በዮሴፍ ሣህለ ሥላሴ
በቅርቡ መንግሥት በኢትዮጵያ ለተከሰተው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት እንደ መፍትሔ ይሆን ዘንድ፣ በ16 የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ተመን በማውጣት ዕርምጃ ወስዷል፡፡ ለመሆኑ መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ ከንግድ አሠራርና ከሸማቾች ጥበቃ አዋጅ አንጻር እንዴት ይታያል፣ በአዋጁ ሸማቾችን ከመጠበቅ አንጻር ድርጊቶች ምንድን ናቸው? የሚለውን ነጥቦች በማንሳት ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ በአንቀጽ 46 አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር [አሁን ንግድ ሚኒስቴርና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተብሎ ተከፍሏል] የዋጋ ቁጥጥር ሊደረግባቸው የሚገቡ መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ ያደረገውን ጥናት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ በማስፈቀድ ዝርዝራቸውንና ዋጋዎቻቸውን በሕዝብ ማስታወቂያ ሊያወጣ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በአዋጁ መሠረት መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎች ማለት በገበያ ላይ እጥረት በመፍጠሩ ምክንያት ተገቢ ያልሆነ የንግድ ሥራ ሊያስከትል የሚችል ከሸማቾች የየዕለት ፍላጐት ጋር የተገናኘ ዕቃ ወይም አገልግሎት ነው፡፡
የንግድ አሠራርና የሸማቾች ባለሥልጣን እንደ ሁኔታው የንግድ ዕቃዎች እንዲያዙ ወይም እንዲሸጡ ሊያደርግ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 35(3)(ሀ) ተደንግጓል፡፡
ሸማቾችን ከመጠበቅ አንጻር አዋጁ በነጋዴዎች ላይ የተለያዩ ክልከላዎችን ያስቀምጣል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ፡-
ዕቃዎችን ማከማቸት (Hoarding)
የንግድ ዕቃዎችን ከመደበኛ የግብይት አሠራር ውጪ ማከማቸት ወይም መደበቅ የተከለከለ ሲሆን፤ የንግድ ዕቃ ተከማችቷል ወይም ተደብቋል የሚባለው በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ዕቃው በገበያ ላይ እጥረት ያለበት መሆኑ የተገለጸ፣ የንግድ ዕቃው ተከማችቶ ወይም ተደብቆ የተገኘበት መጠን የነጋዴዉን የንግድ ካፒታል 25 በመቶ ሲያህል ወይም ነጋዴ ባልሆነ ጊዜ ለግል ወይም ለቤተሰብ ፍጆታ ከሚውል መጠን በላይ በሆነ ጊዜና ከውጭ አገር የመጣ የንግድ ዕቃና ምርት ጥሬ ዕቃ ወይም ከውጭ አገር በመጣ የምርት ጥሬ ዕቃ በአገር ውስጥ የተመረተ የንግድ ዕቃ እንደ ቅደምተከተሉ ወደ አገር ውስጥ ከገባበት ወይም ከተመረተበት ቀን ጀምሮ ለሦስት ወራት ለሽያጭ ወይም ለምርት አገልግሎት ካልዋለ፤ ወይም ከአገር ውስጥ በተገኘ የምርት ጥሬ ዕቃ የተመረተ የንግድ ዕቃ የተመረተ የንግድ ዕቃና ከአገር ውስጥ የተገኘ የምርት ጥሬ ዕቃ ወይም ለቤተሰብ ፍጆታ ከሚውለው በስተቀር በአገር ውስጥ የተመረተ የእርሻ ምርት እንደ ቅደም ተከተሉ ከተመረተበት ወይም ነጋዴው ወይም ሌላ ማንኛውም ሰው ከገዛው ቀን ጀምሮ ለሁለት ወራት ለሽያጭ ወይም ለምርት አገልግሎት ካልዋለ ነው፡፡ (አንቀጽ 45)
በአዋጁ አንቀጽ 49(6) መሠረት የንግድ ዕቃዎችን አከማችቶ ወይም ደብቆ የተገኘ ማንኛውም ነጋዴ ከብር 200,000 እስከ 400,000 በሚደርስ የገንዘብ መቀጫና ከሦስት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡
በበላይነት የተያዘን ገበያ ያለአግባብ መጠቀም
በአዋጁ አንቀጽ 5 በግልጽ እንደተመለከተው፣ ማንኛውም ነጋዴ በግሉም ሆነ ከሌሎች ጋር በመሆን በበላይነት የያዘውን ገበያ በግልጽም ሆነ በስውር ያለአግባብ በመጠቀም የንግድ ሥራ ማካሄድ እንደማይችል ይገልጻል፡፡ ነጋዴ ገበያውን በበላይነት ይዟል የሚባለው፡- ነጋዴው በግሉ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን የአንድ የገበያ ክልል ውስጥ ዋጋን ወይም ሌሎች የንግድ ድርድር ሁኔታዎችን የመቆጣጠር ወይም ውድድርን የማጥፋት ወይም በግልጽ የመገደብ የተረጋገጠ አቅም ያለው ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡
አንድ ገበያ በበላይነት መያዙን ለማረጋገጥ ነጋዴው በገበያው ውስጥ ያለው ድርሻ ወይም ሌሎች ወደ ገበያው እንዳይገቡ ለመከልከል ያለው አቅም፣ የተባለው ገበያ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ወይም የሚተካኩ የንግድ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን የያዘ ሲሆንና የገበያው መልክአ ምድራዊ ክልል የውድድር ሁኔታዎች በበቂ ሁኔታ አንድ ዓይነት የሆነበትና በአጐራባች ገበያዎች ከሚታዩት የውድድር ሁኔታዎች የሚለዩበት መሆኑን አዋጁ ይገልጻል፡፡ የበላይነትን ያለአግባብ የመጠቀም ድርጊቶች የሚባሉት፡-
- ምርትን መገደብ፣ የንግድ ዕቃዎችን ማከማቸት፣ መደበቅ ወይም በመደበኛው የንግድ መስመር እንዳይሸጡ ማድረግ ወይም መያዝ፣
- የንግድ ውድድርን ለመገደብ ወይም ለማጥፋት በማሰብ ከማምረቻ ዋጋ በታች የውስጥ ወይም የተወዳዳሪን ወጪ የማሳደግ ወይም ግብዓቶችን ወይም የሥርጭት መስመሮችን ቀድሞ በመዝጋት ተወዳዳሪ ላይ ያነጣጠረ ድርጊት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መፈጸም፣
- በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ፍትሐዊ ያልሆነ የመሸጫ ዋጋ ወይም የመግዣ ዋጋ መጠየቅ፣
- ግልጽና ወቅታዊ የሆነ የገበያ አሠራርን በሚቃረን መልኩ ገበያን በበላይነት የያዘው ነጋዴ በልማድ የሚያደርገውን ወይም ሊያደርገው የሚችለውን እንደማይችል ሆኖ ለመደራደር ፈቃደኛ አለመሆን፣
- አሳማኝ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ሳይኖር፣ ገበያን በበላይነት በያዘ ነጋዴ ቁጥጥር ስር ያለን ተፈላጊ ግብዓት ተወዳዳሪ ለሆነ ወይም ሊሆን ለሚችል ነጋዴ መከልከል፣
- የንግድ ውድድርን ለመገደብ ወይም ለማጥፋት በማሰብ በዕቃዎችና አገልግሎቶች አቅርቦትና ግዢ ላይ በደንበኞች መካከል በዋጋና በሌሎች ሁኔታዎች ልዩነት መፍጠር፣
