በብርሃኑ ፈቃደ
የአትክልት ተራ ነጋዴዎች በፈቃዳቸው የዋጋ ተመን አወጡ፡፡ በ16 ያህል የምርት ዓይነቶች ላይ የወጣው የዋጋ ተመን ዝርዝር ባለፉት ቀናት በአትክልት ተራ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ነጋዴዎች ሱቆች ላይ ተለጥፎ ሲሠራበት የቆየ ሲሆን፣ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማን መነሻ አድርጐ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተግባራዊ እንደሚደረግ ነጋዴዎቹና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ባለፈው ዓርብ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ለአትክልትና ፍራፍሬዎቹ የወጣው የዋጋ ተመን ገበሬውንም እንዳይጐዳ፣ ነጋዴውንም እንዳያስቸግር ተደርጐ የተዘጋጀ እንደሆነ የነጋዴዎቹ ወኪሎች ገልጸው፣ ዋጋ መለወጥ በሚያስፈልግበት ወቅትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር የሚሻሻል እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡


