በዳንኤል ብርሃነ ሥላሴ
የዘገየው የመንግሥት ዕርምጃ ‹‹ከመቅረት መዘግየት ይሻላል›› የሚለውን ብሒል ቢያስታውሰንም፣ ቅጥ ያጣው የአገሪቱ የግብይት ሥርዓት በእንዲህ ዓይነቱ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ መቀጠል የለበትም ብለው ከሚሟገቱ ሰዎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡
የነፃ ገበያ ሥርዓት በጤናማ ውድድር ታጅቦ እየተካሄደ ነው ለማለት የሚያስችለን የገበያው ተዋንያን በፍትሐዊ መንገድ አቅርቦትንና ፍላጎትን ባማከለ ሁኔታ ግብይት እንዲያካሂዱ የተመቻቹ ነገሮች ሲኖሩ ነው፡፡ በስመ ነፃ ገበያ ከመሠረታዊ የኢኮኖሚ ሕግጋት ውጪ ገበያው ውስጥ መፈንጨት የሚፈልጉ ልጓም አልባዎች ካሉ ለሰበቦቻቸው መነሻ የሚሆኑ መሟገቻዎቻቸውን በአሳማኝ ሁኔታ ያቀርቡ ዘንድ ግድ ሲል፣ ሕገወጥነትን እንከላከላለን የሚሉ ኃይሎችም ለዕርምጃዎቻቸው ሕጋዊ መሠረቶቻቸውን ያቀርቡ ዘንድ እንዲሁ የግድ ይሆናል፡፡
እንደሚታወቀው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በ1984 ዓ.ም. አገሪቱን ከዕዝ ኢኮኖሚ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ሲያዘዋውር፣ በአገሪቱ ውስጥ የነበሩ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ስለ ነፃ ገበያ ሥርዓት የነበራቸው እውቀት እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ የግራ ርዕዮት አቀንቃኝ የነበረው ኢሕአዴግ በወቅቱ አስገዳጅነት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲን ሲያወጣ በርካታ አባላቶቹና ባለሥልጣናቱ ግርታ ውስጥ እንደነበሩም አይዘነጋም፡፡ በዓለም ባንክና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ተጽእኖ ተግባራዊ ይደረግ የነበረው የመዋቅራዊ ማስተካከያ ፕሮግራም በተለይ ለታዳጊ አገሮች እንደመድኃኒት ይታዘዝ ስለነበረ ኢሕአዴግም የዚህ ተጽእኖ ተቋዳሽ ነበር፡፡ የሆኖ ሆኖ በወቅቱ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የነፃ ገበያ ሥርዓት ስያሜ የተሰጠው ኢኮኖሚ እየተንገዳገደና ከዚህም ከዚያም ጋር እየተላተመ ለበርካታ የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ለአስመጪና ላኪ ድርጅቶች፣ ለአክሲዮን ማኅበራትና ለተለያዩ የግል ድርጅቶች እንደ አሸን መፍላት ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ባለፉት 19 ዓመታት የግሉ ዘርፍ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ሁነኛ የሆነ ሚና ለመጫወት የሚያስችለውን ጥንካሬ አግኝቷል ባይባልም፣ በተነጻጻሪ ሁኔታ በተለያዩ ዘርፎች ጉልህ የሆኑ ለውጦች ታይተውበታል፡፡ በእርግጥም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን ሊያሳዩ የሚችሉ አሳማኝ ምክንያቶች ባይኖሩም፣ ወደ ነፃ ገበያ ለመሄድ ያለውን ፍላጎት ሊያመላክቱ የሚችሉ ነገሮች አሉ፡፡ ወደ ንግድ ዓለም ለመግባት ያለው ፍላጎት በማደጉ አሁንም በተለያዩ መስኮች የሚሠማሩ በርካታ የአክሲዮን ኩባንያዎች እየተቋቋሙ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ሒደት ውስጥ በባህላዊ መንግድ ሲነግዱ የነበሩና የደርግ ዘመን የአየር ባየር ንግድ የወለዳቸውም በብዛት ይስተዋላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ባለበት አገር ውስጥ ደግሞ የንግድ አሠራሩ እንቅፋት እየገጠመው እንደሆነም በስፋት ይታያል፡፡
ከታኅሣሥ 28 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት በተወሰኑ መሠረታዊ የፍጆታና የአገልግሎት ምርቶች ላይ የዋጋ ጣሪያ ሲያወጣ፣ በዋነኝነት የተጠቀሰው ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ምክንያት የሆነው ጤነኝንት የጎደለው የንግድ ውድድር መስፈኑ ነው ተብሏል፡፡ የአገሪቱ የግብይት ሥርዓት እጅግ በጣም ኋላቀር ከመሆኑ የተነሳ፣ በእርግጥም በርካታ የአገራችን ነጋዴዎች በነፃ ገበያ ሥርዓት መኖር አለበት የሚባለውን ጤናማ የውድድር ጽንሰ ሐሳብን ያውቁታል ለማለት ይቸግራል፡፡ ገበያው የሚወሰነው ለጤነኛ ውድድር መሠረት የሆነው የአቅርቦት፣ የፍላጎት፣ የጥራትና የዋጋ ግንዛቤ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ሳይሆን፣ ገበያውን በተቆጣጠሩት እጅግ በጣም ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች መሆኑን አገር አውርቶ የጨረሰው ነው፡፡
በ1984 ዓ.ም. መንግሥት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲን አውጆ ተግባራዊነቱ ከመታየቱ በፊት ስጋት የነበራቸው አንዳንድ ሰዎች ያሉት ነገር ነበር፡፡ ከዕዝ ኢኮኖሚ በቀጥታ ወደ ነፃ ገበያ ከመሄድ ይልቅ፣ የቅይጥ ኢኮኖሚን ወይም የማኅበራዊ ግብይት ኢኮኖሚን ማስተዋወቅና ደረጃ በደረጃ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ መግባቱ ይሻላል በማለትም ይሞግቱ ነበር፡፡ በወቅቱ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆኑ አሁን ያሉት የንግድ ተዋናዮች ለዚህ ምክር ጀርባቸውን ቢሰጡም፣ ትልቁ ስጋት በዘፈቀደ በሚዘወረው የገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ ሥርዓተ አልበኝነት ይነግሳል የሚለው ነበር፡፡ በተለይም መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ የንግድ ሰዎች ነፃ ገበያን የተረዱት በኢኮኖሚ ሕግጋት ላይ ተመስርተው ሳይሆን እንደወረደ በተሰጠው ስያሜ ትርጓሜ ነበር፡፡
የነፃ ገበያ ሥርዓት ስሙ እንደሚያመለክተው ልጓሙ እንደተበጠሰ ፈረስ ዝም ብሎ የሚጋልብ ሳይሆን ሕግና ደንብን መሠረት አድርጎ በጤናማ የውድድር መንፈስ እየታገዘ የሚከናወን ነው፡፡ በኃላፊነት ስሜት አቅርቦትና ፍላጎት እየተመዘኑ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በገበያው ተዋናዮች መልካም ፈቃድ ሥር ተግባራዊ መሆን የሚገባው የነፃ ገበያ ሥርዓት፣ በልማዳዊና በአሮጌ አስተሳሰብ በታጠሩ አመለካከቶችና የአየር ባየር ንግድ በወለዳቸው እሳቤዎች ፈሩን ለቋል፡፡ በዚህም ምክንያት የግብይት ሥርዓቱ በአድማኞች ቁጥጥር ሥር ሆኖ የሕግ የበላይነት ባለበት አገር ውስጥ ዋጋ የሚተመነው በዘፈቀደ ሊሆን ችሏል፡፡ ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች እንደማፍያ ራሳቸውን በማደራጀት ገበያውን ከተቆጣጠሩት በእርግጥም ገበያው ጤነኛ አልነበረም፣ የግብይት ሥርዓቱም ሕመምተኛ ነበር፡፡ ከአምራቹ እስከ ቸርቻሪው ድረስ ያለው የአቅርቦቶች ዋጋ ገበያውን እንደፈለጉ በሚያጦዙ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደተፈለገው ይወጣ እንደነበር እማኝ መቁጠርም አያሻም፡፡ ይህንን ዓይነቱን ክሳችንን በቀላሉ የሚያጠናክርልን የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ በአገር ሰላም ምንም ዓይነት ችግር ባልተፈጠረበት ሁኔታ ውስጥ በጨው ገበያ ላይ የተፈጠረው ትርምስ ነው፡፡ መንግሥት በወቅቱ በወሰደው ያልተጠበቀ ዕርምጃ ባይደናገጡ ኖሮ የአገራችን ነጋዴዎች የጨውን ዋጋ በአንድ ጀምበር ከሁለት ብር ወደ 20 ብር አስገብተውት ነበር፡፡ ያ ትዝብት እስከዛሬ ድረስ ልባችን ውስጥ አለ፡፡ ወደፊትም አይረሳም፡፡
የዓለም ኢኮኖሚ መመሰቃቀልን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ በአንዴ እንዘጭ ባለበት ወቅት እንኳን የአገራችን የነዳጅ ዋጋ በተቃራኒው እንዴት ይጨምር እንደነበርም አንዘነጋም፡፡ የዋጋ መውጣትንና መውረድን ተከትሎ የዋጋ ማስተካከያ ሊደረግበት የሚገባው ነዳጅ ዋጋው ሲቀንስ እኛ አገር ባለበት ይቆማል፤ ዋጋው ሲጨምር ከቆመበት ወዲያው ጭማሪ ይደረግበታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስተዛዛቢ ነገር ነበር ለማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን በተለያዩ ተጽእኖዎች ምክንያት የምግብ ዋጋ ማሻቀቡ የማይቀር ዕዳ ቢሆንም፣ አጋጣሚውን እንደ መልካም ዕድል የተመለከቱት የእኛ አገር ነጋዴዎች ያወጡት የነበረው የዋጋ ተመን እጅግ የሚዘገንን ነበር፡፡ ጤፍ፣ ስንዴ፣ አተር፣ ምስር፣ ባቄላ፣ ወዘተ የመሳሰሉ የሰብል ምርቶች ዋጋቸው በአስደንጋጭ ሁኔታ ሲያሻቅብ ይነገሩ የነበሩ ምክንያቶችም አስተዛዛቢ ነበሩ፡፡ መንግሥት ችግሩን በጥልቀት ከመመርመር ይልቅ የሕዝቡ ኢኮኖሚያዊ አቅም በመዳበሩና የመግዛት ኃይሉ በመጨመሩ የኑሮ ውድነቱ መከሰቱን ያስተጋባ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለአገራችን አስደንጋጭ የዋጋ ንረት የዓለም ኢኮኖሚ ትርምስን በምክንያትነት ዘርዝሯል፡፡ መንግሥት የአገር ውስጥ የግብይት ሥርዓቱን በጥሞና ተመልክቶ የራሱን የዳሰሳ ጥናት ከማካሄድ ይልቅ ሳይታወቀው ለአልጠግብ ባይ ነጋዴዎች ከለላ ሲሰጥ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ በመረጃ ላይ ያልተመሠረተ ድምዳሜ ሸማቹን ሕዝብ ለብዝበዛ ከመዳረግ አልፎ ለራሱ ለመንግሥት ህልውና አደገኛ ሁኔታን ይዞ ከተፍ አለ፡፡ በአንድ ወቅት ፖለቲከኛው ዶክተር መረራ ጉዲና፣ ‹‹የሚበላው ያጣ ሕዝብ መንግሥትን መብላቱ አይቀርም፤›› ያሉት ትንቢት ከመድረሱ በፊት መንግሥት አሁን የዘገየውን ዕርምጃ መውሰድ ጀምሯል፡፡ ይህ የዘገየ የመንግሥት ዕርምጃ መንግሥት ራሱ በአማካሪዎቹ ወይም ጉዳዩ በሚመለከታቸው ሹማምንቱ ላይ ሳይቀር ቂም እንደሚያስቋጥረው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስደንጋጭ የዋጋ ንረት ከመከሰቱ በፊትም ሆነ በኋላ መፍትሔ የሚያፈላልጉ ሁነኛ ባለሙያዎች ያለመኖራቸው ጉዳይም ያስተዛዝባል፡፡ እንደ በቀቀን ያሉትን ከማስተጋባት በስተቀር ኃላፊነት የማይሰማው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለው ሚዲያን የሰሞንን ትጋት መመልከት ደግሞ የነበረውን አሳዛኝ ደንታቢስነት ያሳየናል፡፡ ‹‹አበረታች›› በሚባለው አሰልቺ ክሊሼ የተሞላው የመንግሥት ሚዲያ የመንግሥት የማረጋጊያ ዕርምጃን ተከትሎ እያሳየ ያለው ያዙኝ ልቀቁኝ ዓይነት ፈንጠዚያ የሚያሳየን ይህች አገር እንዴት ተበድላ እንደነበር ነው፡፡ በመሆኑም ሚዲያው ከማንም በፊት ቀድሞ ያሉትን ችግሮች ከማሳየት ይልቅ የመሪነት ሚናውን አሳልፎ ሰጥቶ ዛሬ ሁሉንም ነገር ወረት ሆኖበታል፡፡
ሸማቹ ሕዝብ አንገቱን ደፍቶ በሚያለቅስባቸው በእነዚያ በርካታ ዓመታት የግብይት ሥርዓቱን ጤናማ ባልሆነ መንገድ እንደፈለጉት ሲዘውሩት የነበሩት ነጋዴዎቻችን፣ ሰሞኑን መንግሥት በወሰደው ዕርምጃ ምክንያት ቀኑ እንደተደፋባቸው እየነገሩን ነው፡፡ ከአንዳንድ ምርቶች በስተቀር ማለትም ዘይት፣ ቢራ፣ ስኳርና ሳሙና ላይ አንዳንድ መታየት ያለባቸው ነገሮች ቢኖሩም በተቀሩት ምርቶች ላይ የሚያነሱት ጭቅጭቅ ውኃ አይቋጥርም፡፡ ከአንድ በሬ ሥጋ ከስንጥቅ በላይ ትርፍ የሚያገኙ የሥጋ ነጋዴዎቻችንና የተለያዩ ምርቶች አቅራቢዎችና ቸርቻሪዎች ይህንን በሚገባ ይረዱታል፡፡ የጤፍና የወጣ ወጥ እህሎች ነጋዴዎች ደግሞ ከዚህም በላይ ይኼ ሙግት ይገባቸዋል፡፡ የሰብል ምርቶች ውስጥ እብቅ፣ አሸዋ፣ ጠጠርና የመሳሰሉ ባዕድ ነገሮችን ከመጨመር ታልፎ በሚዛን ላይ የሚፈጸመው ውንብድና በርካታ ነገሮችን እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ ሥነ ምግባር የጎደለውና በደንታቢስነት የሚመራው ንግድ በርካታ እንከኖች አሉበት፡፡
ሰሞኑን በተለያዩ ወገኖች እየተነሱ ያሉ ጠንካራ ትችቶች አሉ፡፡ መንግሥት የወሰደው ዋጋን የማረጋጋት ዕርምጃ በነፃ ገበያ ውስጥ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን መፍጠር ነው በሚል ትችቶች ተሰንዝረዋል፡፡ የእኔ ጥያቄ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ አፍን ሞልቶ ለመናገር የሚያስችል የነፃ ገበያ ሥርዓት አለ ወይ ነው፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ በርካታ አምራችና የአገልግሎት ተቋማት ባሉበት አገር ውስጥ፣ የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ሞተር ለመሆን ባልበቃበት ሁኔታ ውስጥ፣ የባለቤትነታቸው ማንነት በውል ተለይቶ የማይታወቁ በርካታ የንግድ ድርጅቶች እያሉ፣ ስለነፃ ገበያ ሥርዓት ያለው ግንዛቤ በቂ ባልሆነበት ሁኔታና በሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች ነፃ ገበያ አለ ማለት ራስን ማታለል ነው፡፡ ለነፃ ገበያ ሥርዓት መኖር ዋነኞቹ ምልክቶች መንግሥት ከአምራችነትና ከአከፋፋይነት ሚና ውስጥ ወጥቶ የሕግ ማዕቀፎችን ማውጣት ላይ ማትኮር ይኖርበታል፤ ለሁሉም ወገኖች እኩል የሆነ የመወዳደሪያ ሜዳ መፈጠር አለበት፤ አቅርቦትና ፍላጎት የገበያውን ፍሰት መምራታቸው መረጋገጥ የግድ ነው፤ ጤናማ የሆነ ውድድር መኖሩ መረጋገጡና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ከላይ በመጠኑ ያነሳናቸው ለመነሻ ያህል የሚያገለግሉ አመላካቾች በሌሉበት ሁኔታ ስለ ነፃ ገበያ መነጋገሩ ፋይዳ የለውም፡፡
ሌላ ሌላውን እንተውና ለዚህ ማጠናከሪያ የሚሆነን የአገሪቱ መሠረታዊ የምግብ ምርቶች ገበያ በእነማን እጅ እንደወደቀ ተጨባጩን ሁኔታ እንመልከት፡፡ መንግሥት የአሁኑን ዕርምጃ እንዲወስድ ካነሳሱት ምክንያቶች መካከል ክንዳቸውም ልባቸውም እንደብረት የጠነከረ ከሰላሳ የማይበልጡ ግለሰቦችና ቡድኖች የምግብ ነክ ገበያውን 57 በመቶ በመቆጣጠራቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡ ጥቂት ግለሰቦች እንደፈለጉ የሚዘውሩት የምግብ ገበያ በነፃ ገበያ ሥር ነበር ሲባል ማንን ለማጃጃል ነው? ሸማቹ መላወሻ እስኪያጣ ድረስ እንደዘንዶ የተጠመጠሙበት እነዚህ ጥቂቶች ገበያውን እንደፈለጋቸው ከፈነጩበት ጤናማ የንግድ ውድድር አልነበረም፡፡ ጤናማ የንግድ ውድድር ካልነበረ ደግሞ አቅርቦትና ፍላጎት ገበያውን ሲወስኑት አልነበሩም፡፡ ስለዚህ የነፃ ገበያ ወሬ ፉርሽ ይሆናል ማለት ነው፡፡
አሁንም ክርክሩ እነዚህ ጥቂት ኃይሎች ለምን ገበያውን ተቆጣጠሩት ለማለት አይደለም፡፡ ጤናማ በሆነ የንግድ ውድድር ውስጥ አንዱ ሌላውን እየዋጠ ሊሄድ የሚችልበት ጤናማ አካሄድ አለ፡፡ አሁን ዋነኛው ክርክር እነዚህ ፈርጣማ ጥቂቶች የግብይት ሥርዓቱን ለምን በስምምነት ይመሩታል ነው፡፡ እነዚህ ጥቂቶች ገበያውን ሲቆጣጠሩት አቅርቦትን በመገደብ ገበያው ውስጥ ሰው ሠራሽ እጥረት ይፈጥራሉ፡፡
