ64 ብር የገዙ ነጋዴዎች፣ በየመደብሮቻቸው በተለያዩ ዋጋዎች ሲሸጡ ተመልክተናል፡፡ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ከተመለከታቸው አከፋፋዮች ውስጥ፣ ኤስ-26 የተባለውን የዱቄት ወተት 65 ብር፣ 66 ብር እና 131 ብር የሚሸጡ ነጋዴዎችን ተመልክቷል፡፡ ይህ ወተትም በአንዳንድ ነጋዴዎች 131 ብር ድረስ የሚሸጠው፣ ሰሞኑን በአካባቢው የመንግሥት ቁጥጥር ባለመኖሩ  መሆኑን አንድ ነጋዴ ገልጸውልናል፡፡

በዚሁ አካባቢ ፎዚያ አብዱልቃድር የተባለች አንድ ነጋዴ የተለያዩ የምግብ ዘይቶችን ከአስመጪዎች በመረከብ ታከፋፍላለች፡፡ ፎዚያ አሁን የምግብ ዘይት የምትሸጥበት ዋጋ ከቀድሞ ጋር ምንም ዓይነት ልዩነት የለውም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት መንግሥት ነጋዴዎችን በሰበሰበበት ወቅት የምግብ ዘይትን ዋጋ አስመልክቶ ተቃውሞ የቀረበበት በመሆኑ፣ ማስተካከያ እንደሚያወጣ በመግለጹ መሆኑን ፎዚያ ታስረዳለች፡፡ ሆኖም ግን በቀን ቢያንስ ከአስር ካርቶን በላይ የምግብ ዘይት የምትሸጠው ፎዚያ፣ ላለፉት ሁለት ቀናት ሱቋን ከመክፈቷ ውጪ ምንም ዓይነት ሽያጭ አለማከናወኗን ገልጻለች፡፡ ምክንያቱም መንግሥት አንድ ሊትር የምግብ ዘይት በ16.50 ብር ይሸጥ የሚለውን ማስታወቂያ ኅብረተሰቡ ስለሰማ፣ ነጋዴው ወደ ሱቅ መጥቶ ከመጠየቅ ውጪ ግዢ ስለማይፈጽም ነው ብላለች፡፡

መርካቶ የሚገኘውንና በብዛት የምግብ ዘይት የሚያስመጣው ጌታስ የተባለው አስመጪም፣ ቀድሞ በነበረው ዋጋ መሠረት የምግብ ዘይቶች ሲሸጥ ተመልክተናል፡፡ አንድ የጌታስ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት በወቅቱ ያወጣው 16.50 ብር ቢሆንም፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ እንኳን በዚህ ዋጋ እንደማይገኝ ገልጸን ዋጋው ይሻሻል ብለናል፡፡ መንግሥትም ወዲያው ዋጋው መሻሻል እንዳለበት ገልጿል፡፡ ሆኖም ሚዲያው የዘይት ዋጋ 16.50 ብር መሆኑን በመናገሩ በኅብረተሰቡ ላይ ውዥንብር ፈጥሯል ብለዋል፡፡ መንግሥት ያወጣው የዘይት የዋጋ ጣሪያ ከዓለም አቀፍ ዋጋ ጋር በፍጹም የማሄድ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን በጉዳዩ ከመንግሥት ጋር እየተወያየንበት ሲሆን፣ ከውጪ ያስመጣንበትን ዋጋ ለንግድ ሚኒስቴር አስገብተን እየተጠባበቅን እንገኛለን ብለዋል፡፡

የሥራ ኃላፊው አክለው፣ ኅብረተሰቡ ዋጋ እየጠየቀን ስለሆነም መንግሥት የምግብ ዘይት የዋጋ ጣሪያን እንዲያሳውቀን በመጠባበቅ ላይ ነን፡፡ ሆኖም ዋጋው ሊቀንስ ይችላል በሚል፣ የነበረው ግብይት በጣም ቀዝቅዟል ብለዋል፡፡ የምግብ ዘይትም አሁን እየገዙ ያሉት ምግብ ቤቶችና በየቀኑ የሚጠቀሙ አካላት ብቻ መሆናቸውን የሥራ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ቦሌ አካባቢ የተለያዩ ሱቆችን ተዘዋውረን ባየንበት ወቅት፣ የክፍለ ከተማው የንግድ ቢሮ በግልጽ በሚታዩ ቦታዎች የምርቶቹ የዋጋ ተመን ተለጥፎ ተመልክተናል፡፡ በዚህ የዋጋ ዝርዝር ውስጥ የምግብ ዘይት ዋጋም መካተቱ ከፍተኛ ውዥንብር መፍጠሩን የሱቆቹ ባለቤቶች አስረድተውናል፡፡ በዚህም መሠረት አንዳንዶች ዋጋው ገና ይስተካከላል ሲሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ ዋጋው ለአገር ውስጥ ዘይት ብቻ ነው ሲሉም ተመልክተናል፡፡

ከስሬ የምሸጠው መንግሥትን ፈርቼ ነው
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አስመጪ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ከስረህ ሽጥ ሊል ይችላል፤ ሆኖም ይህ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ መንግሥት ያወጣውም ይህ የዋጋ ጣሪያ በቂ ጥናት ያልተደረገበት ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የተለያየ የዋጋ ተመን ያላቸውን ሸቀጦች በአንድ ላይ ጨፍልቆ በዚህ ዋጋ ሽጥ ማለቱ በቂ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት በመጀመሪያ የንግድ ማኅበረሰቡን ሰብስቦ ሸቀጦቹ የተገዙበትን ዋጋ በሚገባ አጥንቶ ዋጋ ማውጣት ሲገባው፣ አሁን እየወሰደ የሚገኘው ዕርምጃ ያልተገባ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ግለሰቡ ገለጻ፣ አሁን እየሸጥኩት ያለሁት በኪሳራ ሲሆን፣ ይህም መንግሥት አስሮኝ ስቃይ ከሚደርስብኝ ገንዘቤን ብከስር ይሻላል በሚል ፍርሐት ነው፡፡ ሆኖም ነገሩ በዚሁ ከቀጠለ ወደፊት ቀጥሬ የማሠራቸውን ሠራተኞች መቀነስ የምጀምር ሲሆን፣ ይህም ለመንግሥትም ሆነ ለኅብረተሰቡ መልካም አይደለም ብለዋል፡፡

ግለሰቡ አክለውም፣ እንደ ጀንአድ ያሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንደዚህ ዓይነት የዋጋ ንረት በሚከሰትበት ወቅት ገበያውን ማረጋጋት ሲገባቸው፣ እነርሱም ከእኛ ጋር በገበያ እየተፎካከሩ ሸቀጦችን ይሸጣሉ፡፡ በመሆኑም መንግሥት ራሱ ለገበያው ንረት ተጠያቂ በሆነበት ጉዳይ፣ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ ስለዚህ ገበያውን ለማረጋጋትም ሆነ አሁን ለተፈጠረው ውዥንብር መፍትሔ ለማምጣት መንግሥት ከነጋዴው ጋር መወያየት ይገባዋል ብለዋል፡፡

ግለሰቡ አክለውም፣ አሁን መንግሥት እየወሰደ ባለው ዕርምጃ የግብይት ሁኔታ ይቀዘቅዛል፡፡ በዚህ ምክንያትም መንግሥት ሊያገኝ የሚገባው የታክስ ገቢ ይቀንሳል መንግሥት ይህ ዓይነቱን ዕርምጃም መውሰዱ፣ ችግሩ ለመንግሥት ከፍተኛ ስጋት መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

ከዕርምጃው በኋላ ዕቃዎች ጠፍተዋል
ከስኳር ከአንድ ኩንታል እስከ ሁለት መቶ ብር ኪሳራ የሚያጋጥመው መሆኑን የሚናገረው አንዋር፣ ሳሙናና ፓስታም እንዲሁ ከስሮ እየሸጠ ይገኛል፡፡ ከመመሪያው በኋላም ዋጋ የተተመነላቸውን ምርቶች ከአከፋፋዮች ማግኘት አልቻለም፡፡ መንግሥት ዋጋ ተምኖ በዚህ ሽጡ ያላቸውን ምርቶች መርካቶ ከሚገኙ የማከፋፈያ ሱቆች ለማምጣት ቢሄድም፣ ምንም ዓይነት ግብይት መፈጸም ሳይችል መመለሱንም ገልጾልናል፡፡

ዕቃ ለማምጣት ሔዶ ባዶ እጁን የተመለሰው አብዛኛዎቹ አከፋፋዮች ምርቱ የለንም በማለታቸው ነው፡፡ እንደ አንዋር ገለጻ፣ ‹‹ለምሳሌ የምግብ ዘይት አንዳንዶቹ አከፋፋዮች ጋር አለ ሲሉ፤ ሌሎቹ ጋር ደግሞ የለም ይሉናል፡፡ አለ የሚሉት አከፋፋዮች ደግሞ የምንሸጥላችሁ መንግሥት ባወጣው ተመን መሠረት ነው በማለታቸው በዚያ ዋጋ አምጥቼ እኔም በዚያው ዋጋ መሸጡ ስለማያዋጣኝ ትቼው መጥቻለሁ፤›› ብሏል፡፡

አምስት ብር ይሸጥ የተባለውም ሳሙና አከፋፋዮች ጋር በተመሳሳይ ዋጋ እየተሸጠ መሆኑ ሳሙና ለማስገባት እንቅፋት እንደሆነበት ያስረዳል፡፡ ስምረት ባህሩ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የአነስተኛ መደብር ባለቤት ነች፡፡ የዋጋ ተመንን የሚመለከተው የመንግሥት መመሪያ ከመውጣቱ በፊት በመደብሯ ውስጥ ሦስት የታሸገ ባለአንድ ሊትር የምግብ ዘይት ነበራት፡፡ አንዱን ሊትር ዘይት በ27 ብር ስትሸጠው፣ የቀረውን ሁለት ሊትር ለቤቷ ፍጆታ ተጠቅመዋለች፡፡ ስምረት የምግብ ዘይቱን ከአከፋፋዮች 24.50 ብር እንዳመጣችው ትናገራለች፡፡

በአዲሱ ተመን መሠረት ሰኞ አንዱን ሊትር የምግብ ዘይት 16 ብር በመሸጧ ከአስር ብር በላይ ከስራለች፡፡ በአዲሱ የዋጋ ተመን መሠረት በቅናሽ ለማምጣት ብታስብም አልተሳካላትም፡፡ በመደብሯ የምትቸረችራቸው ሸቀጦች በጅምላ የምትገዛው አቃቂ ገበያ አካባቢ ከሚገኙ አከፋፋዮች ነው፡፡

ከትናንት በስቲያ የምግብ ዘይት፣ ስኳርና ሳሙና ለመግዛት በሄደችበት ወቅት፣ አብዛኛዎቹ አከፋፋዮች እንደ የምግብ ዘይት፣ ሳሙናና ስኳር ምርቶች የሉም በማለታቸው ምርቶቹን ለደንበኞችዋ መሸጥ አለመቻልዋን አብራርታለች፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ሃያ ሁለት ማዞሪያ አካባቢ ያነጋገርነው ባለመደብርም የስምረትና የአንዋር ዓይነት ተመሳሳይ የሆነ አስተያየት አለው፡፡

ከአከፋፋዮች ከተረከበው ዋጋ በታች እየሸጠ መሆኑ ኪሳራ ውስጥ እየከተተው ቢሆንም፣ የመንግሥትን መመሪያ ለማክበርና መደብሩ እንዳይታሸግበት በመፍራት በአዲሱ የዋጋ ተመን መሠረት እየሸጠ መሆኑን ይገልጻል፡፡

አንዋር በበኩሉ እየከሰረ እየሸጠ ያለው ሕግን ለማክበር ነው፡፡ በአካባቢውም ዋጋ አለጠፋችሁም ተብለው ሱቆቻቸው እየታሸጉባቸው መሆኑም ተጠንቅቆ እንዲሸጥ ምክንያት እንደሆነም መረዳት ይቻላል፡፡

በልደታ ክፍለ ከተማ 29 መደብሮች ታሽገዋል
በልደታ ክፍለ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት የዘመናዊ ንግድ ሥርዓት ማስፈን የሥራ ሒደት አስተባባሪ ወ/ት እታፈራሁ አለሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፉት ሁለት ቀናት 29 የሚሆኑ መደብሮች ታሽገዋል፡፡

እንደ አስተባባሪዋ ገለጻ፣ 29ኙ መደብሮች የታሸጉት በመንግሥት ከተተመነው ዋጋ በላይ በመሸጣቸውና የዋጋ ዝርዝር ባለመለጠፋቸው ነው፡፡ መደብሮቻቸው የታሸገባቸው ባለመደብሮች ከዚህ በኋላ ከተተመነው ዋጋ በላይ እንዳይሸጡና የዋጋ ዝርዝር እንዲለጥፉ በሚያስገድደው ሰነድ ላይ ከፈረሙ በኋላ በሁለት ቀናት ውስጥ መደብሮቻቸው እንዲከፈቱላቸው ይደረጋል፡፡ አሁን ባለማወቅና የመጀመሪያቸው በመሆኑም የንግድ ፍቃዳቸው እንዲሰረዝ አልተደረገም ያሉት ወ/ት እታፈራሁ፣ ከዚህ በኋላ ከተተመነው ዋጋ በላይ ቢሸጡ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማም መደብሮቻቸው የታሸጉባቸው ነጋዴዎች ከክፍለ ከተው የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊዎች ጋር ተወያይተው ከዚህ በኋላ ዋጋ ጨምረው እንደማይሸጡ የሚያስገድደውን ሰነድ ፈርመው ሱቆቻቸው እንደሚከፈትላቸው ተገልጾላቸዋል፡፡

ነጋዴዎቹ ከዋጋ በላይ የሸጡት አከፋፋዮች ዋጋ ሊቀንሱላቸው ባለመቻሉ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን ጉዳይ የሚመለከተው አካል እንዲከታተለው ማሳወቃቸውን የጠቆሙት ወ/ት እታፈራሁ፣ ጽ/ቤታቸው ከተለያዩ ጠቋሚዎች በሚደርሳቸው መረጃ መሠረት ክትትል እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚሁ ክፍለ ከተማ ሚቼል ኮትስ በሚባለው ኩባንያ በሚገኝ መጋዘን ውስጥ በባለ 20 ሊትር ጀሪካን የታሸገ አምስት ሺሕ ሊትር የፓልም ዘይት ትናንት መያዙን ወ/ት እታፈራሁ ገልጸዋል፡፡

በመጋዘን ውስጥ የተገኘው ዘይት ባለንብረት የመርካቶ ነጋዴ መሆናቸው በመረጋገጡ፣ የሕግ አካላት በተገኙበት ንብረቱ ታሽጐ ነጋዴው በፈጸሙት ሕገወጥ ተግባር በሕግ እንዲጠየቁ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

ነጋዴው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተመዘገበ፣ በተዘጋጁ ልብሶች የአስመጭነትና የችርቻሮ ንግድ ፈቃድ እንዳላቸውም ታውቋል፡፡ መጋዘኑን በሌላ ሰው ስም የተከራዩ ስለመሆኑም አረጋግጠናል ያሉት አስተባባሪዋ፣ በሕገወጥ መንገድ ተሸሽጓል የተባለውን የፓልም ዘይት መያዝ የተቻለው በኅብረተሰቡ ጥቆማ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

አዲሱ መመሪያና ሥጋ ቤቶች
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሥጋ ቤቶች ለወትሮ የሚሸጡትን ያህል የሥጋ መጠን በሱቆቻቸው አይታይም፡፡

ያነጋገርናቸው አንዳንድ ልኳንዳ ቤቶች እንደሚገልጹት፣ እንደቀድሞው በርከት ያለ ሥጋ ያለመያዛቸው ዋነኛ ምክንያት የከብት ዋጋ በመወደዱ ነው፡፡ መንግሥት ያወጣው አዲሱ የዋጋ ተመን አንድ ኪሎ ሥጋ በ52 ብር ይሸጥ የሚል በመሆኑ፣ አንድ ከብት እስከ 12 ሺሕ ብር ገዝቶ በዚህ ዋጋ መሸጡ አያዋጣንም ይላሉ፡፡

ሰንጋ ተራ አካባቢ የሚገኝ የአንድ ሥጋ ቤት ባለቤት እንደገለጹልን፣ ‹‹ከበዓሉ በፊት በውድ ዋጋ የገዛነው ከብት አክስሮናል፡፡›› ከዚህ በኋላ ከብት ከቀነሰልን እየገዛን እንሸጣለን፤ ካልሆነ አሁንም ኪሳራ ውስጥ መግባታችን ነው፡፡ ሥጋ ቤቱ ውስጥ የሚጠቀሙ ሰዎችም ችግር እየፈጠሩብን ነው የሚሉት እነዚሁ ባለ ሥጋ ቤቶች፣ አንዳንድ ተጠቃሚዎች አንድ ኪሎ ጥብስ በ52 ብር ካልሸጣችሁልን እንደሚሏቸውም ይናገራሉ፡፡

‹‹እኛ ለእንጀራና ለአዋዜ እስከ ስድስት ብር እናስከፍላለን፤ ብዙ ሰዎች ግን ይህንን እንዳናደርግ እየተከላከሉ ናቸው፡፡ በእኛ በኩል መንግሥት ባወጣው ዋጋ መሠረት ለመሸጥ ዝግጁ ነን፤ ነገር ግን የበሬ ዋጋ ካልቀነሰ ምን እንደምናደርግ ግራ ገብቶናል፡፡›› በሌላ በኩልም ሥጋ ቤቶች ከተጠበሰ ሥጋ ጋር ለሚያቀርቡት እንጀራና አዋዜ እስከ አስር ብር የሚደርስ ዋጋ እየጠየቁም ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በመንግሥት የተቀመጠው ዋጋ እንደተስማማቸው፣ በኪሎ ከ45 እስከ 48 ብር ይሸጡ የነበሩ ልኳንዳ ቤቶች ይናገራሉ፡፡ አንዳንዶችም እስከ 90 ብር በሚደርስ ሒሳብ ኪሎ ሥጋ ሲሸጡ እንደነበርና በ52 ብር መሸጣቸው እንደሚያከስራቸው የተናገሩም አሉ፡፡

ቦሌ የሚገኘው ሳሚ ቁርጥ ቤትም ትናንት ከሰዓት ላይ አንድ ኪሎ 80 ብር ሸጧል በሚል ታሽጓል፡፡ የሥጋ ቤቱ ባለቤት አቶ ሳሙኤል ገብረማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሥጋ ቤቱ የታሸገው ለአገልግሎት ክፍያ ብሎ ከ52 ብር በተጨማሪ 28 ብር በማስከፈሉ ነው፡፡ ይህንንም ያደረግነው ክፍለ ከተማው በለጠፈው የዋጋ ተመን ስር በቤቱ ለሚጠቀሙ ደንበኞች ለተጨማሪ ወጪዎች ማስከፈል ትችላላችሁ የሚል ጽሑፍ በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡

የሸማቾች ጥርጣሬ
ስቴዲዮም አካባቢ ከሚገኘው በኮንቴነር ከተሠራው የኢትፍሩት ስኳር ለመግዛት የመጡት ወ/ሮ ላቀች ማሩ፣ መንግሥት የወሰደውን እርምጃ ይደግፋሉ፡፡ አሁን ቅኛሽ ከተደረገባቸው ምርቶች ሌላ በሌሎቹም ላይ ሊቀንስ ይገባል ይላሉ፡፡

