ሾፌሩም፣ ‹‹እሷ እባክህ ሰሞኑን የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋዎች ይጨምራሉ ብላ ሰግታ ያላትን ሁሉ አሟጣ አስቤዛ ስታደርግ ነው የከረመችው፡፡ እናም ወደ አስር ሊትር ዘይት በ40 ብር ሒሳብ፣ ስኳር በርከት አድርጋ፤ እንዲሁም የሳሙና ዓይነት በቃ ያልገዛችው ሸቀጣ ሸቀጥ አልነበረም፡፡ ታዲያ አሁን ዋጋው ተተምኖ ሲወርድ ጨርቋን ልትጥል ምንም አልቀራትም፤›› አለው፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹ሰው 25 ኪሎ ግራም ጨው ይገዛል?›› ብሎ ጥያቄውን ለወያላው ሰነዘረለት፡፡ ወያላውም፣ ‹‹ምናልባት አንተ የማታውቀው የቆዳ ፋብሪካ ይኖራቸው ይሆናል፤›› በማለት አሽሟጠጠው፡፡
እንዲህም በማለት ሌላ ሐሳብ አመጣለት፣ ‹‹የሚገርምህ በየሱቁ ስትሄድ የቀነሰ አንድም ነገር የለም፤ እኔኮ በቅርቡ ለተቀላቀለን ለሲስተር አራስ ልጅ የቆርቆሮ ወተት ቀንሷል ሲባል እንደምንም ልገዛለት ሄጄ ነበር፤›› ሲለው፣ ሾፌሩ፣ ‹‹ሲስተርህ ወለደች እንዴ?›› በማለት የመገረም ጥያቄ አቀረበ፡፡ ወያላው፣ ‹‹አዎ ወለደች፤ ምን የሚያስገርም ነገር አለው?›› ማለት፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹አአይ ነገሩን ነው እናንተ ቤት ሁላችሁም ወላዶች ናችሁ ማለት ነው?›› ብሎ የለበጣ ሳቅ ሳቀ፡፡ ወያላው እንደመበሳጨት ብሎ፣ ‹‹ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው፡፡ እርሱ እስከሰጠን ድረስ እንወልዳለን፤›› በማለት ምላሹን አቀረበ፡፡ ሾፌሩም እየተገረመ፣ ‹‹ሁላችሁም ወልዳችሁ ወልዳችሁ ማሰቃየት እንዳይሆን ብዬ ነው፤›› አለው፡፡ ወያላው ተናዶ፣ ‹‹ልንገርህ ምንም እንኳን የእግዚአብሔርን ቃል ባላውቅም ‹ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት› የሚለውን ቃል አውቀዋለሁ፤›› ሲለው፣ ሾፌሩ ክትክት ብሎ ሳቀ፡፡ ወያላው እየተበሰጫጨ፣ ‹‹ምን ያስቅሃል?›› አለው፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ምድርን ሙሏት የተባለው በእናንተ ቤተሰብ ብቻ ነው እንዴ?›› ብሎ አላገጠበት፡፡
በዚህ ዘመን የቤተሰብ ዕቅድ አለመጠቀም የሚያሳስብ ጉዳይ ነው፡፡ በየሚዲያው የቤተሰብ ዕቅድን ስለመጠቀም ይነገራል፡፡ የቤተሰብ ዕቅዱን ግን የሚጠቀምበት በጣም ትንሽ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ እናቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች ከባድ የጤና ቀውስ ያመጣሉ በሚል የተሳሳተ መረጃ ራሳቸውን ያቅባሉ፡፡ ሆኖም ግን መድኃኒቶቹ የተባለውን ያህል የጐን ጠንቆች እንደማያመጡ በሳይንስ የተረጋገጠ ነው፡፡ ወደ ወያላውና ሾፌሩ ክርክር ስንመለስ ሾፌሩ ወያላውን ለማረጋጋት እየሞከረ ነበር፡፡ የታክሲዋ ተሳፋሪዎች የዘንድሮን የኑሮ ጉዳይ ዘንግተን የወያላና የሾፌርን ውይይት እያዳመጥን ነው፡፡
ሾፌሩ ወያላውን እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ ‹‹በእናትህ የዱቄት ወተት ዋጋ ልትገዛ ሄደህ እንደነበር እኮ ጀምረህልኝ ነበር፤›› አለው፡፡ ወያላው ራሱን ካረጋጋ በኋላ፣ ‹‹የሚገርምህ ከቀድሞው ዋጋ አምስት ሳንቲም አልቀነሰም፤ ለምንድነው የማትቀንሱት? ስላቸው ይህንን ካስገባነው የቆየ ስለሆነ መጀመሪያ በገዛንበት ዋጋ ነው የምንሸጠው አይሉኝ መሰለህ? እከሳችሁኋለሁ! ስላቸው፣ የሚፈሩ ዓይነት አልነበሩም፡፡ እንዲያውም ‹አታስፈራራኝ› የሚለውን የእንትናን ዘፈን አያዘፍኑብኝ መሰለህ?›› በማለት ትከሻውን ሰበቀው፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ለዚህ ነው ሰሞኑን በየሱቁ ‹አታስፈራራኝ› የሚለው ዘፈን ከመጠን በላይ የሚደመጥበት ምክንያት?›› አለ፡፡ ወያላውም፣ ‹‹መሆኑ ነዋ፤›› ብሎ እሱም ‹‹አታስፈራሩና›› ማለት ጀመረ፡፡ የወያላው መልዕክት ለነጋዴዎች መሆኑ ነው፡፡
አንድ በኑሮ የተንገላታ የሚመስል ሰው መናገር ጀመረ፣ ‹‹የሆቴሎች የምግብና የመጠጥ ዋጋ መከለስ አለበት፤›› አለ፡፡ ወንደላጤ ሊሆን ይችላል፡፡ ቤቱ አብስሎ መብላት ስለማይችል የሆቴል ታማኝ ደንበኛ ሊሆን እንደሚችል ከንግግሩ ፍንጭ ማግኘት ይቻላል፡፡ እንዲህ በማለት ምሬቱን ገለጸ፣ ‹‹ስኳር ስለቀነሰ ማኪያቶ፣ ሻይና ኬክ እንዲሁም ከስኳር የሚሠሩ ሁሉ ዋጋ መቀነስ አለባቸው፤›› አለ እንደገና፡፡ ሰውዬው ሲያወራ አንገቱ ላይ ረጅም የደም ስር ይታይበታል፡፡ እልህ ይዞት ለድብድብ የሚጋብዝ እንጂ የሚያወራ አይመስልም፡፡ ለነገሩ ኑሮው በራሱ ሰውን አራስ ነበር አድርጐታል ማለት ይቻላል፡፡
ወያላና ሾፌር በሰውዬው ንግግር የተመሰጡ መስለው ማዳመጣቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሰውዬው ቀጠለ፣ ‹‹አንድ ጐረምሳ ጠቅልሎ የሚጐርሰውን ትንሽዬ በርገር በሃምሳና በስድሳ ብር መሸጥ የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም ዱቄት ቀንሷል ሥጋ ቀንሷል፤ ወዘተ፤›› አለ፡፡ ስለለስላሳ መጠጦችና ስለሌሎች ቅናሽ ስለተደረገባቸው ምርቶች ማብራሪያ አቀረበ፡፡ ሾፌርና ወያላ ተጠቃቀሱ፡፡ እነሱ የዱለት፣ የቀይ ወጥና የቅቅል ዋጋ በጣም አሳስቦአቸው እያለ እሱ ስለበርገር ያወራል በማለትም ተንሾካሾኩ፡፡
በሰውዬው ንግግር ልባቸው የተነካ አንድ እናት፣ ‹‹ልጄ አንተም ብትሆን በየሆቴሉ እየተንከራተትክ ዕድሜህንና ገንዘብህን ከምትጨርስ አንዷን ቆንጆ ብታገባስ? ከዚህ ሁሉ ጣጣ ትገላገል ነበር፤›› አሉት፡፡ ቀጥለውም፣ ‹‹እኔ አሁን በአሥራ ሁለት ዓመቴ ነበር የተዳርኩት፤ ይኸው እስካሁን ድረስ ከባለቤቴ ጋር በሰላምና በፍቅር እየኖርን እንገኛለን፤›› አሉ፡፡ ጐልማሳውም፣ ‹‹ ማዘር ማንን ላግባ?›› አለ በትካዜ መንፈስ፡፡ እማማም በሰውዬው ንግግር እጅግ እየተገረሙ፣ ‹‹ማንን ላግባ አልከኝ? አገሩ ጠቅላላ ሴትም አይደል እንዴ? ሴት አጣሁ ስትል እኔ እንደሰማሁህ ሌላ ሰው እንዳይሰማህ!›› አሉ፡፡ ሰውዬው አሁንም ብሶቱን ቀጠለ፣ ‹‹እርግጥ ነው ሴትማ ሞልቷል ነገር ግን ሚስት ናት የጠፋችው፤›› አላቸው፡፡