እጥረት ሲፈጠር ደግሞ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ንረት ይከሰታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ይሉኝታ ቢስ አካሄድ ያለበት የአገራችን ገበያ ከነፃ ገበያ ሥርዓት ጋር ፈጽሞ ሊነጻጸር አይገባውም፡፡ የቢራ ዋጋ ሲጨምር ፋብሪካዎቹ አንድ ላይ ከወሰኑ፣ የለስላሳ ዋጋ ሲንር ፋብሪካዎቹ አብረው ከመከሩ፣ የሥጋና የእህል ዋጋ ላይ ጭማሪ ሲቆለል ነጋዴዎቹ አብረው ከዶለቱ እንዴት ተብሎ ነው ነፃ ገበያ አለ የሚባለው? በነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ ጥቂቶች ገበያውን ተቆጣጥረው ዋጋን አንድ ላይ በፍፁም አይወስኑም፡፡ ግልጽነትና ፍትሐዊነት በጎደለው መንገድ በአድማና በምክክር የሚደረግ ንግድ በመጨረሻ የጥቃት ዒላማው የሚያደርገው ሸማቹን መሆኑን መዘንጋትም የለበትም፡፡ የነፃ ገበያ ሥርዓት በጤናማ የውድድር መርሆዎች ላይ የሚመሠረት እንጂ የማንም መፈንጪያ አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሳሳቢ ድባብ ውስጥ ሆነን መንግሥት የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ማረጋጋት አለበት ማለት አለብን፡፡ መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት ሲነሳ ግን የራሱን የቤት ሥራ መሥራት ይኖርበታል፡፡ የቤት ሥራው ደግሞ ዕርምጃው ተቀባይነትን ያገኝ ዘንድ ጠብሰቅ ያለ የገበያ ጥናት በማካሄድ የምርቶችን ዋጋ በትክክል ማስቀመጥ፣ የገበያው ዋነኛ ተዋንያን እነማን መሆናቸውን ማወቅ፣ በአምራች/አስመጪ፣ በአከፋፋይና በቸርቻሪ መካከል ያለውን መስተጋብር መረዳት፣ ከጅምላ እስከ ችርቻሮ ድረስ ነጋዴዎች የሚያገኙትን የትርፍ ምጣኔ በትክክል ማወቅ፣ በንግዱ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚደረጉትን አላግባብ የሆኑ ግንኙቶችን ማጤን፣ ለግብይት ሥርዓቱ በዋነኝነት እንከን የሆኑትን ግድፈቶች መለየት፣ ወዘተ ናቸው፡፡ ለዘመናት የተከማቸው ችግር እንዲህ አፍጥጦ ሲመጣ የእሳት ማጥፋት ዓይነት ዘመቻ ተጀምሮ ከሆነ የመንግሥት ዕርምጃ ይነቀፋል፡፡ ድንገት ከእንቅልፉ እንደነቃ ሰው በቅዠት ውስጥ የተጀመረ እንቅስቃሴ እንዳይመስል መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
መንግሥት ዕርምጃውን የወሰድኩት በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረው የዋጋ ንረት አሳማኝ ምክንያቶች በሌሉበት ሁኔታዎች ውስጥ እንዲባባስ በመደረጉና የሕዝቡን ጭንቀትና ዋይታ ማዳማጥ ግዴታዬ በመሆኑ ነው ብሏል፡፡ ሕዝቡ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ሲጠይቅ ደግሞ እጁን አጣጥፎ መቀመጥ እንደሌለበትም አስታውቋል፡፡ በዚህም መነሻነት የአምራቾችን፣ የአከፋፋዮችንና የቸርቻሪዎችን የመሸጫ ዋጋዎች በማገናዘብ በ16 ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ላይ ጣሪያ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በመቀጠልም በሌሎች ተጨማሪ ምርቶች ላይ የዋጋ ማሻሻያ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ዕርምጃ ሲወስድም ደጋፊ የሆኑ ሕጎችን እንደሚጠቀምም አብራርቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል በ1995 ዓ.ም. የወጣውን የንግድ አሠራር አዋጅን የተካውንና ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የወጣውን የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅን እንደ ግብዓት ይጠቀማል፡፡ የሸማቾች መብትን ለማስጠበቅና የንግድ አሠራሩ በጤናማ ሁኔታ እንዲካሄድ ይኼ አዋጅ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት ይጋብዛል ሲልም ይደመጣል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ጣልቃ ገብነት የማይመቻቸው ወገኖች ደግሞ መንግሥት ለዋጋ ግሽበቱ መንስዔ የሚሆኑ ዋነኛ ምክንያቶችን በመፈለግ ፖሊሲዎቹን ሊያስተካክል ይገባል ይላሉ፡፡ ለንግድ አሠራር ጤናማነት እንቅፋት የሚሆኑ ሌሎች ችግሮችን የመመልከት ግዴታ የመንግሥት እንደሆነ ሁላችንም እንገነዘባለን፡፡ መንግሥት ገበያን ለማረጋጋት ጣልቃ ሲገባ በበቂ ሁኔታ ጥናት ማድረግ እንዳለበትም መገንዘብ አለበን፡፡ በዓለም ላይ የተከሰተው የምግብ ዋጋ መናር በበርካታ አገሮች ላይ አሉታዊ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ሲተነበይና በዓለም ባንክና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አማካይነት መንግሥት ለመሠረተ ልማት ከሚያውለው ገንዘብ ላይ የተወሰነውን ለዋጋ ማረጋጊያ እንዲያውል ሲጠየቅ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቱ ይታወሳል፡፡ በዓለም ላይ እያንዣበበ የነበረውን የኢኮኖሚ ውድቀት ተከትሎ የሚመጣው የዋጋ ንረት ከፍተኛ ጉስቁልናን ሊያመጣ እንደሚችል በማሰብ የተደረገውም ዝግጅት ያን ያህል አመርቂ አልነበረም፡፡ አገሪቱ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር የነበራት ትስስር እዚህ ግባ የማይባል ስለነበር በኪነ ጥበቡ ተረፍን እንጂ አያያዛችን አስፈሪ ነበር፡፡
የመንግሥት የወቅቱ ዕርምጃ የመባነን ያህል እንዳይታይ ጥንቃቄ የሚያሻው ነው፡፡ መንግሥት ዕርምጃውን ለመውሰድ ሲነሳ በመረጃ የታገዘ መሆኑኑ ማሳየት አለበት፡፡ አሁን ክርክሩ መንግሥት ጣልቃ መግባት አለበት ወይስ የለበትም የሚለው ሳይሆን ለዕርምጃው ደጋፊ የሆኑ ጤናማ የሆኑ መረጃዎችና ሕጋዊ ድጋፎች አሉት ወይ የሚለው ነው፡፡ በአንዳንድ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ ያወጣው የዋጋ ተመን አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ መንግሥት ራሱ በሞኖፖሊ በያዘው የስኳር ምርት አቅርቦት ያለውን ለአብነት እንመልከት፡፡ የስኳር የጨረታ መነሻ ዋጋ በኪሎ ሒሳብ 12 ብር ነው፡፡ ነጋዴዎች የጨረታውን ጣሪያ 13.78 ብር አድርሰውታል፡፡ ከዚያ ቸርቻሪዎች ዘንድ ሲደርስ የመሸጫ ዋጋው 16 ብር ይደርሳል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ የአሁኑ የችርቻሮ የመሸጫ ዋጋ እንዴት 14 ብር ይሆናል ነው፡፡ ወይስ አንድ ሹም እንዳሉት መልሱ ‹‹ከፈለጋችሁ ክሰሩ›› ብቻ ነው? መንግሥት የጨረታውን ዋጋ ማውረድ አለበት፡፡ የስኳር የመነሻ ዋጋ በተቻለ መጠን ከ10 ብር በታች መውረድ ይኖርበታል፡፡ የአንድ ኪሎ ስኳር የማምረቻ ዋጋና የጨረታ መነሻ ዋጋ መታየት አለበት፡፡ ቢራና ለስላሳ መጠጦች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋቸው ሲቀንስ አምራቾቹስ እንዴት እንደሚቀንሱ ይታወቃል? ወይስ እንደሚባለው ፋብሪካዎቹ የመንግሥትን ማብራሪያ እየጠበቁ ገበያው ውስጥ እጥረት ይፈጠራል? በቂ ጥናት ያልተደረገበት የሸቀጦች ገበያ አስፈላጊው ቅኘት ካልተደረገበት አሁን እየታየ እንዳለው ገበያው በውዥንብር ብቻ የተሞላ ይሆናል፡፡
