Wednesday, May 22nd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

‹‹አይወደኝም››

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

(በምሕረት አስቻለው)

የአሥራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ሳለች የተጀመረው፣ ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የዘለቀው የፍቅር ግንኙነቷ በብዙ ውጣውረዶች የተሞላ ነበር፡፡ ቢሆንም ለአራት ዓመታት ቆይቷል፡፡ ‹‹እነዚያ ዓመታት በጣም የተፈተንኩባቸው የሕይወቴ አስቸጋሪ ጊዜያት ናቸው፡፡ በፍቅር ግንኙነት ምክንያት የምጎዳ ዓይነት ሰው ብሆን ኖሮ አብቅቶልኝ ነበር፤›› የምትለን የሃያ ሦስት ዓመቷ የሕግ ባለሙያ ናት፡፡

ለአሥራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ዝግጅት እያደረገች በነበረችበት ወቅት የማታውቀውን የፍቅር ዓለም ያሳያት ጓደኛዋ ከቀድሞ ፍቅረኛው ጋር ዳግም ፍቅር መጀመሩን፤ ከሷ ጋር መቀጠል እንደማይችል ነግሯታል፡፡ የመጀመርያውና በንጹሕ ልቧ  የጀመረችው የፍቅር ግንኙነት በዚህ መልኩ መጠናቀቁ አሳዝኗታል፤ ተጎድታለችም፡፡ ነገር ግን ደጋግማ ለራሷ ጊዜው በሕይወቷ ወሳኝ መሆኑን በመንገር ጥናት ላይ ከመቼውም በበለጠ ለማተኮር ሞክራለች፡፡ የማትሪክ ውጤት አምጥታም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ችላለች፡፡ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ከትምህርት ቤቱ ሁለተኛ ነበረች፡፡

ፍቅረኛዋ ተመልሶ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ይቅርታ ጠይቋት እሷም ይቅር ብላ ዳግም ፍቅር ተጀመረ፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲ ስገባ እንደ አዲስ ግንኙነት ጀመርን፡፡ ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከሌላ ሴት ጋር ተመሳሳይ የፍቅር ግንኙነት መጀመሩን ሰማሁ፡፡ ስጠይቀው እውነት መሆኑን አመነ፡፡›› ከአምስት ወራት መለያየት በኋላ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ይቅርታ ጠይቋት አብረው ሆኑ፡፡ የጓደኛዋ እሷን እየተወ ሌሎች ሴቶችን የመፈለግ አመል ግን በዚህ አላበቃም፡፡ እሷ እንደምትለው፣ ይህን ያህል ጊዜ ማለት ከምችለው በላይ ድርጊቱን በተደጋጋሚ ፈጽሞታል፡፡ እንዲህ ያደረገው ለምንድነው ብለሽ አሰብሽ? አልኳት፤ ‹‹በቃ አይወደኝም፡፡ ስለማይወደኝ ደግሞ ያን ሁሉ ማድረግ ችሏል፡፡ አይወደኝም የሚለው የዘሪቱ ከበደ ዘፈን ለራሴ የተዘፈነ እስኪመስለኝ ድረስ ደጋግሜ አዳምጨዋለሁ፤›› ስትል መልሳልኛለች፡፡

የቱንም ያህል መስዋዕትነት ቢጠይቅ የመጀመርያ የፍቅር ግንኙነቷን ለማቅናት መድከም እንዳለበት፣ ጥረቷም እንደሚሳካ ታምን ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሌላ አዲስ ሰው መልመድ አስቸጋሪ እንደሚሆን በማሰብ ትፈራ ነበር፡፡ አለመፈለጓን፣ አለመወደዷን ለመቀበል በአእምሮዋ ምንም አይነት ቦታ አልነበረም፡፡ የፍቅር ግንኙነቱም ሊቋረጥ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ማወቅም መቀበልም ፈጽሞ ፍላጎቷ አልነበረም፡፡ ሁኔታዋን የተመለከቱ የፍቅረኛዋ ጓደኞች፣ እህቶቹም ጭምር ጥረቷ ከንቱ መሆኑን፣ እሱንም መተው እንዳለባት ነግረዋታል፡፡

በወቅቱ አለመፈለግን (አለመወደድን) መቀበል ካለመቻል፣ ዳግም አዲስ ሰው መልመድ ከመፍራት በተጨማሪ፣ ሰዎች ምን ይሉኛል? የሚለው ነገርም ያስጨንቃት ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን እውነቱን መጋፈጥ ግድ ሆነባት፡፡ ‹‹ለመጨረሻ ጊዜ ስንለያይ በሕይወቱ ሌላ ሴት ስላለች ሳይሆን እኔን እንደማይፈልገኝ ነግሮ ነው ያባረረኝ፡፡ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነበርኩ፡፡ ፈተናም ተቃርቦ ነበር፡፡ በመንገድ ላይ፣ ክፍል ውስጥና ላይብረሪ ሁሉ አለቅስ ነበር፡፡ ሁሉ ነገሬ ስለተመሰቃቀለ ከA ተማሪነቴ ሁለት D እንዳገኝ አድርጎኛል፡፡ አንድ አለኝ በምለው ትምህርቴ ላይ እንደዚያ መሆኔ አስደንግጦኛል፡፡››

ከዚህ በኋላ ግን ነገሮች ተቀየሩ፡፡ እውነታውን መቀበል፤ የታገለችለትና ስትፈልገው የነበረው ነገር ምን ያህል በሕይወቷ ዋጋ እንደሚኖረው መመዘን፣ ፍላጎቷም ምን ድረስ እውነት እንደነበር ራሷን በመጠየቅ ከራሷ ጋር ትግል ጀመረች፡፡ በዚህ ወቅት ሁኔታውን ‹‹ተይ አይሆንሽም›› ይሏት በነበሩ ሰዎች እይታ ትመለከተው ጀመር፡፡ በመጨረሻም ጊዜዋን፣ ኃይሏን፣ ጤናዋን ለማይረባ ግንኙነት፣ ለማይጠቅማት ነገር እንደከፈለች ተረዳች፡፡ ከአንድ ዓመት ብቸኝነት በኋላ ከሌላ ሰው ጋር ግንኙነት መሥርታለች፡፡ የቀድሞ ፍቅረኛዋ ግን ዛሬም ድረስ ይቅርታ እንድታደርግለት እንደሚጠይቃት ትናገራለች፡፡

‹‹አንድ ሰው በእውነት እየወደደ ተወዳጁ ተመሳሳይ ምላሽ ከሌለው በቃ መሔድ ነው፡፡ እኔ ያላደረግኩት ምን አለ?  ብሎ ራስን መጠየቅ፣ ከዚያ ሁሉንም ማድረጉን ካረጋገጠ አበቃ፤ ከዚያ ሌላ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡›› ዛሬ ላይ ቆማ ወደ ኋላ ስትመለከት፣ በነዚያ አራት ዓመታት የተሰቃየችው፣ ፍቅረኛዋ የምትፈልገው አይነት ሰብዕናና ሌሎችም መለኪያዎች ያሉት ሰው በመሆኑ ሳይሆን፣ ልጅ ስለነበረችና ስላልበሰለች ከምንም በላይ ደግሞ አለመፈለግን አምኖ ለመቀበል ዝግጁ ስላልነበረች እንደሆነ ትናገራለች፡፡

እሷ እንደምትለው፣ ራስን በመጉዳት፣ በመጨቅጨቅና በትግል መወደድን ማግኘት፤ ግንኙነትም እንዲቀጥል ማድረግ አይቻልም፡፡ ይልቁንም ራስን በማሻሻሉ ላይ በማተኮር የሚፈለገውን ሰው መሳብ ይቻላል፡፡ አልፈልግህም/ሽም መባል  ከባድ በመሆኑ ባልተረጋጋ ግንኙነት ውስጥ ካሉ፣ ቀድሞ መገኘትም አዋጭ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ፍቅር ብቻ ሳይሆን አለመፈለግም እልህ ውስጥ ከቶ ይበልጥ ለጉዳት ይዳርጋል፡፡

አለመፈለግን መቀበል ለሷ ምን ይመስል ነበር? ‹‹አጠና ነበር ስል አእምሮዬ ተከፍቶ አልነበረም፡፡ ሦስት ሰዓት ተቀምጬ አንድ ገጽ ሊሆን ይችላል የማነበው፡፡ ግን በጣም እሞክር ነበር፡፡ እዚያው አስቤ አልቅሼ ሳበቃ ማንበብ እጀምራለሁ፡፡ ምግብ አልበላም ነበር፡፡ ስለ ሕይወት ያለኝ ነገር ተዛብቶ ተስፋ የማደረግለት ነገርም አልነበረም፡፡ አንድ ካምፓስ ስለነበርን እያንዳንዷ ቀን ፈታኝ ነበረች፡፡ ግን በመጨረሻ ግንኙነቱ አይቀጥልም ስል አበቃ፤ ራሴን ከማሻሻሉና ከማሳደጉ ላይ ሆነ ትኩረቴ፡፡ ሰዎች ምን ይሉኛል የሚለው ፍርሀቴም ቀርቶ ስጠየቅ አፌን ሞልቼ ተለያየን እል ጀመር፡፡››

አስቸጋሪ የነበረው አለመፈለግን መቀበል ብቻ አልነበረም፡፡ በአሉታዊ ሁኔታዎች የተሞላው ግንኙነቷ በአመለካከቷ ላይ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ እንዳያልፍ ታግላለች፡፡ ወንዶቹ በጥቅሉ እንዲህ ወይም እንዲያ ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ አልደረሰችም፡፡ ከመጀመርያ ግንኙነቷ በመነሣትም የፍቅር ግንኙነቶች እንዲህ ናቸው ብላም በጥቅሉ ከተሳሳተ ድምዳሜ ላይ አልደረሰችም፡፡ ዳግም አለመፈለግ ይገጥመኛል በሚል ፍርሀት ግንኙነት ውስጥ ላለመግባትም ራሷን አላጠረችም፡፡ የቀድሞ ጓደኛዋ ጥሩ የሴት ጓደኞቼ ናቸው በማለት በተለያዩ ሴቶች ስላታለላት በማንኛውም መልኩ የሴት ጓደኞች ካሉት ወንድ ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመመስረት ግን ወስናለች፡፡ ውሳኔዋ ግን ምክንያታዊ ነው ብላ አትከራከርም፡፡ የአሁኑ ጓደኛዋም አንድም የሴት ጓደኛ እንደሌለው ገልጻልኛለች፡፡ አለመፈለግ በራስ መተማመኗ ላይም በተወሰነ መልኩ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ነገር ግን በሌሎች ሰዎችም አልፈለግም ወይም አልወደድም የሚል ሥጋት አላሳደረባትም፡፡

ወንደሰን በየነ፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በ2001 ነው፡፡ አሁን ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ የፋርማሲ ባለሙያ በመሆን እየሠራ ይገኛል፡፡
በዚህ ዘመን የፍቅር ጥያቄ በአብዛኛው የሚቀርበው በቃል ሳይሆን እጅ ወይም አንገት በመሳምና በሌሎችም ተመሳሳይ ድርጊቶች በመሆኑ ይሁንታንም ሆነ አለመፈለግን መረዳት ከባድ እንዳልሆነ ያምናል፡፡

የሴት ጓደኛው በሁለት ዓመት ትበልጠዋለች፡፡ ትምህርቷን የጨረሰችውም ቀድማው ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ሳለም ጥሩ ሥራ ይዛ ሕይወቷ ተደላድሎ የጎደላት ጋብቻ ብቻ ነበር፡፡ እሱ ጅማ፣ እሷ አዲስ አበባ በመሆኗ ርቀት በተወሰነ መልኩ በመካከላቸው ክፍተት ቢፈጥርም የጎላ ችግር አልነበረም፡፡ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ ክረምት ላይ አዲስ አበባ ሲመለስ በፍቅረኛው የተነገረው ነገር ድንገተኛና አስደንጋጭ ነበር፡፡ ‹‹ለኔ መልካም እንደምታስብ አውቃለሁ፤ ግን በቃ፣ አግብቻለሁ፤ አለችኝ፡፡ በዚያ ቅጽበት አዞረኝ፤ አጥወለወለኝ፤ ብዙ ተወዛገብኩ፤ በእረፍትና በመዝናናት ማሳለፍ የሚገባኝን ጊዜ በማሰብና ከራሴ ጋር በመወዛገብ አሳለፍኩ፡፡ እወዳታለሁ፤ ምርጫዋን ማክበር አለብኝ ብዬም ለራሴ ነገርኩት፡፡ እንደ እድል ሆኖ ይህ ሁኔታ የተከሠተው በክረምት  በመሆኑ አዲስ ዓመት ላይ ትምህርት ቤት ስገባ እውነታውን ተቀብዬ ነበር፡፡››

