በብርቱካን ፈንታ
ከዚህ ቀደም በሠራችው ‹‹እንቆቅልሽ›› በተሰኘው ፊልሟ የምትታወቀው ደራሲና ዳይሬክተር ቤዛ ኃይሉ፣ አሁን ደግሞ ‹‹ላም አለኝ...›› የተሰኘውን ሁለተኛውን ፊልሟን ከትናንት በስቲያ በዓለም ሲኒማ አስመረቀች፡፡
የአስቂኝ ድራማ ይዘት ያለው ይኸው በቤተሰብ፣ ጓደኝነትንና ገንዘብ በአቋራጭ ለማግኘት በሚታገል ወጣት ዙርያ የሚያጠነጥን የ1፡32 ሰዓት ርዝማኔ ፊልም ነው፡፡
የፊልሙ ዋናው ገጸ ባሕርይ መሳይ፣ ሀብታም ሆኖ በቪላ ውስጥ ለመኖርና ምርጥ መኪና ለማሽከርከር የሚመኝ ወጣት ቢሆንም፣ ሕልሙና አቅሙ ግን ሊመጣጠኑ አልቻሉም፡፡ ፊልሙ ሕልሙን እውን ለማድረግ የወሰደው አቋራጭ መንገድም እርሱን ብቻ ሳይሆን አብረው ያሉትን ወደ ገደል ሲከታቸው የሚያሳይ አዝናኝ ድራማ ነው፡፡
ፊልሙን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ሩብ ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ እንደተደረገበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ በፊልሙ ላይ ነባርና አዳዲስ ተዋናዮች ተሳትፈውበታል፡፡ ከነዚህም መካከል ሰለሞን ሙሄ፣ ሕይወት አበበና ንጉሤ ጌታቸው ይገኙበታል፡፡