የመንግሥት ዋነኛ ኃላፊነት በአዋጁ መሠረት ነጋዴዎች በዋጋ ላይ እንዳይመሳጠሩ መቆጣጠር፣ ሕገወጥ የሆነ የምክክር ጨረታን መከላከል፣ ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ ሸቀጦችን የሚደብቁትን መቅጣት፣ የንግድ እንቅስቃሴን የሚያውኩ ድርጊቶችን መግታት፣ በአጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱ ውስጥ አሉታዊ ሚና የሚጫወቱ ኃይሎችን በመለየት በሕጋዊ መንገድ ዕርምጃ መውሰድ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር የሚገናዘቡና በሸማቹ ሕዝብም ተቀባይንት ያላቸው የሸቀጦች ዋጋዎች በስምምነት ወጥተው በይፋ ይታወቁ ዘንድ ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡ ዕርምጃዎች ሲወሰዱም ደጋፊ የሆኑ ሕጋዊ ማዕቀፎች በአሳማኝ ሁኔታ መተንተን አለባቸው፡፡ ይህንን ዓይነቱን ሕጋዊ አካሄድ በመቃረን በአገርና በሕዝብ ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ የሚፈልጉ ኃይሎችን ከንግድ ሥራ ውጪ እንዲሆኑ የማድረግ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡
የመንግሥት ሌላው ትልቁ ሚና ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጋር በመመካከር በኢኮኖሚው ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ ፍለጋ ውስጥ መግባት ነው፡፡ እዚህ ላይ እንደአብነት ማንሳት የሚገባን የጋናን ተሞክሮ ነው፡፡ ጋና በዓለም ላይ እያንዣበበ የነበረው የኢኮኖሚ ድቀት ከመከሰቱ በፊት በታዋቂ ልጆቿ አማካይነት ዝግጅት አድርጋ ነበር፡፡ የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናንና የቀድሞው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ኪንግስሊ ዋይ አሞአኮ (በነገራችን ላይ ሁለቱም በተለያዩ ወቅቶች በተባበሩት መንግሥታት አካላት ውስጥ በመመደብ አዲስ አበባ ውስጥ ሠርተዋል) የሚመሩት የአገሪቱ ኢኮኖሚስቶች የተሳተፉበት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ነበር፡፡ በእነዚህ ሁለቱ ታዋቂ ሰዎች የተመራው ግብረ ኃይል የዓለም ኢኮኖሚ ውድቀት በጋና ላይ የሚፈጥረውን ተጽእኖ በመተንተንና መፍትሔ በማፈላለግ አገሪቱን ታድጓል፡፡ በሠሩት አስመስጋኝ ሥራ ጋና በዋጋ ንረትና ተያያዥ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ሳትመታ አስፈሪውን ጊዜ በሰላም አሳልፋዋለች፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው እንዲህ ዓይነት የባለሙያዎች የመፍትሔ ዕርምጃ ነው፡፡ አንድ ችግር ሲያጋጥም እየበረገጉ የሚያስበረግጉ ሳይሆኑ ለአገራቸውና ለሙያቸው ክብር ያላቸው ባለሙያዎች ይፈለጉ ዘንድ የግድ ይላል፡፡ ያልተጠቀምንበትን የተማረ የሰው ኃይል ለአገር ግንባታና ዕድገት መጠቀምን ባህል ማድረግ አለብን፡፡
የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን በሌላ መንግድ ለሚተረጉሙትም ምላሽ ይኖራል፡፡ አንዳንዶች የሰሞኑን የመንግሥት ዕርምጃ ከሶሻሊዝምና ከአምባገነንነት ጋር ያያይዙታል፡፡ ይህን ዓይነቱን አስተያየት ቢሰጡ መብታቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አንዳንድ ግንዛቤዎችን ግን ፈር እንዳይስቱ ያስፈራል፡፡ የአውሮፓና የአሜሪካ የፋይናንስ ተቋማት ኪሳራ በኪሳራ ሲሆኑ ፈጥነው የደረሱላቸው መንግሥታቱ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ ታላላቆቹን የፋይናንስ ተቋማት እነዚህ የነፃ ገበያ አራማጅ መንግሥታት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ባይሰጧቸው ኖሮ አሁን ያለው የዓለማችን ገጽታ ምን ሊመስል እንደሚችል ሁላችንም ይገባናል፡፡ መንግሥታቱ ያንን ዕርምጃ የወሰዱት የሠራተኞች ቅነሳ እንዳይከሰትና አገሮቹ የድህነት ማጥ ውስጥ እንዳይገቡ ነበር፡፡ ያኔም የኦባማ አስተዳደር ሳይቀር ‹‹ሶሻሊስት›› ተብሎ ተተችቷል፡፡ በአንድ ጠበብ ያለ አስተሳሰብ ውስጥ ሆኖ ግዙፉን ምስል እንደተራ ነገር የማየት አባዜ ካለቀቀን አስከፊውን አደጋ እንዴት ልንቋቋመው እንደምንችል መዘንጋት ያሳስባል፡፡ ተወደደም ተጠላ በአገራችን ቅጥ ባጣና መረን በተለቀቀ የግብይት ሥርዓት ውስጥ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መኖሩ የማይቀር ነው፡፡ በነፃ ገበያ ውስጥ እንዴት ጣልቃ ይገባል ለሚሉ የዋሆች ደግሞ ምላሽ የሚሆነው ወትሮስ ነፃ ገበያ የሚባለው ነገር ነበር ወይ ነው፡፡ የአገራችን ሥነ ምግባር የጎደለው የንግድ አሠራር ጣልቃ ካልተገባበት ሥርዓት አልበኝነት ነግሶ ትርምስ ሊፈጠር እንደሚችል መዘንጋት ደግሞ ከየዋህነትም በላይ ጅልነት ነው፡፡
የንግዱ ማኅበረሰቡ ራሱን የአገሪቱ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆን እንደሚገባው እስካላሳመነና ለተግባራዊነቱም እስካልተነሳ ድረስ የችግሩ አካልና ተጠያቂ እንደሚሆን መገንዘብ አለበት፡፡ ጤናማ ውድድር ይኖር ዘንድ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ መሥራት አለበት፡፡ መንግሥትም እከተለዋለሁ የሚለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አዋጭ በሆነ መንገድ ይጓዝ ዘንድም ጤናማ የንግድ አሠራር እንዲሰፍን መሥራት አለበት፡፡ መንግሥት በበኩሉ ኪራይ ሰብሳቢ የሚላቸው ልማታዊ ሆነው ሲገኙ፣ ልማታዊ የሚላቸው በኪራይ ሰብሳቢነት ሲመደቡ ለራሱም ቢሆን የሚተርፈው ትዝብት መሆኑን በማጤን ለፍትሐዊ የንግድ ውድድር መፈጠር መትጋት አለበት፡፡ ይኼ በዘፈቀደ የሚወራለት ነፃ ገበያ የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ጥልቅ ግንዛቤ አግኝቶ የገበያው ተዋንያን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ይዘውሩት ዘንድ አስፈላጊውን መደላድል እንዲፈጠር ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ በመደነባበር ሁሉም እየገባ የሚጨፍርበት ብልሹው የግብይት ሥርዓት የባሰ ጣጣ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ገበያውን በአንድ ጊዜ በምርት እጥረት በመምታት በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የተፈጠረውን ጊዜያዊ ወዳጅነት ይበታትነዋል፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥትና የሕዝብ መተማመን ከተሸረሸረ አደጋው የከፋ ነው፡፡
በሸማቹ ሕዝብ በኩል የሚታየው ትልቁ ድክመት ደግሞ ለመብቱ ጠበቃ ሆኖ የሚከራከርለት ጠንካራ የሸማች ማኅበር አለመኖሩ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ተቋም በከፍተኛ መንፈስ ሲመሠረት በመንግሥት፣ በነጋዴውና በሌሎች የገበያው ኃይሎች ላይ ጫናውን ከማሳረፉም በላይ ሸማቹ ሕዝብ በሸቀጦች ወቅታዊ ዋጋ ላይ በቂና ተጨባጭ መረጃ ይኖረዋል፡፡ መንግሥት ለሚወስደው ፍትሐዊ ዕርምጃም በበቂ ሁኔታ የዋጋ ዝርዝር ግብዓት ማቅረብም ይችላል፡፡ የአገሪቱን ገበያ በሙሉ ኃይላቸው የተቆጣጠሩ ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖችም ከሕገወጥ ድርጊቶቻቸው እንዲታቀቡ ጠንካራ መልዕክት ይተላለፍላቸዋል፡፡ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ማንኛውም ዓይነት ዕርምጃ ጤናማና ፍትሐዊ ተብሎ የሁሉንም ወገን ይሁንታ ያገኛል፡፡ በመረጃ ላይ ያልተመሠረተ ሕዝብ፣ አገርና መንግሥት የትም መድረስ አይችልም፡፡