ነገር ግን ወ/ሮ ላቀች ጥርጣሬ አላቸው፡፡ ሸማቹ እንዲጠቀም ተብሎ የተደረገው የዋጋ ቅናሽ በዚሁ ከቀጠለ ግሩም ተግባር ነው የሚሉት ወ/ሮ ላቀች፣ ሆኖም የመቀጠሉ ነገር ያጠራጥረኛል ባይ ናቸው፡፡

ለጥርጣሬያቸው የሰጡት ምክንያትም ነዳጅ እየጨመረ ስለሆነ መልሶ ዋጋ መጨመሩ አይቀርም፡፡ ይህ ለነጋዴውም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ከዚህ በፊትም የዋጋ ቁጥጥር ይደረጋል ተብሎ አንድ ሰሞን ክትትል ከተደረገ በኋላ መልሶ መቅረቱንም ያስታወሱ ሸማቾች አሉ፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ ለሰብሰባ ተጠርቷል
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መንግሥት ተግባራዊ ባደረገው የዋጋ ተመን ዙሪያ ላይ ለመወያየት ቦርዱ ልዩ ስብሰባ መጠራቱ ታውቋል፡፡

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው ዘገየ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ምክር ቤታቸው በተወሰደው እርምጃ ዙሪያ በመወያየት ውሳኔ ይወስናል፡፡

መንግሥት የወሰደውን እርምጃ በተመለከተ አቶ አያሌው በግል በሰጡት አስተያየት፣ እንዲህ ዓይነት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ብቻ የተጀመረ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አደጉ የሚባሉ እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮች ሳይቀሩ የሚያደርጉት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ምን መሆን አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ግን የምክር ቤቱ ቦርድ የራሱን የሆነ ሐሳብ ያቀርባል፡፡

መንግሥት እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ ሲወስድ ምክር ቤታቸውን ያላነጋገር ቢሆንም፣ በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገ ውይይት ላይ በይፋ እርምጃውን የተቃወሙ አለመኖራቸውም የራሱ የሆነ ምክንያት ይኖረዋል ይላሉ፡፡

የዋጋ ጣራውና ነፃ ገበያ
መንግሥት 16ቱ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጣሪያ ካወጣ ጀምሮ ገበያው ውስጥ እየታየ ያለው ግራ መጋባት እንዳለ ሆኖ፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በበኩላቸው እርምጃውንና የነፃ ኢኮኖሚ ሥርዓቱ አብረው የመሄድ ጉዳይን እየተከራከሩበት ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና የጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክትር አቶ መላኩ ፈንታ በስብሰባው ላይ ከጠቀሷቸው ለእርምጃው መነሻ የሆኑ ምክንያቶች አንዱ፣ በምግብና ዋና ዋና የፍጆታ ዕቃዎች ገበያ ላይ የኦሊጐፖሊስቲክ (Oligopolistic Collusion) የግብይት ሁኔታ የመታየት ጉዳይ ነው፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳስረዱት፣ በቁጥር ከ30 የማይበልጡ ፈርጣማ የግል የንግድ ተቋሞች በአገሪቱ የሚገኘውን የምግብና የምግብ ነክ ገበያ በከፍተኛ ደረጃ (57 በመቶ) ይቆጣጠራሉ፡፡ በመሆኑም እምርጃው ይህንን ተገቢ ያልሆነ በሸማቹ ላይ ከፍተኛ ዋጋ እንዲጫን የሚያደርግን የገበያ አካሄድ ‹መስበር አለበት› የሚል ጠንካራ አቋም የያዘ ነው፡፡

የሆነ ሆኖ ይህ እርምጃ መሠረት ያደረገው የኦሊጐፖሊስቲክ የገበያ ሁኔታ ምንድን ነው? እውን የአገሪቱ ገበያ (በተለይ በፍጆታ ዕቃዎች ዙሪያ) ውስጥ የኦሊጐፖሊስቲክ አካሄድ ይታያል? እርምጃው ከዚህ አንጻርና ላለፉት ሃያ ዓመታት አገሪቱ እከተለዋለሁ የምትለውን የነፃ ገበያ ሥርዓት ጋርስ አብሮ ይሄዳል? የሚሉት ጥያቄዎች መወያያ እርስ ሆነው ሰንብተዋል፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የኦሊጐፖሊስቲክ የገበያ ሁኔታ የሚፈጠረው በነፃ ገበያ ውድድር ውስጥ ጥቂት የንግድ ተቋማት በአቅም ነጥረው ሲወጡና በዘርፉ ከሚካሄደው የንግድ ልውውጥ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዙ ነው፡፡ በነፃ ገበያ ውድድር ሒደት አሸናፊ ሆነው ጡንቻ የሚያፈረጥሙ ጥቂት ድርጅቶች የገበያ ድርሻቸው እየጨመረ በሄደ ቁጥር በአቅርቦት ላይ ያላቸው ተጽእኖ ከፍተኛ ስለሚሆን የምርቱን ዋጋ ላይም ተመሳሳይ ተጽእኖ የማድረግ ኃይል እንደሚኖራቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ነገር ግን የጥቂት ድርጅቶች መጠናከር በራሱ ግን በዋጋ እንዲሁም በሸማች ላይ ተጽእኖ ያሳርፋል ማለት እንዳይደለ የሚስማሙት ባለሙያዎቹ፣ ኦሊጐፖሊ አደጋ መሆን የሚጀምረው ድርጅቶቹ እርስ በእርስ ስምምነት መፍጠርና ዋጋን ሆን ብለው ከፍ ማድረግ ሲጀምሩ ነው፡፡

አቶ ቴዎድሮስ መኮንን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር የማክሮ ክፍል ባልደረባም በዚህ ይስማማሉ፡፡ እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለጻ፣ የኦሊጐፖሊስቲክ የገበያ ሁኔታ በራሱ ሲታይ እጅግ ፉክክር የተሞላበት ገበያ ነው፡፡ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው እነዚህ ድርጅቶች ገበያው ላይ ሲሸጡ ከአቻ (ትላልቅ) ድርጅቶች ጋር በዋጋ ይወዳደራሉ፤ ለዚህም ምርታቸውን የሚሸጥበትን ዋጋ ሲወስኑ የአቻ ድርጅቶችን የዋጋና የአቅርቦት ውሳኔ ባገናዘበ መልኩ መሆኑን ባለሙያዎቹ ይስማሙበታል፡፡

ለምሳሌ ይላሉ አቶ ቴዎድሮስ፣ የኮካ ኮላና የፔፕሲ ምርቶች እርስ በእርስ በኦሊጐፖሊስቲክ ውድድር ውስጥ ሆነው ምርታቸውን ስለሚሸጡ ዋጋው በገበያ ውድድር ላይ የተመሠረተ ብቻ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ጥቂት ፈርጣማ አቅርራቢዎች ወይም አምራቾች ያላቸውን የገበያ ድርሻ በማጤን እርስ በእርስ ለመስማማት ሲንቀሳቀሱ አደጋ አለው፤›› በማለት ያብራራሉ፡፡

በዚህ ረገድ ለምሳሌ ያህል የኦሊጐፖሊስቲክ የገበያ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሦስት አቅራቢዎች (አምራቾች) ቢኖሩና አንዱ ብቻውን ዋጋ ከፍ ቢያደርግ፣ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ሌሎች ሁለት ድርጅቶች ስለሚኖሩ ተጐጂ ይሆናል፤ በመሆኑም የዋጋ ውሳኔው በውድድር ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን ከላይ እንደተጠቀሰው እርስ በእርስ ስምምነት ማድረጉ ዋጋን ከፍ ለማድረግ ጉልበት ይለግሳቸዋል፤ ይህም አደገኛ ይሆናል የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ በኢትዮጵያ ገበያ ይህ ሁኔታ ምንም እንኳን ይህ ሁኔታ አለ ለማለት ዝርዝር ምርምርና ጥናት ቢያስፈልግም፣ ምልክቶች መታየታቸው ግን አልቀረም፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያና ከግል ዘርፉ ጋር እየሠሩ ያሉት አቶ ቡልቲ ተርፋሳ ግን በዚህ እምብዛም አይስማሙም፡፡ እንደሳቸው እምነት አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ ጥቂት በተቋም ደረጃ ከተያዙ ዘርፎች በስተቀር የኦሊጐፖሊስቲክ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡

በሌላ በኩል አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የአርነስት ኤንድ ያንግ የአማካሪ ድርጅት ማኔጂንግ ፓርትነር፣ እርምጃው መታየት ያለበት ሸማቹን አላስቀምጥ ያለውን የዋጋ ንረት ከመግታታ አንጻር ነው፡፡ ‹‹በዚህ ረገድ መንግሥት የዋጋ ንረቱን የማርገብ ኃላፊነት ጭምርም እንዳለበት መዘንጋት የለብንም፤›› ይላሉ፡፡

አቶ መላኩ እርምጃውን ለንግዱ ማኅበረሰብ በሚስታወቁበት ወቅት የጠቆሙት ሌላው ጉዳይ ግን እርምጃው በምንም መልኩ ከነፃ ገበያው ጋር የሚጋጭ አለመሆኑን ነው፡፡ ‹‹የነፃ ገበያውን ሥርዓት ለማበላሸት የታለመ አይደለም›› ካሉት ከእኚሁ ሰው የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ ግን በእጅጉ የተለየ አመለካከት አላቸው፡፡

በዚህ ረገድ አቶ ቡልቲ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በገበያ ላይ ጣልቃ የሚገባ የአስተዳደራዊ ውሳኔ በአብዛኛው ወደ በለጠ የገበያ መዛባት የሚመራ ነው፡፡ አቶ ቴዎድሮስ በበኩላቸው መጀመሪያውኑ የነፃ ገበያ ሥርዓቱ በተገቢው ሁኔታ እየተሠራ ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ያስቀድማሉ፡፡ 

ከዚህ አንጻር የነፃ ገበያ ሥርዓት በኢትዮጵያ የሚጐድሉት ነጥቦች አሉ ያሉት እኚሁ ሰው፣ ከዚህ ውስጥ ዋናው ነገር ጠንካራ የሸማቾች ማኅበርና የገበያ ውድድርን የሚከታተል ተቋም መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ለምሳሌ በአሜሪካ (Central Trade Commission) የተባለ በገበያ ውድድር ውስጥ ከላይ እንደተጠቀሰው ዓይነት እክል የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን የሚቆጣጠር ተቋምን ይጠቅሳሉ፡፡ በተጨማሪም የሸማቾች ማኅበራትም የሸማቹን የድርድር አቅም ከፍ በማድረግ ጠቀሜታቸውን ከፍ ያደረጋል ይላሉ፡፡

ከዚህ ውጪ የገበያ ውስጥ ያለን መረጃን በሁሉም ወገኖች በጋራ እንዲያገኙት የሚያስችል ተቋም አለመኖሩም ሌላው ነፃ ገበያ በቅጡ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለመሆኑን የሚያሳይ ጉዳይ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ይላሉ እኚሁ ባለሙያ፣ የአገር ውስጥ ነጋዴዎች በአሁኑ ወቅት ልዩ ጥቅም እያገኙበት ያለው ከውጪ ድርጅቶች አስከፊ ውድድር የተሰጣቸው ከለላ ነው፡፡ ‹‹በዚህ ረገድ የአገር ውስጥ ገበያው በአብዛኛው ለውጭ ሰዎች የተዘጋ በመሆኑ የነፃ ገበያ በብቃት አለ ለማለት ገና ነው፤›› ሲሉ አቶ ቴዎድሮስ ያስረዳሉ፡፡

ከውጭ ከለላ (Protection) አንጻር አቶ ዘመዴነህም ቢሆኑ የሚስማሙበት ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እንደዚህኛው ባለሙያ እምነት ደግሞ የአገር ውስጥ ከለላው በከፊልም ቢሆን መከለስ ያለበት ወቅት አሁን ነው፡፡ በተለይ እያደገ ካለው የገበያ ፍላጐት አንጻር የአገር ውስጥ አቅራቢዎች አቅም ወደማይችልበት ደረጃ እየተቃረበ ስለመሆኑ የሚናገሩት አቶ ዘመዴነህ፣ እንደ ሕንድ ዓይነት የአገሮች በጅምላና ችርቻሮ ዘርፍ ላይ በከፊል የውጭ ድርጅቶች እንዲገቡ መፍቀዳቸው ለእኛ ትምህርት ሊሆነን ይገባል ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን ሁለቱ ባለሙያዎች የውጪ ከላለው ጉዳይ ላይ  የሚስማሙ ቢመስልም፣ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ላይ ግን ከፍተኛ ልዩነት ይንፀባረቅባቸዋል፡፡ እንደ አቶ ቴዎድሮስ አመለካከት፣ ገበያው በእርግጥ በብቃት እየሠራ ባይሆንም እርምጃውም ቢሆን ግን ትክክለኛ አይደለም፡፡ ‹‹መንግሥት የገበያውን ችግር ‹ኔጌቲቭን በኔጌቲቭ በማባዛት› ለማስተካከል እየሞከረ ነው፤›› የሚሉት እኚሁ ሰው፣ የዋጋ ጣራ እያወጡ እስከመቼ ይዘለቃል የሚል ጥያቄ ያነሳሉ?

‹‹ስህተትን በስህተት ከማረም ይልቅ የገበያ ሥርዓቱ የጐደሉትን ከላይ የተነሱ ተቋማትን ማጠናከር ችግሩን ይቀርፍ ነበር፤›› ሲሉም ይከራከራሉ፡፡

አቶ ዘመዴነህ ግን በእርምጃው ስህተትነት አይስማሙም፡፡ ‹‹የትኛውም መሠረታዊ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መርሆዎችን የሚከተል አገር የሚያደርገው ነው፡፡›› ለዚህም እ.ኤ.አ በ2007/08 በተከሰተው የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ነውጥ ወቅት አሜሪካ ባንኮችን ሳይቀር ወደ መንግሥት አስተዳደር ያዛወረችበት አጋጣሚን ማስታወስ በቂ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹መንግሥት በገበያው ያሉ ግድፈቶችን ለማስተካከል አቅጣጫ ሲያሲዝ በነፃ ገበያው ጣልቃ ገባ ማለት አይቻልም የሚሉት አቶ ዘመዴነህ፣ በተለይ በአሁኑ ወቀት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንኳን ሳይቀር አንገብጋቢ የሆነውን የምግብ ዋጋ ንረትን ዝም ብሎ ይለፍ ማለት እንደማይቻል አክለው ይገልጻሉ፡፡

አቶ ቡልቲና አቶ ቴዎድሮስ በአሁኑ እርምጃ ዘላቂ መፍትሔ አይገኝም፤ በገበያው ውስጥ ያሉትን የሸማች ማኅበራትንና ሌሎች ተቋማትን ከማጠናከር በቀር ሌላ የሚያወጣ አካሄድ አለመኖሩንም ይመክራሉ፡፡

የመንግሥት አቋም
የዋጋ ቁጥጥሩን አስመልክቶ መንግሥት ባወጣው የሕዝብ ማስታወቂያ ባለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ እያደገ የመጣውን አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር መንግሥት በወሰዳቸው የፖሊሲ እርምጃዎች አማካይነት ከ40 በመቶ በላይ አሻቅቦ የነበው አገር አቀፍ የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ መቻሉን ያመለክታል፡፡ ለውጡ በአብዛኛው የታየው በምግቦች ዋጋ ላይ መሆኑን የሚገልጸው ማስታወቂያ፣ ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ላይ ግን ትርጉም ያለው ቅናሽ አለማሳየቱንና በየወሩ በ18 በመቶ በማደግ ላይ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በአንጻሩ ከአገር ውስጥ ምርቶች በስተቀር የምግቦች ዋጋ ግሽበት ተቀባይነት ወዳለው ደረጃ ወደ 2.4 በመቶ መውረዱን ያብራራል፡፡

ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ አሳሳቢ ሆኖ እያለ ከቅርብ ወራት ወዲህ በቂ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር የተለያዩ ምክንያቶች ከሚያስከትሉት ተጨማሪ ወጪ ጋር የማይመጣጠን የመሸጫ ዋጋ ስለሚጠየቅ የዋጋ ንረቱ በሚፈለገው መጠን ሊቀንስ አለመቻሉ በማስታወቂያው ተመልክቷል፡፡ ይህም በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባለው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩንና ይኸው የኅብረተሰብ ክፍልም ቅሬታውን በመግለጽ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ሁኔታውን እንዲያሻሽል ተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቡን ማስታወቂያው ያትታል፡፡

መንግሥት ያወጣው ማስታወቂያ የዋጋው ግሽበቱ በኅብረተሰቡ ላይ ከሚያስከትለው ጫና በተጨማሪ የመጪውን የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ከማሳካት አንጻር ቁልፍ ሚና በሚጫወቱ በብሔራዊ ቁጠባ፣ በኢንቨስትመንትና በውጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ እንቅፋት ስለሚሆን ወደጤናማ ደረጃ ማውረዱ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ይህንኑም ከማሳከት አኳያም በማክሮ ደረጃ ከተወሰዱት እርምጃዎች ጎን ለጎን ችግሩ ጎልቶ በሚታይባቸው የንግድ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ቁጥጥር ማድረግ በማስፈለጉ የዋጋ ቁጥጥር ሥርዓቱ ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑን ይገልጻል፡፡

በንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 658/2002 አንቀጽ 46 መሠረት በንግድ ሚኒስቴር የወጣው የሕዝብ ማስታወቂያ የዋጋ ቁጥጥር ሥርዓቱ የሚሸፍናቸውን በአገር ውስጥ የሚመረቱና ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡

በዚሁ ማስታወቂያ እንደተመለከተው አምራቾች፣ አስመጪዎችና አከፋፋዮች የተወሰነውን ቋሚ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ግምት ውስጥ በማስገባት የጅምላ መሸጫ ዋጋቸው ላይ ማስተካከያ ማድረግ አለባቸው፡፡ የመሸጫ ዋጋቸውንም በግልጽ በሚታይ ቦታ መለጠፍ አለባቸው፡፡

ቀጣይ የዋጋ ማሻሻያ (ቅናሽ ወይም ጭማሪ) የሚደረግበት አግባብ እንደሚኖር የሚያመለክተው ማስታወቂ፣ያ የወቅቱን ሁኔታ ያገናዘበ፣ በጥናትና በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የመሠረተ አስፈላጊ የዋጋ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችል ያመለክታል፡፡

በማስታወቂያው እንደተመለከተው፣ ከተወሰነው ከፍተኛ የችርቻሮ ዋጋ በላይ መሸጥ ክልክል እንደመሆኑ መጠን በመደብር ውስጥ የንግድ ዕቃው እያለ እንደሌለ ወይም እንዳለቀ በማስመሰል ላለመሸጥ መደራደርም አይፈቀድም፡፡

ሚኒስቴሩ በጥናት ላይ በመመስረት በዋጋ ቁጥጥር ሥርዓት የሚሸፈኑ ሌሎች ሸቀጦችና በቋሚ የችርቻሮ ዋጋ መሸጥ ያለባቸውንም መሠረታዊ ዕቃዎች በየጊዜው እያጠና እንደሚያሳውቅ በማስታወቂያው ተመልክቷል፡፡

በማስታወቂያው አፈጻጸም ላይ ቅሬታ ካለው አካል ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ እንደሚሰጥ የሚገልጸው መግለጫ፣ የሕዝብ ማስታወቂያውን የተላላፈ ነጋዴ በንግድ ምዝገባና አዋጅ ቁጥር 686/2002 መሠረት የንግድ ፈቃዱን በሰጠው አግባብ ያለው ባለሥልጣን የንግድ ፈቃዱ እንደሚሰረዝበት አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማስታወቂያውን የተላለፈ ነጋዴ በንግድ ምዝገባና አዋጅ ቁጥር 686/2002 እና በንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 685/2002 መሠረት በወንጀል ተከሶ እንደሚቀጣ ይገልጻል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ተፈጻሚ የሆነውን ቋሚ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ መነሻ በማድረግ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ሌሎች ክልል ከተሞች የሚሰራጩ የንግድ ዕቃዎች ዋጋ የትራንስፖርት፣ የመጫኛና ማውረጃ ወጪዎችና ሌሎች በሕግ ተቀባይነት ያላቸው ክፍያዎችን በማካተት የሚሰላ መሆኑ በማስታወቂያው ተመልክቷል፡፡

ነጋዴና ሸማች ከሕግ አኳያ

ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የፀደቀው የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ በነጋዴው ላይ ያስቀመጣቸው ግዴታዎች ይታወሳሉ፡፡

ሰሞኑን እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችም የንግድ አሠራር ሕጉንም ሆነ የሸማቾችን መብት መሠረት እንዳደረጉ እየተነገረ ይገኛል፡፡

የንግድ አሠራር አዋጅ ቁጥር 329/1995ን የተካው አዲሱ ሕግ፣ ከንግድ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ያልተገቡ ባህርያትንና የሸማቾችን መብት ዘርዝሯል፡፡ ማንኛውም ነጋዴ ለሸማቹ ለሚሸጠው ዕቃ ወይም አገልግሎት ጥራቱ የተሟላ ስለመሆኑና ስለዓይነቱም ጭምር በቂና ትክክልኛ መረጃ ወይም መግለጫ ከመስጠት ባለፈ የዋጋ ዝርዝር በግልጽ የማመልከት፣ የመለጠፍና የዕቃው ወይም የአገልግሎቱ ዋጋም ቀረጥ፣ ታክስ ወይም ሌላ ሕጋዊ ክፍያን ያካተተ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ አለፍ ሲልም የትኛውም ነጋዴ በትህትናና በአክብሮት ሸማቹን የማስተናገድ፣ በንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ግብይት ምክንያትም ለሚደርስበት ጉዳት ካሳ የመፈጸም ግዴታ ተጥሎበታል፡፡

በአዋጁ ከተመለከቱት ጉዳዮች ውስጥ ምርትን መገደብ፣ የንግድ ዕቃዎችን ማከማቸት ወይም መደበቅ፣ በመደበኛ የንግድ መስመር እንዳይሸጡ ማድረግ ወይም መያዝ፣ የንግድ ውድድርን ለመገደብ፣ ለማጥፋት ወይም የተወዳዳሪን ወጪ ለማሳደግ ወይም ግብይቶችን ወይም የስርጭት መስመሮችን ቀድሞ በመያዝ ተወዳዳሪ ላይ ያነጣጠረ ጐጂ ድርጊት መፈጸም፣ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ የተጋነነ የመሸጫ ዋጋ ወይም ተገቢ ያለሆነ የመግዣ ዋጋ መጠየቅ ወዘተ የመሳሰሉትን ድርጊቶች የፈጸመ ማንኛውም ነጋዴ የዓመታዊ ገቢውን 15 በመቶ ይቀጣል በሚል በአዋጁ ተደንግጓል፡፡

በሌላ በኩል ዋጋን በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ መወሰን፣ ተመሳጥሮ መጫረትና ደንበኞችን ወይም የገበያ ክልልን፣ ምርትና ሽያጭን በኮታ መመደብ ‹‹ፍጹም የተከለከሉ›› ድርጊቶች መሆናቸውን የንግድ አሠራር ሕጉ ዘርዘሮ እነኚህን ድንጋጌዎች አስቀምጧል፡፡ የዓመታዊ ገቢውን መጠን መወሰን ባልተቻለ ጊዜ ደግሞ ከብር አንድ ሚሊዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርስ የገንዘብ ቅጣትና፣ ከአምስት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚጠብቀው አዋጁ ደንግጓል፡፡

የዓመታዊ ገቢውን መወሰን ባልተቻለበት ወቅት ደግሞ ከብር 500,000 (አምስት መቶ ሺሕ) እስከ አንድ ሚሊዮን በሚደርስ ገንዘብና 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣም የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ይደነግጋል፡፡

የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 685/2002 እና በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002ን መሠረት አድርጐም የንግድ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ታኅሣሥ 28 ቀን 2003 ዓ.ም. የሕዝብ ማስታወቂያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

በዚህ ደረጃ ከንግድ ፈቃድ ስረዛ እስከ ገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ ነጋዴው ዕቃ ደብቆ ወይም አለአግባብ ከገበያ ሰውሮ ወዘተ ሲገኝም፣ በተለይ ከታክስና ከግብር ጉዳዮች ጋር በተያያዘም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መኖሪያ ቤቱም ሆነ ማከማቻ መጋዘኑ ሊበረበርና ሊፈተሽ እንደሚችል የገቢዎችና የጉምሩክ ባለሥልጣን ሰሞኑን በሚዲያዎች ለሕዝቡ ገልጿል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 26 ላይ በተቀመጠው መሠረት ማንኛውም ሰው የግል ሕይወቱ፣ ግላዊነቱ የመከበር መብት እንዳለውና ይህም መኖሪያ ቤቱ፣ ሰውነቱና ንብረቱ ከመመርመር እንዲሁም በግል ይዞታው ያለ ንብረት ከመያዝ የመጠበቅ መብትን የሚያካትት ነው፡፡

ሆኖም በአንቀጹ ቁጥር ሦስት ላይ የተመቀመጡ ገደቦች ካልተፈጠሩ በቀር መብቱ አይገደብም፡፡ አስገዳጅ ሁኔታዎች፣ ብሔራዊ የደህንነት ስጋት፣ የሕዝብ ሰላም፣ ወንጀልን የመከላከል፣ ጤናንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ የመጠበቅ ወይም የሌሎችን መብትና ነፃነት በማስከበር ዓላማዎች የተመሠቱ ‹‹ሕጐች›› ካሉ የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ መብቶች ተገድበው ብርበራም ሆነ ፍተሻ ሊካሄድ እንደሚችል የሕግ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት አቶ ደጀኔ ግርማ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ነጋዴ የሆነ ግለሰብ የገዛውን ዕቃ እንደፈለገ አከማችቶና ዋጋውን ከፍ አድርጐ መሸጥ የሚችልበት አግባብ ካለመኖሩም በላይ ዕቃን መደበቅ፣ ከገበያ ማሸሽ ወንጀል መሆኑንም ጭምር ገልጸዋል፡፡

ይህ ወንጀል ከተፈጸመና የተፈጸመበት ቦታ ከታወቀም (መጋዘንና ቤት) ያን ለመበርበርና ለመፈተሽ የወንጀል ሕጉ በሚያስቀምጠው መሠረት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚያስፈልግ ቢሆንም ሁልጊዜ ያስፈልጋል ማለት እንዳልሆነም ያብራራሉ፡፡

ከፍርድ ቤት ምንም ዓይነት ትዕዛዝ ሳያስፈልግ ብርበራም ሆነ ፍተሻ ለማካሔድ የተለየ ሕግ ማውጣት ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ መሠረት ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የዕቃ ስወራ ወንጀልን ተከትሎ ከታክስና ገቢ ጋር በተያያዘ ለመበርበርም ሆነ ለመፈተሽ የሕግ ድጋፍና መረጃም እስካገኘ ድረስ የሕግ ግጭት (የሕገ መንግሥቱና የገቢዎች የሕግ አግባብ) ሊፈጠር እንደማይችልም አቶ ደጀኔ ይገልጻሉ፡፡

ከመደበኛ የግብይት አሠራር ወጥቶ እንደተከማቸ ወይም እንደተደበቀ የሚያስቆጥረው ድርጊት በንግድ አሠራርና በሸማቾች ጥበቃ አዋጅ በተቀመጠው መሠረት ከውጪ አገር የመጣ የንግድ ዕቃና የምርት ጥሬ ዕቃ ወይም ከውጪ አገር በመጣ ጥሬ ዕቃ አገር ውስጥ የተመረተ የንግድ ዕቃ፣ ወደ አገር ውስጥ ከገባበት ወይም ከተመረተበት ቀን ጀምሮ፣ ለሦስት ወራት ለሽያጭ ወይም ለምርት አገልግሎት ካልዋለ እንደተደበቀ ወይም ከመደበኛ የግብይት አሠራር ውጭ እንደተደረገ ይቆጠራል፡፡

ከአገር ውስጥ በተገኘ ጥሬ ዕቃ የተመረተ የንግድ ዕቃና ከአገር ውስጥ የተገኘ የምርት ጥሬ ዕቃ ወይም በግብርና ሥራ የሚተዳደር ሆኖ ለግል ወይም ለቤተሰብ ፍጆታ ከሚውለው በቀር፣ በአገር ውስጥ የተመረተ የእርሻ ምርት ከተመረተበት ወይም ነጋዴው ወይም ሌላ ማንኛውም ሰው ከገዛበት ቀን ጀምሮ ለሁለት ወራት ለግብይት ወይም ለምርት አገልግሎት ካላዋለው እንደተደበቀ የሚቆጠር ሲሆን፣ ይህ ድርጊት ወንጀል መሆኑ ደግሞ በወንጀል ሕጉም ተመልክቷል፡፡

በዚህ መሠረት ይህንን ጥፋት የፈጸመ ነጋዴ ወይም ማንኛውም ሰው ፍተሻና ብርበራ ሊካሄድበት በተፈለገ ጊዜ በተለይ ከግብርና ታክስ አኳያ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እበረብራለሁ ማለቱ (የሕግ አግባብ እስካለው ድረስ) አጠያያቂ አለመሆኑን አቶ ደጀኔ የሰጡት ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ገብቶ መበርበርና መፈተሽ እንደሚችል በግለጽ ባይደነገግ እንኳ ያለ አግባብ ዕቃን መደበቅ ወንጀል መሆኑ በሕግ ከተቀመጠና የትኛውም ቦታ የተፈጸመን ወንጀል መበርበር ከተቻለ የሕግ ክፍተት አለ አያሰኘውም ካሉ በኋላ በምን መልኩ መበርበርና መፈተሽ ይቻላል፣ በሚለው ጉዳይ ላይ ካልሆነ በቀር ጥያቄ አይነሳም፡፡ ‹‹ለአብነት አንድ ሰው ወንጀል ሠርቶ የሰው ቤት ውስጥ ሮጦ ቢገባ ያን ሰው የሚከታተለው ፖሊስ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቀጥታ ሊይዘው ይችላል፤›› ይህንና መሰል ለየት ያሉ ሁኔታዎች መኖራቸውን አቶ ደጀኔ አብራርተው፣ በግልጽ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መበርበር እንደሚችል ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በሕግ ተቀምጦለት ካልሆነ በስተቀር ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መበርበር እንደማይችል፣ ከበረበረም ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ሊያስነሳ እንደሚችል አንድምታውን አሳይተዋል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት መምህር አቶ ዓለሙ ምህረቱም ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥተውናል፡፡ ብርበራ የአንድ ግለሰብ የግል ሕይወት መብት የሚገደብበት እንደሆነ የገለጹት አቶ ዓለሙ፣ በቂና አሳማኝ ምክንያት እስካለ ድረስ ይገደባል፡፡ ሆኖም ለመበርበርም ሆነ ለመፈተሽ ቅድመ ሁኔታው፣ ሕግ፣ አስገዳጅ ሁኔታ ማለትም ወንጀል፣ የሕዝብ ጥቅምና የሌላው ሰው መብት ወዘተ ለመጠበቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ሲሟሉ የብርበራ ሕግ ይተገበራል፡፡

ባለሙያዎቹ የሚስማሙበት ነጥብ ገቢዎችና ጉምሩክ ባሥልጣንም ሆነ ሌላ ማንኛውም አካል ብርበራና ፍተሻ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለማካሄድ በሕግ ሊፈቀድለት እንደሚባ ነው፡፡

ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የወንጀል ጉዳዮች ክትትል ያገኘነው ማብራሪያ እንደሚያመለክተው፣ በገበያና በንግድ ማጭበርበር፣ በታክስ ስወራ፣ በሕወጥ ደረሰኝ ግብይትና መሰል ሥራዎች የተሰማሩትን በታክስ ሕጉ አዋጅ ቁጥር 284/95 እና 286/94 (በማሻሻያ አዋጆች 609/2001 እና 608/2001) መሠረት እንዲሁም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 32 እና 33 መሠረት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የመበርበር መብት ተሰጥቶታል፡፡

(በዚህ ዘገባ ላይ ዳዊት ታዬ፣ አስራት ሥዩም፣ ሃያል ዓለማየሁ፣ ብርሃኑ ፈቃደና ዘካሪያስ ስንታየሁ ተሳትፈዋል)