- የአንድን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት አቅርቦት፣ ሌላ ተወዳዳሪ የሆነን ወይም ያልሆነን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ከመቀበል ጋር እንዲገናኝ ማድረግ ወይም ሌላ ተወዳዳሪ የሆነውን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት በማከፋፈል ወይም በማምረት ላይ ገደብ መጣል፣ ወይም በገዥው ከሚፈለገው የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ጋር ግንኙነት ከሌለው የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ጋር እንዲገናኝ ማድረግ፣
- የንግድ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን አቅርቦት በተመለከተ የት? ወይም ለማን? ወይም በምን ሁኔታ? ወይም በምን ያክል መጠን? በምን ያክል ዋጋ? እንደገና መሸጥ ወይም ወደ ውጭ መላክ እንዳለበት ገደቦችን መጣል የበላይነትን ያለአግባብ የመጠቀም ድርጊቶች መሆናቸውን አዋጁ በአንቀጽ (8) ይጠቅሳል፡፡
በበላይነት የተያዘን ገበያ ያለ አግባብ የተጠቀመ ነጋዴ የዓመታዊ ገቢውን 15 በመቶ እንደሚቀጣ ሕጉ በአንቀጽ 49(1) ይደነግጋል፡፡ የዓመታዊ ገቢውን መጠን መወሰን ባልቻለ ጊዜ ከብር 500,000 (አምስት መቶ ሺሕ) እስከ 1,000,000 (አንድ ሚሊዮን) ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጫና ከአምስት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽጉ እሥራት ይቀጣል፡፡
ተገቢ ያልሆነ የውድድር ተግባር
ፀረ ውድድር ወይም የገበያ ውድድርን የሚገድብ ተግባራት ማለት ዋጋ በመቀነስ ተመሳሳይ የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚሸጡ ነጋዴዎችን ኪሳራ ላይ በመጣል ወይም በተመሳሳይ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቅለል ወይም ሌሎች ነጋዴዎች ወደ ንግድ እንዳይገቡ በመከልከል ወይም የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ሻጮች የሚሸጡበትን ዋጋ እንዳይወስኑ በመከልከል ወይም የሸማቾችን ወይም የተጠቃሚዎችን ምርጫ በመገደብ የንግድ ዕቃዎችን ወይም የአልግሎቶች ሽያጭን ከሌሎች ተመሳሳይ ካልሆኑ የንግድ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ሽያጭ ጋር በማያያዝ በንግድ ሥራ ውስጥ የሌሎች ነጋዴዎች የመወዳደር አቅም የሚገድብ ተግባራት ናቸው፡፡
በአዋጅ አንቀጽ 21 (1) እንደተቀመጠው በንግድ ሥራ ሒደት ውስጥ ማንኛውም ሀቀኛ ያልሆነ አሳሳች፣ አታላይነት ያለበትና የተወዳዳሪን የንግድ ጥቅም የጐዳ ወይም ሊጐዳ የሚችል ድርጊት ወይም ተግባር በተወዳዳሪ ላይ ያነጣጠረ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር መሆኑን ይገልጻል፡፡
ተገቢ ያልሆኑ የንግድ ውድድር ተግባራት ተብለው በአዋጁ የተጠቀሱት፡-
- በሌላው ነጋዴ ወይም በነጋዴው ተግባሮች በተለይም ነጋዴው ከሚያቀርበው የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ጋር በተገናኘ ሁኔታ ማደናገርን ያስከተለ ወይም ሊያስከትል የሚችል ማናቸውም ድርጊት ባለመብት ከሆነው የመረጃው ባለቤት ነጋዴ ፈቃድ ውጪ ከሀቀኛ የንግድ አሠራር ተፃራሪ በሆነ ሁኔታ የሌላውን መረጃ የማውጣት፣ የመያዝ ወይም የመጠቀም ማናቸውም ድርጊት፣