ይኼኔ በሴትና በሚስት መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ወደ አዕምሮዬ ቤተመጻሕፍት ጐራ ብዬ ማገላበጥ ጀመርኩ፡፡ ሴትዬዋ፣ ‹‹ወራጅ!›› በማለት ታክሲውን አስቆሙ፡፡ ታክሲው ቦታ ይዞ እሳቸውን ሲያወርድ ማዘር ለሰውዬው አንድ ምክር ጣል አደረጉለት፣ ‹‹ከልብ ካለቀሱ እምባ አይገድም፤ ስለዚህ ከልብህ ፈልጋት በቅርብ ታገኛታለህ፤›› ብለውት ወረዱ፡፡ ሰውዬው ወዲያውኑ ታክሲው ውስጥ ዓይኖቹን አንከራተታቸው፡፡ ወያላውም የሰውዬውን ዓይኖች መንከራተት ተመልክቶ፣ ‹‹እዚሁ መፈለግ ጀመረ፤›› አለ፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ለምን አንደኛዋን እህትህን አትድርለትም?›› አለው፡፡ ወያላውም፣ ‹‹እነሱ እንደ እስር ቤትና እንደ ትዳር የሚፈሩት ነገር የላቸውም፤›› አለው፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ታዲያ ዝም ብለው ከማንም እየወለዱ ለእናታቸው ማስታቀፍ አይሸክካቸውም እንዴ?›› አለው በአራዳ ዘይቤ፡፡
ወያላው መልስ ስላልነበረው፣ ‹‹አቦ ተወኝ፤ ራሳቸው እንደፈለጋቸው መሆን ይችላሉ፡፡ ትክክል ነው ብለህ የምታምንበትን ከመንገር ውጪ መቼም እጃቸውን ጠምዝዘህ አታጋባቸው፤›› አለ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹እነሱማ ልጅ በልጅነት ነው እያሉ መውለድን ፋሽን አድርገው ይዘውታል፤›› ብሎ በሐሳብ ጭልጥ አለ፡፡ ቤት ውስጥ በቅርቡ ስንት ሕፃናት እንደተወለዱ እየቆጠረ ይመስላል፡፡ ከዬትም መውለድ የሚያመጣው ጦስም ያሳሰበው ሳይመስል አይቀርም፡፡ ምስኪን፡፡
ሾፌሩ ሊያናድደው ቢያስብም ወያላው መናደድ አልፈለገም፡፡ ‹‹ቆይ ለምን ግን ሕፃናቱን ለአሳዳጊዎች አትሰጡም?›› በማለት ሾፌሩ ጠየቀ፤ ‹‹አንሰጥም!›› ሲል ወያላው መለሰ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹እናቴ ማደጐ ከምሰጥ እርስ በእርሳችን ተበላልተን ብናልቅ ይሻለኛል ባይ ናት፤›› አለው፡፡ ሾፌሩም በእናትዬው አቋም እየተደነቀ፣ ‹‹ለመሆኑ እናትህ ለምንድነው ለማደጐ መስጠት የማይፈልጉት?›› አለው፡፡ ወያላውም፣ ‹‹አራተኛ ልጇን ከፈረንጅ አገር ለመጡ ሰዎች ሰጥታ እስካሁን ድረስ የት እንደደረሰ አይታወቅም፡፡ ከዚያ በኋላ ይኼው ልጆቿንና የልጅ ልጆቿን እንደ እናት ዶሮ አቅፋ እያኖረችን ነው፤›› አለ ለእናቱ ያለውን ሐዘኔታ በሚገልጽ ስሜት፡፡
ከኑሮ ውድነት እስከ ቤተሰብ ምጣኔ፣ ከቤተሰብ ምጣኔ እስከ ማንን ላግባ፣ ከማንን ላግባ እስከ ማደጎ ልጆች፣ ከማደጐ ልጆች እስከ ወንደላጤ ድረስ የደረሰው የታክሲው ላይ ውይይት ገና መቋጫ አልተበጀለትም ነበር፡፡
ሁሉም የኑሮ ጉዳይ ነውና በሰፊው አጨቃጨቀ፣ አነጋገረ፡፡ ይኼኛው መወራት የለበትም ይኼኛው መነገር አለበት የሚባል የለም፡፡ ሁሉም የኑሮ አባዜ ነው፡፡ የታክሲው መድረክም የኑሮን ውጣ ውረድ መተረኪያ ሆኗል፡፡ ታክሲው ሲጎድል ወዲያው ይሞላል፡፡ ኑሮ ለአንዱ ይሞላል ለሌላው ይጐድላል፡፡ አንዱ ሲወጣ አንዱ ይገባል፡፡ አንዱ ሲደርስ ሌላው ይከተላል፡፡ የኑሮ አዙሪት ሁሉንም ከተለያየ አቅጣጫ እያመጣ ያዟዙረዋል፡፡ ይኼም ኑሮ ነዋ!