በእንደዚህ አይነት ሁኔታ አለመፈለግን መቀበል ከባድ ቢሆንም፣ እሷ ትምህርቷን ጨርሳ፣ ሥራ ይዛ ተደላድላ ስለነበር ቀጣይ ፍላጎቷን (ትዳር) ደግሞ እሱ ፈጽሞ ሊያሟላ በሚችልበት ደረጃ ላይ አለመሆኑ ሁኔታውን ለመቀበል ረድቶታል፡፡ በገንዘብ፣ በትምህርትና በሌሎች ነገሮች አወዳድራ የተወችው ቢሆን ኖሮ የመበለጥና የበታችነት ስሜት እውነታውን ይበልጥ አስከፊ ያደርጉበት እንደነበር ያምናል፡፡ ራሱን ለማረጋጋትና የሆነውን ለመቀበል ቀደም ሲል በመካከላቸው የነበረው ነገር እውነት እንደነበር ማመኑም ረድቶታል፡፡

ዳግም ተመሳሳይ ነገር ይገጥመኝ ይሆናል የሚል ፍርሃት አድሮበት ነበር፡፡ ምንም እንኳ ሴቶች እንደዚህ ወይም እንደዚያ ናቸው ብሎ ባይደመድምም፣ አመኔታን የማሳደር ችግር ግን ገጥሞት ነበር፡፡ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሳለም እንዲሁ ‹‹በመመቻቸት›› ከአንዲት ልጅ ጋር ግንኙነት ጀምሮ ነበር፡፡ ጥሩ ጊዜያትንም አሳልፈዋል፡፡ 2002 ክረምት ሲያልቅ እሱ ትምህርቱን ስለጨረሰ አዲስ አበባ ቀረ፡፡ እሷ ተመልሳ ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሔደች፡፡ በሴት ልጅ ላይ አመኔታን ማሳደር ያቃተው፣ የርቀት ግንኙነት ለመለያየት እንደሚያጋልጥ በሕይወቱ የተማረው ወንድወሰን ያ ግንኙነት በእዚያው ላይ እንዲያበቃ አደረገ፡፡

አለመፈለግን በግንኙነት መሐልም ሆነ መጀመርያ ላይ መቀበል ለማንም ቀላል ሆኖ አያውቅም፡፡ ብዙዎች እውነታውን ለመቀበል ከራሳቸው ጋር በሚያደርጉት ውዝግብ ከትምህርታቸው ወይም ከሥራ ገበታቸው ተስተጓጉለዋል፡፡ ብዙ የደከሙበትንና መስዋእትነት የከፈሉለትን ታላቅ ነገር ወደ ጎን ብለዋል፤ ጤናቸውን አጥተዋል፡፡ ሁኔታው ባሳደረባቸው ጠባሳም ረዥም ዓመታት ተሰቃይተዋል፡፡

ወንድወሰን ግን እውነታውን በመጋፈጥና ለራሱ ምክንያታዊ በመሆን ከከፋ ጉዳት ራሱን ጠብቋል፡፡ ከትናንት ተሞክሮው በመነሣት የወሰነው ውሳኔ ግን፣ ዛሬም ላይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ በሕይወቱ ያስፈልጉኛል ብሎ የሚያስባቸውን ነገሮች ሳያገኝና ሳያሟላ ከምንም አይነት የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ላለመግባት ለራሱ ቃል ገብቷል፡፡ ዛሬም ነጻና ብቸኛ ነው፡፡