- የሌላውን ነጋዴ ወይም የነጋዴውን ተግባራት በተለይም ነጋዴው ከሚያቀርበው የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ጋር በተገናኘ ሁኔታ ታማኝነትን ያሳጣ ወይም ሊያሳጣ የሚችል ማናቸውም ሀሰት የሆነ ወይም ማረጋገጫ የሌለው አገላለጽ፣
- በንግድ ማስተዋወቅ ሥራ ሒደት የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በሀሰት ወይም በተዛባ ሁኔታ ማነጻጸር፣
- ከንግድ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ዋጋ ወይም ባሕሪ ወይም አመራረት ወይም ከማምረቻ ቦታ ወይም ከይዘት ወይም ከአጠቃቀም ምቹነት ወይም ከጥራት ጋር በተገናኘ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ምንጩ ያልታወቀውን ጨምሮ ለሸማቾች ወይም ለተጠቃሚዎች ሀሰተኛ ወይም የተዛባ መረጃ ማሰራጨት፣
- ሚስጥራዊ የሆኑ የሌላ ነጋዴ የንግድ መረጃዎችን በቀድሞ ተቀጣሪዎቹ አማካኝነት ማግኘት ወይም ለማግኘት መሞከር ወይም መረጃዎቹን በማግኘት የነጋዴውን ደንበኞች ለማስኮብለል ወይም ሌላ ተወዳዳሪነቱን ለሚቀንስ ዓላማ መጠቀም ናቸው፡፡
ያለ አግባብ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር ያደረገ ነጋዴ በአዋጁ አንቀጽ 49 (3) በግልጽ እንደተቀመጠው፣ የዓመታዊ ገቢውን አስር በመቶ ወይም የዓመታዊ ገቢውን መጠን መወሰን ባልተቻለ ጊዜ ከብር 300,000 (ሦስት መቶ ሺሕ) እስከ 600,000 (ስድስት መቶ ሺሕ ብር) በሚደርስ የገንዘብ መቀጫና ከሦስት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡
የንግድ ውድድሮችን የሚያግድ ስምምነት ማድረግ
በአዋጁ አንቀጽ 11 በግልጽ እንደተመለከተው፣ የንግድ ውድድርን የሚያግድ ዓላማ ወይም ውጤት ያለው ስምምነት ማድረግ፣ በኅብረት አቋም መያዝ ወይም በማኅበር ውሳኔ ማስተላለፍ የተከለከለ ነው፡፡
በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ዋጋን ለመወሰን፣ ተመሳጥሮ ለመጫረት፣ ደንበኞችን ወይም የገበያ ክልልን ወይም ምርትና ሽያጭን በኮታ ለመመደብ ወደ ጐን ግንኙነት ባላቸው ነጋዴዎች (በአንድ ገበያ ውስጥ ባሉ ተወዳዳሪ ነጋዴዎች መካከል) ስምምነት ማድረግ ወይም በኅብረት አቋም መያዝ ወይም በማኅበር ውሳኔ ማሳለፍ የተከለከለ ድርጊት ነው፡፡ (አንቀጽ 13(1)) ዓላማው ወይም ውጤቱ ዝቅተኛ የችርቻሮ ዋጋ መወሰን የሆነ ስምምነት ግንኙነታቸው ከላይ ወደ ታች በሆኑ ነጋዴዎች (በነጋዴዎችና በደንበኞች ወይም በአቅራቢዎች ወይም ከሁለቱም ጋር በሚኖር ግንኙነት) ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡
ተገቢ ያልሆነ ስምምነት ማድረግ በአዋጁ አንቀጽ 49 (2) መሠረት የሚከተለውን ቅጣት ያስከትላል፡፡ ይኸውም ነጋዴው የዓመታዊ ገቢውን 20 በመቶ ወይም የዓመታዊ ገቢውን መጠን መወሰን ባልተቻለ ጊዜ ከብር 1,000,000 (አንድ ሚሊዮን ብር) እስከ ብር 2,000,000 (ሁለት ቢሊዮን) በሚደርስ የገንዘብ መቀጫና ከአምስት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡


